አባቴ አርተር፣ ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው ሲሆን የሜቶዲስት ቄስ መሆን ይፈልግ ነበር። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ያዘጋጁትን ጽሑፍ ሲያነብና ከእነሱ ጋር መሰብሰብ ሲጀምር ቄስ ለመሆን የነበረውን ሐሳብ ቀየረ። አባቴ በ1914 በ17 ዓመቱ ተጠመቀ። በወቅቱ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት እየተፋፋመ ስለነበር አባቴ የውትድርና አገልግሎት እንዲሰጥ ተጠራ። ይሁን እንጂ የጦር መሣሪያ ታጥቆ ለመዋጋት ፈቃደኛ ባለመሆኑ በኦንታሪዮ፣ ካናዳ በሚገኘው ኪንግስተን ማረሚያ ቤት ለአሥር ወር እንዲታሰር ተፈረደበት። አባቴ ከእስር ከተፈታ በኋላ ኮልፖርተር (አቅኚ) በመሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመረ።

አባቴ በ1926 ሄዘል ዊልከንሰንን አገባ፤ የሄዘል እናት እውነትን የሰማችው በ1908 ነበር። እኔ የተወለድኩት ሚያዝያ 24, 1931 ሲሆን ከአራት ልጆች መካከል ሁለተኛው ነኝ። የቤተሰባችን ሕይወት በይሖዋ አምልኮ ላይ ያተኮረ ነበር፤ እንዲሁም አባባ ለመጽሐፍ ቅዱስ የነበረው ጥልቅ አክብሮት በሕይወት ዘመናችን በሙሉ ለአምላክ ቃል አድናቆት እንድናሳይ አድርጎናል። ቤተሰባችን አንድ ላይ ሆኖ ከቤት ወደ ቤት የማገልገል ልማድ ነበረው።—ሥራ 20:20

እንደ አባባ ገለልተኛ መሆንና በአቅኚነት ማገልገል

በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳ፤ በቀጣዩ ዓመት በካናዳ የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ታገደ። የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ለባንዲራ ሰላምታ እንደመስጠትና ብሔራዊ መዝሙር እንደመዘመር ያሉ የአገር ፍቅር ስሜት የሚንጸባረቅባቸው ሥነ ሥርዓቶችን ያካሂዱ ነበር። እኔና ታላቅ እህቴ ዶሮቲ እነዚህ ሥነ ሥርዓቶች ሲካሄዱ ከክፍል እንድንወጣ ይፈቀድልን ነበር። ሆኖም አንድ ቀን አስተማሪዬ፣ ፈሪ እንደሆንኩ በመናገር ልታሳፍረኝ ሞከረች። ከትምህርት በኋላ ደግሞ አብረውኝ የሚማሩ አንዳንድ ልጆች ደበደቡኝ። ይሁንና ይህ ጥቃት ‘ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢዬ አድርጌ ለመታዘዝ’ ያለኝን ቁርጥ አቋም አጠናክሮልኛል።—ሥራ 5:29

ሐምሌ 1942 በ11 ዓመቴ በአንድ እርሻ ቦታ በሚገኝ የውኃ ማጠራቀሚያ ውስጥ ተጠመቅኩ። በየዓመቱ ትምህርት ቤት ሲዘጋ የእረፍት ጊዜ አቅኚ (አሁን ረዳት አቅኚ ይባላል) ሆኜ  አገለግል ነበር። አንድ ዓመት ላይ ከሦስት ወንድሞች ጋር ሆነን በሰሜናዊ ኦንታሪዮ፣ ሰባኪዎች ባልተመደቡበት አካባቢ ለሚኖሩ ዛፍ በመቁረጥ የሚተዳደሩ ሰዎች መሥክረናል።

ግንቦት 1, 1949 የዘወትር አቅኚ ሆንኩ። ቅርንጫፍ ቢሮው የግንባታ ሥራ ያከናውን ስለነበር በዚህ ሥራ እንድካፈል ተጋበዝኩ፤ በመሆኑም ከታኅሣሥ 1 አንስቶ የካናዳ ቤቴል ቤተሰብ አባል ሆንኩ። በሕትመት ክፍል እንዳገለግል የተመደብኩ ሲሆን በማተሚያ መሣሪያው እንዴት መሥራት እንደሚቻል ሥልጠና አገኘሁ። የይሖዋ ሕዝቦች በካናዳ እየደረሰባቸው ስላለው ስደት የሚናገር ትራክት በማተም ለበርካታ ሳምንታት በሌሊት ፈረቃ ሠርቻለሁ።

ከጊዜ በኋላ በአገልግሎት ዘርፍ ስሠራ ቅርንጫፍ ቢሮውን ለመጎብኘት የመጡ የተወሰኑ አቅኚዎችን አነጋግሬ ነበር፤ እነዚህ አቅኚዎች በወቅቱ ከባድ ተቃውሞ በነበረበት በኩዊቤክ ለማገልገል እየሄዱ ነበር። ከጎብኚዎቹ አንዷ ከኤድመንተን፣ አልበርታ የመጣችው ሜሪ ዛዙላ ነበረች። እሷና ታላቅ ወንድሟ ጆ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸውን ለማቆም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አጥባቂ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የነበሩት ወላጆቻቸው ከቤት አባረዋቸው ነበር። ሰኔ 1951 ሁለቱም ተጠመቁ፤ ከስድስት ወር በኋላ ደግሞ በአቅኚነት ማገልገል ጀመሩ። አቅኚዎቹን ሳነጋግር የሜሪ መንፈሳዊነት ትኩረቴን ስቦት ነበር። ‘የተለየ ነገር ካልመጣ በቀር ይህች ልጅ ጥሩ የትዳር ጓደኛ ትሆነኛለች’ ብዬ አሰብኩ። ከዘጠኝ ወራት በኋላ ጥር 30, 1954 ተጋባን። ከተጋባን ከአንድ ሳምንት በኋላ ለወረዳ ሥራ ሥልጠና እንድንወስድ ተጋበዝን፤ ከዚያም ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በሰሜናዊ ኦንታሪዮ በሚገኝ ወረዳ ውስጥ አገለገልን።

ዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ እያደገ ሲሄድ ሚስዮናውያን እንደሚያስፈልጉ የሚገልጽ ጥሪ ቀረበ። እኔና ባለቤቴ፣ በካናዳ በክረምቱ ወቅት ያለውን ከፍተኛ ቅዝቃዜና በበጋው ወቅት ያሉትን አስቸጋሪ ቢንቢዎች መቋቋም ከቻልን የትኛውም ምድብ ላይ የሚገጥመንን ከባድ ሁኔታ መቋቋም እንደምንችል አሰብን። ሐምሌ 1956 ከጊልያድ ትምህርት ቤት 27ኛ ክፍል ተመረቅን፤ ከዚያም ኅዳር ላይ ወደ ተመደብንበት አገር ይኸውም ወደ ብራዚል ሄድን።

በብራዚል ያከናወንነው የሚስዮናዊነት አገልግሎት

ብራዚል በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ፖርቱጋልኛ መማር ጀመርን። ጥቂት የሰላምታ ቃላት ከተማርንና መጽሔት ለማበርከት የሚያስችል የአንድ ደቂቃ ሐሳብ ሸምድደን ከያዝን በኋላ በመስክ አገልግሎት መካፈል ጀመርን። የምናነጋግረው ሰው ፍላጎት ካሳየ፣ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ስለሚኖረው ሕይወት የሚገልጹ ጥቅሶች እንድናነብለት ሐሳብ ቀረበልን። አገልግሎት በወጣንበት በመጀመሪያው ቀን አንዲት ሴት በትኩረት ስላዳመጠችን ራእይ 21:3, 4ን አነበብኩላት፤ ጥቅሱን አንብቤ ስጨርስ ግን ራሴን ስቼ ወደቅኩ! እርጥበት አዘል የሆነውን ሞቃት አየር ገና አልለመድኩትም ነበር፤ ይህ የአየር ጸባይ ከዚያ በኋላም አስቸጋሪ ሆኖብኛል።

በሚስዮናዊነት እንድናገለግል የተመደብነው ካምፐስ በተባለች ከተማ ነበር፤ አሁን በዚያች ከተማ 15 ጉባኤዎች ይገኛሉ። እኛ በደረስንበት ወቅት ግን በከተማዋ የነበረው አንድ ቡድንና አራት እህቶች የሚኖሩበት የሚስዮናውያን ቤት ብቻ ነበር፤ እዚያ የነበሩት እህቶች ኤስተር ትሬሲ፣ ረሞና ባወር፣ ሉዊዛ ሽቫርትስ እና ሎሬን ብሩክስ (አሁን ሎሬን ዎለን ተብላለች)  ነበሩ። በሚስዮናውያን ቤታችን ውስጥ የነበረኝ የሥራ ድርሻ ልብስ ሲታጠብ ማገዝና ምግብ ለማብሰል የሚያገለግል የማገዶ እንጨት ማምጣት ነበር። አንድ ሰኞ ምሽት የመጠበቂያ ግንብ ጥናታችንን ከጨረስን በኋላ አንድ ያልተጠበቀ እንግዳ መጣብን። ስለ ቀኑ ውሏችን ስናወራ ሚስቴ ሶፋው ላይ ጋደም ብላ ነበር። ከተኛችበት ለመነሳት ቀና ስትል ከትራሱ ሥር አንድ እባብ ብቅ አለ፤ ቤቱ ውስጥ ትርምስ የተፈጠረ ሲሆን በመጨረሻ እባቡን ስገድለው ሁላችንም ተረጋጋን።

ለአንድ ዓመት ያህል ፖርቱጋልኛ ከተማርን በኋላ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። ገጠራማ በሆኑት ስፍራዎች እናገለግል የነበረ ሲሆን በአካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል አልነበረም፤ የምንተኛው ምንጣፍ ላይ ነበር፤ እንዲሁም ከቦታ ወደ ቦታ የምንጓዘው በፈረስና በጋሪ ነበር። ሰባኪዎች ባልተመደቡበት አንድ አካባቢ ለስብከት ዘመቻ በሄድንበት ወቅት በባቡር ተጉዘን ተራራ ላይ ወዳለ አንድ ከተማ ደረስን፤ እዚያም በእንግዳ ማረፊያ ውስጥ አንድ ክፍል ተከራየን። ቅርንጫፍ ቢሮው ለአገልግሎት የሚሆኑን 800 መጽሔቶች ላከልን። መጽሔቶቹን የያዙትን ካርቶኖች ከፖስታ ቤቱ ወደ እንግዳ ማረፊያው ለመውሰድ ብዙ ጊዜ መመላለስ ጠይቆብናል።

በ1962 ወንድሞችንና ሚስዮናዊ እህቶችን ለማሠልጠን የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት በመላው ብራዚል ተካሂዶ ነበር። ለስድስት ወር ያህል ከአንዱ ትምህርት ቤት ወደ ሌላው ትምህርት ቤት እየተጓዝኩ እንዳስተምር ተመድቤ ነበር፤ የምጓዘው ግን ከሜሪ ጋር አልነበረም። በማናውስ፣ በቤሌም፣ በፎርታሌዛ፣ በሪሲፊ እና በሳልቫዶር በተካሄዱ ትምህርት ቤቶች ላይ አስተምሬያለሁ። በማናውስ በነበርኩበት ወቅት ማናውስ ኦፔራ ሃውስ በተባለው ታዋቂ ቲያትር ቤት ውስጥ የተካሄደ አንድ የአውራጃ ስብሰባ በማደራጀቱ ሥራ ተካፍያለሁ። ከባድ ዝናብ በመዝነቡ አብዛኛው የመጠጥ ውኃ የተበከለ ሲሆን ለስብሰባው የመጡ ወንድሞችና እህቶች ምግብ ሊበሉ የሚችሉበት ተስማሚ ቦታ ማግኘትም አልቻልንም። (በወቅቱ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ምግብ ተዘጋጅቶ ይቀርብ ነበር።) በመሆኑም በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ለሚገኝ አንድ ባለ ሥልጣን የገጠመንን ችግር ነገርኩት፤ ባለ ሥልጣኑም ለስብሰባው ወቅት የሚበቃ የመጠጥ ውኃ እንድናገኝ በደግነት ዝግጅት አደረገ፤ እንዲሁም ወታደሮች ልኮ ለምግብ ማብሰያና ለመመገቢያ የሚሆኑ ሁለት ትላልቅ ድንኳኖች አስተከለ።

እኔ ወደተለያዩ ቦታዎች በምሄድበት ወቅት፣ ሜሪ ከፖርቱጋል የመጡ ሰዎች በሚሠሩበት የንግድ አካባቢ ታገለግል ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ከገንዘብ ሌላ የሚታያቸው ነገር አልነበረም። ሜሪ ከማንም ሰው ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት አልቻለችም፤ ስለሆነም ለአንዳንድ ቤቴላውያን “ጨርሶ መሄድ የማልፈልግበት ቦታ ቢኖር ፖርቱጋል ነው” ብላቸው ነበር። ብዙም ሳይቆይ አንድ ደብዳቤ ደረሰን። የሚገርመው ደብዳቤው በፖርቱጋል እንድናገለግል የሚጋብዝ ነበር! በወቅቱ ፖርቱጋል ውስጥ ሥራችን ታግዶ ነበር፤ ሜሪ መጀመሪያ ላይ ተደናግጣ የነበረ ቢሆንም የተሰጠንን ምድብ ተቀብለን ወደ ፖርቱጋል ተጓዝን።

በፖርቱጋል ማገልገል

በነሐሴ ወር 1964 ሊዝበን፣ ፖርቱጋል ደረስን። የፖርቱጋል የሚስጥር ፖሊስ በወንድሞቻችን ላይ ከፍተኛ ስደት ያደርስ ነበር። በዚህም ምክንያት እዚያ ስንደርስ ወንድሞች  መጥተው አልተቀበሉንም፤ መጀመሪያ ላይ ከአካባቢው የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ምንም ግንኙነት አለማድረጋችን የተሻለ እንደሚሆን አሰብን። የመኖሪያ ፈቃድ እስክናገኝ ድረስ በእንግዳ ማረፊያ ውስጥ ቆየን። ከዚያም ቪዛ ስናገኝ አንድ አፓርታማ ተከራየን። በመጨረሻም ጥር 1965 ቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ ከሚሠሩ ወንድሞች ጋር ተገናኘን። ከአምስት ወር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ ላይ ስንገኝ ምን ያህል እንደተደሰትን መገመት ይቻላል!

ፖሊሶች በየቀኑ የወንድሞቻችንን ቤት ይፈትሹ ነበር። የመንግሥት አዳራሾች ስለታሸጉ የጉባኤ ስብሰባ የምናደርገው በወንድሞች ቤቶች ውስጥ ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለምርመራ ወደ ፖሊስ ጣቢያዎች ይወሰዱ ነበር። ኃላፊነት ያላቸውን ወንድሞች ስም እንዲናገሩ ለማድረግ ሲሉ ፖሊሶች ከፍተኛ እንግልት ያደርሱባቸው ነበር። በዚህም ምክንያት ወንድሞች እርስ በርስ ሲጠራሩ የቤተሰብ ስማቸውን ሳይሆን የግል ስማቸውን (ለምሳሌ ዡዜ ወይም ፓውሉ) ይጠቀሙ ነበር። ስለዚህ እኛም እንደዚያው ማድረግ ጀመርን።

ከሁሉ ይበልጥ የሚያሳስበን ለወንድሞቻችን መንፈሳዊ ምግብ የማቅረቡ ጉዳይ ነበር። የሜሪ ኃላፊነት የመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕሶችንና ሌሎች ጽሑፎችን በስቴንስል ላይ መተየብ ነበር፤ ከዚያም ስቴንስሎቹን በመጠቀም ጽሑፎቹ ይባዛሉ።

በፍርድ ቤት ለምሥራቹ መሟገት

ሰኔ 1966 ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አንድ የፍርድ ጉዳይ በሊዝበን ፍርድ ቤት ታየ። የፊዦ ጉባኤ አባላት የሆኑት 49 ሰዎች በሙሉ በግል ቤት ውስጥ በተደረገ ሕጋዊ ያልሆነ ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል በሚል ተከስሰው ለፍርድ ቀረቡ። የጉባኤው አባላት ፍርድ ቤቱ ውስጥ ለሚቀርብላቸው መስቀለኛ ጥያቄ እንዴት መልስ መስጠት እንደሚችሉ እንዲዘጋጁ ስል እኔ እንደ አቃቤ ሕግ ሆኜ ጥያቄ በማቅረብ አለማመድኳቸው። በክርክሩ መሸነፋችን እንደማይቀር ብናውቅም ይህ የፍርድ ሂደት ትልቅ ምሥክርነት ለመስጠት እንደሚያስችል ተገንዝበን ነበር። ጠበቃችን ክርክሩን የደመደመው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረውን የገማልያልን ሐሳብ በድፍረት በመጥቀስ ነበር። (ሥራ 5:33-39) የመገናኛ ብዙኃን ስለ ፍርድ ሂደቱ ዘገቡ፤ ለፍርድ የቀረቡት 49 ወንድሞችና እህቶች ከ45 ቀን አንስቶ እስከ አምስት ወር ተኩል የሚደርስ እስር ተበየነባቸው። ደስ የሚለው ነገር፣ በድፍረት የተከራከረልን ጠበቃ ከመሞቱ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ጀምሮ ነበር።

ታኅሣሥ 1966 የቅርንጫፍ ቢሮው የበላይ ተመልካች ሆኜ የተሾምኩ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው ሕግ ነክ ጉዳዮችን በመከታተል ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች የአምልኮ ነፃነት ማግኘት እንዲችሉ የምንችለውን ሁሉ አድርገናል። (ፊልጵ. 1:7) በመጨረሻም ታኅሣሥ 18, 1974 የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና አገኙ። በዋናው መሥሪያ ቤት የሚያገለግሉት ወንድም ናታን ኖር እና ወንድም ፍሬድሪክ ፍራንዝ በኦፖርቶ እና በሊዝበን በተካሄደ ታሪካዊ ስብሰባ ላይ በመገኘት የደስታችን ተካፋይ ሆነዋል፤ በድምሩ 46,870 ሰዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል።

ይሖዋ ፖርቱጋልኛ በሚነገርባቸው የተለያዩ ደሴቶች ምሥራቹ እንዲስፋፋ መንገድ ከፍቷል፤ ከእነዚህም መካከል ማዴይራ፣  ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ፣ ኤዞርዝ እንዲሁም ኬፕ ቨርድ ይገኙበታል። በእነዚህ ቦታዎች ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ ትልቅ ቅርንጫፍ ቢሮ ተገነባ። ሚያዝያ 23, 1988 ወንድም ሚልተን ሄንሼል የአዲሱን ቅርንጫፍ ቢሮ የውሰና ንግግር አቀረበ፤ በዚህ ፕሮግራም ላይ 45,522 አስፋፊዎች ተገኝተው ነበር። በፖርቱጋል በሚስዮናዊነት ያገለገሉ 20 ወንድሞችና እህቶች በዚህ ታሪካዊ ክንውን ላይ ለመገኘት ወደ ፖርቱጋል ተመልሰው መምጣታቸው በጣም አስደሳች ነበር።

ታማኝ ሰዎች ከተዉት ምሳሌ ተምረናል

ባለፉት ዓመታት ከታማኝ ወንድሞች ጋር አብረን መሥራታችን ብዙ ትምህርት ለመቅሰም አስችሎናል። በአንድ የዞን ጉብኝት ወቅት ወንድም ቴዎዶር ጃራዝን በማገዝ አብሬው በመሥራቴ ትልቅ ትምህርት አግኝቻለሁ። ወንድም ጃራዝ የሚጎበኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ከባድ ችግር አጋጥሞት የነበረ ሲሆን የቅርንጫፍ ኮሚቴው አባላት ችግሩን ለመፍታት የቻሉትን ሁሉ አድርገው ነበር። ወንድም ጃራዝ “አሁን ጉዳዩን ለመንፈስ ቅዱስ ብትተዉት የተሻለ ይሆናል” በማለት ወንድሞችን አረጋጋቸው። ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በፊት ደግሞ እኔና ባለቤቴ ሜሪ፣ ብሩክሊንን ለመጎብኘት ሄደን በነበረበት ወቅት አንድ ምሽት ላይ ከወንድም ፍራንዝና ከሌሎች ወንድሞች ጋር የመገናኘት አጋጣሚ አግኝተን ነበር። ከመለያየታችን በፊት ወንድም ፍራንዝ በይሖዋ አገልግሎት ስላሳለፋቸው በርካታ ዓመታት እንዲናገር ሲጋበዝ እንዲህ አለ፦ “ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠር ከሚታየው የይሖዋ ድርጅት ጋር ተጣብቃችሁ እንድትኖሩ አበረታታችኋለሁ። ኢየሱስ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠውን ተልእኮ ይኸውም የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበኩን ሥራ እያከናወነ ያለው ይህ ድርጅት ብቻ ነው!”

እኔና ባለቤቴ ይህን በማድረጋችን ታላቅ ደስታ አግኝተናል። የዞን የበላይ ተመልካች ሆኜ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ስንጎበኝ ያሳለፍናቸውን አስደሳች ገጠመኞች ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን። እነዚህ ጉብኝቶች ወጣቶችም ሆኑ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶች በታማኝነት ለሚያከናውኑት አገልግሎት ያለንን አድናቆት ለመግለጽ እንዲሁም ይሖዋን የማገልገል ልዩ መብታቸውን ከፍ አድርገው መመልከታቸውን እንዲቀጥሉ ለማበረታታት ጥሩ አጋጣሚ ሰጥተውናል።

ይሖዋን በማገልገል በርካታ ዓመታት አሳልፈናል፤ አሁን ሁለታችንም በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እንገኛለን። ሜሪ ከበርካታ የጤና ችግሮች ጋር ትታገላለች። (2 ቆሮ. 12:9) የገጠሙን ፈተናዎች እምነታችንን ያጠሩልን ከመሆኑም ሌላ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያለንን ቁርጠኝነት አጠናክረውልናል። ያሳለፍነውን ሕይወት መለስ ብለን ስናስብ የይሖዋን ጸጋ በበርካታ መንገዶች እንደተመለከትን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። *

^ አን.29 ይህ ተሞክሮ ለሕትመት በመዘጋጀት ላይ እያለ ወንድም ዳግላስ ገስት ለይሖዋ ታማኝነቱን እንደጠበቀ ጥቅምት 25, 2015 በሞት አንቀላፍቷል።