በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  መጋቢት 2016

የወንድሞቻችሁንና የእህቶቻችሁን ቁሳዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ለመረዳት ጥረት አድርጉ

በጉባኤህ ውስጥ እርዳታ ማበርከት ትችላለህ?

በጉባኤህ ውስጥ እርዳታ ማበርከት ትችላለህ?

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ደቀ መዛሙርቱን “እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ሥራ 1:8) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህን ከባድ ኃላፊነት መወጣት የሚችሉት እንዴት ነው?

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርቲን ጉድማን “በጥንቱ የሮም ግዛት ውስጥ ይህ ተልእኮ ክርስቲያኖችን ከአይሁዳውያንና ከሌሎች የሃይማኖት ቡድኖች የተለዩ አድርጓቸዋል” ሲሉ ገልጸዋል። ኢየሱስ አገልግሎቱን ለማከናወን ከቦታ ቦታ ተጉዟል። የእሱን ምሳሌ የሚከተሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች “የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ” የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቅ የሚሹ ሰዎችን ፈልጎ ማግኘትን እንደሚጨምር ተገንዝበው ነበር። (ሉቃስ 4:43) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ “ሐዋርያት” የነበሩበት አንዱ ምክንያት ምሥራቹን በየቦታው እንዲያዳርሱ ነው፤ ይህ ስያሜ ቃል በቃል ሲወሰድ የተላኩ ወይም መልእክተኞች የሚል ትርጉም አለው። (ማር. 3:14) ኢየሱስ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚል ትእዛዝ ለተከታዮቹ ሰጥቷቸዋል።—ማቴ. 28:18-20

በዛሬው ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ የኢየሱስ ሐዋርያት መካከል አንዳቸውም ምድር ላይ የሉም፤ ያም ቢሆን በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች የሚስዮናዊነት መንፈስ ያንጸባርቃሉ። የስብከቱን ሥራ እንዲያሰፉ ለተሰጣቸው ግብዣ “እነሆኝ! እኔን ላከኝ!” የሚል ምላሽ ይሰጣሉ። (ኢሳ. 6:8) አንዳንዶች ወደ ሩቅ አገር ሄደዋል፤ ከእነዚህ መካከል በሺህ የሚቆጠሩ የጊልያድ ተመራቂዎች ይገኛሉ። ሌሎች ደግሞ በትውልድ አገራቸው ውስጥ ወደ ሌላ አካባቢ ተዛውረዋል። በርካታ ክርስቲያኖች አዲስ ቋንቋ በመማር በዚያ ቋንቋ ወደሚደረጉ ጉባኤዎችና ቡድኖች ተዛውረው ቋንቋውን የሚናገሩ ሰዎችን በመንፈሳዊ ረድተዋል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ የተዛወሩት ወይም አዲስ ቋንቋ የተማሩት ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው ወይም ተመቻችቶላቸው አይደለም። ለይሖዋና ለሰዎች ያላቸውን ፍቅር ለማሳየት የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት አድርገዋል። ወጪያቸውን ካሰሉ በኋላ ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል። (ሉቃስ 14:28-30) እንዲህ ያለ እርምጃ የሚወስዱ ወንድሞችና እህቶች ትልቅ ክፍተት እየሸፈኑ ነው።

 ይሁን እንጂ ሁሉም ክርስቲያን ያለበት ሁኔታ አንድ አይደለም። ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ መዛወር አሊያም አዲስ ቋንቋ መማር የሚችሉት ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች አይደሉም። ታዲያ ከጉባኤያችን ሳንወጣ የሚስዮናዊነት መንፈስ ማሳየት እንችላለን?

በራስህ ጉባኤ ውስጥ ሚስዮናዊ ሁን

አሁን ያላችሁበትን ሁኔታ ጥሩ አድርጋችሁ በመጠቀም ለወንድሞቻችሁ ጠቃሚ ነገሮች ማድረግ ትችላላችሁ

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በግልጽ የሚታይ የሚስዮናዊነት መንፈስ ቢኖራቸውም አብዛኞቹ በተወለዱበት ከተማ ውስጥ ያገለግሉ የነበረ ይመስላል። ያም ቢሆን ለጢሞቴዎስ የተሰጠው የሚከተለው ማሳሰቢያ እነሱንም ይመለከት ነበር፤ ይህ ማሳሰቢያ በዘመናችን ላሉ የአምላክ አገልጋዮችም ይሠራል፦ “የወንጌላዊነትን ሥራ አከናውን እንዲሁም አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም።” (2 ጢሞ. 4:5) የመንግሥቱን መልእክት የመስበኩና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ተልእኮ የትም ይኑሩ የት ሁሉንም ክርስቲያኖች ይመለከታል። በተጨማሪም ከሚስዮናዊነት አገልግሎት ጋር የተያያዙ በርካታ ሥራዎችን በራሳችን ጉባኤም ውስጥ ሆነን ልናከናውናቸው እንችላለን።

ለምሳሌ ወደ ሌላ አገር ሄዶ የሚያገለግል ሚስዮናዊ ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር መላመድ ይኖርበታል። በተመደበበት አዲስ ቦታ የሚያጋጥሙት ብዙ ነገሮች ቀደም ሲል ከለመደው በጣም የተለዩ እንደሚሆኑ ግልጽ ነው። እኛስ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ለመሄድ ሁኔታችን ባይፈቅድ ምን ማድረግ እንችላለን? በጉባኤያችን ክልል ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ እንደምናውቀው ሊሰማን ይገባል? ወይስ ሰዎችን ለማግኘት አዳዲስ ዘዴዎች መቀየስ እንችላለን? ለምሳሌ ያህል፣ በ1940 ወንድሞች መንገድ ላይ ለመመሥከር በሳምንት አንድ ቀን እንዲመድቡ ተበረታተው ነበር። አንተስ በዚህ የአገልግሎት መስክ መሳተፍ ትችላለህ? የጽሑፍ ጋሪ ተጠቅሞ እንደ መመሥከር ያለ አዲስ ነገር ለመሞከርስ ትነሳሳለህ? ነጥቡ ይህ ነው፦ ቀደም ሲል ሞክረኸው ባታውቅም እንዲህ ባሉት ምሥራቹን ለመስበክ የሚያስችሉ መንገዶች ለመጠቀም አስበሃል?

‘የወንጌላዊነትን ሥራ እንዲያከናውኑ’ አበረታቷቸው

አዎንታዊ አመለካከት መያዝ አገልግሎታችንን በቅንዓትና በጋለ ስሜት ለማከናወን ይረዳናል። ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ለመሄድ ወይም አዲስ ቋንቋ ለመማር ራሳቸውን የሚያቀርቡ አስፋፊዎች በአብዛኛው ጥሩ ችሎታ አላቸው። በዚህ መንገድ ለብዙዎች በረከት መሆን ይችላሉ፤ ለምሳሌ በመስክ አገልግሎት ለሌሎች አርዓያ መሆናቸው እንዲህ ዓይነት ውጤት ያስገኛል። ከዚህ በተጨማሪ ሚስዮናውያን በተመደቡበት ጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ለመቀበል ብቁ የሆኑ ወንድሞች እስኪገኙ ድረስ ግንባር ቀደም በመሆን የጉባኤውን ሥራ ያከናውናሉ። አንተም የተጠመቅክ ወንድም ከሆንክ በጉባኤው ውስጥ ያሉትን የእምነት ባልንጀሮችህን ለማገልገል  ፈቃደኛ በመሆን ብቃቱን ለማሟላት ‘እየተጣጣርክ’ ነው?—1 ጢሞ. 3:1

“የብርታት ምንጭ” ሁኑ

እነሱን ለመርዳት ተግባራዊ እርምጃ ውሰዱ

በመስክ አገልግሎት በቅንዓት ከመካፈልና ለጉባኤ ኃላፊነት ራስን ከማቅረብ በተጨማሪ ጉባኤያችንን ልንረዳ የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶች አሉ። ልጅ አዋቂ፣ ወንድ ሴት ሳይል እያንዳንዱ ክርስቲያን ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የእምነት ባልንጀሮቹ “የብርታት ምንጭ” መሆን ይችላል።—ቆላ. 4:11

የእምነት ባልንጀሮቻችንን መርዳት እንድንችል በሚገባ ልናውቃቸው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ አብረን በምንሰበሰብበት ጊዜ “አንዳችን ለሌላው ትኩረት [እንድንሰጥ]” ያሳስበናል። (ዕብ. 10:24) እንዲህ ሲባል በሌሎች ሰዎች የግል ጉዳይ ጣልቃ እንገባለን ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ጥቅሱ ወንድሞቻችን ያሉበትን ሁኔታ ለመረዳትና የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማወቅ ጥረት ማድረግ እንዳለብን ያሳያል። ወንድሞቻችን የሚያስፈልጋቸው ቁሳዊ፣ ስሜታዊ አሊያም መንፈሳዊ እርዳታ ሊሆን ይችላል። የእምነት ባልንጀሮቻችንን መርዳት ለሽማግሌዎችና ለጉባኤ አገልጋዮች ብቻ የተተወ ኃላፊነት አይደለም። እርግጥ እነዚህ ወንድሞች እርዳታ መስጠታቸው ተገቢ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች አሉ። (ገላ. 6:1) ያም ቢሆን ሁላችንም በችግር ላይ ያሉ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶችን አሊያም ቤተሰቦችን መርዳት እንችላለን።

በሕይወታቸው ውስጥ አስጨናቂ ነገር ሲያጋጥማቸው ስሜታዊ ድጋፍ ስጧቸው

ለምሳሌ ያህል፣ ሳልቫቶሬ ባጋጠመው ኪሳራ ምክንያት ድርጅቱን፣ ቤቱንና አብዛኛውን የቤተሰቡን ንብረት ለመሸጥ በተገደደ ጊዜ ቤተሰቡ ይህን ሁኔታ መቋቋም የሚችለው እንዴት እንደሆነ አሳስቦት ነበር። በዚህ ጊዜ በጉባኤው ውስጥ ያለ ሌላ ቤተሰብ የሳልቫቶሬ ቤተሰብ ያሉበትን ሁኔታ አስተዋለ። በመሆኑም የገንዘብ ድጋፍ አደረጉላቸው፣ ሳልቫቶሬንና ባለቤቱን ሥራ እንዲያገኙ ረዷቸው እንዲሁም ምሽት ላይ እየመጡ አብረዋቸው ጊዜ በማሳለፍ ቤተሰቡን ያበረታቷቸው ነበር። በዚህም የተነሳ በመካከላቸው ለብዙ ዓመት የዘለቀ ወዳጅነት ተመሠረተ። ቀደም ሲል አስጨናቂ ሕይወት ያሳለፉ ቢሆንም አሁን ሁለቱም ቤተሰቦች አብረው ስላሳለፉት ጊዜ አስደሳች ትዝታዎች አሏቸው።

እውነተኛ ክርስቲያኖች እምነታቸውን ለራሳቸው ይዘው አይቀመጡም። ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ ሰዎች አስደናቂ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች እንዲያውቁ ማድረግ ያስፈልገናል። ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ለመዛወር ባንችልም እንኳ ለሰው ሁሉ መልካም ለማድረግ የተቻለንን ጥረት ማድረግ እንችላለን። ይህን ደግሞ አሁን ባለንበት ጉባኤ ውስጥም ልናከናውን እንችላለን። (ገላ. 6:10) ይህም በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ለማጣጣም የሚረዳን ከመሆኑም በላይ “በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ” እያፈራን እንድንቀጥል ያስችለናል።—ቆላ. 1:10፤ ሥራ 20:35