በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  የካቲት 2016

 ከታሪክ ማኅደራችን

ሚሊዮኖች የሚያውቁት ባለ ድምፅ ማጉያ መኪና

ሚሊዮኖች የሚያውቁት ባለ ድምፅ ማጉያ መኪና

“በብራዚል ለጌታ ሥራ የዋለው ባለ ድምፅ ማጉያ መኪና አንድ ብቻ ሲሆን እሱም ሚሊዮኖች የሚያውቁት ‘የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የድምፅ መኪና’ ነው።”—ናታንዬል አልስተን ዩል፣ 1938

በ1930ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በብራዚል የመንግሥቱ መልእክት የሚሰበክበት ፍጥነት በአንጻራዊ ሁኔታ አዝጋሚ ነበር። ይሁን እንጂ በ1935 ናታንዬል እና ሞድ ዩል የሚባሉ አቅኚ ባልና ሚስት፣ በወቅቱ ለስብከቱ ሥራ አመራር ይሰጥ ለነበረው ለጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ ደብዳቤ ጻፉለት። በአገልግሎት ይበልጥ ለመካፈል ፈቃደኞች መሆናቸውንና “የትም ቢመደቡ ደስተኞች” እንደሚሆኑ ገለጹ።

ጡረታ የወጣ የሲቪል መሐንዲስ የነበረው ናታንዬል በዚያ ወቅት 62 ዓመቱ ነበር። በሳን ፍራንሲስኮ፣ ካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ የአገልግሎት ዳይሬክተር ሆኖ አገልግሏል። በዚያ ጉባኤ ውስጥ የስብከቱን ሥራ ያደራጀ ከመሆኑም ሌላ ምሥራቹን ለማስፋፋት የድምፅ መሣሪያ ይጠቀም ነበር። ያካበተው ተሞክሮና ያሳየው የፈቃደኝነት መንፈስ፣ በአዲሱ ምድቡ ይኸውም ብዙ ቋንቋ በሚነገርበትና ሰፊ በሆነው በብራዚል፣ የቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች ሆኖ ሲሠራ በጣም ጠቅሞታል።

ናታንዬልና ሞድ፣ አስተርጓሚና እንደ እነሱ አቅኚ ከሆነው አንቶኒዮ አንድሬዲ ጋር በ1936 ብራዚል ደረሱ። ወደ ብራዚል የሄዱት ውድ የሆኑ ነገሮች ይኸውም 35 የሸክላ ማጫወቻዎችና የድምፅ ማጉያ የተገጠመለት መኪና ይዘው ነበር። በቆዳ ስፋቷ በዓለም ላይ አምስተኛ በሆነችው በብራዚል በዚያ ጊዜ የነበሩት የመንግሥቱ አስፋፊዎች 60 ያህል ብቻ ነበሩ! ሆኖም በወቅቱ አዲስ ግኝት በሆኑት የድምፅ መሣሪያዎች አማካኝነት በጥቂት ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ምሥራቹን ማድረስ ተችሏል።

ናታንዬልና ሞድ ብራዚል ከደረሱ ከአንድ ወር በኋላ ቅርንጫፍ ቢሮው፣ በብራዚል የመጀመሪያው ትልቅ ስብሰባ በሳኦ ፓውሎ ከተማ እንዲካሄድ አደረገ። * የድምፅ ማጉያ የተገጠመለት መኪና የሕዝብ ንግግሩን በማስተዋወቅ ሥራ የጀመረ ሲሆን ንግግሩን ለማዳመጥ 110 ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል! መኪናውን ትነዳ የነበረችው ሞድ ሳትሆን አትቀርም። ስብሰባው አስፋፊዎቹን ያነቃቃቸው  ሲሆን በመስክ አገልግሎት ያላቸውን ተሳትፎ ለመጨመር ተነሳሱ። አስፋፊዎቹ ጽሑፎችንና የምሥክርነት መስጫ ካርዶችን እንዲሁም በሸክላ ላይ የተቀዱ ንግግሮችን በመጠቀም እንዴት እንደሚሰብኩ ተማሩ፤ ንግግሮቹ የተቀዱት በሃንጋሪያኛ፣ በስፓንኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በጀርመንኛና በፖሊሽ ከጊዜ በኋላ ደግሞ በፖርቱጋልኛ ነው።

ይህ ባለ ድምፅ ማጉያ መኪና በብራዚል ለሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ምሥራቹን ለማዳረስ አስችሏል

በ1937 በሳኦ ፓውሎ፣ በሪዮ ዴ ጄኔሮ እና በኩሪቲባ የተደረጉት ሦስት አገልግሎት መውጣትን ያካተቱ ትላልቅ ስብሰባዎች፣ አስፋፊዎቹን ለወንጌላዊነቱ ሥራ እንደ አዲስ አበረታቷቸው። ተሰብሳቢዎቹ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ሲሰብኩ የድምፅ ማጉያ የተገጠመለት መኪና አብሯቸው ይሄድ ነበር። በዚያን ጊዜ ወጣት ልጅ የነበረው ዦዜ ማግሎቭስኪ ከጊዜ በኋላ የሚከተለውን ጽፏል፦ “መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን፣ የጽሑፍ መደርደሪያ ላይ እናስቀምጣለን፤ ከዚያም የድምፅ ማጉያ የተገጠመለት መኪና የተቀረጸውን መልእክት ያሰማል፤ እኛ ደግሞ ምን እንደተፈጠረ ለማየት ከቤታቸው ከወጡት ሰዎች ጋር እንወያይ ነበር።”

ጥምቀት የሚካሄደው በወንዞች ውስጥ ሲሆን ወንዙ ውስጥ የሚታጠቡ ሌሎች ሰዎችም በአቅራቢያው ፀሐይ ይሞቁ ነበር። የድምፅ ማጉያ በተገጠመለት መኪና በመታገዝ ምሥራቹን ለመስበክ ይህ እንዴት ያለ ግሩም አጋጣሚ ነበር! ወንድም ራዘርፎርድ ያቀረበው የጥምቀት ንግግር በድምፅ ማጉያዎቹ ያስተጋባ ነበር። የማወቅ ጉጉት ያደረባቸው ሰዎች፣ መኪናውን ከበው በመቆም ንግግሩ ወደ ፖርቱጋልኛ ሲተረጎም ያዳምጡ ነበር። ከዚያም በፖሊሽ ቋንቋ የተቀዳው የመንግሥቱ መዝሙር እየተደመጠ የጥምቀት ዕጩዎቹ ይጠመቃሉ። ወንድሞችና እህቶችም በተቀዳው መዝሙር እየታጀቡ በተለያዩ ቋንቋዎች አብረው ይዘምሩ ነበር። የ1938 የዓመት መጽሐፍ “ሁኔታው እያንዳንዱ ሰው በራሱ ቋንቋ ይሰማ ከነበረበት ከጴንጤቆስጤ ዕለት ጋር ተመሳሳይ ነበር” በማለት ሪፖርት አድርጓል።

ከስብሰባዎቹ በኋላ ሁልጊዜ እሁድ እሁድ በዝናብም ሆነ በፀሐይ፣ የድምፅ ማጉያ ከተገጠመለት መኪና ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮች በተለያዩ ቦታዎች ይደመጡ ነበር፤ በመሃል ሳኦ ፓውሎና በአቅራቢያው ባሉ ከተሞች ውስጥ በመናፈሻዎች፣ በመኖሪያ አካባቢዎች እና በፋብሪካዎች የነበሩ ሰዎች ንግግሮቹን አዳምጠዋል። ከሳኦ ፓውሎ በስተ ሰሜን ምዕራብ 97 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሥጋ ደዌ ሕመምተኞች በሚኖሩበት መንደር ለነበሩ 3,000 ነዋሪዎች የድምፅ ማጉያ በተገጠመለት መኪና አማካኝነት ወርኃዊ ፕሮግራም ይቀርብላቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ በዚያ መንደር፣ ፈጣን እድገት የሚያደርግ አንድ ጉባኤ ተቋቋመ። በዚህ ጉባኤ ያሉት የመንግሥቱ አስፋፊዎች፣ ከባድ ሕመም ቢኖርባቸውም በሌላ መንደር ለሚኖሩ የሥጋ ደዌ ሕመምተኞች ሄደው ለመስበክ ፈቃድ ካገኙ በኋላ አጽናኝ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለእነዚያ ሰዎች ማድረስ ችለዋል።

በፖርቱጋልኛ ቋንቋ የተቀዱ የመንግሥቱ ንግግሮች በ1938 መገባደጃ አካባቢ ብራዚል ደረሱ። ወንድሞች የድምፅ ማጉያ በተገጠመለት መኪና በመጠቀም፣ ‘የሁሉም ነፍሳት ቀን’ በሚባለው በዓል ላይ ወደተለያዩ የመቃብር ቦታዎች እየሄዱ “ሙታን የት ናቸው?፣” “ይሖዋ” እና “ሀብት” የሚሉትን የተቀዱ ንግግሮች ከ40,000 ለሚበልጡ ለቀስተኞች አስደምጠዋል!

በቁጣ የተሞሉ ቀሳውስት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለሕዝብ በድፍረት መታወጁን ይቃወሙ ነበር፤ ብዙውን ጊዜም፣ የድምፅ ማጉያ በተገጠመለት መኪና አማካኝነት የሚካሄደውን ስብከት እንዲያስቆሙ በአካባቢው ባለሥልጣናት ላይ ግፊት ያደርጉ ነበር። እህት ዩል በአንድ ወቅት አንድ የአካባቢው ቄስ የሕዝብ ረብሻ እንዳነሳሳና ይህን መኪና ሰዎች እንዲከቡት እንዳደረገ ታስታውሳለች። ይሁን እንጂ ከንቲባውና የፖሊስ መኮንኖች በቦታው የደረሱ ሲሆን ሙሉውን ፕሮግራም አዳመጡ። ከንቲባው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ወሰዱ። በዚያ ቀን ረብሻ ሳይቀሰቀስ ቀረ። እንደዚህ ዓይነት ተቃውሞ ቢኖርም በ1940 የዓመት መጽሐፍ ላይ ስለ ብራዚል የወጣው ሪፖርት፣ 1939 “ታላቁን ገዢ ለማገልገልና ስሙን ለማስታወቅ ከመቼውም ይበልጥ የተመቸ ጊዜ” እንደነበረ ገልጿል።

በእርግጥም “የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የድምፅ መኪና” ወደ ብራዚል መምጣቱ በዚያ ለሚካሄደው የስብከት እንቅስቃሴ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። የመንግሥቱ መልእክት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች እንዲዳረስ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ታዋቂ የሆነው ያ መኪና በ1941 ቢሸጥም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰፊ በሆነው የብራዚል ክልል ውስጥ ለሚገኙ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ምሥራቹን ማወጃቸውን ቀጥለዋል።—በብራዚል ካለው የታሪክ ማኅደራችን

^ አን.7 በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ወንድሞችና እህቶች አገልግሎት እንዲወጡ ዝግጅት ይደረግ ነበር።