በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

‘እጆቻችሁ አይዛሉ’

‘እጆቻችሁ አይዛሉ’

‘እጆቻችሁ አይዛሉ።’—ሶፎ. 3:16

መዝሙሮች፦ 81, 32

1, 2. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ምን ዓይነት ችግሮች ያጋጥሟቸዋል? ይህስ ምን ያስከትልባቸዋል? (ለ) ኢሳይያስ 41:10, 13 ምን አስተማማኝ ተስፋ ይሰጣል?

የአንድ ሽማግሌ ሚስት የሆነች አንዲት የዘወትር አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ቢኖረኝም ለዓመታት ከጭንቀት ጋር ስታገል ኖሬያለሁ። የሚሰማኝ ጭንቀት፣ እንቅልፍ የሚነሳኝ ከመሆኑም ሌላ በጤንነቴና ከሌሎች ጋር ባለኝ ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፤ አንዳንድ ጊዜ፣ ‘ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጌ በተውኩትና የሆነ ነገር ውስጥ ገብቼ በተሸሸግኩ’ ብዬ እመኛለሁ።”

2 የዚህችን እህት ስሜት መረዳት ትችላለህ? ክፉ የሆነው የሰይጣን ዓለም ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድርብን ሲሆን ይህም ጭንቀት ሊፈጥርብንና ከባድ ሸክም የተጫነን ያህል እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል። የሚሰማን ጭንቀት አንዲትን መርከብ ወዴትም እንዳትንቀሳቀስ ወጥሮ ከሚይዛት መልሕቅ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። (ምሳሌ 12:25) እንዲህ እንዲሰማህ የሚያደርግህ ምን ሊሆን ይችላል? የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ወይም በከባድ ሕመም እየተሠቃየህ ይሆናል፤ አሊያም ኑሮ በተወደደበት በዚህ ዘመን ለቤተሰብህ የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ እየታገልክ ወይም ደግሞ ስደት እየደረሰብህ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለው ውጥረት፣ ውሎ አድሮ ኃይልህን ያሟጥጠዋል፤ አልፎ ተርፎም ደስታህን ያሳጣሃል። ይሁንና አምላክ አንተን ለመርዳት እጁን እንደሚዘረጋልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—ኢሳይያስ 41:10, 13ን አንብብ።

3, 4. (ሀ) ‘እጅ’ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በየትኞቹ መንገዶች ተሠርቶበታል? (ለ) እጃችን እንዲዝል የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?

3 ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ባሕርያትንና ድርጊቶችን በምሳሌያዊ መንገድ ለመግለጽ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን ይጠቀማል። ለአብነት  ያህል፣ ‘እጅ’ በመቶዎች በሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል። የአንድን ሰው እጅ ማበርታት ሲባል ማበረታቻ መስጠትን፣ ማጠናከርን እንዲሁም ለተግባር ማነሳሳትን ሊያመለክት ይችላል። (1 ሳሙ. 23:16 ግርጌ፤ ዕዝራ 1:6 ግርጌ) በተጨማሪም ግለሰቡ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አዎንታዊና ብሩህ አመለካከት መያዙን ሊጠቁም ይችላል።

4 በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ተስፋ መቁረጡን ለማመልከት እጆቹ እንደዛሉ ተደርጎ የተገለጸበት ጊዜ አለ። (2 ዜና 15:7 ግርጌ፤ ዕብ. 12:12) በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያለ ሰው፣ ሁሉ ነገር ይጨልምበታል። አንተስ ውጥረት የሚፈጥርብህ ወይም ኃይልህ እንደተሟጠጠ፣ ስሜትህ እንደተደቆሰና በመንፈሳዊም እየተዳከምክ እንደሆነ እንዲሰማህ የሚያደርግ ሁኔታ ቢያጋጥምህ የሚያስፈልግህን ብርታት ማግኘት የምትችለው ከየት ነው? ለመጽናትና ደስተኛ ለመሆን የሚያስችልህን ማበረታቻና ጥንካሬ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

“የይሖዋ እጅ ማዳን ይሳናት ዘንድ አላጠረችም”

5. (ሀ) ችግሮች ሲያጋጥሙን ምን እናደርግ ይሆናል? ይሁንና ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

5 ሶፎንያስ 3:16, 17ን አንብብ። ችግሮች ሲያጋጥሙን፣ በፍርሃት መራድና ተስፋ መቁረጥ በምሳሌያዊ አባባል እጆቻችን እንዲዝሉ መፍቀድ አይኖርብንም፤ ከዚህ ይልቅ ‘የሚያስጨንቀንን ነገር ሁሉ’ አሳቢ በሆነው በአባታችን ‘በይሖዋ ላይ ላይ እንጣል።’ (1 ጴጥ. 5:7) አምላክ ለእስራኤላውያን የተናገረውን ነገር ማስታወሳችን ይጠቅመናል፤ ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዮቹን ‘ለማዳን’ ኃያል የሆነው ‘እጁ አጭር’ እንዳልሆነ ገልጿል። (ኢሳ. 59:1) ሕዝቦቹ ከአቅማቸው በላይ የሚመስሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ይሖዋ ፈቃዱን እንዲያደርጉ እነሱን ለማበረታታት ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው እንዳለው የሚያሳዩ ሦስት ግሩም የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመለከታለን። አንተም ከእነዚህ ምሳሌዎች ምን ማበረታቻ ማግኘት እንደምትችል ለማስተዋል ሞክር።

6, 7. እስራኤላውያን በአማሌቃውያን ላይ ድል ከተጎናጸፉበት መንገድ ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን?

6 እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት በተአምራዊ መንገድ ነፃ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ አማሌቃውያን ጥቃት ሰነዘሩባቸው። ደፋር የሆነው ኢያሱ የሙሴን አመራር በመከተል እስራኤላውያንን እየመራ ለጦርነት ዘመተ። በዚህ ጊዜ ሙሴ፣ ከአሮንና ከሁር ጋር በመሆን በአቅራቢያው ወደሚገኝና ጦር ሜዳውን ለማየት ወደሚያስችል ኮረብታ ወጣ። እነዚህ ሦስት ሰዎች ፈርተው ከጦርነቱ መሸሻቸው ነበር? በፍጹም!

7 ሙሴ ይህን ያደረገው እስራኤላውያን ድል እንዲቀዳጁ የሚያስችላቸውን ስልት ለመጠቀም ስላሰበ ነው። በመሆኑም ሙሴ የእውነተኛውን አምላክ በትር በእጆቹ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ያዘ። እሱ እጆቹን እስካላወረደ ድረስ እስራኤላውያን በአማሌቃውያን ላይ እንዲያይሉና ድል እንዲያደርጓቸው ይሖዋ ይረዳቸው ነበር። ይሁንና ሙሴ እጆቹ ሲዝሉ ወደ ታች ያወርዳቸው ነበር፤ በዚህ ጊዜ አማሌቃውያን ያይሉባቸዋል። አሮንና ሁር ይህን ሲመለከቱ ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ “ድንጋይ ወስደው [ከሙሴ ሥር] አስቀመጡለት፤ እሱም በድንጋዩ ላይ ተቀመጠ። ከዚያም አሮንና ሁር አንዱ በአንደኛው በኩል፣ ሌላው ደግሞ በሌላኛው በኩል ሆነው እጆቹን ደገፉለት፤ በመሆኑም ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ እጆቹ ባሉበት ጸኑ።” እስራኤላውያን፣ አምላክ በኃያል እጁ ስለደገፋቸው በውጊያው ድል አደረጉ።—ዘፀ. 17:8-13

8. (ሀ) ኢትዮጵያውያን በይሁዳ ላይ በተነሱ ጊዜ አሳ ምን አደረገ? (ለ) እኛስ እንደ አሳ በአምላክ መታመን የምንችለው እንዴት ነው?

8 ይሖዋ በንጉሥ አሳ ዘመንም እጁ አጭር እንዳልሆነ አሳይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለተለያዩ ጦርነቶች ይጠቅሳል። ይሁንና እስራኤላውያንን ለመውጋት ከመጡት ሠራዊቶች ሁሉ ትልቁ፣ ኢትዮጵያዊው ዛራ ያሰለፈው ሠራዊት ነበር። ዛራ፣ ልምድ ያላቸው 1,000,000 ወታደሮች ነበሩት። የኢትዮጵያውያኑ ሠራዊት ከአሳ ሠራዊት በእጥፍ ይበልጥ ነበር። አሳ ይህን ሲያይ በጭንቀትና በፍርሃት ተውጦ እጆቹ ቢዝሉ የሚገርም አይሆንም ነበር። አሳ ግን ይሖዋ እንዲረዳው ወዲያውኑ ወደ እሱ ዞር አለ። ኢትዮጵያውያኑ ከነበራቸው ሠራዊት አንጻር እነሱን ማሸነፍ  ፈጽሞ የማይቻል ነገር ይመስል ይሆናል፤ “በአምላክ ዘንድ ግን ሁሉ ነገር ይቻላል።” (ማቴ. 19:26) አምላክ ታላቅ ኃይሉን ተጠቅሞ “ኢትዮጵያውያንን በአሳ . . . ፊት ድል አደረጋቸው”፤ አሳ “በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ልቡ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ ነበር።”—2 ዜና 14:8-13፤ 1 ነገ. 15:14

9. (ሀ) ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች መልሶ እንዳይገነባ የትኛው ሁኔታ እንቅፋት እንዲሆንበት አልፈቀደም? (ለ) አምላክ የነህምያን ጸሎት የመለሰለት እንዴት ነው?

9 እስቲ አሁን ደግሞ ነህምያ ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት፤ ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት ጊዜ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል አስበው። ከተማዋ ለጥቃት የተጋለጠች ነበረች፤ በዚያ የሚኖሩት አይሁዳውያንም በጣም ተስፋ ቆርጠዋል። የባዕድ አገር ዜጎች የሆኑት ተቃዋሚዎቻቸው በሚሰነዝሩባቸው ዛቻ የተነሳ እጃቸው በመዛሉ የኢየሩሳሌምን ቅጥር መልሰው መገንባታቸውን አቁመው ነበር። ታዲያ ነህምያስ በዚህ ሁኔታ ተስፋ ቆርጦ እጆቹ እንዲዝሉ ፈቅዶ ይሆን? በጭራሽ! ልክ እንደ ሙሴ፣ አሳና ሌሎች ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ሁሉ ነህምያም ወደ ይሖዋ የመጸለይ ልማድ ነበረው፤ ይህም በእሱ እንደሚታመን የሚያሳይ ነው። በዚህ ወቅትም ያደረገው ይህንኑ ነው። አይሁዳውያኑ ከአቅማቸው በላይ የሆነ መሰናክል እንደተጋረጠባቸው ተሰምቷቸው ነበር፤ ይሖዋ ግን ነህምያ ላቀረበው ልባዊ ጸሎት ምላሽ በመስጠት ‘በታላቅ ኃይሉ’ እና ‘በብርቱ እጁ’ ተጠቅሞ የዛሉትን የአይሁዳውያኑን እጆች አበረታ። (ነህምያ 1:10ን፤ 2:17-20ን፤ 6:9ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜስ ይሖዋ ‘በታላቅ ኃይሉ’ እና ‘በብርቱ እጁ’ ተጠቅሞ አገልጋዮቹን እንደሚያበረታ እምነት አለህ?

ይሖዋ እጃችሁን ያበረታል

10, 11. (ሀ) ሰይጣን እጃችን እንዲዝል ለማድረግ የሚሞክረው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ለእኛ ብርታትና ኃይል ለመስጠት በየትኞቹ መንገዶች ይጠቀማል? (ሐ) ከቲኦክራሲያዊ ትምህርቶችና ሥልጠናዎች ምን ጥቅም አግኝተሃል?

10 ዲያብሎስ፣ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎቻችንን እንዳናከናውን ለማደናቀፍ በሚያደርገው ጥረት ተስፋ ቆርጦ እጁን አጣጥፎ ይቀመጣል ብለን ፈጽሞ መጠበቅ የለብንም። መንግሥታት፣ የሃይማኖት መሪዎችና ከሃዲዎች ዛቻ እንዲሰነዝሩብን ብሎም ስለ እኛ ውሸት እንዲያናፍሱ ያደርጋል። ዓላማው ምንድን ነው? እጃችን እንዲዝልና የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩን ሥራ እንድናቆም ማድረግ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እኛን ለማበርታት ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ አለው። (1 ዜና 29:12) በመሆኑም ሰይጣንና ይህ ክፉ ሥርዓት የሚያመጡብንን ማንኛውንም ፈተና መቋቋም እንድንችል ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን መጠየቃችን ወሳኝ ነገር ነው። (መዝ. 18:39፤ 1 ቆሮ. 10:13) በተጨማሪም በአምላክ ቅዱስ መንፈስ መሪነት የተጻፈው ቃሉ ስላለን እጅግ አመስጋኞች ነን። እስቲ በየወሩ ስለምናገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መንፈሳዊ ምግብም አስቡ። በዘካርያስ 8:9, 13 (ጥቅሱን አንብብ) ላይ የሚገኘው ትንቢት የተነገረው በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ በድጋሚ በሚገነባበት ወቅት ነው፤ በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ማበረታቻ ለእኛም በጣም ጠቃሚ ነው።

11 ከዚህም ሌላ በጉባኤ ስብሰባዎችና በትላልቅ ስብሰባዎች እንዲሁም በቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች አማካኝነት ከሚሰጠን ትምህርት ብርታት እናገኛለን። የምናገኘው ሥልጠና መንፈሳዊ ግቦች እንድናወጣ እንዲሁም ያሉብንን በርካታ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶች እንድንፈጽም ያነሳሳናል። (መዝ. 119:32) አንተስ በዚህ መንገድ ከሚቀርብልን ትምህርት ብርታት ለማግኘት እንደምትጓጓ ታሳያለህ?

12. በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆነን ለመቀጠል ምን ማድረግ ይኖርብናል?

12 ይሖዋ፣ አማሌቃውያንን እና ኢትዮጵያውያንን ድል እንዲያደርጉ እስራኤላውያንን ረድቷቸዋል፤ ለነህምያና አብረውት ለነበሩት አይሁዳውያንም የከተማዋን ቅጥር እንደገና ገንብተው ለማጠናቀቅ የሚያስችል ኃይል ሰጥቷቸዋል። ዛሬም በተመሳሳይ የሚያጋጥመንን ተቃውሞ፣ የሰዎችን ግዴለሽነትና ያለብንን ጭንቀት ተቋቁመን የስብከቱን ሥራ ማከናወን እንድንችል ብርታት ይሰጠናል። (1 ጴጥ. 5:10) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ተአምር ይፈጽምልናል ብለን መጠበቅ የለብንም። ከዚህ ይልቅ እኛ የበኩላችንን ማድረግ ይኖርብናል። ይህም የአምላክን ቃል በየዕለቱ ማንበብን፣ ለሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን መዘጋጀትንና በስብሰባዎች ላይ መገኘትን፣ በግል ጥናትና በቤተሰብ አምልኮ  አማካኝነት በመንፈሳዊ ራሳችንን መመገብን እንዲሁም በይሖዋ በመታመን አዘውትረን ወደ እሱ መጸለይን ይጨምራል። ሌሎች እንቅስቃሴዎች፣ ይሖዋ እኛን ለማበርታትና ለማጠናከር ባደረጋቸው ዝግጅቶች እንዳንጠቀም እንቅፋት እንዲሆኑብን ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም። ከላይ ከተጠቀሰው ከየትኛውም ዝግጅት ጋር በተያያዘ እጃችሁ እንደዛለ ከተሰማችሁ አምላክ እንዲረዳችሁ ጸልዩ። ከዚያም መንፈሱ “ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ለተግባር እንድትነሳሱ በማድረግ ኃይል የሚሰጣችሁ” እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክሩ። (ፊልጵ. 2:13) በሌላ በኩል ደግሞ የሌሎችን እጆች ማበርታት የምትችሉት እንዴት ነው?

የዛሉትን እጆች አበርቱ

13, 14. (ሀ) ባለቤቱን በሞት ያጣ አንድ ወንድም የተበረታታው እንዴት ነው? (ለ) ሌሎችን ማበረታታት የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

13 ይሖዋ፣ ማበረታቻ ሊሰጡን የሚችሉ አሳቢ የሆኑ ወንድሞች የሚገኙበት ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር ሰጥቶናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የዛሉትን እጆችና የተብረከረኩትን ጉልበቶች አበርቱ፤ . . . እግራችሁ ዘወትር ቀና በሆነ መንገድ እንዲጓዝ አድርጉ” በማለት እንደጻፈ አስታውሱ። (ዕብ. 12:12, 13) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ በርካታ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለ መንፈሳዊ ማበረታቻ አግኝተዋል። በዛሬው ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንድ ወንድም ባለቤቱን በሞት ካጣና ሌሎች አሳዛኝ ሁኔታዎች ካጋጠሙት በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “የሚደርሱብንን ፈተናዎች መምረጥ እንደማንችል ተምሬያለሁ፤ ፈተናዎቹ የሚመጡበት ጊዜም ሆነ የፈተናዎቹ ብዛትም ቢሆን በእኛ ምርጫ ላይ የተመካ አይደለም። አንድ ሰው ውኃ ውስጥ እንዳይሰምጥ እንደሚረዳ የሚያንሳፍፍ ጃኬት ሁሉ፣ ጸሎትና የግል ጥናትም በፈተናዎቹ ብዛት ተሸንፌ እንዳልሰምጥ ረድተውኛል። መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ የሰጡኝ ድጋፍም በጣም አጽናንቶኛል። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከመፈጠራቸው በፊት በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ።”

እያንዳንዱ የጉባኤ አባል ሌሎችን ማበረታታት ይችላል (አንቀጽ 14ን ተመልከት)

14 አሮን እና ሁር በውጊያው ወቅት ቃል በቃል የሙሴን እጅ ደግፈውለት ነበር። እኛም ሌሎችን መደገፍና መርዳት የምንችልባቸውን መንገዶች መፈለግ እንችላለን። ማንን መርዳት እንችላለን? የዕድሜ መግፋት፣ የጤና እክል፣ የቤተሰብ ተቃውሞ፣ ብቸኝነት ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ከሚያስከትለው ተፈታታኝ ሁኔታ ጋር እየታገሉ ያሉ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መርዳት እንችላለን። በተጨማሪም መጥፎ ነገር እንዲሠሩ ወይም በዚህ ሥርዓት በትምህርትም ይሁን በሙያቸው ጥሩ ደረጃ የሚባለው ቦታ ላይ እንዲደርሱ አሊያም ሀብት እንዲያሳድዱ ከፍተኛ ጫና የሚደርስባቸውን ወጣቶች ማበረታታት እንችላለን። (1 ተሰ. 3:1-3፤ 5:11, 14) ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር በመንግሥት አዳራሽ ውስጥም ሆነ በአገልግሎት ላይ ስትሆኑ አሊያም አብራችሁ ስትመገቡ ወይም በስልክ ስታወሩ ልባዊ አሳቢነት ልታሳዩ የምትችሉባቸውን መንገዶች ለማሰብ ሞክሩ።

15. የሚያበረታታ ሐሳብ መስጠታችሁ በእምነት ባልንጀሮቻችሁ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል?

15 አሳ አስደናቂ ድል ከተቀዳጀ በኋላ ነቢዩ አዛርያስ፣ ንጉሡንና ሕዝቡን “እናንተ ግን የድካማችሁን ዋጋ ስለምታገኙ በርቱ፤ እጆቻችሁ አይዛሉ” በማለት አበረታቷቸዋል። (2 ዜና 15:7 ግርጌ) ይህ ማበረታቻ አሳ ንጹሑን አምልኮ መልሶ ለማቋቋም ሲል ብዙ ለውጦችን እንዲያካሂድ አነሳስቶታል። በተመሳሳይም የምትናገሩት የሚያበረታታ ቃል በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በዚህ መንገድ ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል እንዲነሳሱ ልትረዷቸው ትችላላችሁ። (ምሳሌ 15:23) በስብሰባዎች ላይ እጃችሁን አውጥታችሁ የሚያንጽ ሐሳብ መስጠታችሁም ሌሎችን በጣም ያበረታታል።

16. ሽማግሌዎች የነህምያን ምሳሌ በመከተል የጉባኤያቸውን አባላት እጆች ማበርታት የሚችሉት እንዴት ነው? የእምነት ባልንጀሮችህ በግለሰብ ደረጃ እንዴት እንደረዱህ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ተናገር።

16 ነህምያና አብረውት የነበሩት ሰዎች የይሖዋን እርዳታ በማግኘታቸው እጃቸውን አበርትተው ሥራውን ማከናወን ችለዋል። በመሆኑም የኢየሩሳሌምን ቅጥር በ52 ቀናት ውስጥ ገንብተው ማጠናቀቅ ችለዋል! (ነህ. 2:18 ግርጌ፤ 6:15, 16) ነህምያ ሥራውን በበላይነት በመከታተል ብቻ ከመወሰን ይልቅ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች መልሶ በመገንባቱ ሥራ ተካፍሏል።  (ነህ. 5:16) በተመሳሳይም በርካታ አፍቃሪ ሽማግሌዎች፣ በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በመካፈል ወይም የመንግሥት አዳራሻቸውን በማጽዳቱና በማደሱ ሥራ ላይ በመሳተፍ የነህምያን ምሳሌ ተከትለዋል። በተጨማሪም ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር አብረው ያገለግላሉ እንዲሁም እረኝነት ያደርጉላቸዋል፤ በዚህ መንገድ፣ በጭንቀት የተዋጠ ልብ ያላቸውን አስፋፊዎች የዛሉ እጆች ያበረታሉ።—ኢሳይያስ 35:3, 4ን አንብብ።

‘እጆቻችሁ አይዛሉ’

17, 18. ችግሮች ሲያጋጥሙን ወይም ስንጨነቅ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

17 ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ማገልገላችን አንድነት እንዲኖረን ያደርጋል። በተጨማሪም ዘላቂ ወዳጅነት እንድንመሠርትና የአምላክ መንግሥት በሚያመጣቸው በረከቶች ላይ ያለን እምነት እንዲጠናከር ይረዳናል። የሌሎችን እጅ በምናበረታበት ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችን እንዲቋቋሙ ብሎም ስለ ወደፊቱ ጊዜ አዎንታዊና ብሩህ አመለካከት እንዲኖራቸው እንረዳቸዋለን። ከዚህም ሌላ ለሌሎች እንዲህ ዓይነት እገዛ ማድረጋችን እኛም ምንጊዜም መንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት እንድናደርግና አምላክ ያዘጋጀልን ሽልማት እውን ሆኖ እንዲታየን ያደርጋል። በእርግጥም ሌሎችን ስናበረታታ የእኛም እጆች ይበረታሉ።

18 ይሖዋ፣ በጥንት ጊዜ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ታማኝ አገልጋዮቹን እንዴት እንደረዳቸውና ጥበቃ እንዳደረገላቸው መመልከታችን በዛሬው ጊዜ በእሱ ላይ እንድንተማመን ያደርገናል። እንግዲያው ተጽዕኖ ሲደርስባችሁና ችግሮች ሲያጋጥሟችሁ ‘እጆቻችሁ አይዛሉ!’ ይልቁንም በጸሎት የይሖዋን እርዳታ ጠይቁ፤ እንዲሁም በኃያል እጁ እንዲያጠነክራችሁና የመንግሥቱን በረከቶች ለማግኘት እንዲረዳችሁ ፍቀዱለት።—መዝ. 73:23, 24