በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  የካቲት 2016

ይሖዋ “ወዳጄ” በማለት ጠርቶታል

ይሖዋ “ወዳጄ” በማለት ጠርቶታል

“እስራኤል ሆይ፣ አንተ . . . አገልጋዬ ነህ፤ ያዕቆብ ሆይ፣ አንተን መርጬሃለሁ፤ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ነህ።”—ኢሳ. 41:8

መዝሙሮች፦ 91, 22

1, 2. (ሀ) የሰው ልጆች የአምላክ ወዳጆች መሆን እንደሚችሉ እንዴት ማወቅ እንችላለን? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

ከተወለድንበት ጊዜ ጀምሮ እስከምንሞትበት ጊዜ ድረስ ፍቅር ማግኘት እንፈልጋለን። በእርግጥም እኛ የሰው ልጆች ፍቅር ያስፈልገናል፤ እንዲያውም ፍቅር እንደ ምግብ ይርበናል። ይህን ስንል በተቃራኒ ፆታዎች መካከል ያለውን ፍቅር ብቻ ማለታችን አይደለም። ሁላችንም ከሌሎች ጋር ወዳጅነት የመመሥረትና የመቀራረብ ከፍተኛ ፍላጎት አለን። ይሁንና ከሁሉ በላይ የሚያስፈልገን የይሖዋን ፍቅር ማግኘት ነው። ብዙ ሰዎች፣ በሰማይ የሚኖር የማይታይ መንፈሳዊ አካል ከሆነው ሁሉን ቻይ አምላክ ጋር በፍቅር ላይ የተመሠረተ የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ይቻላል ብሎ ማሰብ ይከብዳቸዋል። እኛስ እንዲህ ዓይነት ጥርጣሬ አለን? በፍጹም!

2 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች የአምላክ ወዳጆች መሆን እንደቻሉ ይናገራል። በእነዚህ ሰዎች ታሪክ ላይ ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም በሕይወታችን ውስጥ ሊኖሩን ከሚችሉት ግቦች ሁሉ የላቀው ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ነው። እንዲህ ዓይነት ወዳጅነት ከመሠረቱ ሰዎች መካከል አብርሃም በምሳሌነቱ የሚጠቀስ ነው። (ያዕቆብ 2:23ን አንብብ።) አብርሃም ከይሖዋ ጋር ይህን ያህል የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የቻለው እንዴት ነው? ለወዳጅነታቸው ቁልፍ ሚና የተጫወተው እምነት ነው። መጽሐፍ  ቅዱስ፣ አብርሃም “በእምነታቸው የተነሳ እንደ ጻድቃን ለተቆጠሩት ሁሉ አባት” እንደሆነ ይናገራል። (ሮም 4:11) የአብርሃም እምነት ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት የረዳው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። እያንዳንዳችን ‘አብርሃምን በእምነቱ መምሰል እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ያለኝን ወዳጅነት ማጠናከር የምችለው እንዴት ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው።

አብርሃም የይሖዋ ወዳጅ ለመሆን የበቃው እንዴት ነው?

3, 4. (ሀ) አብርሃም በሕይወቱ ካጋጠሙት የእምነት ፈተናዎች ሁሉ ከባድ የሆነው የትኛው ነው? (ለ) አብርሃም፣ ይስሐቅን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነው ለምንድን ነው?

3 አንድ አረጋዊ ሰው እያዘገመ ተራራ ሲወጣ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። በሕይወቱ ውስጥ ካደረጋቸው ጉዞዎች ሁሉ ይህ ከባዱ ሳይሆን አይቀርም። ጉዞውን ከባድ ያደረገበት የዕድሜው መግፋት አይደለም። አብርሃም 125 ዓመት ገደማ ቢሆነውም ጉልበቱ አሁንም ጠንካራ ነው። [1] አብሮት የሚጓዘው ወጣት 25 ዓመት ገደማ ይሆነዋል። ይህ ወጣት፣ የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ ሲሆን የማገዶ እንጨት ተሸክሟል። አብርሃም ደግሞ ቢላ እንዲሁም እሳት ለማቀጣጠል የሚያስፈልገውን ነገር ይዟል። አብርሃም የገዛ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ይሖዋ ጠይቆት ነበር!—ዘፍ. 22:1-8

4 አብርሃም በሕይወቱ ካጋጠሙት ሁሉ ከባድ የሆነ የእምነት ፈተና ተደቅኖበታል። አንዳንዶች፣ አምላክ ለአብርሃም እንዲህ ዓይነት ጥያቄ በማቅረቡ ጨካኝ እንደሆነ ያስባሉ፤ ሌሎች ደግሞ አብርሃም አምላክን የታዘዘው እንዲሁ በጭፍን እንደሆነ ይናገራሉ፤ እንዲሁም ለልጁ ፍቅር እንደሌለው ይሰማቸዋል። እንዲህ ያለ አስተያየት የሚሰነዝሩት ግን እምነት ስለሌላቸውና የእምነት ትርጉም ስለማይገባቸው ነው። (1 ቆሮ. 2:14-16) አብርሃም አምላክን የታዘዘው በጭፍን አይደለም። ከዚህ ይልቅ የታዘዘው ነገሮችን በእምነት ዓይን ስለተመለከተ ነው። አብርሃም የእምነት ዓይን ስለነበረው በሰማይ ያለው አባቱ ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዮቹ ዘላቂ ጉዳት የሚያመጣባቸውን ነገር እንዲፈጽሙ እንደማይጠይቃቸው መመልከት ችሏል። ይሖዋን ከታዘዘ፣ አምላኩ እሱንም ሆነ የሚወደውን ልጁን እንደሚባርካቸው ያውቅ ነበር። ይሁንና ለእምነቱ መሠረት የሆነው ምን ነበር? እውቀትና ተሞክሮ ነው።

5. አብርሃም ስለ ይሖዋ የተማረው እንዴት ሊሆን ይችላል? ያወቀው ነገር ምን እንዲሰማው አድርጓል?

5 እውቀት። አብርሃም የጣዖት አምልኮ በተስፋፋባት ዑር የተባለች የከለዳውያን ከተማ ያደገ ቢሆንም ስለ ይሖዋ ያውቅ ነበር። አባቱ ታራ፣ ጣዖት አምላኪ ከመሆኑ አንጻር አብርሃም ይሖዋን ማወቅ የቻለው እንዴት ነው? (ኢያሱ 24:2) መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የሚነግረን ነገር ባይኖርም አብርሃም ከሴም ጀምሮ ሲቆጠር ዘጠነኛው ትውልድ ላይ እንደኖረ ይጠቁመናል፤ ሴም ከኖኅ ልጆች አንዱ ሲሆን ታላቅ እምነት ነበረው። አብርሃም 150 ዓመት ገደማ እስኪሆነው ድረስ ሴም በሕይወት ነበር። አብርሃም ስለ ይሖዋ ከሴም የተማረው ነገር ይኑር አይኑር በእርግጠኝነት ማወቅ አንችልም። ያም ቢሆን ሴም ስለ ይሖዋ የሚያውቀውን ነገር ለቤተሰቡ ነግሯቸው እንደሚሆን ማሰቡ ምክንያታዊ ይመስላል። አብርሃም ስለ ይሖዋ ያወቀው ነገር ልቡን ነክቶታል። ስለ አምላክ የተማረው ነገር እሱን እንዲወደው ያደረገ ሲሆን እውቀቱ ደግሞ እምነት እንዲያዳብር ረድቶታል።

6, 7. የአብርሃምን እምነት ያጠናከሩለት የትኞቹ ተሞክሮዎች ናቸው?

6 ተሞክሮ። አብርሃም በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት የሚያጠናክር ተሞክሮ ያገኘው እንዴት ነው? ሐሳብ ወደ ስሜት፣ ስሜት ደግሞ ወደ ድርጊት እንደሚመራ ሲነገር እንሰማለን። አብርሃም ስለ አምላክ የተማረው ነገር ‘ሰማይንና ምድርን ለሠራው ለልዑሉ አምላክ ለይሖዋ’ ጥልቅ አክብሮት ብሎም ከልብ የመነጨ የአድናቆት ስሜት እንዲያድርበት አድርጓል። (ዘፍ. 14:22) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ስሜት “አምላካዊ ፍርሃት” በማለት የሚጠራው ሲሆን ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ይህ ባሕርይ አስፈላጊ ነው። (ዕብ. 5:7፤ መዝ. 25:14) እንዲህ ያለው አምላካዊ ፍርሃት፣ አብርሃምን ለተግባር አነሳስቶታል።

7 አምላክ በዕድሜ የገፉትን አብርሃምንና ሣራን፣ ዑርን ለቀው በመውጣት ወደማያውቁት አገር  እንዲሄዱ አዘዛቸው። እነዚህ ባልና ሚስት ቀሪ ሕይወታቸውን የሚያሳልፉት በድንኳን ውስጥ ይሆናል። አብርሃም ታዛዥ መሆኑ ይሖዋ እንዲባርከውና ጥበቃ እንዲያደርግለት መንገድ ከፍቷል። ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም ውብ የሆነችውን ሚስቱን ሣራን ሌሎች እንዳይነጥቁትና እሱን እንዳይገድሉት ሰግቶ ነበር። ደግሞም መፍራቱ ተገቢ ነበር፤ ሆኖም እንዲህ ያለው ፍርሃት ይሖዋን ከመታዘዝ ወደኋላ እንዲል አላደረገውም። ይሖዋም በተደጋጋሚ ጊዜ ጣልቃ በመግባት ለአብርሃምና ለሣራ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ጥበቃ አድርጎላቸዋል። (ዘፍ. 12:10-20፤ 20:2-7, 10-12, 17, 18) እነዚህ ተሞክሮዎች የአብርሃምን እምነት አጠናክረውለታል።

8. ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት የሚያጠናክር እውቀትና ተሞክሮ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

8 እኛስ የይሖዋ ወዳጆች መሆን እንችላለን? እንዴታ! ይህን ለማድረግ የሚያስፈልገንን እውቀትና ተሞክሮ በቀላሉ ማግኘት እንችላለን። በአሁኑ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ማለቂያ የሌለው ጥበብ ውስጥ አብርሃም ያገኘው በጣም ጥቂቱን ብቻ ነበር። (ዳን. 12:4፤ ሮም 11:33) የአምላክ ቃል ‘ሰማይንና ምድርን ስለሠራው’ አምላክ ያለን እውቀት ጥልቀት እንዲኖረው እንዲሁም ለእሱ አክብሮትና ፍቅር እንድናዳብር በሚረዳን ውድ ሀብት የተሞላ ነው። እንዲህ ያለው አክብሮትና ፍቅር አምላክን እንድንታዘዝ ያነሳሳናል፤ እሱን መታዘዝ የሚያስገኘውን ውጤት ስናይ ደግሞ ተሞክሮ እናገኛለን። ይሖዋ የሚሰጠን ምክር ጥበቃ እንደሚሆንልን በሕይወታችን እንመለከታለን፤ እንዲሁም አምላክ እንደሚባርከንና እንደሚያጠነክረን እንገነዘባለን። አምላክን በሙሉ ልብ ማገልገል እርካታ፣ ሰላምና ደስታ እንደሚያስገኝ እንረዳለን። (መዝ. 34:8፤ ምሳሌ 10:22) እውቀታችንና ተሞክሯችን በዚህ መንገድ እየጨመረ ሲሄድ በይሖዋ ላይ ያለን እምነትና ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነትም እየተጠናከረ ይሄዳል።

አብርሃም ከአምላክ ጋር ያለው ወዳጅነት ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ያደረገው እንዴት ነው?

9, 10. (ሀ) ወዳጅነት እንዲጠናከር ምን ያስፈልጋል? (ለ) አብርሃም ከይሖዋ ጋር ያለውን ወዳጅነት ይንከባከበውና ወዳጅነቱ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ይጥር እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?

9 ወዳጅነት እንደ ውድ ሀብት ሊቆጠር ይችላል። (ምሳሌ 17:17ን አንብብ።) ይሁንና ወዳጅነት፣ አንዴ ከገዛነው በኋላ የሆነ ቦታ አስቀምጠነው የአቧራ መከማቻ እንደሚሆን ዕቃ አይደለም። ወዳጅነት፣ እየፋፋና እየተመቸው እንዲሄድ እንክብካቤና ምግብ እንደሚሻ ሕይወት ያለው ነገር ነው። አብርሃም ከይሖዋ ጋር ያለውን ወዳጅነት ይንከባከበው እንዲሁም ወዳጅነቱ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ይጥር ነበር። ይህን ያደረገው እንዴት ነው?

10 አብርሃም፣ ፈሪሃ አምላክና ታዛዥነት በማሳየት ረገድ ቀደም ሲል ያስመዘገበው ታሪክ በቂ እንደሆነ ፈጽሞ ተሰምቶት አያውቅም። ሰፊ የሆነውን ቤተሰቡን ይዞ ወደ ከነአን ሲጓዝ ቀላልም ይሁን ከባድ ውሳኔዎች ማድረግ አስፈልጎታል፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ ይሖዋ እንዲመራው ፈቅዷል። ይስሐቅ ከመወለዱ ከአንድ ዓመት በፊት ይኸውም አብርሃም የ99 ዓመት ሰው እያለ ይሖዋ በቤተሰቡ ውስጥ ያሉትን ወንዶች ሁሉ እንዲገርዝ አብርሃምን አዘዘው። አብርሃም በዚህ ትእዛዝ ላይ ጥያቄ አንስቶ ነበር? አሊያም ላለመታዘዝ ሰበብ ፈልጎ ይሆን? በፍጹም፤ በአምላክ  በመታመን የታዘዘውን “በዚያኑ ዕለት” ፈጽሟል።—ዘፍ. 17:10-14, 23

11. አብርሃም የሰዶምና የገሞራ ጥፋት ያሳሰበው ለምንድን ነው? ይሖዋስ ከዚህ ጋር በተያያዘ የረዳው እንዴት ነው?

11 አብርሃም፣ ትናንሽ በሚመስሉ ጉዳዮች እንኳ ይሖዋን የመታዘዝ ልማድ ስለነበረው ከአምላክ ጋር ያለው ወዳጅነት ይበልጥ እየጠነከረ እንዲሄድ ማድረግ ችሏል። የልቡን አውጥቶ ለይሖዋ ለመናገር ነፃነት ይሰማው ነበር፤ ከበድ ያሉ ጥያቄዎች ሲፈጠሩበትም ይሖዋን ከመጠየቅ ወደኋላ አላለም። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ሰዶምንና ገሞራን ሊያጠፋቸው እንደሆነ አብርሃም ሲያውቅ ‘ጻድቃን ከክፉዎች ጋር አብረው ይጠፉ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ አሳስቦት ነበር። ምናልባትም አብርሃም በወቅቱ በሰዶም ይኖር የነበረው የወንድሙ ልጅ የሎጥና የቤተሰቡ ሁኔታ አስጨንቆት ይሆናል። አብርሃም “የምድር ሁሉ ዳኛ” ለሆነው አምላክ ጥያቄዎቹን ያቀረበው በታላቅ ትሕትና ሲሆን በእሱም ይተማመን ነበር። ይሖዋም ምን ያህል መሐሪ አምላክ እንደሆነ አብርሃም እንዲገነዘብ በትዕግሥት ረድቶታል፤ የፍርድ እርምጃ በሚወስድበት ጊዜም እንኳ ከጥፋቱ የሚተርፉ ጻድቃንን ለማግኘት የእያንዳንዱን ሰው ልብ እንደሚመረምር ለአብርሃም አስገንዝቦታል።—ዘፍ. 18:22-33

12, 13. (ሀ) አብርሃም ያካበተው እውቀትና ተሞክሮ ከጊዜ በኋላ የጠቀመው እንዴት ነው? (ለ) አብርሃም በይሖዋ ላይ እምነት እንደነበረው የሚያሳየው ምንድን ነው?

12 አብርሃም ያካበተው እውቀትና ተሞክሮ በሙሉ ከይሖዋ ጋር ያለውን የጠበቀ ወዳጅነት ለማጠናከር እንደረዳው ምንም ጥርጥር የለውም። ከጊዜ በኋላ ከባድ ፈተና ባጋጠመው ይኸውም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት እንዲያደርግ ይሖዋ በጠየቀው ወቅት፣ በሰማይ ስላለው ወዳጁ የሚያውቀው ነገር ወደ አእምሮው መጥቶ መሆን አለበት። እስቲ በመግቢያው ላይ ወዳነሳነው ዘገባ እንመለስና ይህ ታማኝ ሰው በሞሪያ ምድር የሚገኘውን ተራራ ሲወጣ በዓይነ ሕሊናችን ለመመልከት እንሞክር። በዚህ ወቅት አብርሃም፣ ይሖዋ ባሕርይው ተለውጦ ጨካኝና ምሕረት የለሽ እንደሆነ አስቦ ይሆን? አብርሃም ይህ ፈጽሞ ሊሆን እንደማይችል ያውቃል! እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

13 አብርሃም አብረውት ከተጓዙት አገልጋዮቹ ከመለየቱ በፊት “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ በመሄድ በአምላክ ፊት ሰግደን ወደ እናንተ እንመለሳለን” ብሏቸዋል። (ዘፍ. 22:5) አብርሃም ምን ማለቱ ነበር? ይስሐቅን መሥዋዕት ሊያደርገው እንደሆነ እያወቀ ከይስሐቅ ጋር እንደሚመለስ ለአገልጋዮቹ ሲናገር እየዋሸ ነበር? በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ አብርሃም ምን አስቦ እንደነበር ለማወቅ ይረዳናል። (ዕብራውያን 11:19ን አንብብ።) አብርሃም “አምላክ [ይስሐቅን] ከሞት እንኳ ሳይቀር ሊያስነሳው እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር።” አዎ፣ አብርሃም በትንሣኤ ያምን ነበር። እሱም ሆነ ሣራ በስተርጅናቸው ልጅ መውለድ እንዲችሉ ይሖዋ እንደረዳቸው ያውቃል። (ዕብ. 11:11, 12, 18) አብርሃም በይሖዋ ዘንድ የማይቻል ነገር እንደሌለ ተገንዝቧል። በመሆኑም በዚያ ፈታኝ ወቅት የሚፈጠረው ነገር ምንም ይሁን ምን፣ የሚወደውን ልጁን መልሶ እንደሚያገኘው እርግጠኛ ነበር፤ ምክንያቱም ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች በሙሉ የሚፈጸሙት በይስሐቅ በኩል ነው። በእርግጥም አብርሃም “በእምነታቸው የተነሳ እንደ ጻድቃን ለተቆጠሩት ሁሉ አባት” ተብሎ መጠራቱ ምንም አያስደንቅም!

14. ይሖዋን ስታገለግል ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙሃል? አብርሃም የተወው ምሳሌ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

 14 ስለ እኛስ ምን ማለት ይቻላል? በዛሬው ጊዜ አምላክ እንዲህ ያለ ጥያቄ እንደማያቀርብልን የታወቀ ነው። ሆኖም ትእዛዛቱን መፈጸም ከባድ በሚሆንብን ወይም አንድ ዓይነት መመሪያ የተሰጠበትን ምክንያት ሙሉ በሙሉ በማንረዳበት ጊዜም እንኳ እንድንታዘዘው ይጠብቅብናል። ከአምላክ ትእዛዛት መካከል ለመታዘዝ የሚከብድህ አለ? አንዳንዶች የስብከቱ ሥራ ከባድ ይሆንባቸዋል። ዓይናፋር በመሆናቸው ለማያውቁት ሰው ምሥራቹን መንገር ይጨንቃቸው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ በትምህርት ቤት አሊያም በሥራ ቦታ አብረዋቸው ካሉት ሰዎች የተለዩ መሆን ተፈታታኝ ሊሆንባቸው ይችላል። (ዘፀ. 23:2፤ 1 ተሰ. 2:2) አንተም ልክ እንደ አብርሃም የሞሪያን ተራራ እየወጣህ ያለ ያህል፣ የተሰጠህ ሥራ ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ይሰማሃል? ከሆነ ስለ አብርሃምና ስላሳየው እምነት ማሰብህ ደፋር እንድትሆን ይረዳሃል! ታማኝ ወንዶችና ሴቶች በተዉት ምሳሌ ላይ ማሰላሰላችን እነሱን ለመምሰልና ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖረን ለማድረግ ያነሳሳናል።—ዕብ. 12:1, 2

በረከት የሚያስገኝ ወዳጅነት

15. አብርሃም በታማኝነት ይሖዋን መታዘዙ ቆጭቶት እንደማያውቅ እርግጠኞች የምንሆነው ለምንድን ነው?

15 አብርሃም በታማኝነት ይሖዋን መታዘዙ ቆጭቶት የሚያውቅ ይመስልሃል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወቱ መጨረሻ ሲናገር “አብርሃም እስትንፋሱ ቀጥ አለ፤ ሸምግሎ፣ በሕይወቱ ረክቶና ዕድሜ ጠግቦ ሞተ” ይላል። (ዘፍ. 25:8) አብርሃም 175 ዓመት ሲሆነው ጉልበቱ ቢደክምም ያሳለፈውን ግሩም ሕይወት ወደኋላ መለስ ብሎ ሲያስብ እርካታ ተሰምቶታል። በሕይወቱ ውስጥ ዋናውን ቦታ የያዘው ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለው ወዳጅነት ነበር። ይሁንና አብርሃም “በሕይወቱ ረክቶና ዕድሜ ጠግቦ” እንደሞተ ስናነብ ወደፊት ለመኖር እንደማይጓጓ ልናስብ አይገባም።

16. አብርሃም በገነት ውስጥ የትኞቹን ነገሮች ማወቁ ያስደስተዋል?

16 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አብርሃም ሲናገር “አምላክ ንድፍ ያወጣላትንና የገነባትን፣ እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር” ይላል። (ዕብ. 11:10) አብርሃም ይህች ከተማ ይኸውም የአምላክ መንግሥት ምድርን ስትገዛ የሚያይበት ቀን እንደሚመጣ እምነት ነበረው፤ ደግሞም ይህ ሲሆን ያያል! አብርሃም ገነት በሆነችው ምድር ላይ መኖር እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ያለውን ወዳጅነት ምንጊዜም ማጠናከር ምን ያህል ሊያስደስተው እንደሚችል መገመት ትችላለህ! አብርሃም የተወው የእምነት ምሳሌ፣ እሱ ከሞተ በኋላ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የይሖዋ አገልጋዮችን እንደረዳ ሲያውቅ በጣም እንደሚደሰት ግልጽ ነው! አብርሃም፣ ይስሐቅን ከሞት አፋፍ መልሶ ማግኘቱ ከዚያ ለላቀ ነገር “እንደ ምሳሌ ሆኖ” እንዳገለገለም በገነት በሚኖርበት ጊዜ ይገነዘባል። (ዕብ. 11:19) በተጨማሪም ይስሐቅን መሥዋዕት ለማድረግ ሲዘጋጅ የተሰማው ሥቃይ ይሖዋ፣ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በሆነበት ወቅት የተሰማውን ሥቃይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታማኝ ሰዎች እንዲገነዘቡ ረድቷል፤ አብርሃም በገነት ውስጥ ሲኖር ይህንንም ያውቃል። (ዮሐ. 3:16) የአብርሃም ምሳሌ፣ በታሪክ ውስጥ ከታዩት ሁሉ የላቀውን የፍቅር መግለጫ ማለትም የቤዛውን ስጦታ ሁላችንም ይበልጥ ማድነቅ እንድንችል ረድቶናል!

17. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

17 ሁላችንም አብርሃምን በእምነቱ ለመምሰል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ይሖዋን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን በመመላለስ ረገድ በእሱ ዘንድ ጥሩ ስም እናተርፋለን፤ እንዲሁም እሱን በታማኝነት ማገልገል ስለሚያስገኘው ሽልማት ብዙ ተሞክሮ ይኖረናል። (ዕብራውያን 6:10-12ን አንብብ።) ይሖዋ ለዘላለም ወዳጃችን እንዲሆን ምኞታችን ነው! በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ደግሞ ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የነበራቸውን የሦስት ታማኝ ሰዎች ምሳሌ እንመለከታለን።

^ [1] (አንቀጽ 3) ይህ ሰውና ሚስቱ መጀመሪያ ላይ አብራም እና ሦራ ተብለው ይጠሩ ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ይሖዋ፣ አብርሃም እና ሣራ የሚል ስም ሰጥቷቸዋል። በዚህ ርዕስ ላይ ሁለቱንም የምንጠራቸው ይሖዋ በሰጣቸው ስም ነው።