“በመካከላችሁ ሆነው አመራር የሚሰጡትን አስቡ።”—ዕብ. 13:7

መዝሙሮች፦ 123, 126

1, 2. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ሐዋርያቱ ምን ጥያቄ ተፈጥሮባቸው ሊሆን ይችላል?

የኢየሱስ ሐዋርያት በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆነው ወደ ሰማይ አሻቅበው እየተመለከቱ ነው። ጌታቸውና ወዳጃቸው የሆነው ኢየሱስ እያዩት ወደ ላይ ወጣ፤ ከዚያም ደመና ከዓይናቸው ሰወረው። (ሥራ 1:9, 10) ኢየሱስ ለሁለት ዓመት ገደማ ያህል ሲያስተምራቸው፣ ሲያበረታታቸውና ሲመራቸው ቆይቷል። አሁን ግን ተለይቷቸዋል። ታዲያ ምን ያደርጉ ይሆን?

2 ኢየሱስ ለተከታዮቹ እንዲህ የሚል ተልእኮ ሰጥቷቸዋል፦ “በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።” (ሥራ 1:8) ይህን ተልእኮ መወጣት የሚችሉት እንዴት ነው? እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ መንፈስ ቅዱስን እንደሚቀበሉ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ሥራ 1:5) ያም ቢሆን በዓለም ዙሪያ የስብከት ዘመቻ ለማካሄድ አመራር የሚሰጣቸውና ሥራውን የሚያደራጅ አካል ያስፈልጋል። ይሖዋ በጥንት ዘመን የነበሩ ሕዝቦቹን ለመምራትና ለማደራጀት በሰዎች ተጠቅሟል። በመሆኑም ሐዋርያቱ ‘ይሖዋ አዲስ መሪ ይሾም ይሆን?’ የሚል ጥያቄ ተፈጥሮባቸው ሊሆን ይችላል።

3. (ሀ) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ታማኞቹ ሐዋርያት የትኛውን አስፈላጊ ውሳኔ አደረጉ? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ የትኞቹን ነጥቦች እንመለከታለን?

 3 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደቀ መዛሙርቱ አንድ ላይ ተሰበሰቡ፤ ከዚያም ቅዱሳን መጻሕፍትን ከመረመሩና መለኮታዊ እርዳታ ለማግኘት ከጸለዩ በኋላ የአስቆሮቱ ይሁዳን ተክቶ 12ኛ ሐዋርያ እንዲሆን ማትያስን መረጡ። (ሥራ 1:15-26) ሐዋርያቱም ሆኑ ይሖዋ 12ኛ ሐዋርያ የመመረጡን ጉዳይ ትልቅ ቦታ የሰጡት ለምንድን ነው? ደቀ መዛሙርቱ፣ 12 ሐዋርያት እንደሚያስፈልጉ ተገንዝበው ነበር። * ኢየሱስ ሐዋርያቱን የመረጠው አገልግሎቱን ሲያከናውን እንዲሁ አብረውት እንዲሆኑ ስለፈለገ ሳይሆን በአምላክ ሕዝቦች መካከል ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ ስላሰበ ነው። ሐዋርያቱ የሚጫወቱት ሚና ምንድን ነው? ይህን ሚና እንዲጫወቱ ይሖዋ በኢየሱስ በኩል ያስታጠቃቸው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ በአምላክ ሕዝቦች መካከል ምን ተመሳሳይ ዝግጅት አለ? እኛስ ‘በመካከላችን ሆነው አመራር የሚሰጡትን’ በተለይ ደግሞ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ እንደምናስብ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?—ዕብ. 13:7፤ ማቴ. 24:45

በኢየሱስ የሚመራ የበላይ አካል

4. በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሌሎች ሽማግሌዎች ምን ሚና ይጫወቱ ነበር?

4 በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ ሐዋርያት ለክርስቲያን ጉባኤ አመራር መስጠት ጀመሩ። በዚያ ወቅት “ጴጥሮስ . . . ከአሥራ አንዱ ጋር ተነስቶ በመቆም” በቦታው ለተሰበሰቡት በርካታ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ሕይወት አድን የሆነውን እውነት ተናገረ። (ሥራ 2:14, 15) ከእነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ አማኞች ሆኑ። ከዚያ በኋላ እነዚህ አዳዲስ ክርስቲያኖች “[የሐዋርያቱን] ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን ቀጠሉ።” (ሥራ 2:42) የጉባኤው ገንዘብ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርጉት ሐዋርያቱ ነበሩ። (ሥራ 4:34, 35) በተጨማሪም የአምላክ ሕዝቦች የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ምግብ ያቀርቡ ነበር፤ ሐዋርያቱ “እኛ . . . በጸሎትና ቃሉን በማስተማሩ ሥራ ላይ ሙሉ በሙሉ እናተኩራለን” ሲሉ ተናግረዋል። (ሥራ 6:4) ከዚህም ሌላ አዳዲስ ወደሆኑ ክልሎች ሄደው የወንጌላዊነቱን ሥራ እንዲያከናውኑ ተሞክሮ ያላቸውን ክርስቲያኖች ይመድቡ ነበር። (ሥራ 8:14, 15) ውሎ አድሮ ሌሎች ቅቡዓን ሽማግሌዎችም ከሐዋርያት ጋር ሆነው ከጉባኤዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መከታተል ጀመሩ። እነዚህ ሽማግሌዎችና ሐዋርያት፣ የበላይ አካል ሆነው ለሁሉም ጉባኤዎች አመራር ይሰጡ ነበር።—ሥራ 15:2

5, 6. (ሀ) መንፈስ ቅዱስ ለበላይ አካሉ ኃይል የሰጠው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) መላእክት የበላይ አካሉን የረዱት እንዴት ነው? (ሐ) የአምላክ ቃል የበላይ አካሉን ይመራው የነበረው እንዴት ነው?

5 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ይሖዋ አምላክ፣ መሪያቸው በሆነው በኢየሱስ አማካኝነት የበላይ አካሉን እንደሚመራው ተገንዝበው ነበር። ይህን በእርግጠኝነት ማወቅ የቻሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ መንፈስ ቅዱስ ለበላይ አካሉ ኃይል ሰጥቶታል። (ዮሐ. 16:13) መንፈስ ቅዱስ በሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ እንደወረደ የታወቀ ነው፤ በተለይ ግን በኢየሩሳሌም የነበሩትን ሐዋርያትና ሌሎች ሽማግሌዎች የበላይ ተመልካችነት ሚናቸውን እንዲወጡ ረድቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ49 ዓ.ም. የበላይ አካሉ ግርዘትን በተመለከተ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ መንፈስ ቅዱስ ረድቶታል። ጉባኤዎቹ የበላይ አካሉን አመራር በመከተላቸው “በእምነት እየጠነከሩና ከዕለት ወደ ዕለት በቁጥር እየጨመሩ ሄዱ።” (ሥራ 16:4, 5) ውሳኔውን የያዘው ደብዳቤም፣ የበላይ አካሉ ፍቅርንና እምነትን ጨምሮ የአምላክን መንፈስ ፍሬ ያንጸባርቅ እንደነበረ የሚያሳይ ነው።—ሥራ 15:11, 25-29፤ ገላ. 5:22, 23

6 በሁለተኛ ደረጃ፣ መላእክት የበላይ አካሉን ረድተውታል። ለምሳሌ ያህል፣ ቆርኔሌዎስ ሰዎች ልኮ ሐዋርያው ጴጥሮስን እንዲያስመጣው አንድ  መልአክ ነግሮት ነበር። ቆርኔሌዎስና ዘመዶቹ ያልተገረዙ ቢሆኑም እንኳ ጴጥሮስ ከሰበከላቸው በኋላ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው። በመሆኑም ቆርኔሌዎስ ከአሕዛብ ወገን ከሆኑት መካከል ክርስትናን የተቀበለ የመጀመሪያው ሰው ሆነ። ሐዋርያትና ሌሎች ወንድሞች የሆነውን ሲሰሙ ይህ የአምላክ ፈቃድ መሆኑን ስለተገነዘቡ ያልተገረዙ አሕዛብን የክርስቲያን ጉባኤ አባላት አድርገው ተቀበሏቸው። (ሥራ 11:13-18) ከዚህም ሌላ መላእክት፣ የበላይ አካሉ የሚመራው የስብከት ሥራ እንዲስፋፋና እንዲፋጠን አስተዋጽኦ አድርገዋል። (ሥራ 5:19, 20) በሦስተኛ ደረጃ፣ የአምላክ ቃል የበላይ አካሉን ይመራው ነበር። በመንፈስ የተቀቡት እነዚህ ሽማግሌዎች፣ ከመሠረተ ትምህርት ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን ሲያደርጉም ሆነ ድርጅታዊ አመራር ሲሰጡ በቅዱሳን መጻሕፍት ይጠቀሙ ነበር።—ሥራ 1:20-22፤ 15:15-20

7. በጥንት ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች ይመራቸው የነበረው ኢየሱስ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

7 የበላይ አካሉ አባላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው ጉባኤ ላይ ሥልጣን ቢኖራቸውም መሪያቸው ኢየሱስ መሆኑን ያውቁ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቶስ ‘አንዳንዶቹን ሐዋርያት አድርጎ ሰጠ’ ሲል ጽፏል፤ አክሎም “በሁሉም ነገር ወደ እሱ ይኸውም የአካሉ ራስ ወደሆነው ወደ ክርስቶስ በፍቅር እንደግ” ብሏል። (ኤፌ. 4:11, 15) ደቀ መዛሙርቱ በአንድ ታዋቂ ሐዋርያ ስም ከመጠራት ይልቅ ‘በመለኮታዊ አመራር ክርስቲያኖች ተብለው ተጠርተዋል።’ (ሥራ 11:26) እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ሐዋርያትና አመራር የሚሰጡ ሌሎች ወንዶች ያስተላለፏቸውን “ወጎች” ወይም በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ ልማዶች ‘አጥብቆ መያዝ’ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል። ይሁንና “[እያንዳንዱን የበላይ አካል አባል ጨምሮ] የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ . . . የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ እንደሆነ እንድታውቁ እወዳለሁ” በማለት አክሎ ተናግሯል። (1 ቆሮ. 11:2, 3) በሰማይ ያለውና ክብር የተጎናጸፈው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ በይሖዋ አምላክ ሥር ሆኖ ጉባኤውን እየመራ ነበር።

“ይህ የአምላክ እንጂ የሰው ሥራ አይደለም”

8, 9. ከ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ ጀምሮ ወንድም ራስል ምን ጠቃሚ ሚና ተጫውቷል?

8 በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ ቻርልስ ቴዝ ራስልና አጋሮቹ እውነተኛውን ክርስትና መልሰው ለማቋቋም ጥረት ማድረግ ጀመሩ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በተለያዩ ቋንቋዎች ለማሰራጨት እንዲያግዛቸው ሲሉ ዛየንስ ዎች ታወር ትራክት ሶሳይቲ የተባለውን ማኅበር በ1884 አቋቋሙ፤ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ወንድም ራስል ነበር። * ወንድም ራስል መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ያጠና የነበረ ሲሆን አምላክ ሥላሴ እንደሆነና ነፍስ እንደማትሞት የሚገልጹት ትምህርቶች ሐሰት መሆናቸውን በድፍረት አጋልጧል። ክርስቶስ የሚመለሰው በማይታይ ሁኔታ እንደሆነ እንዲሁም “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” በ1914 እንደሚያበቁ ተገንዝቦ ነበር። (ሉቃስ 21:24) ወንድም ራስል ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን ምንም ሳይቆጥብ እነዚህን እውነቶች ለሌሎች አካፍሏል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋና የጉባኤው ራስ የሆነው ኢየሱስ በዚያ ወሳኝ ወቅት ወንድም ራስልን ተጠቅመውበታል።

9 ወንድም ራስል ከሰዎች ክብር ለማግኘት አልሞከረም። በ1896 እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለእኛም ሆነ ለምናዘጋጃቸው ጽሑፎች ሙገሳና ውዳሴ መቀበል አንፈልግም፤ ‘አባ’ ወይም ‘ረቢ’ ተብለን መጠራት አንፈልግም። ማንም ሰው በእኛ ስም እንዲጠራም አንፈልግም።” አክሎም “ይህ የአምላክ እንጂ የሰው ሥራ አይደለም” ብሏል።

10. (ሀ) ኢየሱስ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ የሾመው መቼ ነው? (ለ) የበላይ አካሉ ከዎች ታወር ሶሳይቲ የተለየ መሆኑ ግልጽ የተደረገው እንዴት ነው?

10 ወንድም ራስል ከሞተ ከሦስት ዓመት በኋላ ይኸውም በ1919 ኢየሱስ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ ሾመ። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? ለቤተሰቦቹ “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው” ነው። (ማቴ. 24:45) በእነዚያ ዓመታት እንኳ በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ዋና  መሥሪያ ቤት የሚያገለግሉ ጥቂት የተቀቡ ወንድሞችን ያቀፈ አንድ ቡድን፣ ለኢየሱስ ተከታዮች መንፈሳዊ ምግብ ያዘጋጅ እንዲሁም ያቀርብ ነበር። “የበላይ አካል” የሚለው አገላለጽ በጽሑፎቻችን ላይ መጠቀስ የጀመረው ከ1940ዎቹ አንስቶ ሲሆን ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ የተባለውን ማኅበር እንደሚያመለክት ይታሰብ ነበር። ይሁንና በ1971 የበላይ አካሉ ከዎች ታወር ሶሳይቲ እና ከዳይሬክተሮቹ የተለየ እንደሆነ ተገለጸ፤ ዎች ታወር ሶሳይቲ ሕግ ነክ ጉዳዮችን ለማስፈጸም እንጂ መንፈሳዊ ሥራዎችን ለማከናወን የተቋቋመ ማኅበር አይደለም። በመሆኑም ከዚያ ጊዜ አንስቶ የበላይ አካሉ፣ የማኅበሩ ዳይሬክተሮች ያልሆኑ ቅቡዓን ወንድሞችን ያቀፈ እንዲሆን ተደረገ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የዚህ ሕጋዊ ማኅበር እና የአምላክ ሕዝቦች የሚጠቀሙባቸው ሌሎች ኮርፖሬሽኖች ዳይሬክተሮች ሆነው እያገለገሉ ነው፤ ይህም የበላይ አካሉ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብና አመራር በመስጠት ሥራ ላይ እንዲያተኩር አስችሎታል። (ዮሐ. 10:16፤ ሥራ 6:4) የሐምሌ 15, 2013 መጠበቂያ ግንብ ታማኝና ልባም ባሪያ”፣ የበላይ አካል ሆነው የሚያገለግሉትን ጥቂት ቁጥር ያላቸው የተቀቡ ወንድሞች እንደሚያመለክት ገልጾ ነበር።

በ1950ዎቹ የነበረው የበላይ አካል

11. የበላይ አካሉ ሥራውን የሚያከናውነው እንዴት ነው?

11 የበላይ አካሉ አባላት ትላልቅ ውሳኔዎችን የሚያደርጉት በቡድን ሆነው ነው። አባላቱ በሳምንት አንድ ጊዜ ይሰበሰባሉ፤ ይህም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለመመካከር የሚያስችላቸው ከመሆኑም ሌላ አንድነት እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ ያደርጋል። (ምሳሌ 20:18) የበላይ አካሉ አባላት በሙሉ፣ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ሊቀ መንበር ሆነው የማገልገል ኃላፊነት በየዓመቱ በዙር ይደርሳቸዋል፤ አባላቱ አንዳቸው ከሌላው እንደሚበልጡ አድርገው አያስቡም። (1 ጴጥ. 5:1) በበላይ አካሉ ሥር ያሉት ስድስት ኮሚቴዎች አባላትም ልክ እንደዚሁ በዙር ሊቀ መንበር ሆነው ያገለግላሉ። ማንኛውም የበላይ አካል አባል በወንድሞቹ ላይ መሪ እንደሆነ አድርጎ ራሱን አይቆጥርም፤ ከዚህ ይልቅ በግለሰብ ደረጃ ‘ከቤተሰቦቹ’ አንዱ እንደሆነ አድርጎ ያስባል፤ በመሆኑም ታማኙ ባሪያ የሚያቀርበውን ምግብ ይመገባል እንዲሁም የባሪያውን አመራር ይከተላል።

ታማኙ ባሪያ በ1919 ከተሾመበት ጊዜ አንስቶ ለአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ምግብ ሲያዘጋጅ ቆይቷል (አንቀጽ 10, 11ን ተመልከት)

“ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?”

12. ከበላይ አካሉ ጋር በተያያዘ የትኞቹ ጥያቄዎች ይነሳሉ?

12 የበላይ አካሉ መለኮታዊ ራእይ አይገለጥለትም፤ ደግሞም ጨርሶ ስህተት አይሠራም ማለት አይደለም። በመሆኑም ከመሠረተ ትምህርቶች ወይም ከድርጅታዊ አሠራር ጋር በተያያዘ አንዳንድ ስህተቶች ሊሠራ ይችላል። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) እንዲሁም የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች በተባሉት መጻሕፍት ላይ “ስለምናምንባቸው ነገሮች ያገኘነው አዲስ ግንዛቤ” የሚል ርዕስ አለ፤ በዚህ ርዕስ ሥር፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶችን ከምንረዳበት መንገድ ጋር በተያያዘ ከ1870 ጀምሮ ማስተካከያ የተደረገባቸው ነገሮች ተዘርዝረዋል። ኢየሱስ፣ ታማኙ ባሪያ ምንም እንከን የሌለበት መንፈሳዊ ምግብ እንደሚያቀርብ ቃል አልገባም። ታዲያ ኢየሱስ “ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?” በማለት ላቀረበው ጥያቄ መልስ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (ማቴ. 24:45) ይህን ሚና እየተጫወተ ያለው የበላይ አካሉ እንደሆነ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ? በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው የበላይ አካል ጋር በተያያዘ ያነሳናቸውን ሦስት ነጥቦች እስቲ እንመልከት።

13. መንፈስ ቅዱስ የበላይ አካሉን የረዳው እንዴት ነው?

13 መንፈስ ቅዱስ እንደሚመራው የሚያሳይ ማስረጃ። የበላይ አካሉ ቀደም ሲል ግልጽ ያልነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እንዲገነዘብ መንፈስ ቅዱስ ረድቶታል። የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች በተባለው መጽሐፍ ላይ፣ “ስለምናምንባቸው ነገሮች ያገኘነው አዲስ ግንዛቤ” በሚለው ርዕስ ሥር የተዘረዘሩትን ነገሮች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እነዚህን ‘የአምላክ ጥልቅ ነገሮች’ መረዳትና ማብራራት የተቻለው በሰዎች ችሎታ እንዳልሆነ ጥርጥር የለውም! (1 ቆሮንቶስ 2:10ን አንብብ።) የበላይ አካሉ የሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት አመለካከት አለው፤ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር፦ “እነዚህን ነገሮች እንናገራለን፤ የምንናገረው  ግን ከሰው ጥበብ በተማርነው ቃል አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ . . . ከመንፈስ በተማርነው ቃል እንናገራለን።” (1 ቆሮ. 2:13) ለበርካታ መቶ ዓመታት ክህደት ሲስፋፋ ከቆየ በኋላ መንፈሳዊው ጨለማ ተገፍፎ በተለይ ከ1919 ወዲህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ይበልጥ በግልጽ መረዳት የተቻለው ለምንድን ነው? አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት የበላይ አካሉን ስለረዳው እንደሆነ ምንም አያጠያይቅም!

14. ራእይ 14:6, 7 እንደሚያሳየው መላእክት በዛሬው ጊዜ የአምላክን ሕዝቦች እየረዱ ያሉት እንዴት ነው?

14 የመላእክት ድጋፍ እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ። በዛሬው ጊዜ የበላይ አካሉ ከስምንት ሚሊዮን የሚበልጡ ወንጌላውያን እያከናወኑት ያለውን ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ የመምራት ትልቅ ኃላፊነት አለበት። ይህ ሥራ ውጤታማ የሆነው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት መላእክት ለዚህ ሥራ እገዛ ስለሚያደርጉ ነው። (ራእይ 14:6, 7ን አንብብ።) አስፋፊዎች፣ እርዳታ ለማግኘት ሲጸልዩ የነበሩ ሰዎችን ሄደው እንዲያነጋግሩ መላእክት እንደመሯቸው የሚያሳዩ በርካታ ተሞክሮዎች አሉ! * በተጨማሪም በአንዳንድ አገሮች ከባድ ተቃውሞ ቢኖርም ከስብከቱና ደቀ መዛሙርት ከማድረጉ ሥራ ጋር በተያያዘ በዓለም ዙሪያ የሚታየው እድገት ሥራው የመላእክት ድጋፍ እንዳለው የሚያሳይ ነው።

15. በይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካልና በሕዝበ ክርስትና መሪዎች መካከል ምን ልዩነት አለ? ምሳሌ ስጥ።

15 በአምላክ ቃል እንደሚመራ የሚያሳይ ማስረጃ። (ዮሐንስ 17:17ን አንብብ።) በ1973 የተከናወነውን ነገር እንመልከት። በሰኔ 1 መጠበቂያ ግንብ ላይ “ከትንባሆ ሱስ መላቀቅ ያልቻሉ ሰዎች ለመጠመቅ ብቁ ይሆናሉ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር። መልሱ “ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚያሳዩት  እንዲህ ያሉ ሰዎች ለመጠመቅ ብቁ አይሆኑም” የሚል ነበር። መጠበቂያ ግንቡ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አንዳንድ ጥቅሶችን ከጠቀሰ በኋላ ንስሐ የማይገቡ አጫሾች ከጉባኤ መወገድ ያለባቸው ለምን እንደሆነ አብራርቷል። (1 ቆሮ. 5:7፤ 2 ቆሮ. 7:1) መጠበቂያ ግንቡ እንዲህ ይላል፦ “ይህ እንዲሁ በጭፍን የተደረገ ፍትሐዊ ያልሆነ ውሳኔ አይደለም። የዚህ ጥብቅ መመሪያ ምንጭ አምላክ ነው፤ እሱም ሐሳቡን በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ አማካኝነት ገልጾልናል።” ለአንዳንድ አባላቱ ሊከብድ ቢችልም እንኳ ሙሉ በሙሉ በአምላክ ቃል ለመመራት ጥረት የሚያደርግ ሌላ የሃይማኖት ድርጅት አለ? በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ ስለ ሃይማኖት የተጻፈ አንድ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “የክርስትና ሃይማኖት መሪዎች፣ በአባሎቻቸውና በብዙኃኑ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን እምነቶችና አመለካከቶች ለማስተናገድ ሲሉ በየጊዜው በትምህርቶቻቸው ላይ ማስተካከያ ያደርጋሉ።” የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ግን የሚመራው በብዙኃኑ አመለካከት ሳይሆን በአምላክ ቃል ነው፤ ይህም በዛሬው ጊዜ ያሉትን የአምላክ ሕዝቦች የሚመራቸው ይሖዋ መሆኑን ያረጋግጣል።

“አመራር የሚሰጡትን አስቡ”

16. የበላይ አካሉን ማሰብ የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

16 ዕብራውያን 13:7ን አንብብ። እዚህ ላይ “አስቡ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “ጥቀሱ” የሚል ፍቺም ሊሰጠው ይችላል። በመሆኑም ‘አመራር የሚሰጡትን ማሰብ’ የምትችሉበት አንዱ መንገድ የበላይ አካሉን አባላት በጸሎታችሁ ላይ መጥቀስ ነው። (ኤፌ. 6:18) መንፈሳዊ ምግብ የማቅረብ፣ ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ በበላይነት የመምራት እንዲሁም በመዋጮ የተሰበሰበውን ገንዘብ በአግባቡ ጥቅም ላይ የማዋል ኃላፊነት እንዳለባቸው አስታውሱ። በእርግጥም ስለ እነዚህ ወንድሞች አዘውትረን መጸለይ አለብን!

17, 18. (ሀ) ከበላይ አካሉ ጋር እንደምንተባበር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በስብከቱ ሥራ በትጋት መካፈል ያለብን ለምንድን ነው?

17 የበላይ አካሉን ማሰብ ሲባል የሚሰጠንን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግንም ይጨምራል። የበላይ አካሉ በጽሑፎቻችን እንዲሁም በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች አማካኝነት መመሪያ ይሰጠናል። ከዚህም ሌላ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችን ይሾምልናል፤ እነሱ ደግሞ የጉባኤ ሽማግሌዎችን ይሾማሉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ የሚተላለፉትን መመሪያዎች በጥብቅ በመከተል የበላይ አካሉን እንደሚያስቡ ያሳያሉ። ሁላችንም መሪያችን የሆነው ኢየሱስ እኛን ለመምራት የሚጠቀምባቸውን ወንዶች በመታዘዝና ለእነሱ በመገዛት ለአመራሩ አክብሮት እንዳለን እናሳያለን።—ዕብ. 13:17

18 የበላይ አካሉን እንደምናስብ የምናሳይበት ሌላው መንገድ በስብከቱ ሥራ በትጋት መካፈል ነው። ጳውሎስም ቢሆን ክርስቲያኖች፣ በመካከላቸው ሆነው አመራር የሚሰጡትን ወንድሞች በእምነታቸው እንዲመስሏቸው አሳስቧል። ታማኙ ባሪያ የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት በማስፋፋትና በማዳረስ ታላቅ እምነት እንዳለው አሳይቷል። አንተስ በዚህ አስፈላጊ ሥራ በመካፈል ቅቡዓኑን እየደገፍክ ነው? ከሆነ መሪያችን ኢየሱስ “ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል” ብሎ በሚናገርበት ጊዜ እንደምትደሰት ጥርጥር የለውም።—ማቴ. 25:34-40

19. መሪያችን የሆነውን ኢየሱስን ለመከተል የወሰንከው ለምንድን ነው?

19 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲመለስ ተከታዮቹን አልረሳቸውም። (ማቴ. 28:20) ምድር ላይ ሆኖ አመራር ይሰጥ በነበረበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ፣ መላእክትና የአምላክ ቃል ምን ያህል እንደረዱት ያውቃል። በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ታማኙን ባሪያ በእነዚህ ሦስት መንገዶች እየረዳው ነው። የዚህ ባሪያ አባላት የሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ምንጊዜም በጉ በሄደበት ሁሉ ይከተሉታል።” (ራእይ 14:4) እኛም የእነሱን መመሪያ ከተከተልን መሪያችን የሆነውን ኢየሱስን እየተከተልን ነው። በቅርቡ ደግሞ በእሱ አመራር ሥር የዘላለም ሕይወት እናገኛለን። (ራእይ 7:14-17) የትኛውም ሰብዓዊ መሪ እንዲህ ዓይነት ተስፋ ሊሰጠን አይችልም!

^ አን.3 ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው የይሖዋ ዓላማ 12 ሐዋርያት፣ ወደፊት የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም “12 የመሠረት ድንጋዮች” እንዲሆኑ ነው። (ራእይ 21:14) በመሆኑም ከጊዜ በኋላ ምድራዊ ሕይወቱን በታማኝነት ያጠናቀቀን ማንኛውንም ሐዋርያ መተካት አላስፈለገም።

^ አን.8 ከ1955 ወዲህ ይህ ኮርፖሬሽን ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንስልቬንያ ተብሏል።

^ አን.14 ስለ አምላክ መንግሥት ‘የተሟላ ምሥክርነት መስጠት’ የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 58-59 ተመልከት።