በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  መጋቢት 2016

ወጣቶች—ለመጠመቅ ዝግጁ ናችሁ?

ወጣቶች—ለመጠመቅ ዝግጁ ናችሁ?

“ከእናንተ መካከል፣ ግንብ ለመገንባት ፈልጎ ለመጨረስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን የማያሰላ ማን ነው?”ሉቃስ 14:28

መዝሙሮች፦ 120, 64

እነዚህ ሁለት ርዕሶች የተዘጋጁት ለመጠመቅ እያሰቡ ላሉ ወጣቶች ነው

1, 2. (ሀ) በዛሬው ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች እንዲደሰቱ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያን ወላጆችና ሽማግሌዎች ጥምቀት ምን ትርጉም እንዳለው እንዲገነዘቡ ወጣቶችን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

አንድ ሽማግሌ የ12 ዓመቱን ክርስቶፈርን እንዲህ አለው፦ “ከተወለድክበት ጊዜ አንስቶ ነው የማውቅህ፤ እናም መጠመቅ እንደምትፈልግ በመስማቴ በጣም ተደስቻለሁ። አንድ ጥያቄ ብጠይቅህ ግን ደስ ይለኛል፦ ‘መጠመቅ የፈለግከው ለምንድን ነው?’” ሽማግሌው ይህን ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ነው። ሁላችንም በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች እንደሚጠመቁ ማወቃችን በጣም እንደሚያስደስተን ግልጽ ነው። (መክ. 12:1) በሌላ በኩል ደግሞ ክርስቲያን ወላጆችና የጉባኤ ሽማግሌዎች እነዚህ ወጣቶች ለመጠመቅ የወሰኑት በራሳቸው ተነሳሽነት መሆኑን ብቻ ሳይሆን በሚገባ አስበውበት ጭምር መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ።

 2 የአምላክ ቃል እንደሚያሳየው አንድ ክርስቲያን ራሱን ወስኖ በሚጠመቅበት ጊዜ በሕይወቱ ውስጥ የይሖዋን በረከት እንደሚያገኝ ብቻ ሳይሆን ከሰይጣን ዲያብሎስ ተቃውሞ እንደሚደርስበትም መጠበቅ ይኖርበታል። (ምሳሌ 10:22፤ 1 ጴጥ. 5:8) በመሆኑም ክርስቲያን ወላጆች የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ጊዜ ወስደው ልጆቻቸውን ያስተምራሉ። ወላጆቻቸው የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ወጣቶችን ደግሞ የጉባኤው ሽማግሌዎች የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ምን ወጪ እንደሚያስከፍላቸው እንዲያሰሉ በፍቅር ይረዷቸዋል። (ሉቃስ 14:27-30ን አንብብ።) አንድን ሕንፃ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ማውጣት እንደሚጠይቅ ሁሉ ይሖዋን በታማኝነት “እስከ መጨረሻው” ለማገልገልም ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል። (ማቴ. 24:13) ይሁንና ወጣቶች በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ይሖዋን በቁርጠኝነት ለማገልገል በግለሰብ ደረጃ ምን ማድረግ ይችላሉ? እስቲ እንመልከት።

3. (ሀ) ኢየሱስና ጴጥሮስ የተናገሩት ሐሳብ ስለ ጥምቀት አስፈላጊነት ምን ያስገነዝበናል? (ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ጴጥ. 3:21) (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን? ለምንስ?

3 ለመጠመቅ እያሰብክ ያለህ ወጣት ነህ? ከሆነ ልትመሰገን ይገባል! ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር መሆን ትልቅ መብት ነው። በተጨማሪም ጥምቀት ከእያንዳንዱ ክርስቲያን የሚጠበቅ ብቃት ከመሆኑም ሌላ መዳን ለማግኘት ሊወሰድ የሚገባው ወሳኝ እርምጃ ነው። (ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ጴጥ. 3:21) ለይሖዋ የምትገባውን ቃል የመጠበቅ ልባዊ ፍላጎት ስላለህ በሕይወትህ ለምትወስደው ለዚህ ትልቅ እርምጃ አስቀድመህ መዘጋጀት እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። በመሆኑም ለጥምቀት ብቁ መሆን አለመሆንህን ለማወቅ በሚከተሉት ሦስት ጥያቄዎች ላይ ትኩረት ሰጥተህ ማሰብህ የተገባ ነው፦ (1) ይህን ውሳኔ ለማድረግ በሚያስችል የጉልምስና ደረጃ ላይ ደርሻለሁ? (2) ይህን እርምጃ የምወስደው በራሴ ፍላጎት ተነሳስቼ ነው? (3) ራስን ለይሖዋ መወሰን ምን ትርጉም እንዳለው ገብቶኛል? እስቲ እነዚህን ጥያቄዎች አንድ በአንድ እንመርምር።

ጉልምስና ላይ መድረስ

4, 5. (ሀ) መጠመቅ ያለባቸው በዕድሜ የበሰሉ ሰዎች ብቻ አይደሉም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን ጎለመሰ ሲባል ምን ማለት ነው?

4 መጠመቅ ያለባቸው በዕድሜ የበሰሉ ወይም ሕግ በሚፈቅደው መሠረት አንዳንድ መብቶች ለማግኘት  ዕድሜያቸው የሚፈቅድላቸው ሰዎች ብቻ እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። ምሳሌ 20:11 “ሕፃን እንኳ ባሕርይው ንጹሕና ትክክል መሆኑ በአድራጎቱ ይታወቃል” ይላል። በዕድሜ ትንሽ ሊባል የሚችል ልጅ እንኳ ትክክለኛውን ነገር ማድረግና ራሱን ለፈጣሪው መወሰን ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ሊገነዘብ ይችላል። በመሆኑም አንድ ወጣት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከጎለመሰና ራሱን ለይሖዋ ከወሰነ መጠመቁ አስፈላጊ ብሎም ተገቢ እርምጃ ነው።—ምሳሌ 20:7

5 አንድ ሰው ጎለመሰ ሲባል ምን ማለት ነው? ጉልምስና ሲባል አካላዊ እድገት ማድረግ ማለት ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የጎለመሱ ሰዎች “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት [አሠልጥነዋል]።” (ዕብ. 5:14) በመሆኑም የጎለመሱ ሰዎች በይሖዋ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር የሚያውቁ ከመሆኑም በላይ እነዚህን ነገሮች ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። ስለዚህ ስህተት የሆነውን ነገር ለማድረግ በቀላሉ አይፈተኑም፤ እንዲሁም ትክክል የሆነውን ነገር ለመፈጸም ሁልጊዜ ጉትጎታ አያስፈልጋቸውም። በእርግጥም አንድ የተጠመቀ ወጣት ወላጆቹ ወይም ሌሎች አዋቂዎች በሌሉበት እንኳ የአምላክን መሥፈርቶች ይጠብቃል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው።—ከፊልጵስዩስ 2:12 ጋር አወዳድር።

6, 7. (ሀ) ዳንኤል በባቢሎን መኖር በጀመረበት ጊዜ ያጋጠሙትን ፈታኝ ሁኔታዎች ግለጽ። (ለ) ዳንኤል የጎለመሰ ሰው መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

6 ወጣቶች በእርግጥ እንዲህ ያለ ጉልምስና ሊያሳዩ ይችላሉ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የዳንኤልን ምሳሌ እንመልከት። ዳንኤል ከወላጆቹ ተነጥሎ ወደ ባቢሎን በግዞት ሲወሰድ ገና በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወጣት ሳይሆን አይቀርም። ዳንኤል ድንገት ሁኔታው ተቀይሮ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ፈጽሞ የተለየ አመለካከት ባላቸው ሰዎች መካከል መኖር ጀመረ። ሌላም ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሞታል፦ በባቢሎን ውስጥ በሌሎች ዘንድ በጣም ተፈላጊ ሰው ሆነ። ዳንኤል ንጉሡ ፊት እንዲቆሙ ተመርጠው ከመጡ ጥቂት ወጣቶች አንዱ ነበር! (ዳን. 1:3-5, 13) በእስራኤል ፈጽሞ ሊያገኛቸው የማይችሉ አጋጣሚዎች ባቢሎን ውስጥ የተከፈቱለት ይመስላል።

7 ይህ ሁሉ ሲሆን ወጣቱ ዳንኤል ምን ተሰማው? የባቢሎን ውበትና ክብር ቀልቡን ስቦት ይሆን? የሚኖርበት አዲስ አካባቢ ማንነቱን እንዲቀይርበት ወይም እምነቱን እንዲያዳክምበት ፈቅዷል? በጭራሽ! መጽሐፍ ቅዱስ ዳንኤል ባቢሎን በነበረበት ጊዜ ከሐሰት አምልኮ ጋር ንክኪ ባላቸው ነገሮች “ላለመርከስ በልቡ ቁርጥ ውሳኔ” ማድረጉን ይገልጻል። (ዳን. 1:8) አዎ፣ ዳንኤል የሚደነቅ ጉልምስና አሳይቷል!

አንድ የጎለመሰ ወጣት በመንግሥት አዳራሽ የአምላክ ወዳጅ፣ በትምህርት ቤት ደግሞ የዓለም ወዳጅ መስሎ ለመታየት አይሞክርም (አንቀጽ 8ን ተመልከት)

8. ዳንኤል ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?

8 ዳንኤል ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ? አንደኛ ነገር የጎለመሰ ወጣት ያመነበትን ነገር አጥብቆ ይይዛል። ከአካባቢው ጋር ለመመሳሰል ሲል ቀለሙን እንደሚቀያይር እስስት አይደለም። በመንግሥት አዳራሽ የአምላክ ወዳጅ፣ በትምህርት ቤት ደግሞ የዓለም ወዳጅ መስሎ ለመታየት አይሞክርም። የእምነት ፈተና በሚያጋጥመው ጊዜ እንኳ ከመወላወል ይልቅ ከአቋሙ ፍንክች አይልም።ኤፌሶን 4:14, 15ን አንብብ።

9, 10. (ሀ) ወጣቶች በቅርቡ ላጋጠሟቸው የእምነት ፈተናዎች ምላሽ ስለሰጡበት መንገድ ማሰባቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው? (ለ) ጥምቀት ምን ትርጉም አለው?

9 እርግጥ ነው፣ ፍጹም የሆነ ሰው የለም፤ ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች አልፎ አልፎ ስህተት ይሠራሉ። (መክ. 7:20) ሆኖም ለመጠመቅ እያሰብክ እንደመሆኑ መጠን የይሖዋን መሥፈርቶች ለመጠበቅ ምን ያህል ቁርጥ አቋም እንዳለህ መገምገምህ ጥበብ ነው። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ‘አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች በጥብቅ በመከተል ረገድ ምን ዓይነት አቋም አለኝ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። በቅርቡ ላጋጠሙህ የእምነት ፈተናዎች ምን ምላሽ እንደሰጠህ ቆም ብለህ አስብ። ክፉን ከደጉ ለመለየት የሚያስችል ማስተዋል እንዳለህ አሳይተሃል? አንተስ ዳንኤል እንዳጋጠመው ሁሉ በሰይጣን ዓለም ውስጥ  ያለ ሰው ልዩ ቦታ ቢሰጥህ ምን ይሰማሃል? የአምላክ ፈቃድ፣ ለአንተ ፈተና ከሆነብህ ነገር ጋር በሚጋጭበት ጊዜም “የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ [ማስተዋል]” ትችላለህ?—ኤፌ. 5:17

10 እነዚህን ቀጥተኛ ጥያቄዎች ማንሳት ያስፈለገን ለምንድን ነው? እነዚህ ጥያቄዎች ለጥምቀት ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖርህ ይረዱሃል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ጥምቀት ለይሖዋ ቃል መግባትህን የምታሳይበት በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ውሳኔ ነው። በዚህ መንገድ ይሖዋን በሙሉ ልብ ለመውደድና እሱን ለዘላለም ለማገልገል ቃል ትገባለህ። (ማር. 12:30) ራሱን ወስኖ የተጠመቀ ሰው ሁሉ ቃሉን ጠብቆ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለበት።—መክብብ 5:4, 5ን አንብብ።

ለመጠመቅ የወሰንከው በራስህ ፍላጎት ተነሳስተህ ነው?

11, 12. (ሀ) ለመጠመቅ እያሰበ ያለ ሰው ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን አለበት? (ለ) ይሖዋ ስላደረገው የጥምቀት ዝግጅት ተገቢ አመለካከት እንዲኖርህ ምን ይረዳሃል?

11 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ወጣቶችን ጨምሮ የይሖዋ ሕዝብ በአጠቃላይ ለአምላክ አገልግሎት “በገዛ ፈቃዱ ራሱን ያቀርባል።” (መዝ. 110:3) በመሆኑም ለመጠመቅ የሚያስብ አንድ ሰው ይህን ውሳኔ የሚያደርገው በራሱ ፍላጎት ተነሳስቶ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን አለበት። ይህ ደግሞ ራስህን በጥሞና መመርመር ይጠይቅብህ ይሆናል። ለምን? በወጣትነት ዕድሜህ ያለህበት ሁኔታ ለየት ያለ ሊሆን ስለሚችል ነው። ለምሳሌ ያደግከው እውነት ቤት ውስጥ ሊሆን ይችላል።

12 ባለፉት ዓመታት አንዳንድ እኩዮችህን አልፎ ተርፎም ወንድሞችህንና እህቶችህን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ሲጠመቁ ተመልከተህ ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል? ጥምቀት፣ ይዋል ይደር እንጂ ሁሉም ወጣቶች የሆነ ዕድሜ ላይ ሲደርሱ በዘልማድ ሊወስዱት የሚገባ እርምጃ እንደሆነ አድርገህ እንዳታስብ ተጠንቀቅ። ታዲያ ይሖዋ ስላደረገው የጥምቀት ዝግጅት ተገቢ አመለካከት እንዲኖርህ ምን ይረዳሃል? መጠመቅ በጣም አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ቆም ብሎ ማሰብን ልማድ አድርግ። እንዲያውም በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ አጥጋቢ የሆኑ በርካታ ምክንያቶች ልታገኝ ትችላለህ።

13. ለመጠመቅ የወሰንከው ከልብህ ተነሳስተህ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ምን ማድረግ ትችላለህ?

13 ለመጠመቅ ውሳኔ ያደረግከው ከልብህ ተነሳስተህ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ የምትችልባቸው መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ይሖዋን ለማገልገል ያለህ ልባዊ ፍላጎት በምታቀርበው ጸሎት ላይ ሊታይ ይችላል። በተደጋጋሚ መጸለይህና በጸሎትህ ላይ አንዳንድ ነገሮችን ለይተህ መጥቀስህ ከይሖዋ ጋር ምን ያህል የጠበቀ ዝምድና እንዳለህ ሊያሳይ ይችላል። (መዝ. 25:4) ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጥበት አንዱ ወሳኝ መንገድ ቃሉ ላይ ትኩረት እንድናደርግ መርዳት ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የምናደርገው ጥረት ወደ ይሖዋ ለመቅረብና እሱን ከልብ ለማገልገል እንደምንፈልግ የሚታይበት ሌላ መንገድ ነው። (ኢያሱ 1:8) ስለዚህ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘የሚያሳስቡኝን ነገሮች ለይቼ በመጥቀስ የመጸለይ ልማድ አለኝ? በግሌ መጽሐፍ ቅዱስን የማጠናበት ቋሚ ፕሮግራም አለኝ?’ ቤተሰብህ፣ የቤተሰብ አምልኮ የሚያደርግ ከሆነ ደግሞ ‘ቤተሰባችን በሚያደርገው በዚህ ፕሮግራም ላይ በደስታ እሳተፋለሁ?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ ለመጠመቅ የወሰንከው በራስህ ፍላጎት ተነሳስተህ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ይረዳሃል።

ራስን መወሰን ሲባል ምን ማለት ነው?

14. ራስን በመወሰንና በመጠመቅ መካከል ያለውን ልዩነት ግለጽ።

14 አንዳንዶች ራስን በመወሰንና በመጠመቅ መካከል ያለው ልዩነት በግልጽ ላይገባቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ወጣቶች ራሳቸውን ለይሖዋ እንደወሰኑ፣ ለመጠመቅ ግን ዝግጁ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። ይህ አባባል ያስኬዳል? ራስን መወሰን ማለት ይሖዋን ለዘላለም እንደምታገለግለው በጸሎት መንገር ማለት ነው። አንድ ሰው  ሲጠመቅ፣ ራሱን መወሰኑን ሌሎች እንዲያውቁ ያደርጋል። በመሆኑም ጥምቀት፣ ለይሖዋ ባቀረብከው የግል ጸሎት አማካኝነት ቀደም ሲል ራስህን መወሰንህን ሰዎች እንዲያውቁ ማድረግ ማለት ነው። ከመጠመቅህ በፊት ራስን መወሰን ምን ትርጉም እንዳለው በሚገባ መረዳት ይኖርብሃል።

15. ራስን መወሰን ሲባል ምን ማለት ነው?

15 በቀላል አነጋገር፣ ራስህን ለይሖዋ ስትወስን ሕይወትህ የአንተ ንብረት መሆኑ ያበቃል ማለት ነው። በሕይወትህ ውስጥ የይሖዋን ፈቃድ ከምንም ነገር በላይ እንደምታስቀድም በመግለጽ ለእሱ ቃል ትገባለህ። (ማቴዎስ 16:24ን አንብብ።) መቼም ቢሆን ቃል ስትገባ ጉዳዩን አክብደህ ማየት ይኖርብሃል፤ ይህ ከሆነ ታዲያ ለይሖዋ አምላክ የምትገባውን ቃል እጅግ አክብደህ ልታየው አይገባም? (ማቴ. 5:33) ይሁንና ራስህን መካድህንና የይሖዋ መሆንህን ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?—ሮም 14:8

16, 17. (ሀ) ራስን መካድ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ። (ለ) አንድ ሰው ራሱን ሲወስን ምን እንዳለ ይቆጠራል?

16 ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አንድ ወዳጅህ መኪና በስጦታ ሰጠህ እንበል። ሊብሬውን ካስረከበህ በኋላ “ይሄ መኪና ያንተ ንብረት ነው” ይልሃል። አክሎ ግን “ቁልፉን አልሰጥህም። ደግሞም መኪናውን የምትነዳው አንተ ሳትሆን እኔ ነኝ” አለህ እንበል። ስለ “ስጦታው” ምን ይሰማሃል? “ስጦታውን” ስለሰጠህ ወዳጅህስ ምን ታስባለህ?

17 አሁን ደግሞ ይሖዋ ራሱን ከወሰነ ሰው ምን እንደሚጠብቅበት አስብ፤ ግለሰቡ “ሕይወቴን ሰጥቼሃለሁ። የአንተ ንብረት ነኝ” በማለት ራሱን ለይሖዋ ይወስናል። ሆኖም ይህ ሰው ሁለት ዓይነት ሕይወት የሚመራ ቢሆንስ? ምናልባት ከማያምን ሰው ጋር በድብቅ መጠናናት ቢጀምርስ? አሊያም ደግሞ በአገልግሎት ወይም በስብሰባዎች ላይ ለይሖዋ የሙሉ ነፍስ አገልግሎት ማቅረብ እንዲሳነው የሚያደርግ ሥራ ቢቀጠርስ? እንዲህ ማድረግ ‘የመኪናውን ቁልፍ አልሰጥህም’ ከማለት ተለይቶ ይታያል? ራሱን ለይሖዋ የሚወስን ግለሰብ እንዲህ የሚል ያህል ነው፦ “ሕይወቴ የእኔ ሳይሆን የአንተ ንብረት ነው። አንተ በምትጠብቅብኝና እኔ ማድረግ በምፈልገው ነገር መካከል ልዩነት ከተፈጠረ ምንጊዜም የአንተ ምርጫ ይቀድማል።” ይህ ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ “ከሰማይ የመጣሁት የራሴን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ነው” በማለት ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል።—ዮሐ. 6:38

18, 19. (ሀ) ሮዝና ክርስቶፈር የተናገሩት ሐሳብ ጥምቀት ብዙ በረከት የሚያስገኝ መብት እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) መጠመቅ መብት እንደሆነ ይሰማሃል? ለምንስ?

18 በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጥምቀት አንተም ሆንክ ሌላ ማንኛውም ሰው አቅልሎ ሊመለከተው የማይገባ ከባድ እርምጃ ነው። በተጨማሪም ራስን መወሰንና መጠመቅ ትልቅ መብት ነው። ይሖዋን የሚወዱና ራስን ለይሖዋ የመወሰን ትርጉም የገባቸው ወጣቶች ከመጠመቅ ወደኋላ አይሉም፤ እንዲሁም መቼም ቢሆን በዚህ ውሳኔያቸው አይቆጩም። ሮዝ የተባለች በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ የተጠመቀች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋን እወደዋለሁ፤ ደግሞም እሱን ከማገልገል የተሻለ ደስታ የሚያስገኝልኝ ነገር የለም። ይህ በሕይወቴ ካደረግኳቸው ውሳኔዎች ሁሉ በእርግጠኝነት የማምንበት ውሳኔ ነው።”

19 በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ ስለተጠቀሰው ስለ ክርስቶፈርስ ምን ማለት ይቻላል? በ12 ዓመቱ ለመጠመቅ ያደረገው ውሳኔ በሚገባ የታሰበበት ነበር? ክርስቶፈር ራሱን ለመወሰንና ለመጠመቅ ስላደረገው ውሳኔ ሲያስብ ደስ ይለዋል። በ17 ዓመቱ የዘወትር አቅኚ ሆኖ ማገልገል የጀመረ ሲሆን በ18 ዓመቱ ደግሞ የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ ተሾመ። በአሁኑ ጊዜ በቤቴል እያገለገለ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “መጠመቄ ትክክለኛ ውሳኔ ነበር። ለይሖዋና ለድርጅቱ የማከናውነው ሥራ በእርካታ የተሞላ ሕይወት እንድመራ አስችሎኛል።” አንተም ለመጠመቅ እያሰብክ ከሆነ ይህን እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።