ይህ ሐሳብ እውነት እንደሆነና ይሖዋ በእርግጥ እንደሚያስብልህ እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ እንደሚያስብልን በግልጽ የሚናገር መሆኑ ነው። አንደኛ ጴጥሮስ 5:7 “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል” በማለት ይናገራል። ታዲያ ይሖዋ ስለ አንተ እንደሚያስብ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ያቀርባል

ይሖዋ በሚከተሉት መንገዶች ምሳሌ ትቶልናል፦ ደግና ለጋስ ነው

በአንደኛ ደረጃ፣ አምላክ በጣም የምትቀርበው ጓደኛህ እንዲኖሩት የምትፈልጋቸው ዓይነት ባሕርያት አሉት። አንዳቸው ለሌላው ደግና ለጋስ የሆኑ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የጠበቀ ወዳጅነት ይመሠርታሉ። ይሖዋ፣ ለሰዎች ደግና ለጋስ እንደሆነ በየዕለቱ ከሚያደርገው ነገር በግልጽ ማየት ይቻላል። አንድ ምሳሌ ተመልከት፦ “እሱ በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣልና፤ በጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ዝናብ ያዘንባል።” (ማቴ. 5:45) የፀሐይ ብርሃንና ዝናብ ምን ያከናውናሉ? አምላክ ለሰዎች ‘የተትረፈረፈ ምግብ ለማቅረብና ልባቸውን በደስታ ለመሙላት’ በፀሐይና በዝናብ ይጠቀማል። (ሥራ 14:17) በእርግጥም ይሖዋ ምድር የተትረፈረፈ ምግብ እንድታቀርብ አድርጓል፤ ደግሞም በጣም ከሚያስደስቱን ነገሮች አንዱ ጥሩ ምግብ ነው።

ታዲያ ብዙ ሰዎች እየተራቡ ያሉት ለምንድን ነው? ሰብዓዊ መሪዎች የሕዝቡን ሕይወት ከማሻሻል ይልቅ ብዙውን ጊዜ የሚያተኩሩት ፖለቲካዊ ሥልጣን በመያዝና ሀብት በማጋበስ ላይ ስለሆነ ነው። ይሖዋ አሁን ያለውን ፖለቲካዊ ሥርዓት ካጠፋ በኋላ፣ ልጁ ንጉሥ ሆኖ የሚያስተዳድረው ሰማያዊ መንግሥት ምድርን እንዲቆጣጠራት በማድረግ ስግብግብነት ያስከተለውን ይህን ችግር በቅርቡ ያስወግደዋል። በዚያን ጊዜ ማንም ሰው አይራብም። እስከዚያው ድረስ ግን አምላክ ለታማኝ  አገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ይሰጣቸዋል። (መዝ. 37:25) ይህ፣ አምላክ እንደሚያስብልህ የሚያሳይ አይደለም?

ይሖዋ ጊዜውን ለመስጠት አይሰስትም

ይሖዋ በሚከተሉት መንገዶች ምሳሌ ትቶልናል፦ ጊዜውን ለመስጠት አይሰስትም

ጥሩ ጓደኛ ጊዜውን ከአንተ ጋር ለማሳለፍ አይሳሳም። የሁለታችሁን ትኩረት ስለሚስቡ ነገሮች ለሰዓታት ሊያዋራህ ፈቃደኛ ነው። ደግሞም ጥሩ ጓደኛ ችግሮችህንና የሚያስጨንቁህን ነገሮች ስትነግረው በጥሞና ያዳምጥሃል። ታዲያ ይሖዋ እንዲህ ያለ ትኩረት ይሰጥሃል? አዎ! ጸሎቶቻችንን ይሰማል። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሳንታክት እንድንጸልይ’ አልፎ ተርፎም ‘ዘወትር እንድንጸልይ’ ያበረታታናል።—ሮም 12:12፤ 1 ተሰ. 5:17

ይሖዋ የምታቀርበውን ጸሎት ለመስማት ምን ያህል ጊዜ ይሰጥሃል? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኝ አንድ ታሪክ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። ኢየሱስ ሐዋርያቱን ከመምረጡ በፊት ‘ሌሊቱን ሙሉ ወደ አምላክ ሲጸልይ አድሯል።’ (ሉቃስ 6:12) ኢየሱስ በዚያ ጸሎት ላይ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹን በስም እየጠቀሰ ያላቸውን መልካም ባሕርይና ድክመታቸውን በማንሳት፣ ከመካከላቸው ሐዋርያቱን ለመምረጥ እንዲረዳው አባቱን ሳይለምን አልቀረም። በማግስቱ ጎህ ሲቀድ ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱ ሆነው ለማገልገል የላቀ ብቃት ያላቸውን እንደመረጠ ተገንዝቦ ነበር። ይሖዋ “ጸሎት ሰሚ” እንደመሆኑ መጠን ማንኛውም ሰው የሚያቀርበውን ከልብ የመነጨ ጸሎት መስማት ያስደስተዋል። (መዝ. 65:2) አንድ ሰው በጣም ስላሳሰበው ጉዳይ ለሰዓታት ቢጸልይ እንኳ ይሖዋ ጊዜውን እንደወሰደበት አይሰማውም።

አምላክ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነው

ይሖዋ በሚከተሉት መንገዶች ምሳሌ ትቶልናል፦ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነው

አንዳንድ ጊዜ ጥሩ ጓደኛሞችም እንኳ በደልን ይቅር ማለት ይከብዳቸዋል። ይቅርታ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ስለሚሆንባቸው ለረጅም ጊዜ የቆየ ወዳጅነታቸውን የሚያፈርሱ ሰዎች አሉ። ይሖዋ ግን እንዲህ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ “ይቅርታው ብዙ” ስለሆነ ቅን ልብ ያላቸው ግለሰቦች ሁሉ ምሕረት እንዲያደርግላቸው ሊለምኑት እንደሚችሉ ይናገራል። (ኢሳ. 55:6, 7) ይሁንና አምላክ በነፃ ይቅር እንዲል የሚገፋፋው ምንድን ነው?

ተወዳዳሪ የሌለው ፍቅር ስላለው ነው። አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ፣ ሰዎችን ከኃጢአትና ኃጢአት በሰው ልጆች ላይ ካስከተለው ጉዳት ለማዳን ልጁን ኢየሱስን ሰጥቷል። (ዮሐ. 3:16) ቤዛው  ከዚህም የበለጠ ነገር ያከናውናል። አምላክ የሚወዳቸውን ሰዎች በክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት በነፃ ይቅር ይላል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ኃጢአታችንን የምንናዘዝ ከሆነ እሱ ታማኝና ጻድቅ ስለሆነ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐ. 1:9) ይሖዋ መሐሪ በመሆኑ ሰዎች ከእሱ ጋር የመሠረቱትን ወዳጅነት ጠብቀው መኖር ይችላሉ፤ ይህን ማወቃችን ደግሞ ልባችን እንዲነካ ያደርጋል።

በምትፈልገው ጊዜ ይደርስልሃል

ይሖዋ በሚከተሉት መንገዶች ምሳሌ ትቶልናል፦ በምትፈልገው ጊዜ ይደርስልሃል

እውነተኛ ወዳጅ፣ ጓደኞቹ እርዳታ ሲፈልጉ ይደርስላቸዋል። ይሖዋስ እንዲህ ያደርጋል? የአምላክ ቃል፣ የይሖዋ አገልጋይ ስለሆነ ሰው ሲናገር “ቢወድቅም እንኳ አይዘረርም፤ ይሖዋ እጁን ይዞ ይደግፈዋልና” ይላል። (መዝ. 37:24) ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች ‘አገልጋዮቹን ይደግፋል።’ ሴንት ክሮይ ከተባለችው የካሪቢያን ደሴት የተገኘውን የሚከተለውን ተሞክሮ ተመልከት።

አንዲት ልጅ፣ በእምነቷ ምክንያት ለባንዲራ ሰላምታ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነችም፤ በመሆኑም የክፍሏ ተማሪዎች ጫና አሳደሩባት። ይህች ልጅ ይሖዋ እንዲረዳት ከጸለየች በኋላ ችግሩን ለመጋፈጥ ወሰነች። ከዚያም በክፍሏ ልጆች ፊት ሪፖርት የማቅረብ አጋጣሚ ስታገኝ ለባንዲራ ሰላምታ መስጠትን በተመለከተ ተናገረች። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተሰኘውን መጽሐፍ ተጠቅማ የሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ታሪክ ውሳኔ ለማድረግ እንዴት እንደረዳት አብራራች። ቀጥላም “ይሖዋ ለእነዚያ ሦስት ዕብራውያን ጥበቃ ያደረገላቸው ምስሉን ለማምለክ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው” አለች። ከዚያም በክፍሉ ውስጥ የሚገኙት ተማሪዎች መጽሐፉን እንዲወስዱ ጋበዘቻቸው። አብረዋት ከሚማሩት ልጆች መካከል አሥራ አንዱ የየራሳቸው ቅጂ እንዲሰጣቸው ፈለጉ። ይህች ልጅ፣ አወዛጋቢ ከሆነው ከዚህ ርዕስ ጋር በተያያዘ ምሥክርነት መስጠት በመቻሏ በጣም ተደሰተች፤ ይህን ማድረግ የቻለችው ከይሖዋ ባገኘችው ብርታትና ጥበብ መሆኑን ተገንዝባ ነበር።

ይሖዋ ለአንተም እንደሚያስብልህ ከተጠራጠርክ እንደ መዝሙር 34:17-19፤ 55:22፤ 145:18, 19 ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ አሰላስል። በእውነት ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆዩ የይሖዋ ምሥክሮችን፣ ይሖዋ እንደሚያስብላቸው በሕይወታቸው ውስጥ የተመለከቱት እንዴት እንደሆነ ጠይቃቸው። የአምላክን እርዳታ በምትፈልግበት ጊዜ ስለ ጉዳዩ ወደ እሱ ጸልይ። ይሖዋ ‘ስለ አንተ እንደሚያስብ’ የሚያሳይ ማስረጃ ታገኛለህ።