በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ በአገልግሎቱ ውጤታማ እንድሆን ረድቶኛል

ይሖዋ በአገልግሎቱ ውጤታማ እንድሆን ረድቶኛል

ለመዋጋት ፈቃደኛ ባለመሆኔ ከዚህ ቀደም ታስሬ እንደነበር ለመኮንኑ ነገርኩት። “ታዲያ አሁንም እንደገና እንድታሰር ልታደርገኝ ነው?” ብዬ ጠየቅሁት። ይህን የተናገርኩት በዩናይትድ ስቴትስ ሠራዊት ውስጥ እንዳገለግል ድጋሚ በተጠራሁ ጊዜ ነበር።

የተወለድኩት በ1926 ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በክሩክስቪል፣ ኦሃዮ ነው። አባቴና እናቴ ሃይማኖተኛ ባይሆኑም እኛን ስምንት ልጆቻቸውን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንድንሄድ ይነግሩን ነበር። እኔም ወደ ሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን መሄድ ጀመርኩ። እሁድ እሁድ ከሚካሄዱት የአምልኮ ፕሮግራሞች አንድ ዓመት ሙሉ ስላልቀረሁ በ14 ዓመቴ የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋይ ሽልማት ሰጠኝ።

ማርጋሬት ዎከር (በስተ ግራ በኩል ሁለተኛዋ እህት) እውነትን እንድማር ረድታኛለች

በዚያው ጊዜ አካባቢ ማርጋሬት ዎከር የምትባል አንዲት የይሖዋ ምሥክር ጎረቤታችን፣ ቤታችን እየመጣች እናቴን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማነጋገር ጀመረች። አንድ ቀን እኔም ውይይታቸውን ለማዳመጥ ወሰንኩ። እናቴ እንደምረብሻት ስለተሰማት ከቤት እንድወጣ ነገረችኝ። እኔ ግን ውይይታቸውን ለማዳመጥ ጥረት ማድረጌን አልተውኩም። ማርጋሬት እናቴ ጋ የተወሰነ ጊዜ ከመጣች በኋላ “የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ታውቃለህ?” ብላ ጠየቀችኝ። እኔም “ይህን የማያውቅ ሰው አለ እንዴ? ስሙ አምላክ ነው” አልኳት። እሷ ግን “መጽሐፍ ቅዱስህን አምጣና መዝሙር 83:18ን ተመልከት” አለችኝ። ጥቅሱን አውጥቼ ሳነበው የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ተረዳሁ። ወደ ጓደኞቼ ሮጬ በመሄድ “ዛሬ ማታ ቤት ስትገቡ  ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መዝሙር 83:18ን አውጡና የአምላክ ስም ማን እንደሆነ እዩ” አልኳቸው። መመሥከር የጀመርኩት ወዲያውኑ ነው ማለት ይቻላል።

መጽሐፍ ቅዱስን አጠናሁና በ1941 ተጠመቅሁ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት እንድመራ ተመደብኩ። እናቴን እንዲሁም ወንድሞቼንና እህቶቼን ወደ መጽሐፍ ጥናቱ እንዲመጡ አበረታታኋቸው፤ ሁሉም እኔ በምመራው መጽሐፍ ጥናት ላይ መገኘት ጀመሩ። አባቴ ግን ፍላጎት አልነበረውም።

ከቤተሰብ ተቃውሞ ገጠመኝ

በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት የተሰጠኝ ሲሆን ቲኦክራሲያዊ ጽሑፎችን የያዘ የራሴ ቤተ መጻሕፍት አደራጀሁ። አንድ ቀን አባቴ ወደ መጽሐፎቼ እያመለከተ “እዛ ጋ ያከማቸኸው ነገር ከቤቴ እንዲወጣ እፈልጋለሁ፤ አንተም አብረህ መውጣት ትችላለህ” አለኝ። በመሆኑም ቤቱን ለቅቄ ወጣሁና በአቅራቢያው ባለችው ዜንዝቪል፣ ኦሃዮ መኖር ጀመርኩ፤ ይሁን እንጂ ቤተሰቦቼን እየሄድኩ አበረታታቸው ነበር።

እናቴ በስብሰባዎች ላይ እንዳትገኝ ለማድረግ አባቴ ብዙ ጥሯል። አንዳንድ ጊዜ መንገድ ከጀመረች በኋላ ተከትሏት በመሄድ ወደ ቤት ይመልሳት ነበር። እሷ ግን በሌላኛው በር ሮጣ በመውጣት ወደ ስብሰባ ትሄዳለች። እኔም ለእናቴ “አይዞሽ። አንቺን ማሳደድ ሲደክመው ይተወዋል” እላት ነበር። ከጊዜ በኋላ አባቴ፣ እናቴን ከስብሰባ ለማስቀረት የሚያደርገውን ጥረት አቆመ፤ ስለዚህ ያለ ችግር በስብሰባዎች ላይ መገኘት ቻለች።

በ1943 በጉባኤያችን ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የተጀመረ ሲሆን እኔም የተማሪ ንግግሮች መስጠት ጀመርኩ። በትምህርት ቤቱ ክፍል ካቀረብኩ በኋላ የተሰጡኝ ምክሮች የንግግር ችሎታዬን ለማሻሻል ረድተውኛል።

በጦርነት ወቅት ገለልተኛ መሆን

በወቅቱ መንግሥታት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ላይ ነበሩ። በ1944 ለወታደራዊ አገልግሎት ተጠራሁ። በፎርት ሄዝ፣ ኮለምበስ ኦሃዮ በሚገኘው ወታደራዊ መሥሪያ ቤት ቀርቤ የጤና ምርመራ ካደረግሁ በኋላ የቀረበልኝን ቅጽ ሞላሁ። በተጨማሪም ወታደር እንደማልሆን ለባለሥልጣናቱ ነገርኳቸው። እነሱም እንድሄድ ፈቀዱልኝ። ከቀናት በኋላ አንድ ፖሊስ ቤቴ ድረስ መጣና “ኮርዊን ሮቢሰን፣ አንተን እንዳስር የፍርድ ቤት ማዘዣ ተሰጥቶኛል” አለኝ።

ከሁለት ሳምንት በኋላ ፍርድ ቤት ቀርቤ ሳለሁ ዳኛው “እንደ እኔ ቢሆን ኖሮ የዕድሜ ልክ እስራት እፈርድብህ ነበር። መናገር የምትፈልገው ነገር አለ?” አለኝ። እኔም “ክቡር ዳኛ፣ እንደ ሃይማኖታዊ አገልጋይ ልቆጠር ይገባል። በየቤቱ እየሄድኩ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለብዙ ሰዎች ሰብኬያለሁ” በማለት መልስ ሰጠሁ። * ዳኛውም፣ ፍርድ እንዲሰጡ ከሕዝብ መካከል ተመርጠው ለተሰየሙት ሰዎች እንዲህ አላቸው፦ “እዚህ የተቀመጣችሁት ‘ይህ ወጣት ሃይማኖታዊ አገልጋይ ነው ወይስ አይደለም?’ የሚለውን ለመፍረድ አይደለም። እዚህ የተቀመጣችሁት ‘ሠራዊቱን ለመቀላቀል ፈቃደኛ ነው ወይስ አይደለም?’ የሚለውን ለመወሰን ነው።” ፍርድ ለመስጠት የተሰየሙት ሰዎች፣ ‘ጥፋተኛ ነው’ ብለው በየኑ፤ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ግማሽ ሰዓት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ነው። ዳኛው በአሽላንድ፣ ኬንታኪ በሚገኘው የፌዴራል ማረሚያ ቤት የአምስት ዓመት እስራት ፈረደብኝ።

ይሖዋ በእስር ቤት ጥበቃ አደረገልኝ

የመጀመሪያዎቹን ሁለት ሳምንታት በኮለምበስ፣ ኦሃዮ በሚገኝ እስር ቤት የቆየሁ ሲሆን የመጀመሪያውን ቀን ያሳለፍኩት ከክፍሌ ሳልወጣ ነው። በመሆኑም “አንድ ክፍል  ውስጥ ተዘግቼ አምስት ዓመት መቆየት አልችልም። ምን እንደማደርግ አላውቅም” ብዬ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ።

በቀጣዩ ቀን ዘቦቹ ከክፍሌ እንድወጣ ፈቀዱልኝ። እኔም ረጅምና ትከሻው ሰፊ የሆነ አንድ እስረኛ አጠገብ ሄጄ ቆምኩ፤ ሁለታችንም በመስኮቱ አሻግረን እየተመለከትን ነበር። ሰውየው “አጭሬ፣ ምን አድርገህ ነው እዚህ የገባኸው?” አለኝ። እኔም “የይሖዋ ምሥክር ነኝ” አልኩት። “ኧረ? ታዲያ እዚህ ለምን መጣህ?” አለኝ። “እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ጦርነት ሄደን ሰው አንገድልም” አልኩት። እሱም “እናንተን ሰው ስለማትገድሉ ያስሯችኋል። ሌሎችን ደግሞ ሰው ስለሚገድሉ ያስሯቸዋል። ይህ ግራ የሚገባ ነገር አይደለም?” አለኝ። “ልክ ነህ” አልኩት።

ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “ለ15 ዓመታት ሌላ እስር ቤት እያለሁ አንዳንድ ጽሑፎቻችሁን አነብ ነበር።” ይህን ስሰማ “ይሖዋ፣ ይህ ሰው ከእኔ ጎን እንዲሆን እርዳኝ” ብዬ ጸለይኩ። በዚያው ቅጽበት ፖል (የሰውየው ስም ነው) እንዲህ አለኝ፦ “ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ቢነካህ፣ ጩኽ። እኔ ዋጋቸውን እሰጣቸዋለሁ።” ለነገሩ በዚያ የነበሩት 50 እስረኞች ምንም አላስቸገሩኝም።

በገለልተኝነታቸው ምክንያት በአሽላንድ፣ ኬንታኪ ከታሰሩት ወንድሞች አንዱ ነበርኩ

የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት ወደ አሽላንድ ባዛወሩኝ ጊዜ በዚያ የታሰሩ በርካታ የጎለመሱ ወንድሞች አገኘሁ። እኔም ሆንኩ ሌሎች፣ ከእነሱ ጋር መሆናችን በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆነን እንድንቀጥል ረድቶናል። እነዚህ ወንድሞች ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የሚመድቡልን ከመሆኑም ሌላ አብረን የምንሰበሰብበት ፕሮግራም ያደራጁ ነበር፤ እኛም ለስብሰባዎቹ የሚሆኑ ጥያቄዎችና መልሶች እናዘጋጃለን። በተጨማሪም የክልል አገልጋይ ሆኖ የተሾመ ወንድም ነበር። የታሰርነው ትልቅ ክፍል ውስጥ ሲሆን በግድግዳዎቹ ዙሪያ አልጋዎች ተደርድረዋል። የክልል አገልጋዩ “ሮቢሰን፣ እነዚያ አልጋዎች የአንተ ኃላፊነት ናቸው። እዚያ አልጋ ላይ የተመደበ ሰው ሁሉ በአንተ ክልል ውስጥ ነው። ከመውጣቱ በፊት ስበክለት” ብሎ ይነግረኝ ነበር። በዚህ መልኩ በተደራጀ መንገድ ሰብከናል።

ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1945 አበቃ፤ ያም ቢሆን ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከእስር አልተፈታሁም። አባቴ “አንተን ከተገላገልኩ ስለ ሌሎቹ የማደርገውን አውቃለሁ” ብሎኝ ስለነበረ የቤተሰቤ ጉዳይ ያሳስበኝ ነበር። ከእስር ቤት ስለቀቅ ያላሰብኩት ምሥራች ጠበቀኝ። ከቤተሰቤ ውስጥ ሰባቱ፣ የአባቴ ተቃውሞ ሳይበግራቸው በስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሲሆን ከእህቶቼ አንዷ ተጠምቃ ነበር።

ዲሚትሪየስ ፓፓጆርጅ ከሚባሉ በ1913 ይሖዋን ማገልገል የጀመሩ ቅቡዕ ወንድም ጋር አገልግሎት ስንወጣ

በ1950 የኮሪያ ጦርነት ሲፈነዳ የጦር ሠራዊቱን እንድቀላቀል በድጋሚ ተጠራሁ፤ ስለዚህ ወደ ፎርት ሄዝ ሄድኩ። የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ከወሰድኩ በኋላ መኮንኑ “ከቡድንህ ውስጥ ከፍተኛ ውጤት ካገኙት አንዱ አንተ ነህ” አለኝ። እኔም “ጥሩ ነው፤ እኔ ግን ሠራዊቱን አልቀላቀልም” ብዬ መለስኩለት። ከዚያም 2 ጢሞቴዎስ 2:3ን ጠቀስኩና “እኔ የክርስቶስ ወታደር ነኝ” አልኩት።  ለረጅም ጊዜ ጸጥ ብሎ ከቆየ በኋላ “መሄድ ትችላለህ” አለኝ።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በሲንሲናቲ፣ ኦሃዮ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ወቅት ለቤቴል አመልካቾች በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ወንድም ሚልተን ሄንሼል፣ ወንድሞች ለአምላክ መንግሥት አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ ማድረግ የሚፈልጉ ከሆነ ድርጅቱ በቤቴል ሊጠቀምባቸው እንደሚችል ነገረን። እኔም ለቤቴል አገልግሎት አመልክቼ ተቀባይነት አገኘሁ፤ ከዚያም ነሐሴ 1954 ብሩክሊን ቤቴል ገባሁ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በቤቴል እያገለገልኩ ነው።

በቤቴል የምሠራው ነገር አጥቼ አላውቅም። ለብዙ ዓመታት በማተሚያውና በቢሮው ሕንፃ ላይ ካሉት የውኃ ማሞቂያዎች ጋር የተያያዙ ሥራዎችን አከናውኛለሁ፤ እንዲሁም ማሽኖችንና ቁልፎችን እጠግን ነበር። በተጨማሪም በኒው ዮርክ ሲቲ ባሉት የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች ውስጥ ሠርቻለሁ።

በብሩክሊን ቤቴል በቢሮው ሕንፃ ውስጥ በሚገኙት የውኃ ማሞቂያዎች ላይ ስሠራ

የቤቴልን ቋሚ መንፈሳዊ ፕሮግራም እወደዋለሁ፤ የቤቴላውያን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በማለዳ አምልኮና በቤተሰቡ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ መገኘትን እንዲሁም ከጉባኤው ጋር በአገልግሎት መሳተፍን ያካትታል። ደግሞም ስታስቡት ማንኛውም የይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ እንዲህ ዓይነት መንፈሳዊ ፕሮግራም እንዲኖረው ማድረግ ይችላል፤ ሊኖረውም ይገባል። ወላጆችና ልጆች የዕለቱን ጥቅስ አንድ ላይ የሚመረምሩ፣ ቋሚ የቤተሰብ አምልኮ የሚያደርጉ እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎችና ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ የሚጠመዱ ከሆነ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በመንፈሳዊ ጤናማ መሆናቸው አይቀርም።

በቤቴልና በጉባኤ ውስጥ ብዙ ወዳጆች አፍርቻለሁ። አንዳንዶቹ ቅቡዓን የነበሩ ሲሆን አሁን ሰማያዊ ሽልማታቸውን አግኝተዋል። ሌሎቹ ወዳጆቼ ደግሞ ቅቡዓን አልነበሩም። እርግጥ ነው፣ ቤቴላውያንን ጨምሮ ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ፍጹማን አይደሉም። ከአንድ ወንድም ጋር ከተጋጨሁ ሁልጊዜ ሰላም ለመፍጠር እጥራለሁ። በመካከላችን የተፈጠረውን አለመግባባት እንዴት መፍታት እንዳለብን የሚገልጸውን በማቴዎስ 5:23, 24 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ አስታውሳለሁ። ይቅርታ መጠየቅ ቀላል ባይሆንም ይህን ካደረግኩ ከወዳጄ ጋር የተፈጠረው አለመግባባት አብዛኛውን ጊዜ ይፈታል።

አገልግሎቴ ያስገኛቸው ጥሩ ውጤቶች

በዕድሜዬ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ከቤት ወደ ቤት መሄድ አስቸጋሪ ቢሆንብኝም አገልግሎቴን አላቆምኩም። ማንዳሪን ቻይንኛ በመጠኑም ቢሆን ስለተማርኩ ቻይናውያንን  መንገድ ላይ ማነጋገር ያስደስተኛል። አንዳንድ ቀን ጠዋት ላይ፣ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ከ30 እስከ 40 መጽሔቶችን አበረክታለሁ።

በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ለቻይናውያን ስሰብክ

እንዲያውም ቻይና ለምትኖር ሴት ተመላልሶ መጠየቅ አድርጌያለሁ! አንድ ቀን፣ አንዲት ደስተኛ ወጣት ስለ አንድ የፍራፍሬ መሸጫ ማስታወቂያ ስታድል ፈገግ ብላ አየችኝ። እኔም ፈገግ አልኩና በቻይንኛ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! እንድትወስድ ጋበዝኳት። ወጣቷ ጽሑፎቹን የወሰደች ሲሆን ስሟ ኬቲ መሆኑን ነገረችኝ። ከዚያ በኋላ ኬቲ ስታየኝ መጥታ ታነጋግረኝ ነበር። በእንግሊዝኛ የፍራፍሬዎችንና የአትክልቶችን ስም ያስተማርኳት ሲሆን እሷም ቃላቱን ትደግም ነበር። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አብራራሁላት፤ ኬቲ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ወሰደች። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ግን ጠፋችብኝ።

ከተወሰኑ ወራት በኋላ፣ ማስታወቂያ ታድል የነበረች አንዲት ሌላ ወጣት መጽሔቶች ስሰጣት ተቀበለች። በቀጣዩ ሳምንት ሞባይል ስልኳን ሰጠችኝና በተሰባበረ እንግሊዝኛ “ከቻይና ስልክ አለህ” አለችኝ። እኔም “ቻይና ውስጥ የማውቀው ሰው የለም” አልኳት። እሷ ግን እንዳነጋግር አጥብቃ ስለጠየቀችኝ ስልኩን ተቀበልኩና “ሃሎ፣ ሮቢሰን ነኝ” አልኩ። ደዋይዋም “ሮቢ፣ ኬቲ ነኝ። ወደ ቻይና ተመልሻለሁ” አለችኝ። እኔም “ቻይና?” አልኩ። ኬቲ እንዲህ አለችኝ፦ “አዎ። ሮቢ፣ ስልኩን የሰጠችህ ልጅ እህቴ ናት። አንተ ብዙ ጥሩ ነገሮች አስተምረኸኛል። እባክህ እኔን እንዳስተማርከኝ ሁሉ እሷንም አስተምራት።” እኔም “ኬቲ፣ የቻልኩትን ሁሉ አደርጋለሁ። የት እንዳለሽ ስለነገርሽኝ አመሰግናለሁ” አልኳት። ከኬቲ እህት ጋር መነጋገራችንን ቀጠልን፤ ብዙም ሳይቆይ ግን ተጠፋፋን። እነዚያ ሁለት ወጣቶች ያሉት የትም ይሁን፣ ስለ ይሖዋ ተጨማሪ ነገር እንደሚማሩ ተስፋ አደርጋለሁ።

በይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት 73 ዓመታት አሳልፌያለሁ። ይሖዋ በእስር ቤት ገለልተኛ ሆኜ እንድቀጥልና ታማኝ እንድሆን ስለረዳኝ ደስተኛ ነኝ። በተጨማሪም ወንድሞቼና እህቶቼ፣ የአባቴን ተቃውሞ ተስፋ ሳልቆርጥ መቋቋሜ ድፍረት እንዲያገኙ እንደረዳቸው ይነግሩኛል። እናቴ እንዲሁም ስድስት ወንድሞቼና እህቶቼ ውሎ አድሮ ተጠምቀዋል። አባቴም እንኳ አመለካከቱ የተለወጠ ሲሆን ከመሞቱ በፊት በአንዳንድ ስብሰባዎች ላይ ይገኝ ነበር።

የአምላክ ፈቃድ ከሆነ፣ በሞት ያጣኋቸው የቤተሰቤ አባላትና ወዳጆቼ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ትንሣኤ ያገኛሉ። ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ይሖዋን ለዘላለም ስናመልክ የሚኖረንን ደስታ አስቡት! *

^ አን.14 በዩናይትድ ስቴትስ ሃይማኖታዊ አገልጋዮች ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ ይደረጉ ነበር።

^ አን.32 ይህ ተሞክሮ ለሕትመት በመዘጋጀት ላይ እያለ ወንድም ኮርዊን ሮቢሰን ለይሖዋ ታማኝነቱን እንደጠበቀ በሞት አንቀላፍቷል።