በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ከወርቅ የሚልቀውን ነገር ፈልጉ

ከወርቅ የሚልቀውን ነገር ፈልጉ

ንጹሕ ወርቅ አግኝተህ ታውቃለህ? እንዲህ ዓይነት ወርቅ አግኝተው የሚያውቁት ጥቂት ሰዎች ናቸው። ሆኖም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከወርቅ የላቀ ነገር አግኝተዋል። ይህም መለኮታዊ ጥበብ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለውን ጥበብ “በንጹሕ ወርቅ መግዛት አይቻልም” ይላል።—ኢዮብ 28:12, 15

ቅን ልብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በአንዳንድ መንገዶች፣ ወርቅ ከሚፈልጉ ማዕድን ቆፋሪዎች ጋር ይመሳሰላሉ። እንዲህ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በዋጋ ሊተመን የማይችል ጥበብ ለማግኘት፣ ጠንክረው መሥራትና ቅዱሳን መጻሕፍትን አዘውትረው መመርመር ያስፈልጋቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ወርቅ የሚፈለግባቸውን ሦስት መንገዶች በመመልከት ምን መማር ይችላሉ?

ወርቅ አገኘህ!

በአንድ ወንዝ ዳር እየሄድክ ሳለህ የፀሐይን ብርሃን ሲያርፍባት የምታንጸባርቅ ትንሽ ጠጠር የምትመስል ነገር አየህ እንበል። ጎንበስ ብለህ ስታያት ንጹሕ ወርቅ መሆኗን ትገነዘባለህ፤ በጣም እንደምትደሰት የታወቀ ነው። ያገኘሃት ወርቅ፣ መጠኗ ከክብሪት አናት ያነሰ ሲሆን ከፍተኛ ጥራት ካለው አልማዝ ይበልጥ ለማግኘት አስቸጋሪ ናት። በአካባቢው እንዲህ ዓይነት ሌሎች ወርቆች እንዳሉ ለማየት ዙሪያውን መቃኘትህ አይቀርም።

ወርቅ ከማግኘት ጋር በሚመሳሰል መንገድ፣ አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤትህ መጥቶ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ነግሮህ ይሆናል፤ ያንን ቀን ፈጽሞ አትረሳውም። ምናልባትም በመንፈሳዊ ሁኔታ ወርቅ እንዳገኘህ የተሰማህ ጊዜ ትላንት የሆነ ያህል ቁልጭ ብሎ ይታይህ ይሆናል። እንዲህ የተሰማህ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ባየህበት ወቅት ሊሆን ይችላል። (መዝ. 83:18) አሊያም የይሖዋ ወዳጅ መሆን እንደምትችል ስትማር ይሆናል። (ያዕ. 2:23) ከወርቅ የላቀ ነገር እንዳገኘህ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደብህም! በመሆኑም ውድ የሆኑ ተጨማሪ መንፈሳዊ እውነቶች ለማግኘት ጉጉት አድሮብህ ይሆናል።

ተጨማሪ ወርቅ አገኘህ!

አንዳንድ ጊዜ በጅረቶችና በወንዞች ውስጥ በጣም ጥቃቅን የሆኑ የወርቅ ቅንጣቶች ተከማችተው ይገኛሉ። ይህም የደለል ወርቅ ተብሎ ይጠራል። ተግተው የሚሠሩ ወርቅ ፈላጊዎች፣ እንደነዚህ ባሉ ደለላማ ስፍራዎች ላይ በጥቂት ወራት ውስጥ ብዙ ግራም ወርቅ ሊያገኙ ይችላሉ፤ ይህም በአሥር ሺዎች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ያወጣል።

ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስትጀምር፣ በርከት ያለ ወርቅ የተከማቸበትን ቦታ እንዳገኘ ማዕድን ፈላጊ ተሰምቶህ ይሆናል። በእያንዳንዱ ጥቅስ ላይ ማሰላሰልህ እውቀት እንድታካብት ረድቶህ መሆን አለበት፤ ይህ ደግሞ በመንፈሳዊ ለማደግ አስችሎሃል። እነዚያን ውድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች በጉጉት ስታጠና፣ ይበልጥ ወደ ይሖዋ መቅረብና የዘላለም ሕይወት ከሚያስገኝልህ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጣ መኖር የምትችለው እንዴት እንደሆነ ተማርክ።—ያዕ. 4:8፤ ይሁዳ 20, 21

ወርቅ ለማግኘት ተግቶ እንደሚሠራ ማዕድን ፈላጊ ሁሉ አንተም ውድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት ታደርጋለህ?

 አንድ ማዕድን ፈላጊ ውድ የሆነውን የደለል ወርቅ ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ አንተም በዋጋ ሊተመን የማይችለውን መንፈሳዊ ሀብት በትጋት ስትፈልግ ቆይተህ ሊሆን ይችላል። መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ከተማርክ በኋላ ራስህን ለአምላክ ወስነህ ለመጠመቅ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደተነሳሳህ ግልጽ ነው።—ማቴ. 28:19, 20

ፍለጋህን አታቋርጥ!

ወርቅ ፈላጊ የሆነ ሰው፣ በእሳተ ገሞራ ቀልጠው በጠጠሩ ድንጋዮች ውስጥ በጣም አነስተኛ መጠን ያለው ወርቅ ሊያገኝ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ባሉት ድንጋዮች ውስጥ ብዛት ያለው ወርቅ ተከማችቶ ስለሚገኝ ወርቁን ለማውጣት ሲባል ማዕድን አውጪዎች ድንጋዩን ይፈልጡታል። ድንጋዩን በደንብ ላልተመለከተው ሰው ወርቁ ላይታየው ይችላል። ለምን? ምክንያቱም ማዕድናት በተቀላቀሉበት አንድ ሺህ ኪሎ ግራም ዓለት ውስጥ የሚገኘው ወርቅ 10 ግራም ብቻ ሊሆን ይችላል! ይሁን እንጂ ወርቅ ፈላጊው ይህን ያህል ጥረት በማድረጉ አይቆጭም።

በተመሳሳይም አንድ ሰው ‘ስለ ክርስቶስ ከተማረው መሠረታዊ ትምህርት’ አልፎ ከሄደ በኋላም ጥረት ማድረጉን መቀጠል ያስፈልገዋል። (ዕብ. 6:1, 2) ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ አዳዲስ ነጥቦችንና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ ትምህርቶችን ለማግኘት በትጋት መፈለግ ይኖርብሃል። ቅዱሳን መጻሕፍትን ለብዙ ዓመታት ስታጠና የቆየህ ብትሆንም እንኳ ከግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ጥቅም ማግኘትህን ለመቀጠል ምን ማድረግ ትችላለህ?

የማወቅ ጉጉትህ መቼም ቢሆን እንዳይጠፋ ጥረት አድርግ። ለዝርዝር ነጥቦች ትኩረት ስጥ። ጥረት ማድረግህን ከቀጠልክ ከቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እንደ ወርቅ ውድ የሆነ መለኮታዊ ጥበብና መመሪያ ታገኛለህ። (ሮም 11:33) የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀትህን ለመጨመር በቋንቋህ የሚገኙ የምርምር መሣሪያዎችን ጥሩ አድርገህ ተጠቀምባቸው። የሚያስፈልግህን መመሪያ እንዲሁም ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎችህ መልስ ለማግኘት በትዕግሥት ፍለጋ ማድረግህን ቀጥል። በጣም ጠቃሚና አበረታች ሆነው ያገኟቸውን ጥቅሶችና ርዕሶች እንዲነግሩህ ሌሎችን ጠይቅ። አንተም የአምላክን ቃል ስታጠና ያገኘሃቸውን ጠቃሚ ነጥቦች ለሌሎች አካፍል።

እርግጥ ነው፣ ግብህ እውቀት ማካበት ብቻ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ “እውቀት ያስታብያል” በማለት አስጠንቅቋል። (1 ቆሮ. 8:1) በመሆኑም ምንጊዜም ትሑት ለመሆንና ጠንካራ እምነት ለማዳበር ጥረት አድርግ። ቋሚ የቤተሰብ አምልኮና የግል ጥናት ማድረግህ ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተህ ለመኖር የሚያስችልህ ከመሆኑም ሌላ ሌሎችን ለመርዳት ያነሳሳሃል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከወርቅ የሚልቀውን ነገር በማግኘትህ ትደሰታለህ።—ምሳሌ 3:13, 14