በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ነሐሴ 2016

የጋብቻ አጀማመርና ዓላማው

የጋብቻ አጀማመርና ዓላማው

“ይሖዋ አምላክ ‘ሰውየው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለም። ማሟያ የምትሆነውን ረዳት እሠራለታለሁ’ አለ።”—ዘፍ. 2:18

መዝሙሮች፦ 36, 11

1, 2. (ሀ) ጋብቻ የተጀመረው እንዴት ነው? (ለ) የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ስለ ጋብቻ ምን ተገንዝበው መሆን አለበት? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

ጋብቻ በታሪክ ዘመናት ሁሉ የነበረ ነገር ነው። ጋብቻ እንዴት እንደተጀመረና ዓላማው ምን እንደሆነ መመርመራችን፣ የጋብቻን ጥምረት በተመለከተ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረንና የሚያስገኛቸውን በረከቶች ይበልጥ ማጣጣም እንድንችል ይረዳናል። አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን ከፈጠረ በኋላ ለእንስሳቱ ስም እንዲያወጣላቸው ወደ እሱ አመጣቸው። “ለሰው ግን ማሟያ የሚሆን ረዳት አልነበረውም።” በመሆኑም አምላክ፣ አዳም ከባድ እንቅልፍ እንዲወስደው ካደረገ በኋላ ከጎድን አጥንቶቹ አንዷን ወስዶ ሴት አድርጎ ሠራት፤ ከዚያም ወደ አዳም አመጣት። (ዘፍጥረት 2:20-24ን አንብብ።) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው የጋብቻ መሥራች አምላክ ነው።

2 ይሖዋ “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ብሎ ተናግሮ ነበር፤ ኢየሱስም ይህንኑ መሠረታዊ ሥርዓት በድጋሚ ተናግሯል። (ማቴ. 19:4, 5) አምላክ የመጀመሪያዋን ሴት ሔዋንን የፈጠራት ከአዳም የጎድን አጥንት መሆኑ፣ ባልና ሚስት ምን ያህል የጠበቀ ጥምረት እንዳላቸው ለመጀመሪያዎቹ ጥንዶች አስገንዝቧቸው መሆን አለበት። አምላክ፣ ባልና ሚስት እንዲፋቱ ወይም በትዳር ጓደኛቸው ላይ ሌላ ደርበው እንዲያገቡ ዓላማው አልነበረም።

 ጋብቻ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ያለው ቦታ ምንድን ነው?

3. ከጋብቻ ዓላማዎች አንዱ ምን ነበር?

3 አዳም፣ ቆንጆ ሚስት በማግኘቱ በጣም የተደሰተ ሲሆን በኋላ ላይ ሔዋን ብሎ ጠራት። ሔዋን ለአዳም “ማሟያ” እንደመሆኗ መጠን “ረዳት” ትሆንለታለች፤ አዳምና ሔዋን በትዳር ሕይወታቸው ውስጥ የየራሳቸውን ድርሻ ከተወጡ አንዳቸው ለሌላው የደስታ ምንጭ ይሆናሉ። (ዘፍ. 2:18) ከጋብቻ ዓላማዎች አንዱ ምድር በሰዎች እንድትሞላ ማድረግ ነበር። (ዘፍ. 1:28) ልጆች ወላጆቻቸውን ቢወዱም እንኳ አግብተው የራሳቸውን ቤተሰብ ሲመሠርቱ ከአባትና ከእናታቸው ይለያሉ። የአምላክ ዓላማ የሰው ልጆች ምድርን እንዲሞሉና መላዋን ምድር ገነት እንዲያደርጓት ነበር።

4. የመጀመሪያው ጋብቻ ምን አጋጠመው?

4 አዳምና ሔዋን የመምረጥ ነፃነታቸውን አላግባብ ስለተጠቀሙበት ይኸውም በይሖዋ ላይ ስላመፁ የመጀመሪያው ጋብቻ ችግር አጋጠመው። “የጥንቱ እባብ” የተባለው ሰይጣን ዲያብሎስ፣ ሔዋን “ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ” ፍሬ ብትበላ ልዩ እውቀት እንደምታገኝና መልካም ወይም ክፉ የሆነውን ነገር ራሷ የመወሰን ችሎታ እንደሚኖራት እንድታምን በማድረግ አታለላት። ሔዋን ስለ ጉዳዩ ባሏን አለማማከሯ ለእሱ የራስነት ሥልጣን አክብሮት እንደሌላት የሚያሳይ ነው። አዳምም ቢሆን አምላክን ከመታዘዝ ይልቅ ሔዋን የሰጠችውን ፍሬ ተቀብሎ በላ።—ራእይ 12:9፤ ዘፍ. 2:9, 16, 17፤ 3:1-6

5. አዳምና ሔዋን ለይሖዋ ከሰጡት መልስ ምን እንማራለን?

5 አዳም የሠራውን ኃጢአት በተመለከተ አምላክ ሲጠይቀው “ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ይህች ሴት ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” በማለት ጥፋቱን በሚስቱ ላይ አላከከ። ሔዋን ደግሞ እባብ እንዳታለላት በመግለጽ ጥፋቷን በእሱ አሳበበች። (ዘፍ. 3:12, 13) ይህ አሳማኝ ያልሆነ ሰንካላ ምክንያት ነው! የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ሳይታዘዙ በመቅረታቸው ይሖዋ በእነዚህ ዓመፀኞች ላይ ፍርድ አስተላለፈ። ይህ ለእኛ ትልቅ ማስጠንቀቂያ ነው! ትዳር የሰመረ እንዲሆን ሁለቱም ተጋቢዎች ለድርጊታቸው ኃላፊነቱን መውሰድና ይሖዋን መታዘዝ አለባቸው።

6. ዘፍጥረት 3:15ን አብራራ።

6 ሰይጣን በኤደን ውስጥ ችግር እንዲፈጠር ቢያደርግም ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የመጀመሪያውን ትንቢት በመናገር ለሰው ዘር ተስፋ ፈነጠቀ። (ዘፍጥረት 3:15ን አንብብ።) ይህ ትንቢት ‘የሴቲቱ ዘር’ የመጀመሪያውን ዓመፀኛ መንፈሳዊ ፍጡር እንደሚጨፈልቀው ያሳያል። ይሖዋ የተናገረው ይህ ትንቢት፣ በእሱና በሰማይ ሆነው በሚያገለግሉት ጻድቅ የሆኑ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መንፈሳዊ ፍጥረታት መካከል ያለውን ልዩ ዝምድና እንድናውቅ መንገድ ከፍቶልናል። እነዚህን መንፈሳዊ ፍጥረታት ያቀፈው ድርጅት እንደ ይሖዋ ሚስት ተደርጎ ተገልጿል፤ ከጊዜ በኋላ የሰፈረው የቅዱሳን መጻሕፍት ዘገባ እንደሚያሳየው ዲያብሎስን ‘የሚጨፈልቀው’ ከዚህ ድርጅት የሚወጣው ዘር ነው፤ በዚህ መንገድ፣ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ያጡትን ነገር ይኸውም በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያገኛሉ፤ ይህም የመጀመሪያው የይሖዋ ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋል።—ዮሐ. 3:16

7. (ሀ) አዳምና ሔዋን ማመፃቸው በትዳር ላይ ምን አስከተለ? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ባሎችና ሚስቶች ምን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል?

7 አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ማመፃቸው በራሳቸው ትዳርም ሆነ ከዚያ በኋላ በተመሠረቱ ሌሎች ጋብቻዎች ሁሉ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ለምሳሌ፣ ሔዋንና ዘሮቿ የሆኑት ሴቶች በእርግዝናቸው ወቅት ከባድ ሕመም የሚኖራቸው ሲሆን የሚወልዱትም በሥቃይ ይሆናል። ሴቶች ምኞታቸው በሙሉ ወደ ባሎቻቸው ይሆናል፤ ባሎች ግን በሚስቶቻቸው ላይ ገዢ ከመሆንም አልፈው በዛሬው ጊዜ በብዙ ትዳሮች ውስጥ እንደሚታየው በሚስቶቻቸው ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ። (ዘፍ. 3:16) መጽሐፍ ቅዱስ ባሎች የራስነት ሥልጣናቸውን ፍቅር በተሞላበት መንገድ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ይገልጻል። ሚስቶች ደግሞ ለባሎቻቸው የራስነት ሥልጣን መገዛት አለባቸው። (ኤፌ. 5:33)  ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ባልና ሚስት፣ እርስ በርስ ስለሚደጋገፉ በመካከላቸው ሊፈጠር የሚችለውን ግጭት መቀነስ ወይም ጨርሶ ማስቀረት ይችላሉ።

ጋብቻ—ከአዳም እስከ ጥፋት ውኃ

8. ከአዳም አንስቶ እስከ ጥፋት ውኃ ባሉት ዘመናት ጋብቻ ምን ይመስል እንደነበር ግለጽ።

8 አዳምና ሔዋን በሠሩት ኃጢአት ምክንያት ከመሞታቸው በፊት ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወለዱ። (ዘፍ. 5:4) የመጀመሪያ ልጃቸው ቃየን ዘመዶቹ ከሆኑት ሴቶች አንዷን አገባ። ሁለት ሚስቶችን እንዳገባ የተገለጸው የመጀመሪያው ሰው የቃየን የልጅ ልጅ የሆነው ላሜህ ነው። (ዘፍ. 4:17, 19) ከአዳም ጀምሮ በኖኅ ዘመን እስከተከሰተው የጥፋት ውኃ ድረስ ካሉት ትውልዶች መካከል የይሖዋ አምላኪዎች እንደሆኑ የተገለጹት ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ አቤልና ሄኖክ እንዲሁም ኖኅና ቤተሰቡ ይገኙበታል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በኖኅ ዘመን “የእውነተኛው አምላክ [ልጆች] የሰዎች ሴቶች ልጆች ውብ እንደሆኑ” ማየታቸውን ይናገራል። “በመሆኑም የመረጧቸውን ሁሉ ለራሳቸው ሚስቶች አድርገው ወሰዱ።” እንዲህ ያለው ጥምረት ከተፈጥሮ ውጭ ነበር፤ ሥጋ የለበሱት መላእክትና የሰው ሴቶች ልጆች፣ ኔፍሊም ተብለው የተጠሩ ዓመፀኛ ልጆች ወለዱ። በወቅቱ “የሰው ልጅ ክፋት በምድር ላይ” የበዛ ሲሆን “የልቡም ሐሳብ ሁሉ ምንጊዜም ወደ መጥፎ ብቻ ያዘነበለ” ሆኖ ነበር።—ዘፍ. 6:1-5

9. ይሖዋ በኖኅ ዘመን የነበሩትን ክፉ ሰዎች ምን አደረጋቸው? በዚያ ዘመን ከነበረው ሁኔታ ምን ትምህርት ልናገኝ ይገባል?

9 ይሖዋ ክፉዎችን ለማጥፋት ሲል በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ አመጣ። በወቅቱ የነበሩት ሰዎች፣ ትዳርን ጨምሮ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ከሚገባው በላይ ተጠምደው ስለነበር ‘የጽድቅ ሰባኪ የነበረው ኖኅ’ ስለሚመጣው ጥፋት የሚናገረውን መልእክት በቁም ነገር አልተመለከቱትም። (2 ጴጥ. 2:5) ኢየሱስ በኖኅ ዘመን የነበረውን ሁኔታ በዘመናችን ካለው ሁኔታ ጋር አመሳስሎታል። (ማቴዎስ 24:37-39ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች፣ ይህ ክፉ ሥርዓት ከመጥፋቱ በፊት ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር እየተሰበከ ያለውን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስማት አሻፈረን ብለዋል። እኛም እንደ ትዳርና ልጆችን እንደ ማሳደግ የመሳሰሉት የቤተሰብ ጉዳዮችም እንኳ የይሖዋን ቀን በጥድፊያ ስሜት እንዳንጠባበቅ እንቅፋት እንዲሆኑብን ልንፈቅድ አይገባም።

ጋብቻ—ከጥፋት ውኃ እስከ ኢየሱስ ዘመን

10. (ሀ) በብዙ ባሕሎች ውስጥ ከፆታ ጋር በተያያዘ የትኞቹ ልማዶች እየተስፋፉ መጡ? (ለ) የአብርሃምና የሣራ ትዳር ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?

10 ኖኅና ሦስቱ ወንዶች ልጆቹ ከአንድ በላይ ባያገቡም በጥንት ዘመን ብዙ ሚስቶችን ማግባት የተለመደ ነበር። በብዙ ባሕሎች ውስጥ የፆታ ብልግና በጣም የተስፋፋ ከመሆንም አልፎ በአንዳንድ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ውስጥ እንኳ ተካትቶ ነበር። አብራም (አብርሃም) እና ሚስቱ ሦራ (ሣራ) አምላክ በሰጣቸው መመሪያ መሠረት ወደ ከነዓን በሄዱበት ወቅት የጋብቻ ዝግጅትን የሚያቃልሉ ልማዶች በዚያ አካባቢ ተስፋፍተው ነበር። የሰዶምና የገሞራ ነዋሪዎች ልቅ የሆነ የፆታ ብልግና ይፈጽሙ ወይም እንዲህ ያለውን ድርጊት በቸልታ ያልፉ ስለነበር ይሖዋ እነዚህ ከተሞች እንዲጠፉ ወሰነ። አብርሃም በቤተሰቡ ላይ የራስነት ሥልጣኑን በአግባቡ ይጠቀምበት የነበረ ሲሆን ሣራም ለባሏ በመገዛት ረገድ ግሩም ምሳሌ ነች። (1 ጴጥሮስ 3:3-6ን አንብብ።) አብርሃም፣ ልጁ ይስሐቅ ይሖዋን የምታመልክ ሴት እንዲያገባ አድርጓል። ይስሐቅም ለልጁ ለያዕቆብ እንዲህ ያደረገ ሲሆን ከጊዜ በኋላ 12ቱ የእስራኤል ነገዶች የተገኙት ከያዕቆብ ወንዶች ልጆች ነው።

11. የሙሴ ሕግ እስራኤላውያንን የጠቀማቸው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

11 ከጊዜ በኋላ ይሖዋ፣ ከያዕቆብ (ከእስራኤል) ዘሮች ጋር ቃል ኪዳን ገባ። ከአንድ በላይ ማግባትን ጨምሮ ቀደም ባሉት ዘመናት የነበሩትን ከጋብቻ ጋር የተያያዙ ልማዶች የሚመለከቱ መመሪያዎች በሙሴ ሕግ ውስጥ ተካትተው ነበር። ሕጉ፣ እስራኤላውያን የሐሰት አማልክትን የሚያመልኩ ሰዎችን እንዳያገቡ የሚከለክል ሲሆን ይህም ሕዝቡ  በመንፈሳዊ እንዳይበከል አድርጓል። (ዘዳግም 7:3, 4ን አንብብ።) በትዳር ውስጥ ከባድ ችግሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ በሕዝቡ መካከል የሚገኙ ሽማግሌዎች እርዳታ ይሰጡ ነበር። በትዳር ጓደኛ ላይ ክህደት መፈጸምን፣ ቅናትንና የትዳር ጓደኛን መጠርጠርን የመሳሰሉትን ጉዳዮች ለመዳኘት የሚያስችል ሕግ ነበር። ፍቺ ይፈቀድ የነበረ ቢሆንም አንዱ ሌላውን እንዳይበድል የሚከላከል ሕግ ነበር። አንድ ሰው በሚስቱ ላይ “ነውር የሆነ ነገር” ቢያገኝባት ሊፈታት ይችላል። (ዘዳ. 24:1) “ነውር የሆነ ነገር” የተባለው ምን እንደሆነ ባይገለጽም አንድ ባል በማይረባ ምክንያት ሚስቱን መፍታት እንደማይችል ግልጽ ነው።—ዘሌ. 19:18ለ

በትዳር ጓደኛችሁ ላይ ክህደት አትፈጽሙ

12, 13. (ሀ) በሚልክያስ ዘመን አንዳንድ ወንዶች በሚስቶቻቸው ላይ ምን ይፈጽሙ ነበር? (ለ) ራሱን ለአምላክ ወስኖ የተጠመቀ አንድ ባለትዳር ከሌላ ሰው የትዳር ጓደኛ ጋር ቢኮበልል ምን ይደርስበታል?

12 በነቢዩ ሚልክያስ ዘመን በርካታ አይሁዳውያን ባሎች፣ በረባ ባልረባው ሚስቶቻቸውን በመፍታት ክህደት ይፈጽሙባቸው ነበር። እንደነዚህ ያሉት ባሎች፣ ወጣት የሆኑ ይባስ ብሎም ይሖዋን የማያመልኩ ሴቶችን ለማግባት ሲሉ የወጣትነት ሚስቶቻቸውን ይፈቱ ነበር። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜም አይሁዳውያን ወንዶች ሚስቶቻቸውን “በማንኛውም ምክንያት” በመፍታት ክህደት ይፈጽሙባቸው ነበር። (ማቴ. 19:3) ይሖዋ አምላክ እንዲህ ያለውን ፍቺ ይጠላል።ሚልክያስ 2:13-16ን አንብብ።

13 በዛሬው ጊዜ ባሉት የይሖዋ ሕዝቦች ዘንድ በትዳር ጓደኛ ላይ ክህደት መፈጸም በቸልታ የሚታለፍ ነገር አይደለም። ለምሳሌ፣ ራሱን ለአምላክ ወስኖ የተጠመቀ አንድ ባለትዳር ከሌላ ሰው የትዳር ጓደኛ ጋር ኮበለለ እንበል። ግለሰቡ የቀድሞ ትዳሩን በፍቺ ካፈረሰ በኋላ ይህችኛዋን ሴት ቢያገባ ንስሐ እስካልገባ ድረስ ከክርስቲያን ጉባኤ ይወገዳል፤ እንዲህ ዓይነት እርምጃ የሚወሰደው የጉባኤውን መንፈሳዊ ንጽሕና ለመጠበቅ ሲባል ነው። (1 ቆሮ. 5:11-13) እንዲህ ያለው ሰው ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ለመመለስ ከፈለገ “ለንስሐ የሚገባ ፍሬ” ማፍራት ይጠበቅበታል። (ሉቃስ 3:8፤ 2 ቆሮ. 2:5-10) የተወገደው ግለሰብ ወደ ጉባኤው እስኪመለስ ድረስ ምን ያህል ጊዜ ማለፍ እንዳለበት የተደነገገ ሕግ ባይኖርም እንዲህ ያለው የክህደት ድርጊት በቀላሉ የሚታይ ነገር አይደለም። ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ ከልቡ ንስሐ መግባቱን ለማየት ረዘም ያለ ጊዜ ምናልባትም አንድ ዓመት ወይም ከዚያ የበለጠ ጊዜ ማለፍ ይኖርበት ይሆናል። ግለሰቡ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ቢመለስም እንኳ ከልቡ ንስሐ ስለመግባቱ “በአምላክ የፍርድ ወንበር ፊት” ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለው ሁኔታ በአምላክ ሕዝቦች መካከል ብዙ ጊዜ ያጋጥማል ማለት አይደለም።—ሮም 14:10-12፤ የኅዳር 15, 1979 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 31-32 ተመልከት።

የክርስቲያኖች ጋብቻ

14. ሕጉ ምን አከናውኗል?

14 የሙሴ ሕግ ከ1,500 ለሚበልጡ ዓመታት ለእስራኤላውያን መመሪያ ሆኖ አገልግሏል። ሕጉ፣ የአምላክ ሕዝቦች ከቤተሰብ ጋር የተያያዙ ወይም ሌሎች ጉዳዮች ሲያጋጥሟቸው ምንጊዜም የአምላክን የጽድቅ መሥፈርቶች እንዲያስታውሱ የረዳቸው ከመሆኑም ሌላ ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ሞግዚት ሆኖላቸዋል። (ገላ. 3:23, 24) ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ሕጉ ስለተወገደ አምላክ አዲስ ዝግጅት አደረገ። (ዕብ. 8:6) በሕጉ ሥር የሚፈቀዱ አንዳንድ ነገሮች በአዲሱ ዝግጅት ውስጥ አይፈቀዱም።

15. (ሀ) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከጋብቻ ጋር በተያያዘ የምንከተለው መመሪያ ምንድን ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን ስለ ፍቺ ሲያስብ የትኞቹን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል?

15 ኢየሱስ አንዳንድ ፈሪሳውያን ላቀረቡለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ፣ የሙሴ ሕግ ፍቺን ቢፈቅድም ሁኔታው ‘ከመጀመሪያ እንዲህ እንዳልነበረ’ ተናግሯል። (ማቴ. 19:6-8) ኢየሱስ ይህን ማለቱ፣ አምላክ ከጋብቻ ጋር በተያያዘ በኤደን ያወጣው መመሪያ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም እንደሚሠራ ይጠቁማል። (1 ጢሞ. 3:2, 12) ባልና ሚስት “አንድ ሥጋ” ናቸው፤ በመሆኑም ለአምላክና ለትዳር ጓደኛቸው ያላቸው ፍቅር ጥምረታቸውን  ሊያጠናክረው ይገባል። አንድ ሰው በፆታ ብልግና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሕጋዊ ፍቺ ቢፈጽምም እንኳ ሌላ ሰው ለማግባት ነፃ አይሆንም። (ማቴ. 19:9) እርግጥ ነው፣ ሆሴዕ የፆታ ብልግና የፈጸመችውን ሚስቱን ጎሜርን ይቅር እንዳላት ሁሉ ክህደት የተፈጸመበት አንድ ባለትዳርም ንስሐ የገባውን የትዳር ጓደኛውን ይቅር ለማለት ሊመርጥ ይችላል። በመንፈሳዊ ሁኔታ ምንዝር የፈጸሙት እስራኤላውያን ንስሐ ሲገቡ ይሖዋ ምሕረት አድርጎላቸዋል። (ሆሴዕ 3:1-5) በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ባለትዳር፣ የትዳር ጓደኛው ምንዝር እንደፈጸመ ካወቀ በኋላም ከእሱ ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸሙን ቢቀጥል እንዲህ ማድረጉ ለበዳዩ ይቅርታ እንዳደረገለት ስለሚቆጠር ከዚያ በኋላ ፍቺ ለመፈጸም የሚያስችል ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት አይኖረውም።

16. ኢየሱስ ስለ ነጠላነት ምን ብሏል?

16 ኢየሱስ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች በፆታ ብልግና ምክንያት ካልሆነ በቀር መፋታት እንደማይችሉ ከተናገረ በኋላ ነጠላ ሆነው ለመኖር “ስጦታው ያላቸው” ሰዎች እንዳሉ ገልጿል። አክሎም “ይህን ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 19:10-12) ብዙዎች፣ ሐሳባቸው ሳይከፋፈል ይሖዋን ለማገልገል ሲሉ ነጠላ ሆነው ለመኖር መርጠዋል። እንዲህ በማድረጋቸውም አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል።

17. አንድ ክርስቲያን ማግባት ይኖርበት እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን ምን ሊረዳው ይችላል?

17 አንድ ሰው፣ ‘ነጠላ ሆኜ ብኖር ይሻላል ወይስ ባገባ?’ የሚለውን ለመወሰን ምን ሊረዳው ይችላል? የነጠላነትን ስጦታ መቀበል ይችል እንደሆነ ራሱን መመርመሩ ጠቃሚ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የነጠላነት ሕይወትን ያበረታታ ቢሆንም እንዲህ በማለትም ተናግሯል፦ “የፆታ ብልግና ስለተስፋፋ እያንዳንዱ ወንድ የራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዷም ሴት የራሷ ባል ይኑራት።” አክሎም “ራሳቸውን መግዛት ካቃታቸው . . . ያግቡ፤ በፍትወት ከመቃጠል ማግባት ይሻላልና” ብሏል። አንድ ሰው ትዳር መመሥረቱ፣ እንደ ማስተርቤሽን ወይም እንደ ፆታ ብልግና ያሉ ድርጊቶችን ከመፈጸም እንዲርቅ ሊረዳው ይችላል። እርግጥ ነው፣ ያላገቡ ሰዎች ዕድሜያቸው ለትዳር መድረሱን ሊያስቡበት ይገባል፤ ሐዋርያው እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሰው ሳያገባ ቀርቶ ራሱን መቆጣጠር እንደተሳነው ከተሰማው፣ በተለይ ደግሞ አፍላ የጉርምስና ዕድሜን ያለፈ ከሆነና ማግባቱ የሚመረጥ ከሆነ የፈለገውን ያድርግ፤ ኃጢአት አይሆንበትም። እንዲህ ያሉ ሰዎች ያግቡ።” (1 ቆሮ. 7:2, 9, 36፤ 1 ጢሞ. 4:1-3) አንድ ሰው በወጣትነት ዕድሜ በሚኖረው ከፍተኛ የፆታ ስሜት ተገፋፍቶ ለማግባት መወሰን የለበትም። ምክንያቱም እንዲህ ያለው ሰው፣ ትዳር የሚያስከትለውን ኃላፊነት ለመሸከም የሚያስፈልገው ብስለት ላይኖረው ይችላል።

18, 19. (ሀ) ክርስቲያኖች ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ሊከተሉት የሚገባው መሥፈርት ምንድን ነው? (ለ) የሚቀጥለው ርዕስ የትኛውን ጉዳይ ያብራራል?

18 በክርስቲያኖች መካከል ትዳር የሚመሠርቱ አንድ ወንድና አንዲት ሴት፣ ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑና እሱን ከልብ የሚወዱ መሆን አለባቸው። በተጨማሪም በትዳር ተጣምረው ለመኖር የሚያስችል ጠንካራ ፍቅር በመካከላቸው ሊኖር ይገባል። ተጋቢዎቹ “በጌታ ብቻ” እንድናገባ የተሰጠንን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው በረከት እንደሚያስገኝላቸው ምንም ጥያቄ የለውም። (1 ቆሮ. 7:39) ከተጋቡ በኋላም ትዳራቸው የሰመረ እንዲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ከሁሉ የላቀ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኞች መሆን ይኖርባቸዋል።

19 የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ እንደመሆኑ መጠን የብዙዎች ባሕርይ ለትዳር መሳካት እንቅፋት እንደሚሆን በግልጽ ማየት ይቻላል፤ በመሆኑም በዚህ ዘመን የሚኖሩ ክርስቲያን ባለትዳሮች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል፤ የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዴት መወጣት እንደሚቻል ያብራራል። (2 ጢሞ. 3:1-5) ይሖዋ ትዳራችን አስደሳችና ስኬታማ እንዲሆን የሚያስፈልገንን መመሪያ ውድ በሆነው በቃሉ ውስጥ አስፍሮልናል፤ ይህም ከሕዝቡ ጋር ሆነን ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ መጓዛችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።—ማቴ. 7:13, 14