በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  የካቲት 2017

ቤዛው—ከአባታችን የተገኘ “ፍጹም ገጸ በረከት”

ቤዛው—ከአባታችን የተገኘ “ፍጹም ገጸ በረከት”

“መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ ከላይ [ከአባት] ነው።” —ያዕ. 1:17

መዝሙሮች፦ 20, 15

1. ቤዛው የትኞቹን በረከቶች ያስገኝልናል?

የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ብዙ በረከቶች አስገኝቷል። ቤዛው ጽድቅን የሚወዱ የአዳም ልጆች በሙሉ ውሎ አድሮ የአምላክ ቤተሰብ አባል እንዲሆኑ መንገድ ከፍቷል። ቤዛው ለዘላለም በደስታ የመኖር አጋጣሚ እንድናገኝም አድርጓል። ይሁን እንጂ የክርስቶስ ቤዛ፣ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች በረከት ከማምጣት ያለፈ ነገርም ያከናውናል። ኢየሱስ ከይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ አገዛዝ ጎን በመቆም ለመሞት ፈቃደኛ መሆኑ፣ ከአምላክ አገዛዝ ትክክለኛነት ጋር በተያያዘ ለተነሳው ትልቅ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።—ዕብ. 1:8, 9

2. (ሀ) ኢየሱስ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን የትኞቹን ነጥቦች በጸሎቱ ውስጥ አካትቷል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

2 ኢየሱስ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት ቤዛውን ከመክፈሉ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸው ነበር፦ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ  ይፈጸም።” (ማቴ. 6:9, 10) ቤዛው ከአምላክ ስም መቀደስ፣ ከአምላክ መንግሥት አገዛዝና ከአምላክ ዓላማ መፈጸም ጋር ምን ዝምድና እንዳለው እስቲ እንመልከት፤ ይህን ማድረጋችን ለቤዛው ያለን አድናቆት እንዲጨምር ይረዳናል።

“ስምህ ይቀደስ”

3. የይሖዋ ስም የትኞቹን ነገሮች አካትቶ የያዘ ነው? ሰይጣን የአምላክን ቅዱስ ስም ያጠፋው እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ በጸሎት ናሙናው ላይ ያቀረበው የመጀመሪያው ልመና ከአምላክ ስም መቀደስ ጋር የተያያዘ ነው። የይሖዋ ስም ታላቅነቱን፣ ግርማዊነቱንና ቅድስናውን አካትቶ የያዘ ነው። ኢየሱስ በሌላ ጸሎቱ ላይ ይሖዋን “ቅዱስ አባት” በማለት ጠርቶታል። (ዮሐ. 17:11) ይሖዋ ቅዱስ ስለሆነ እሱ የሚያወጣቸው መመሪያዎችና ሕጎች በሙሉ ቅዱስ ናቸው። ይሁንና ሰይጣን በኤደን የአትክልት ስፍራ፣ አምላክ ለሰው ልጆች ሕግ ለማውጣት ባለው መብት ላይ ጥያቄ አንስቷል። ሰይጣን ስለ ይሖዋ ውሸት በመናገር የአምላክን ቅዱስ ስም አጥፍቷል።—ዘፍ. 3:1-5

4. ኢየሱስ የአምላክ ስም እንዲቀደስ አስተዋጽኦ ያደረገው እንዴት ነው?

4 በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ የይሖዋን ስም ከልቡ ይወደዋል። (ዮሐ. 17:25, 26) ኢየሱስ፣ መለኮታዊው ስም እንዲቀደስ አስተዋጽኦ አበርክቷል። (መዝሙር 40:8-10ን አንብብ።) እንዴት? ኢየሱስ በአኗኗሩና ባስተማራቸው ነገሮች፣ ይሖዋ የሚያወጣቸው መሥፈርቶች ትክክለኛ እንደሆኑና ማንኛውንም መመሪያ የሚሰጠን ለራሳችን ጥቅም መሆኑን ሰዎች እንዲገነዘቡ አድርጓል። ኢየሱስ በሰይጣን ቆስቋሽነት ከፍተኛ ሥቃይ ደርሶበት ቢሞትም በሰማይ ላለው አባቱ ፍጹም ታማኝ መሆኑን አሳይቷል። ኢየሱስ ታማኝ መሆኑ፣ አንድ ፍጹም ሰው አምላክ ላወጣቸው የጽድቅ መሥፈርቶች ሙሉ በሙሉ ታዛዥ መሆን እንደሚችል አረጋግጧል።

5. የአምላክ ስም እንዲቀደስ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

5 እኛስ የይሖዋን ስም እንደምንወድ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በአኗኗራችን ይህን ማሳየት እንችላለን። ይሖዋ ቅዱስ እንድንሆን ይጠብቅብናል። (1 ጴጥሮስ 1:15, 16ን አንብብ።) ይህም ሲባል እሱን ብቻ እንድናመልክና በሙሉ ልባችን እንድንታዘዘው ይፈልጋል ማለት ነው። ስደት ቢደርስብንም እንኳ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶችና ሕጎች ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። የይሖዋን መመሪያዎች በሕይወታችን ውስጥ በሥራ ላይ በማዋል ብርሃናችን በሰው ፊት እንዲበራ እናደርጋለን፤ ይህ ደግሞ ለይሖዋ ስም ክብር ያመጣል። (ማቴ. 5:14-16) የአምላክ ቅዱስ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን፣ የይሖዋ ሕጎች ትክክለኛ መሆናቸውንና የሰይጣን ክስ ሐሰት መሆኑን በአኗኗራችን እናሳያለን። እርግጥ ነው፣ እንደ ማንኛውም ሰው ስህተት መሥራታችን አይቀርም፤ በዚህ ጊዜ ከልባችን ንስሐ በመግባት ይሖዋን ከሚያስነቅፉ ድርጊቶች እንርቃለን።—መዝ. 79:9

6. ፍጽምና ቢጎድለንም እንኳ ይሖዋ እንደ ጻድቃን አድርጎ ሊመለከተን የሚችለው ለምንድን ነው?

6 ይሖዋ በክርስቶስ መሥዋዕት ላይ እምነት ካለን ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል። ራሳቸውን ለእሱ የወሰኑ ሰዎችን አገልጋዮቹ አድርጎ ይቀበላቸዋል። ይሖዋ፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ልጆቹ አድርጎ በመቀበል ጻድቃን ብሎ ጠርቷቸዋል፤ ‘ሌሎች በጎችን’ ደግሞ ወዳጆቹ አድርጎ በመቀበል እንደ ጻድቃን ይቆጥራቸዋል። (ዮሐ. 10:16፤ ሮም 5:1, 2፤ ያዕ. 2:21-25) በመሆኑም በአሁኑ ጊዜም እንኳ ቤዛው፣ በሰማዩ አባታችን ዘንድ የጽድቅ አቋም እንዲኖረንና ስሙን በማስቀደስ ረገድ የበኩላችንን ድርሻ እንድናበረክት አስችሎናል።

“መንግሥትህ ይምጣ”

7. ቤዛው በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የትኞቹን በረከቶች እንድናገኝ መንገድ ከፍቷል?

7 ኢየሱስ በጸሎት ናሙናው ላይ ቀጥሎ ያቀረበው ልመና “መንግሥትህ ይምጣ” የሚል ነው። ቤዛው ከአምላክ መንግሥት ጋር ምን ዝምድና አለው? የአምላክ መንግሥት ገዢዎች ኢየሱስና ከምድር የተመረጡ 144,000 ሰዎች ናቸው።  ቤዛው ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት ሆነው የሚያገለግሉት እነዚህ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ መሄድ እንዲችሉ መንገድ ከፍቷል። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:1) ኢየሱስና ተባባሪ ገዢዎቹ ለአንድ ሺህ ዓመት በሚገዙበት ወቅት፣ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ቤዛው ከሚያስገኛቸው በረከቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋሉ። ምድር ገነት ትሆናለች፤ እንዲሁም ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ፍጹማን ይሆናሉ። በመሆኑም በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በመጨረሻ አንድ ቤተሰብ ይሆናሉ። (ራእይ 5:13፤ 20:6) ኢየሱስ የእባቡን ራስ ይጨፈልቃል፤ እንዲሁም ሰይጣን ያስነሳው ዓመፅ ያስከተላቸውን ችግሮች በሙሉ ያስወግዳል።—ዘፍ. 3:15

8. (ሀ) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንዳለው እንዲገነዘቡ ደቀ መዛሙርቱን የረዳቸው እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ መንግሥቱን እንደምንደግፍ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት፣ ደቀ መዛሙርቱ የአምላክ መንግሥት ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንዳለው እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያውኑ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች” በስፋት ማወጅ ጀምሯል። (ሉቃስ 4:43) ወደ ሰማይ ከመመለሱ በፊት ደቀ መዛሙርቱን ለመጨረሻ ጊዜ ባነጋገራቸው ወቅት “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ምሥክሮቹ እንዲሆኑ አዟቸዋል። (ሥራ 1:6-8) በመላው ምድር የሚኖሩ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት በሚገልጸው የስብከት ሥራ አማካኝነት ስለ ቤዛው መማርና የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች መሆን የሚችሉበት አጋጣሚ ያገኛሉ። በዛሬው ጊዜ የመንግሥቱን ምሥራች በዓለም ዙሪያ እንድንሰብክ የተሰጠንን ተልዕኮ በመወጣት በምድር ያሉትን የክርስቶስ ወንድሞች ስንረዳ መንግሥቱን እንደምንደግፍ እናሳያለን።—ማቴ. 24:14፤ 25:40

‘ፈቃድህ ይፈጸም’

9. ይሖዋ ለሰው ዘር ያለውን ዓላማ እንደሚፈጽም መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

9 ኢየሱስ በጸሎት ናሙናው ላይ ‘ፈቃድህ ይፈጸም’ ሲል ምን ማለቱ ነው? ይሖዋ ፈጣሪ ነው። አንድ ነገር እንደሚከናወን ከተናገረ፣ መፈጸሙ አይቀርም። (ኢሳ. 55:11) ሰይጣን ያስነሳው ዓመፅ ይሖዋ ለሰው ዘር ያለውን ዓላማ ሊያሰናክለው አይችልም። መጀመሪያ ላይ የይሖዋ ፈቃድ ወይም ዓላማ፣ ምድር ፍጹም በሆኑ የአዳምና የሔዋን ልጆች እንድትሞላ ነበር። (ዘፍ. 1:28) አዳምና ሔዋን ልጅ ሳይወልዱ ቢሞቱ ኖሮ ይሖዋ በዘሮቻቸው አማካኝነት ምድርን ለመሙላት የነበረው ዓላማ ዳር አይደርስም ነበር። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩም በኋላ ይሖዋ ልጆች እንዲወልዱ የፈቀደው ለዚህ ነው። አምላክ ቤዛውን በማዘጋጀት፣ እምነት ያላቸው የሰው ልጆች በሙሉ ፍጹም ሆነው ለዘላለም መኖር የሚችሉበት አጋጣሚ እንዲያገኙ አድርጓል። ይሖዋ፣ የሰው ልጆችን ይወዳል፤ ፈቃዱ ወይም ዓላማው ታዛዥ የሆኑ ሰዎች እሱ ባሰበው መንገድ እንዲኖሩ ማድረግ ነው።

10. በሞት ያንቀላፉ ሰዎች ከቤዛው ጥቅም የሚያገኙት እንዴት ነው?

10 ይሖዋን የማወቅና የማገልገል አጋጣሚ ሳያገኙ ሕይወታቸው ስላለፈ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ቤዛው፣ ሙታን ትንሣኤ ማግኘት እንዲችሉ መንገድ ከፍቷል። አፍቃሪ የሆነው ሰማያዊ አባታችን እነዚህን ሰዎች ከሞት በማስነሳት ስለ ዓላማው የመማርና የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (ሥራ 24:15) ይሖዋ፣ ሰዎች በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ እንዲሞቱ አይፈልግም። የሕይወት ምንጭ እንደመሆኑ መጠን ከሞት ለተነሱ ሁሉ አባት ይሆንላቸዋል። (መዝ. 36:9) ከዚህ አንጻር ኢየሱስ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” ብለን እንድንጸልይ ማስተማሩ ተገቢ ነው። (ማቴ. 6:9) ይሖዋ ሙታንን ከማስነሳት ጋር በተያያዘ ኢየሱስ ትልቅ ሚና እንዲኖረው አድርጓል። (ዮሐ. 6:40, 44) ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት” እንደሆነ የተናገረው ቃል በገነት ውስጥ ፍጻሜውን ያገኛል።—ዮሐ. 11:25

11. ‘እጅግ ብዙ ሕዝብን’ በተመለከተ የአምላክ ፈቃድ ምንድን ነው?

 11 ይሖዋ የቤተሰቡ አባላት እንዲሆኑ የጋበዘው የተመረጡ ጥቂት ሰዎችን ብቻ አይደለም፤ ኢየሱስ “የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ ለእኔ ወንድሜ፣ እህቴና እናቴ ነው” በማለት መናገሩ ይህን ያሳያል። (ማር. 3:35) የአምላክ ፈቃድ ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡና ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” አገልጋዮቹ እንዲሆኑ ነው። በክርስቶስ ቤዛ ላይ እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩና የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ሁሉ “መዳን ያገኘነው በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከአምላካችን እንዲሁም ከበጉ ነው” በማለት በታላቅ ድምፅ ከሚጮኹት ሰዎች መካከል የመሆን አጋጣሚ አላቸው።—ራእይ 7:9, 10

12. ኢየሱስ የሰጠው የጸሎት ናሙና ይሖዋ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ስላለው ዓላማ ምን ይጠቁማል?

12 ኢየሱስ በሰጠው የጸሎት ናሙና ላይ የሚገኙት ልመናዎች ይሖዋ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ያለውን ዓላማ በግልጽ ያሳያሉ። አንደኛ፣ ከዚህ ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ የይሖዋ ስም እንዲቀደስ ወይም እንዲከበር የምንችለውን ሁሉ ማድረግ እንዳለብን ይጠቁማሉ። (ኢሳ. 8:13) መዳን እንድናገኝ መንገድ የከፈተልን የኢየሱስ ቤዛ የአምላክ ስም እንዲከበር ያደርጋል። እንዲያውም የኢየሱስ ስም ትርጉም “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ነው። ሁለተኛ፣ ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ቤዛው ከሚያስገኛቸው በረከቶች እንዲጠቀሙ ያደርጋል። ሦስተኛ፣ የጸሎት ናሙናው የአምላክ ፈቃድ እንዳይፈጸም ምንም ነገር ሊያግደው እንደማይችል ያረጋግጥልናል።—መዝ. 135:6፤ ኢሳ. 46:9, 10

ለቤዛው አድናቆት እንዳላችሁ አሳዩ

13. መጠመቃችን ምን ያሳያል?

13 በቤዛው በማመን ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን ስንጠመቅ ለቤዛው አድናቆት እንዳለን እናሳያለን። መጠመቃችን ‘የይሖዋ እንደሆንን’ ያሳያል። (ሮም 14:8) ጥምቀት ጥሩ ሕሊና ለማግኘት  ለአምላክ የምናቀርበው ልመና ነው። (1 ጴጥ. 3:21) ይሖዋ በክርስቶስ ደም አማካኝነት እኛን በማንጻት ለዚህ ልመና ምላሽ ይሰጠናል። ይሖዋ ይህን ማድረጉ ቃል የገባልንን ነገሮች ሁሉ እንደሚፈጽምልን ዋስትና ይሆነናል።—ሮም 8:32

ለቤዛው አድናቆት እንዳለን የምናሳይባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? (አንቀጽ 13, 14ን ተመልከት)

14. ባልንጀራችንን እንድንወድ የታዘዝነው ለምንድን ነው?

14 ለቤዛው አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው? ይሖዋ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ስለሆነ አገልጋዮቹ በሙሉ የእሱ ዓይነት ፍቅር እንዲያሳዩ ይፈልጋል። (1 ዮሐ. 4:8-11) ባልንጀራችንን የምንወድ ከሆነ “በሰማያት ላለው [አባታችን] ልጆች” መሆን እንደምንፈልግ እናሳያለን። (ማቴ. 5:43-48) ከሁሉ ከሚበልጡት ሁለት ትእዛዛት የመጀመሪያው ይሖዋን እንድንወድ የሚያዘው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ባልንጀራችንን መውደድ እንዳለብን ይገልጻል። (ማቴ. 22:37-40) ለባልንጀራችን እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዳለን ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዱ የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክ ነው። ለሰዎች ፍቅር ስናሳይ የአምላክን ክብር እናንጸባርቃለን። እንዲያውም ሌሎችን በተለይ ደግሞ ወንድሞቻችንን እንድንወድ የተሰጠንን መመሪያ ስንታዘዝ ለአምላክ ያለን ፍቅር “ፍጹም ይሆናል።”—1 ዮሐ. 4:12, 20

ቤዛው ከይሖዋ ዘንድ “የመታደስ ዘመን” ያመጣላችኋል

15. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ ከይሖዋ ምን በረከት አግኝተናል? (ለ) ወደፊት ምን በረከት እናገኛለን?

15 ይሖዋ ኃጢአታችንን ሙሉ በሙሉ ይቅር የሚለን በቤዛው ላይ እምነት ካለን ነው። የአምላክ ቃል ኃጢአታችን ‘ሊደመሰስ’ እንደሚችል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (የሐዋርያት ሥራ 3:19-21ን አንብብ።) ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ይሖዋ በመንፈስ የተቀቡ አገልጋዮቹን በቤዛው አማካኝነት ልጆቹ አድርጎ ተቀብሏቸዋል። (ሮም 8:15-17) ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆንነውን ደግሞ እንደ ልጆቹ አድርጎ ለመቀበል የሚያስችል፣ ስማችን የተጻፈበት የምሥክር ወረቀት ያዘጋጀልን ያህል ነው። ወደ ፍጽምና ደረጃ ከደረስንና የመጨረሻውን ፈተና ካለፍን በኋላ ይሖዋ በምሳሌያዊ አነጋገር በምሥክር ወረቀቱ ላይ በመፈረም ምድራዊ ልጆቹ አድርጎ ይቀበለናል። (ሮም 8:20, 21፤ ራእይ 20:7-9) ይሖዋ ውድ ለሆኑት ልጆቹ ያለው ፍቅር ዘላለማዊ ነው። ቤዛው የሚያስገኛቸው ጥቅሞችም ቢሆኑ ዘላለማዊ ናቸው። (ዕብ. 9:12) ይህ ስጦታ መቼም ቢሆን ዋጋው አይቀንስም። ማንኛውም ሰውም ሆነ ኃይል ይህን ስጦታ ሊወስድብን አይችልም።

16. ቤዛው እውነተኛ ነፃነት ያስገኘልን እንዴት ነው?

16 ዲያብሎስ ከልባቸው ንስሐ የሚገቡ ሰዎችን ውሎ አድሮ የይሖዋ ቤተሰብ አባላት እንዳይሆኑ ፈጽሞ ሊያግዳቸው አይችልም። ኢየሱስ ወደ ምድር መጥቶ “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” ሕይወቱን ሰጥቷል። በመሆኑም ቤዛው በድጋሚ መከፈል አያስፈልገውም። (ዕብ. 9:24-26) ቤዛው ከአዳም የወረስነውን ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ይደመስስልናል። የክርስቶስ መሥዋዕት የሰይጣን ዓለም ባሪያ ከመሆን ነፃ አውጥቶናል፤ እንዲሁም ከሞት ፍርሃት እንድንላቀቅ አድርጎናል።—ዕብ. 2:14, 15

17. ይሖዋ ያሳየን ፍቅር ምን እንድታደርግ ያነሳሳሃል?

17 አምላክ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ምንም ጥርጥር የለውም። ይሖዋ ያወጣቸው የተፈጥሮ ሕጎች እንደማይለዋወጡ ሁሉ ይሖዋም አይለወጥም። አምላክ ፈጽሞ አያሳፍረንም። (ሚል. 3:6) ይሖዋ ለእኛ ሕይወትን በመስጠት ብቻ ሳይወሰን ፍቅሩንም አሳይቶናል። “አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል፤ እንዲሁም አምነናል። አምላክ ፍቅር ነው።” (1 ዮሐ. 4:16) በቅርቡ መላዋ ምድር ውብ ገነት ትሆናለች፤ በምድር ላይ የሚኖሩ ሁሉ አምላክን በመምሰል አንዳቸው ለሌላው ፍቅር ያሳያሉ። በዚያ ጊዜ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ሁሉ እንዲህ ይላሉ፦ “ውዳሴ፣ ግርማ፣ ጥበብ፣ ምስጋና፣ ክብር፣ ኃይልና ብርታት ለዘላለም ለአምላካችን ይሁን። አሜን።”—ራእይ 7:12