“ይሖዋ ምንጊዜም ይመራሃል።”—ኢሳ. 58:11

መዝሙሮች፦ 3, 4

1, 2. (ሀ) በይሖዋ ምሥክሮች መካከል አመራር የሚሰጡት ሰዎች በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ ካሉት መሪዎች የሚለዩት እንዴት ነው? (ለ) በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

“መሪያችሁ ማን ነው?” የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ይቀርብላቸዋል። ይህ የሚያስገርም አይደለም። ምክንያቱም ብዙ ሃይማኖቶች አንድን ወንድ ወይም አንዲትን ሴት መሪ አድርገው ይሾማሉ። ከዚህ በተለየ መልኩ እኛ የይሖዋ ምሥክሮች፣ መሪያችን ፍጽምና የሚጎድለው ሰው አይደለም። መሪያችን ከሞት የተነሳው ክርስቶስ ነው፤ እሱን የሚመራው ደግሞ አባቱ ይሖዋ ነው።—ማቴ. 23:10

2 እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ላሉት የአምላክ ሕዝቦች አመራር የሚሰጥ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ተብሎ የሚጠራ ጥቂት ወንድሞችን ያቀፈ ቡድን አለ። (ማቴ. 24:45) ታዲያ በልጁ አማካኝነት እየመራን ያለው ይሖዋ መሆኑን እንዴት ማወቅ እንችላለን? ይሖዋ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በአንዳንድ ሰዎች ተጠቅሞ አመራር ይሰጥ የነበረው እንዴት እንደሆነ በዚህና በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንመለከታለን። ሁለቱም ርዕሶች፣ ይሖዋ በእነዚህ ሰዎች ይጠቀም እንደነበር የሚያሳዩ ሦስት ነጥቦችን ይዘዋል፤ እነዚህ ነጥቦች ይሖዋ በጥንት ዘመን ሕዝቡን ይመራ እንደነበረና ዛሬም ቢሆን መሪያቸው እንደሆነ ያረጋግጣሉ።—ኢሳ. 58:11

መንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰጥቷቸዋል

3. ሙሴ እስራኤላውያንን ለመምራት ብቁ እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው?

3 መንፈስ ቅዱስ ለአምላክ ወኪሎች ኃይል ሰጥቷቸዋል። እስራኤላውያንን የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶት የነበረውን ሙሴን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።  ይህን ከባድ ኃላፊነት ለመሸከም ብቁ እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው? ይሖዋ “ቅዱስ መንፈሱን” ሰጥቶት ነበር። (ኢሳይያስ 63:11-14ን አንብብ።) ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ለሙሴ ኃይል በመስጠት ሕዝቡን ይመራ ነበር።

4. እስራኤላውያን በሙሴ ላይ እየሠራ ያለው የአምላክ መንፈስ መሆኑን ማወቅ የሚችሉት እንዴት ነበር? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

4 መንፈስ ቅዱስ የማይታይ ኃይል ከመሆኑ አንጻር እስራኤላውያን በሙሴ ላይ እየሠራ ያለው የአምላክ መንፈስ መሆኑን ማወቅ የሚችሉት እንዴት ነበር? መንፈስ ቅዱስ፣ ሙሴ ተአምራትን እንዲፈጽምና የአምላክን ስም ለፈርዖን እንዲያሳውቅ ረድቶታል። (ዘፀ. 7:1-3) በተጨማሪም ሙሴ እንደ ፍቅር፣ የዋህነትና ትዕግሥት ያሉትን ግሩም ባሕርያት እንዲያፈራ መንፈስ ቅዱስ ረድቶታል፤ እነዚህ ባሕርያት ደግሞ እስራኤላውያንን ለመምራት ብቁ እንዲሆን አስችለውታል። ሙሴ፣ ክፉና ራስ ወዳድ ከነበሩት የሌሎች አገሮች መሪዎች ምንኛ የተለየ ነበር! (ዘፀ. 5:2, 6-9) ይሖዋ ሕዝቡን እንዲመራ ሙሴን እንደመረጠው በግልጽ ማየት ይቻል ነበር።

5. ይሖዋ ሌሎች እስራኤላውያንም ሕዝቡን እንዲመሩ ኃይል የሰጣቸው እንዴት ነው?

5 ከጊዜ በኋላ ደግሞ ይሖዋ ሕዝቡን እንዲመሩ ለሾማቸው ሌሎች ሰዎች በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ኃይል ሰጥቷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “የነዌ ልጅ ኢያሱ . . . የጥበብ መንፈስ ተሞልቶ ነበር።” (ዘዳ. 34:9) “የይሖዋም መንፈስ በጌድዮን ላይ ወረደ።” (መሳ. 6:34) እንዲሁም “የይሖዋ መንፈስ ለዳዊት ኃይል ሰጠው።” (1 ሳሙ. 16:13) እነዚህን ሰዎች የረዳቸው መንፈስ ቅዱስ ሲሆን ይህ መንፈስ በራሳቸው ሊያከናውኑ የማይችሉትን አስደናቂ ነገር መሥራት እንዲችሉ ኃይል ሰጥቷቸዋል። (ኢያሱ 11:16, 17፤ መሳ. 7:7, 22፤ 1 ሳሙ. 17:37, 50) በመሆኑም ለእነዚህ ታላላቅ ሥራዎች ይሖዋ መመስገኑ የተገባ ነበር።

6. አምላክ የእስራኤልን መሪዎች ሕዝቡ እንዲያከብራቸው ይፈልግ የነበረው ለምንድን ነው?

6 ታዲያ እስራኤላውያን ለእነዚህ ሰዎች ኃይል የሰጣቸው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ መሆኑን የሚጠቁም ግልጽ ማስረጃ ሲመለከቱ ምን ሊያደርጉ ይገባ ነበር? እነዚህን ሰዎች ሊያከብሯቸው ይገባ ነበር። ሕዝቡ በሙሴ ላይ ባጉረመረሙ ጊዜ ይሖዋ “ይህ ሕዝብ የሚንቀኝ እስከ መቼ ነው?” ብሏል። (ዘኁ. 14:2, 11) በእርግጥም ሙሴ፣ ኢያሱ፣ ጌድዮንና ዳዊት እሱን ወክለው መሪ እንዲሆኑ የሾማቸው ይሖዋ ነው። ሕዝቡ እነዚህን ሰዎች መታዘዛቸው ይሖዋ መሪያቸው መሆኑን እንደተገነዘቡ ያሳያል።

መላእክት ረድተዋቸዋል

7. መላእክት ሙሴን የረዱት እንዴት ነው?

7 መላእክት የአምላክን ወኪሎች ረድተዋቸዋል። (ዕብራውያን 1:7, 14ን አንብብ።) ይሖዋ ሙሴን ለመምራት በመላእክት ተጠቅሟል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ አንድ መልአክ ለሙሴ “በቁጥቋጦው ውስጥ [ተገልጦ]” እስራኤላውያንን ነፃ እንዲያወጣና እንዲመራቸው ተልእኮ ሰጥቶታል። (ሥራ 7:35) ሁለተኛ፣ ይሖዋ “በመላእክት አማካኝነት” ለሙሴ ሕጉን ሰጥቶታል፤ ሙሴም ይህን ሕግ ለእስራኤላውያን አስተምሯል። (ገላ. 3:19) በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ ብሎታል፦ “ሕዝቡን ወደነገርኩህ ስፍራ እየመራህ ውሰዳቸው። እነሆ መልአኬ ከፊት ከፊትህ ይሄዳል።” (ዘፀ. 32:34) እስራኤላውያን፣ ሥጋ የለበሰ መልአክ እነዚህን ነገሮች ሲያከናውን እንደተመለከቱ የሚገልጽ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። ሆኖም ሙሴ ሕዝቡን ያስተማረበትና የመራበት መንገድ ከሰው በላይ የሆነ ኃይል ይረዳው እንደነበር በግልጽ ያሳያል።

8. መላእክት ኢያሱንና ሕዝቅያስን የረዷቸው እንዴት ነው?

8 ሙሴን ተክቶ የእስራኤል መሪ የሆነው ኢያሱ፣ የአምላክን ሕዝቦች እየመራ ከከነዓናውያን ጋር በተዋጋበት ወቅት “የይሖዋ ሠራዊት አለቃ” ረድቶታል፤ በመሆኑም እስራኤላውያን በጦርነቱ አሸናፊ ሆነዋል። (ኢያሱ 5:13-15፤ 6:2, 21) ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ደግሞ ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ ኢየሩሳሌምን ሊወር ከመጣው አስፈሪ የአሦራውያን ሠራዊት ጋር ተፋጥጦ ነበር። በዚህ ጊዜ “የይሖዋ መልአክ ወጥቶ በአሦራውያን ሰፈር የነበሩትን  185,000 ሰዎች [በአንድ ሌሊት] ገደለ።”—2 ነገ. 19:35

9. የአምላክ ወኪሎች ፍጹማን ባይሆኑም እስራኤላውያን ምን ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር?

9 እርግጥ ነው፣ መላእክቱ ፍጹማን ቢሆኑም የእነሱን እርዳታ ያገኙት ሰዎች ፍጹማን አልነበሩም። ለምሳሌ፣ ሙሴ በአንድ ወቅት ለይሖዋ ክብር ሳይሰጥ ቀርቷል። (ዘኁ. 20:12) ኢያሱ የአምላክን መመሪያ ሳይጠይቅ ከገባኦናውያን ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል። (ኢያሱ 9:14, 15) ሕዝቅያስም ቢሆን በአንድ ወቅት “ልቡ ታብዮ” ነበር። (2 ዜና 32:25, 26) እነዚህ ሰዎች ፍጽምና የጎደላቸው ቢሆኑም እንኳ እስራኤላውያን የእነሱን አመራር መከተል ይጠበቅባቸው ነበር። ይሖዋ፣ በመላእክቱ ተጠቅሞ እነዚህን ሰዎች ደግፏቸዋል። በእርግጥም ሕዝቡን የሚመራው ይሖዋ ነበር።

የአምላክ ቃል መርቷቸዋል

10. ሙሴ በአምላክ ሕግ ይመራ የነበረው እንዴት ነው?

10 የአምላክ ቃል የእሱን ወኪሎች መርቷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ለእስራኤላውያን የተሰጠውን ሕግ ‘የሙሴ ሕግ’ በማለት ይጠራዋል። (1 ነገ. 2:3) ያም ቢሆን የዚህ ሕግ ባለቤት ይሖዋ እንደሆነ ቅዱሳን መጻሕፍት ይገልጻሉ፤ ሙሴ ራሱ ለሕጉ መገዛት ይጠበቅበት ነበር። (2 ዜና 34:14) ለምሳሌ፣ ይሖዋ የማደሪያውን ድንኳን አሠራር በተመለከተ ለሙሴ መመሪያ ሰጥቶት ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አስመልክቶ ሲናገር “ሙሴም ይሖዋ ባዘዘው መሠረት አደረገ። ልክ እንደዚሁ አደረገ” ይላል።—ዘፀ. 40:1-16

11, 12. (ሀ) ኢያሱም ሆነ የአምላክን ሕዝብ ያስተዳደሩት ነገሥታት ምን እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸው ነበር? (ለ) የአምላክ ቃል፣ በሕዝቡ ላይ የተሾሙትን ሰዎች ይመራቸው የነበረው እንዴት ነው?

11 ኢያሱ መሪ እንዲሆን ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ በጽሑፍ የሰፈረው የአምላክ ቃል ቅጂ ነበረው። “በውስጡ የተጻፈውንም በጥንቃቄ መፈጸም እንድትችል ቀንም ሆነ ሌሊት በለሆሳስ አንብበው” የሚል መመሪያ ተሰጥቶት ነበር። (ኢያሱ 1:8) ከጊዜ በኋላ በአምላክ ሕዝብ ላይ የተሾሙት ነገሥታትም ይህንኑ ልማድ ተከትለዋል። ሕጉን በየዕለቱ እንዲያነቡ፣ ለራሳቸው እንዲገለብጡ እንዲሁም “በዚህ ሕግና በእነዚህ ሥርዓቶች ላይ የሰፈሩትን ቃላት በሙሉ በመፈጸም [እንዲጠብቋቸው]” ታዘው ነበር።—ዘዳግም 17:18-20ን አንብብ።

12 የአምላክ ቃል፣ በሕዝቡ ላይ የተሾሙትን ሰዎች ይመራቸው የነበረው እንዴት ነው? ንጉሥ ኢዮስያስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የሙሴ ሕግ መጽሐፍ ከተገኘ በኋላ የኢዮስያስ ጸሐፊ ሕጉን አነበበለት። * ንጉሡ ይህን ሲሰማ ምን አደረገ? “ንጉሡ የሕጉን መጽሐፍ ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ።” በተጨማሪም ኢዮስያስ በአምላክ ቃል በመመራት የጣዖት አምልኮን ለማጥፋት ከፍተኛ ዘመቻ አካሄደ፤ እንዲሁም የፋሲካን በዓል ከዚያ በፊት ታይቶ በማያውቅ መልኩ አከበረ። (2 ነገ. 22:11፤ 23:1-23) ኢዮስያስና ሌሎች ታማኝ መሪዎች፣ በአምላክ ቃል ይመሩ ስለነበር ለሕዝቡ የሚሰጡትን መመሪያ ለማስተካከል ፈቃደኞች ሆነዋል። እነዚህ ለውጦች የጥንቱ የአምላክ ሕዝብ ከእሱ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲመላለስ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

13. በአምላክ ሕዝብ መሪዎችና በሌሎች ብሔራት መሪዎች መካከል ምን ልዩነት ነበር?

13 ታማኝ የሆኑት ነገሥታት፣ በሰብዓዊ ጥበብ እና ዕቅድ ከሚመሩ ማስተዋል የጎደላቸው የሌሎች ሕዝቦች ነገሥታት ምንኛ የተለዩ ነበሩ! ከነዓናውያን መሪዎችና ሕዝቦቻቸው በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚደረግ የፆታ ግንኙነትን፣ ግብረ ሰዶምን፣ ከእንስሳ ጋር የሚደረግ የፆታ ግንኙነትን፣ ልጆችን መሥዋዕት ማድረግን እንዲሁም ጣዖት አምልኮን የመሳሰሉ አስጸያፊ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ነበር። (ዘሌ. 18:6, 21-25) በተጨማሪም ባቢሎናውያንና ግብፃውያን መሪዎች፣ አምላክ ከንጽሕና ጋር በተያያዘ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ጠቃሚ መመሪያዎች አይከተሉም ነበር። (ዘኁ. 19:13) ከዚህ በተቃራኒ ታማኝ የሆኑት የእስራኤል መሪዎች ሕዝቡ መንፈሳዊ፣ አካላዊና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናውን እንዲጠብቅ ያበረታቱ ነበር። ታማኞቹን  መሪዎች የሚመራቸው ይሖዋ እንደነበር በግልጽ መረዳት ይቻላል።

14. ይሖዋ ለአንዳንዶቹ መሪዎች ተግሣጽ የሰጠው ለምንድን ነው?

14 የጥንቶቹን የአምላክ ሕዝቦች ይገዙ ከነበሩት ነገሥታት አንዳንዶቹ የአምላክን መመሪያዎች አልታዘዙም። ይሖዋን ያልታዘዙት መሪዎች የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እንዲሁም የመላእክቱንና የቃሉን አመራር ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም። ይሖዋ ለእነዚህ መሪዎች ተግሣጽ የሰጠባቸው ወይም በሌላ መሪ እንዲተኩ ያደረገባቸው ጊዜያት ነበሩ። (1 ሳሙ. 13:13, 14) እሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ደግሞ ከዚህ በፊት ይጠቀምባቸው ከነበሩት መሪዎች ሁሉ የላቀ መሪ ሾመ።

ይሖዋ ፍጹም የሆነ መሪ ሾሟል

15. (ሀ) ነቢያት አንድ ልዩ መሪ እንደሚመጣ የጠቆሙት እንዴት ነው? (ለ) በትንቢት የተነገረለት መሪ ማን ነው?

15 ይሖዋ፣ አንድ ልዩ ብቃት ያለው መሪ ለሕዝቡ እንደሚሾም ከበርካታ ዘመናት አስቀድሞ በትንቢት አስነግሯል። ሙሴ እስራኤላውያንን “አምላክህ ይሖዋ ከወንድሞችህ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳልሃል። እናንተም እሱን ማዳመጥ ይኖርባችኋል” ብሏቸው ነበር። (ዘዳ. 18:15) ኢሳይያስ፣ ይህ ነቢይ “መሪና አዛዥ” እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል። (ኢሳ. 55:4) ዳንኤልም “መሪ የሆነው መሲሕ” እንደሚመጣ በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (ዳን. 9:25) በመጨረሻም ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ሕዝቦች “መሪ” እሱ እንደሆነ ገልጿል። (ማቴዎስ 23:10ን አንብብ።) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በገዛ ፈቃዳቸው ተነሳስተው የተከተሉት ሲሆን ይሖዋ እሱን እንደመረጠው ያምኑ ነበር። (ዮሐ. 6:68, 69) ይሁንና ደቀ መዛሙርቱ፣ ይሖዋ ሕዝቡን ለመምራት የሚጠቀመው በኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ያሳመናቸው ምንድን ነው?

16. መንፈስ ቅዱስ ለኢየሱስ ኃይል እንደሰጠው የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

16 መንፈስ ቅዱስ ለኢየሱስ ኃይል ሰጥቶታል። አጥማቂው ዮሐንስ፣ ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት “ሰማያት ተከፍተው መንፈስ እንደ ርግብ በእሱ ላይ ሲወርድ” ተመልክቶ ነበር። ከዚያም ኢየሱስን “መንፈስ ወደ ምድረ በዳ እንዲሄድ ገፋፋው።” (ማር. 1:10-12) ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ ተአምራትን እንዲፈጽምና ይሖዋ በሰጠው ሥልጣን እንዲናገር መንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰጥቶታል። (ሥራ 10:38) በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ፣ ኢየሱስ እንደ ፍቅር፣ ደስታና ጠንካራ እምነት ያሉትን ባሕርያት እንዲያፈራ ረድቶታል። (ዮሐ. 15:9፤ ዕብ. 12:2) ኢየሱስ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ድጋፍ እንዳለው በግልጽ ታይቷል። ኢየሱስን መሪ እንዲሆን የመረጠው ይሖዋ ነው።

ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ መላእክት የረዱት እንዴት ነው? (አንቀጽ 17ን ተመልከት)

17. መላእክት ኢየሱስን የረዱት እንዴት ነው?

17 መላእክት ኢየሱስን ረድተውታል። ኢየሱስ ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ ‘መላእክት መጥተው አገልግለውታል።’ (ማቴ. 4:11) ከመሞቱ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ደግሞ “አንድ መልአክ ከሰማይ ተገልጦለት [አበረታቶታል]።” (ሉቃስ 22:43) ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም የመላእክት እርዳታ በሚያስፈልገው ጊዜ ሁሉ ይሖዋ እንደሚልክለት እርግጠኛ ነበር።—ማቴ. 26:53

18, 19. የኢየሱስ አኗኗርም ሆነ የሚያስተምረው ትምህርት በአምላክ ቃል ይመራ እንደነበር የሚያሳየው እንዴት ነው?

 18 የአምላክ ቃል ኢየሱስን መርቶታል። ኢየሱስ አገልግሎቱን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በቅዱሳን መጻሕፍት ይመራ ነበር። (ማቴ. 4:4) እንዲያውም በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ እስከመሞት ድረስ ለአምላክ ቃል ታዛዥ መሆኑን አሳይቷል። ከመሞቱ በፊት የተናገረው የመጨረሻ ሐሳብ እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መሲሑ የተነገሩ ትንቢቶችን የያዘ ነበር። (ማቴ. 27:46፤ ሉቃስ 23:46) በተቃራኒው በወቅቱ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች፣ የአምላክ ቃል ከራሳቸው ወግ ጋር በሚጋጭበት ጊዜ ቃሉን ችላ ይሉት ነበር። ኢየሱስ ስለ እነዚህ ሰዎች ሲናገር ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ያስነገረውን ትንቢት በመጥቀስ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው። የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።” (ማቴ. 15:7-9) ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ሕዝቡን እንዲመሩ መርጧቸዋል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው።

19 ኢየሱስ የሚያስተምረውም ትምህርት ቢሆን በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ነበር። ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹ ጥያቄ በሚያነሱበት ጊዜ መልስ ይሰጥ የነበረው የራሱን ጥበብ ወይም ተሞክሮ በመጠቀም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንደ መጨረሻ ባለሥልጣን አድርጎ ይጠቅስ ነበር። (ማቴ. 22:33-40) በተጨማሪም በሰማይ ስላሳለፈው ሕይወት ወይም ስለ አጽናፈ ዓለም አፈጣጠር በማውራት አድማጮቹን ለማስደመም ከመሞከር ይልቅ “የቅዱሳን መጻሕፍትን ትርጉም መረዳት እንዲችሉ አእምሯቸውን ከፈተላቸው።” (ሉቃስ 24:32, 45) ኢየሱስ የአምላክን ቃል ይወድ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ቃሉን ለሌሎች ለመናገር ጉጉት ነበረው።

20. (ሀ) ኢየሱስ ለአምላክ ክብር የሰጠው እንዴት ነው? (ለ) በኢየሱስና በቀዳማዊ ሄሮድስ አግሪጳ መካከል ምን ልዩነት ነበር?

20 ኢየሱስ አድማጮቹን የሚያስደምሙ “የሚማርኩ ቃላት” ይናገር የነበረ ቢሆንም ክብር የሚገባው እሱን ያስተማረው አካል ይኸውም ይሖዋ መሆኑን ገልጿል። (ሉቃስ 4:22) አንድ ሀብታም ሰው ለኢየሱስ “ጥሩ መምህር” የሚል የማዕረግ ስም በመስጠት ከፍ ከፍ ሊያደርገው በሞከረ ጊዜ ኢየሱስ “ለምን ጥሩ ብለህ ትጠራኛለህ? ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም” በማለት ትሕትና የሚንጸባረቅበት ምላሽ ሰጥቶታል። (ማር. 10:17, 18) ኢየሱስ፣ ከስምንት ዓመት ገደማ በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ወይም መሪ ከሆነው ከቀዳማዊ ሄሮድስ አግሪጳ ምንኛ የተለየ ነበር! ሄሮድስ በአንድ ልዩ ዝግጅት ላይ “ልብሰ መንግሥቱን” ለብሶ ነበር። በአድናቆት የተዋጠው ሕዝብ “ይህ የአምላክ ድምፅ ነው እንጂ የሰው አይደለም!” እያለ ጮኸ። ሄሮድስ የሕዝቡ ውዳሴ ሳያስደስተው አልቀረም። በዚህ ጊዜ “ለአምላክ ክብር ባለመስጠቱ ወዲያውኑ የይሖዋ መልአክ ቀሰፈው፤ በትል ተበልቶም ሞተ።” (ሥራ 12:21-23) ይህን የተመለከተ ማንኛውም ሰው ሄሮድስ በይሖዋ የተመረጠ መሪ አለመሆኑን መገንዘቡ አይቀርም። በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ በአምላክ የተሾመ መሪ መሆኑን በግልጽ ማየት ይቻል ነበር፤ ኢየሱስ ከሁሉ የላቀው የአምላክ ሕዝቦች መሪ ይሖዋ እንደሆነ ሌሎች እንዲገነዘቡ በማድረግ ምንጊዜም ለእሱ ክብር ይሰጥ ነበር።

21. የሚቀጥለው ርዕስ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል?

21 ኢየሱስ መሪ የሚሆነው ለጥቂት ዓመታት ብቻ አይደለም። ከሞት ከተነሳ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል። . . . እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ. 28:18-20) ይሁንና ኢየሱስ በሰማይ የሚኖር መንፈሳዊ አካል ከመሆኑ አንጻር በምድር ያሉትን የአምላክ ሕዝቦች መምራት የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ በክርስቶስ አመራር ሥር ሆነው ሕዝቡን እንዲመሩ የሚጠቀመው እነማንን ነው? ክርስቲያኖች የአምላክን ወኪሎች እንዴት መለየት ይችላሉ? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

^ አን.12 ይህ መጽሐፍ ሙሴ ያዘጋጀው የመጀመሪያው መጽሐፍ ሳይሆን አይቀርም።