ጥንት ከኖሩት ነቢያት ጋር የምትመሳሰልበት ነገር አለ? አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ የሚገኘው “የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፍቻ” ነቢይ ለሚለው ቃል የሚከተለውን ትርጉም ይሰጣል፦ “አምላክ ዓላማውን ለሰዎች ለመግለጽ የሚጠቀምበትን ግለሰብ ያመለክታል። ነቢያት፣ ትንቢት በመተንበይ ብቻ ሳይሆን የይሖዋን ትምህርቶች፣ ትእዛዞችና የፍርድ መልእክቶች ለሰዎች በመናገር የአምላክ ቃል አቀባይ ሆነው አገልግለዋል።” እርግጥ ነው፣ አንተ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አትተነብይም፤ ሆኖም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ሐሳብ በምታውጅበት ጊዜ አምላክን ወክለህ ትናገራለህ።—ማቴ. 24:14

ለሌሎች ስለ አምላካችን ስለ ይሖዋ መናገርና ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ ማስተማር ውድ መብት ነው! በዚህ ሥራ ስንሳተፍ ‘በሰማይ መካከል የሚበረው መልእክ’ አብሮን ይሠራል። (ራእይ 14:6) ይሁንና ይህ ግሩም መብት እንዳይታየን ሊያደርጉ የሚችሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙን ይሆናል። አንዳንዶቹ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? ሰውነታችን ሊዝል፣ ተስፋ ልንቆርጥ ወይም አልረባም የሚል ስሜት ሊያድርብን ይችላል። የጥንቶቹ ታማኝ ነቢያት እንዲህ ዓይነት ስሜት ተሰምቷቸዋል፤ ሆኖም እጅ አልሰጡም። ይሖዋ ደግሞ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዲችሉ ረድቷቸዋል። እስቲ አንዳንድ ሁኔታዎችን እናንሳና የነቢያትን ምሳሌ እንዴት መከተል እንደምንችል እንመልከት።

ጉልበታቸውን ሳይቆጥቡ ሠርተዋል

አንዳንድ ጊዜ የዕለት ተዕለት ሩጫ እንድንዝል ሊያደርገንና አገልግሎት የመውጣት ፍላጎታችንን ሊያጠፋው ይችላል። እርግጥ፣ እረፍት ማድረግ የግድ ያስፈልገናል፤ ኢየሱስና ሐዋርያቱም እንኳ አርፈዋል። (ማር. 6:31) ይሁንና በባቢሎን ስለነበረው ስለ ሕዝቅኤል እንዲሁም ከኢየሩሳሌም በምርኮ ከተወሰዱት እስራኤላውያን ጋር በተያያዘ እንዲያከናውን ስለተሰጠው ተልእኮ ለማሰብ ሞክር። በአንድ ወቅት አምላክ ሕዝቅኤልን ጡብ ወስዶ በላዩ ላይ የኢየሩሳሌምን ከተማ እንዲቀርጽበት ነግሮት ነበር። ከዚያም ሕዝቅኤል በግራ ጎኑ ለ390 ቀናት፣ በመቀጠል ደግሞ በቀኝ ጎኑ ለ40 ቀናት ተኝቶ በተቀረጸችው ከተማ ላይ ምሳሌያዊ ከበባ እንዲያካሂድ ተነገረው።  ይሖዋ ሕዝቅኤልን “እነሆ፣ የከበባህን ጊዜ እስክታጠናቅቅ ድረስ ከአንዱ ጎንህ ወደ ሌላው መገላበጥ እንዳትችል በገመድ አስርሃለሁ” አለው። (ሕዝ. 4:1-8) ይህ ሁኔታ በግዞት የነበሩትን እስራኤላውያን ትኩረት ስቦ መሆን አለበት። ሕዝቅኤል ሰውነቱ እንዲዝል የሚያደርገውን ይህን ተግባር ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ መፈጸም ነበረበት። ታዲያ ነቢዩ ኃላፊነቱን መወጣት የሚችለው እንዴት ነው?

ሕዝቅኤል ነቢይ ሆኖ የተላከበት ዓላማ ገብቶታል። አምላክ ሕዝቅኤልን ሲልከው እንዲህ ብሎት ነበር፦ “[እስራኤላውያን] ቢሰሙም ባይሰሙም በመካከላቸው ነቢይ እንደነበረ በእርግጥ ያውቃሉ።” (ሕዝ. 2:5) ይህ ተልእኮ የተሰጠው ለምን እንደሆነ ፈጽሞ አልዘነጋም። በመሆኑም በምሳሌያዊ ሁኔታ ኢየሩሳሌምን እንዲከብ የተሰጠውን ትእዛዝ በፈቃደኝነት ፈጽሟል። እውነተኛ ነቢይ መሆኑንም አስመሥክሯል። እሱም ሆነ አብረውት በግዞት የነበሩት ሰዎች “ከተማዋ ተመታች!” የሚል ሪፖርት ደረሳቸው። በእርግጥም እስራኤላውያን በመካከላቸው ነቢይ እንደነበረ ተገንዝበዋል።—ሕዝ. 33:21, 33

በዛሬው ጊዜ፣ መላው የሰይጣን ሥርዓት በቅርቡ እንደሚጠፋ ሰዎችን እያስጠነቀቅን ነው። ሰውነታችን ቢዝልም እንኳ ኃይላችንን ተጠቅመን የአምላክን ቃል እንሰብካለን፣ ተመላልሶ መጠየቅ እናደርጋለን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንመራለን። የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ በተመለከተ የተነገሩት ትንቢቶች እየተፈጸሙ ሲመጡ “አምላክ ዓላማውን ለሰዎች ለመግለጽ” የሚጠቀምባቸው ግለሰቦች በመሆናችን ውስጣዊ እርካታ ይሰማናል።

የተስፋ መቁረጥን ስሜት ተቋቁመዋል

ከይሖዋ መንፈስ በምናገኘው እርዳታ ራሳችንን ሳንቆጥብ እንሠራለን፤ ያም ሆኖ ሰዎች ለመልእክታችን የሚሰጡት ምላሽ አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል። እንግዲያው ነቢዩ ኤርምያስ የተወውን ምሳሌ ማስታወሳችን ይጠቅመናል። ከአምላክ የመጣለትን መልእክት ለእስራኤላውያን በማወጁ ፌዝ፣ ስድብና ነቀፋ ደርሶበታል። እንዲያውም በአንድ ወቅት ኤርምያስ “እሱን አላነሳም፤ ከእንግዲህም በስሙ አልናገርም” እስከማለት ደርሶ ነበር። ኤርምያስ የእኛው ዓይነት ስሜት የነበረው ሰው ነው። ያም ቢሆን የአምላክን መልእክት ማወጁን ቀጥሏል። ለምን? ነቢዩ እክሎ እንዲህ ብሏል፦ “ይሁንና ቃሉ በልቤ ውስጥ እንዳለ፣ በአጥንቶቼም ውስጥ እንደገባ የሚነድ እሳት ሆነብኝ፤ አፍኜ መያዝ አቃተኝ፤ ከዚህ በላይ መቋቋም አልቻልኩም።”—ኤር. 20:7-9

እኛም በተመሳሳይ ሰዎች ለመልእክታችን በሚሰጡት ምላሽ የተነሳ ተስፋ ከቆረጥን በምናውጀው መልእክት ላይ ማሰላሰላችን ይህን ስሜት ለማሸነፍ ይረዳናል። መልእክቱ ‘በአጥንቶቻችን ውስጥ እንደገባ የሚነድ እሳት’ ሊሆንብን ይችላል። በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማድ ማዳበራችን በውስጣችን ያለው እሳት እንዳይጠፋ ያስችላል።

አሉታዊ ስሜቶችን አሸንፈዋል

አንዳንድ ክርስቲያኖች ፈጽሞ ያልጠበቁት ሥራ ሲሰጣቸው በሁኔታው ግራ ተጋብተዋል። ነቢዩ ሆሴዕ እንዲህ ሳይሰማው አልቀረም። ይሖዋ ይህን መመሪያ ሰጥቶት ነበር፦ “ሄደህ ዝሙት አዳሪ ሴት አግባ፤ እሷ በምትፈጽመውም ምንዝር ልጆች ይወለዱልሃል።” (ሆሴዕ 1:2) በቅርቡ የምታገባ ቢሆንና የምታገባት ሴት ዝሙት አዳሪ እንደምትሆን አምላክ ቢነግርህ ምን ሊሰማህ እንደሚችል ገምት! ሆሴዕ እንዲያደርግ የታዘዘውን ነገር ፈጽሟል። ጎሜርን አግብቶ ከእሷ ወንድ ልጅ ወለደ። ከጊዜ በኋላ ጎሜር ሴት ልጅ ከዚያም ሌላ ወንድ ልጅ ወለደች። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው የመጨረሻዎቹን ሁለት ልጆች የወለደችው በምንዝር ነው። ይሖዋ፣ ሆሴዕ የሚያገባት ሚስት “አጥብቀው የሚወዷትን ተከትላ” እንደምትሄድ ነግሮት ነበር። “የሚወዷትን” የሚለው ቃል በብዙ ቁጥር እንደተገለጸ ልብ በል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ሆሴዕ ለመመለስ ጥረት ታደርጋለች። አንተ በእሱ ቦታ ብትሆን ኖሮ ዳግመኛ እንደ ሚስትህ አድርገህ ትቀበላት ነበር? ይሖዋ ለሆሴዕ የነገረው እንዲህ እንዲያደርግ ነበር! እንዲያውም ነቢዩ እሷን መልሶ ለመግዛት ከፍተኛ ወጪ አውጥቷል።—ሆሴዕ 2:7፤ 3:1-5

ሆሴዕ ‘እንዲህ ማድረጌ ምን ፋይዳ አለው?’ የሚል ጥያቄ ተፈጥሮበት ሊሆን ይችላል። ይሁንና ሆሴዕ በታማኝነት ድራማውን በሕይወቱ መፈጸሙ እስራኤል ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ስትከዳ አምላክ ምን ያህል አዝኖ እንደሚሆን እንዲገባን ይረዳናል። ደግሞም ሐቁ እንደሚያሳየው፣ አንዳንድ ቅን ልብ ያላቸው እስራኤላውያን ወደ አምላክ ተመልሰዋል።

በዛሬው ጊዜ አምላክ “ሄደህ ዝሙት አዳሪ ሴት አግባ” ብሎ ማንንም አያዝም። ሆኖም ሆሴዕ የተሰጠውን ሥራ በፈቃደኝነት መቀበሉ የሚያስተምረን ነገር ይኖራል? አንዱ የምናገኘው ትምህርት “በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት” እየሄድን የመንግሥቱን ምሥራች ማወጅ ቢከብደንም እንኳ ይህን ሥራ በፈቃደኝነት ማከናወን እንዳለብን ነው። (ሥራ 20:20)  የመንግሥቱን ምሥራች የምንሰብክባቸው አንዳንድ መንገዶች ይከብዱህ ይሆናል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያጠኑ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቱን ቢወዱትም መቼም ቢሆን የሰው በር እያንኳኩ እንደማይሰብኩ ይናገራሉ። ከጊዜ በኋላ ግን ብዙዎች በአንድ ወቅት በጭራሽ አናደርገውም ያሉትን ነገር ማከናወን ጀምረዋል። ከዚህ ምን ትምህርት እንደምናገኝ አስተዋልክ?

ሆሴዕ የተሰጠውን አስቸጋሪ ሥራ መቀበሉ ሌላም የሚያስተምረን ነገር አለ። ሚስቱ በተካተተችበት ምሳሌያዊ ድራማ ውስጥ መሳተፍ አልችልም እንዲል የሚያደርጉት ብዙ ምክንያቶች ነበሩ። ሆሴዕ ይህን ዘገባ በጽሑፍ ባያሰፍር ኖሮ ስለዚህ ዘገባ ሰዎች ማወቅ ይችሉ ነበር? እኛም ለአንድ ሰው ስለ ይሖዋ መናገር የምንችልበት ሁኔታ ሊከፈትልን ይችላል፤ ምናልባትም ስለዚህ አጋጣሚ ከእኛ ሌላ የሚያውቅ አይኖር ይሆናል። ዩናይትድ ስቴትስ ወስጥ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የሆነችው አና እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟታል። አስተማሪያቸው ለክፍሉ ተማሪዎች በጣም ስለሚወዱት ርዕሰ ጉዳይ ጽሑፍ እንዲያዘጋጁና ከዚያም የክፍሉን ተማሪዎች ለማሳመን ጥረት እንዲያደርጉ ነገረቻቸው። አና ለመመሥከር የሚያስችላትን ይህን አጋጣሚ ችላ ብላ ልታልፈው ትችል ነበር። እሷ ግን ይህ አምላክ የሰጣት አጋጣሚ እንደሆነ ተሰማት። ተማሪዎቹ ሊሰጡት የሚችሉትን ምላሽ ግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ይሖዋ ጸለየች፤ በዚህ ጊዜ ይህን አጋጣሚ ለመጠቀም ያላት ፍላጎት ይበልጥ ተጠናከረ። አና “ዝግመተ ለውጥ፦ ማስረጃውን መርምሩ” በሚል ርዕስ ጽሑፍ አዘጋጀች።

በመካከላችን ያሉ ወጣቶች ነቢያት ያሳዩትን መንፈስ ያንጸባርቃሉ፤ ይሖዋ ፈጣሪያችን መሆኑን በማወጅ ለእሱ ጥብቅና ይቆማሉ

አና ያዘጋጀችውን ጽሑፍ ለክፍሉ ተማሪዎች ካቀረበች በኋላ በዝግመተ ለውጥ የምታምን አንዲት ልጅ ጥያቄ አዥጎደጎደችባት። እሷ ግን ለምታምንበት ነገር ጥብቅና በመቆም ጥሩ ምላሽ ሰጠች። አስተማሪዋ በጉዳዩ በጣም ተገረመች፤ በመሆኑም ከሁሉም የሚበልጥ አሳማኝ ማስረጃ የያዘ ጽሑፍ በማዘጋጀቷ ለአና ሽልማት ሰጠቻት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አና ከተከራከረቻት ልጅ ጋር በፍጥረት ዙሪያ ብዙ ጊዜ መወያየት ችላለች። አና ከይሖዋ የመጣውን ይህን “ሥራ” በመቀበሏ “በአሁኑ ጊዜ ያለ ምንም ፍርሃት ምሥራቹን በሙሉ ልብ መስበክ ችያለሁ” ብላለች።

እርግጥ ነው፣ ነቢይ የሚለው ቃል የሚያስተላልፈውን ትርጉም ሙሉ በሙሉ ማሟላት አንችልም፤ ሆኖም እንደ ሕዝቅኤል፣ ኤርምያስና ሆሴዕ ያሉ ነቢያት የተዉትን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ በመኮረጅ እኛም ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እንድንሠራው የሚፈልገውን ሥራ በተሳካ ሁኔታ ማከናወን እንችላለን! በቤተሰብ አምልኮ ወይም በግል ጥናት አማካኝነት በጥንት ዘመን ስለኖሩ ሌሎች ነቢያት በማንበብ ምሳሌያቸውን እንዴት መከተል እንደምትችል ለምን አታሰላስልም?