በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ፍትሕና ምሕረት በማሳየት ይሖዋን ምሰሉ

ፍትሕና ምሕረት በማሳየት ይሖዋን ምሰሉ

“በእውነተኛ ፍትሕ ላይ ተመሥርታችሁ ፍረዱ፤ አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ፍቅርና ምሕረት አሳዩ።”—ዘካ. 7:9

መዝሙሮች፦ 125, 88

1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ለአምላክ ሕግ ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው? (ለ) ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ሰዎች ስለ ሕጉ የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው ያደረጉት እንዴት ነው?

ኢየሱስ የሙሴን ሕግ ይወደው ነበር። ይህም የሚያስገርም አይደለም! ይህን ሕግ ያወጣው በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው አካል ማለትም አባቱ ይሖዋ ነው። በመዝሙር 40:8 ላይ የሚገኘው ትንቢታዊ ሐሳብ ኢየሱስ ለአምላክ ሕግ የነበረውን ጥልቅ ፍቅር የሚገልጽ ነው፤ ጥቅሱ “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው” ይላል። ኢየሱስ የአምላክ ሕግ ፍጹምና ጠቃሚ እንደሆነ ብሎም መፈጸሙ እንደማይቀር በንግግሩና በተግባሩ አሳይቷል።—ማቴ. 5:17-19

2 ከዚህ አንጻር ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ሰዎች ስለ ሕጉ የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው ሲያደርጉ ኢየሱስ ምንኛ አዝኖ ይሆን! ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በሕጉ ውስጥ የተካተቱትን አንዳንድ ጥቃቅን ነገሮች ምንም ሳያዛንፉ ይታዘዙ ነበር፤ ክርስቶስ “ከኮሰረት፣ ከእንስላልና ከከሙን አሥራት” እንደሚሰጡ ተናግሯል። ታዲያ ችግሩ ምን ነበር? ኢየሱስ አክሎ “በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን እንደ ፍትሕ፣ ምሕረትና ታማኝነት ያሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ችላ ትላላችሁ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 23:23) ከእነዚህ ተመጻዳቂ ሰዎች በተለየ ክርስቶስ፣ ሕጉ የወጣበትን ዓላማ እንዲሁም በእያንዳንዱ ትእዛዝ ላይ የተንጸባረቁትን የይሖዋ ባሕርያት ተገንዝቦ ነበር።

3. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

3 ክርስቲያኖች በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር አይደለንም። (ሮም 7:6) ሆኖም ይሖዋ ሕጉ፣ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተካትቶ እንዲቆይልን አድርጓል። ይሖዋ በሕጉ ውስጥ ላሉት ዝርዝር ነገሮች ከሚገባው በላይ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ “ይበልጥ አስፈላጊ [የሆኑትን] ነገሮች” ይኸውም ትእዛዛቱ የተመሠረቱባቸውን ላቅ ያሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድናስተውልና ተግባራዊ እንድናደርግ ይፈልጋል። የመማጸኛ ከተሞች እንዲኖሩ የተደረገውን ዝግጅት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህ ዝግጅት የትኞቹን  መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድናስተውል ይረዳናል? ከዚህ በፊት ያለው የጥናት ርዕስ ወደ መማጸኛ ከተማ ሸሽቶ የሚሄደው ሰው ከሚወስደው እርምጃ የምናገኛቸውን ትምህርቶች አብራርቶ ነበር። ይሁንና ከመማጸኛ ከተሞች ዝግጅት ስለ ይሖዋ እንዲሁም የእሱን ባሕርያት ማንጸባረቅ ስለምንችልበት መንገድ የምናገኘው ትምህርትም አለ። በዚህ ርዕስ ላይ ለሦስት ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን፦ የመማጸኛ ከተሞች ዝግጅት ይሖዋ መሐሪ አምላክ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው? ይሖዋ ለሕይወት ስላለው አመለካከት ምን ያስተምረናል? ይህ ዝግጅት የይሖዋ ፍትሕ ፍጹም እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው? ለእያንዳንዱ ጥያቄ ከሚሰጠው መልስ ጋር በተያያዘ በሰማይ ያለውን አባትህን መምሰል የምትችልባቸውን መንገዶች ለማስተዋል ሞክር።ኤፌሶን 5:1ን አንብብ።

“አመቺ የሆኑ የመማጸኛ ከተሞች”—የይሖዋ ምሕረት መገለጫ

4, 5. (ሀ) ወደ መማጸኛ ከተሞች መድረስ ቀላል እንዲሆን ሲባል ምን ዝግጅቶች ተደርገው ነበር? እንዲህ የተደረገውስ ለምንድን ነው? (ለ) ይህ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

4 ስድስቱ የመማጸኛ ከተሞች ወደነበሩበት ቦታ መድረስ አስቸጋሪ አልነበረም። ይሖዋ ሦስቱን የመማጸኛ ከተሞች ከዮርዳኖስ ወዲህ፣ ሦስቱን ከተሞች ደግሞ ከዮርዳኖስ ወዲያ እንዲያደርጓቸው እስራኤላውያንን አዟቸው ነበር። ይህን ያላቸው ለምንድን ነው? ሳያስበው ነፍስ ያጠፋ ማንኛውም ሰው ብዙም ሳይቸገር በፍጥነት ወደ መማጸኛ ከተማ መድረስ እንዲችል ነው። (ዘኁ. 35:11-14) ወደ መማጸኛ ከተሞች የሚወስዱት መንገዶች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዲገኙ ይደረግ ነበር። (ዘዳ. 19:3) በተጨማሪም የአይሁዳውያን የማመሣከሪያ ጽሑፎች እንደሚገልጹት ወደ መማጸኛ ከተሞች የሚሸሹ ሰዎችን ለመርዳት ሲባል በመንገዶቹ ላይ አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶች ይቆሙ ነበር። በእስራኤል ውስጥ የመማጸኛ ከተሞች ስለተዘጋጁ፣ ሳያውቅ ሰው የገደለ ግለሰብ ወደ ሌላ አገር ለመሸሽ የሚገደድበት ምክንያት አይኖርም፤ ግለሰቡ ወደ ባዕድ አገር መሸሽ ቢኖርበት ግን የሐሰት አምልኮን ለመከተል ሊፈተን ይችላል።

5 እስቲ አስበው፦ ሆን ብለው ነፍስ ያጠፉ ግለሰቦች በሞት እንዲቀጡ የሚያዝዝ ሕግ ያወጣው ይሖዋ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሳያውቁ ነፍስ ያጠፉ ሰዎች በርኅራኄ እንዲያዙ እንዲሁም ምሕረትና ጥበቃ የሚያገኙበት አጋጣሚ እንዲያገኙ ዝግጅት ያደረገውም እሱ ራሱ ነው! አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደገለጹት “በተቻለ መጠን ሁሉም ነገር ግልጽ፣ ያልተወሳሰበና ቀላል ተደርጎ ነበር።” እኚህ ምሁር አክለውም “ይህ የአምላክን ጸጋ የሚያሳይ ነው” ብለዋል። ይሖዋ፣ አገልጋዮቹን ለመቅጣት የሚቸኩል ጨካኝ ዳኛ አይደለም። ከዚህ ይልቅ “አምላክ ምሕረቱ ብዙ ነው።”—ኤፌ. 2:4

6. የፈሪሳውያን አመለካከት ይሖዋ ስለ ምሕረት ካለው አመለካከት ጋር የሚጋጨው እንዴት ነው?

6 ከዚህ በተቃራኒ ግን ፈሪሳውያን ምሕረት ለማሳየት ፈቃደኞች አልነበሩም። ለምሳሌ ያህል፣ የአይሁዳውያን ወግ እንደሚገልጸው አንድ ሰው ከሦስት ጊዜ በላይ ተመሳሳይ በደል ከፈጸመባቸው ይቅር ለማለት ፈቃደኞች አይደሉም። ኢየሱስ ስለ አንድ ፈሪሳዊ የተናገረው ምሳሌ፣ ፈሪሳውያን በደል ለፈጸሙ ሰዎች የነበራቸውን አመለካከት በግልጽ የሚያሳይ ነው። ፈሪሳዊው “አምላክ ሆይ፣ እንደ ሌላው ሰው ቀማኛ፣ ዓመፀኛ፣ አመንዝራ፣ በተለይ ደግሞ እንደዚህ ቀረጥ ሰብሳቢ ስላልሆንኩ አመሰግንሃለሁ” በማለት ጸልዮአል፤ የሚገርመው እዚህ ላይ የተጠቀሰው ቀረጥ ሰብሳቢ የአምላክን ምሕረት ለማግኘት በትሕትና እየጸለየ ነበር። እነዚህ ሰዎች ምሕረት ማሳየት ይህን ያህል የሚከብዳቸው ለምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ  እንደሚገልጸው “ሌሎችን በንቀት ዓይን [ይመለከቱ]” ስለነበር ነው።—ሉቃስ 18:9-14

የበደሉህ ሰዎች ይቅርታ ሊጠይቁህ ሲመጡ “መንገዱ” አመቺ እንዲሆንላቸው ታደርጋለህ? በቀላሉ የምትቀረብ ሁን (ከአንቀጽ 4-8⁠ን ተመልከት)

7, 8. (ሀ) አንድ ሰው በሚበድላችሁ ጊዜ ይሖዋን መምሰል የምትችሉት እንዴት ነው? (ለ) ይቅር ባይነት ትሕትናችን የሚፈተንበት ጉዳይ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

7 ፈሪሳውያንን ሳይሆን ይሖዋን ለመምሰል ጥረት አድርጉ። ርኅራኄና ምሕረት አሳዩ። (ቆላስይስ 3:13ን አንብብ።) እነዚህን ባሕርያት ማሳየት የምትችሉበት አንዱ መንገድ፣ ሌሎች እናንተን ይቅርታ መጠየቅ ከባድ እንዳይሆንባቸው በማድረግ ነው። (ሉቃስ 17:3, 4) እንደሚከተለው በማለት ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘የበደሉኝን ሰዎች ሌላው ቀርቶ በተደጋጋሚ ያስከፉኝንም እንኳ ቶሎ ይቅር እላለሁ? ከበደለኝ ወይም ከጎዳኝ ሰው ጋር ሰላም ለመፍጠር የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ?’

8 እንደ እውነቱ ከሆነ ይቅር ባይነት፣ ትሕትናችን የሚፈተንበት ጉዳይ ነው። ፈሪሳውያን ሌሎችን ዝቅ አድርገው ይመለከቱ ስለነበር ይህን ፈተና አላለፉም። ክርስቲያኖች ግን “ሌሎች [ከእኛ] እንደሚበልጡ በትሕትና” ልናስብና በነፃ ይቅር ልንላቸው ይገባል። (ፊልጵ. 2:3) አንተስ ይሖዋን በመምሰል ትሕትና ታሳያለህ? የበደሉህ ሰዎች አንተን ይቅርታ ለመጠየቅ ሲመጡ “መንገዱ” አመቺ እንዲሆንላቸው በሌላ አባባል ይቅርታ መጠየቅ ቀላል እንዲሆንላቸው አድርግ። ምሕረት ለማሳየት ፈጣን ሁን፤ እንዲሁም ለቁጣ አትቸኩል።—መክ. 7:8, 9

ለሕይወት አክብሮት ማሳየት “በደም ዕዳ ተጠያቂ” እንዳንሆን ያደርጋል

9. ይሖዋ የሰው ሕይወት ቅዱስ መሆኑን እስራኤላውያን እንዲገነዘቡ ያደረገው እንዴት ነው?

9 የመማጸኛ ከተሞች የተዘጋጁበት ዋነኛ ዓላማ እስራኤላውያን በደም ዕዳ ተጠያቂ እንዳይሆኑ ሲባል ነው። (ዘዳ. 19:10) ይሖዋ ለሕይወት ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ሲሆን “ንጹሕ ደም የሚያፈሱ [እጆችን]” ይጠላል። (ምሳሌ 6:16, 17) ይሖዋ ፍትሐዊና ቅዱስ አምላክ ስለሆነ፣ ሳያውቅ የሰው ሕይወት ያጠፋ ግለሰብ እንኳ በቸልታ እንዲታለፍ አይፈቅድም። እርግጥ፣ ሳያስበው ነፍስ ያጠፋው ሰው ምሕረት የሚያገኝበት ዝግጅት ተደርጓል። ያም ቢሆን ጉዳዩን ለሽማግሌዎች መናገር ነበረበት፤ ሽማግሌዎቹ፣ ነፍስ ያጠፋው ሳያውቅ እንደሆነ ከፈረዱለት ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በመማጸኛ ከተማ ውስጥ መቆየት አለበት። ምናልባትም ቀሪ ሕይወቱን በመማጸኛ ከተማ ውስጥ ማሳለፍ ሊኖርበት ይችላል። እንዲህ ያለ ከባድ እርምጃ መወሰዱ፣ ሁሉም እስራኤላውያን የሰው ሕይወት ቅዱስ መሆኑን እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል። ሕይወት ሰጪያቸው ለሆነው አምላክ አክብሮት ለማሳየት ሲሉ፣ የሌላ ሰውን ሕይወት አደጋ ላይ ላለመጣል የሚችሉትን ሁሉ ማድረግ ነበረባቸው።

10. ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ለሕይወት ጨርሶ አክብሮት እንደሌላቸው ኢየሱስ የገለጸው እንዴት ነው?

10 ከይሖዋ በተለየ መልኩ፣ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ለሕይወት ጨርሶ አክብሮት አልነበራቸውም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ “የእውቀትን ቁልፍ ነጥቃችሁ ወስዳችኋል። እናንተ ራሳችሁ አልገባችሁም፤ ለመግባት የሚሞክሩትንም ትከለክላላችሁ” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 11:52) እነዚህ ሰዎች፣ የእውቀትን ቁልፍ በመጠቀም የአምላክን ቃል ትርጉም ማብራራትና ሌሎች ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ እንዲጓዙ መርዳት ነበረባቸው። እነሱ ግን ሰዎች ‘የሕይወት “ዋና ወኪል”’ ከሆነው ከኢየሱስ እንዲርቁና ወደ ዘላለም ጥፋት በሚወስደው መንገድ ላይ እንዲጓዙ አድርገዋል። (ሥራ 3:15) ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ኩሩና ራስ ወዳድ በመሆናቸው ለሌሎች ሕይወትና ደህንነት ግድ አልነበራቸውም። እነዚህ ሰዎች ምንኛ ጨካኝና ምሕረት የጎደላቸው ነበሩ!

11. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ሕይወት የአምላክ ዓይነት አመለካከት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ለአገልግሎታችን የጳውሎስ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ምን ሊረዳን ይችላል?

11 የጸሐፍትና የፈሪሳውያን ዓይነት አመለካከት ከማዳበር ይልቅ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት መያዝ የምንችለው እንዴት ነው? ሕይወት ስጦታ ነው፤ በመሆኑም ለሕይወት አክብሮት ልናሳይና ይህን ስጦታ ከፍ አድርገን ልንመለከተው ይገባል። ሐዋርያው ጳውሎስ የተሟላ  ምሥክርነት በመስጠት እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዳለው አሳይቷል። በመሆኑም “ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ [ነኝ]” በማለት መናገር ችሏል። (የሐዋርያት ሥራ 20:26, 27ን አንብብ።) ይሁንና ጳውሎስ ለመስበክ የተነሳሳው የጥፋተኝነት ስሜት ስለተሰማው ወይም ግድ ስለሆነበት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሚሰብከው ሰዎችን ስለሚወድና ለሰው ሕይወት አክብሮት ስለነበረው ነው። (1 ቆሮ. 9:19-23) እኛም በተመሳሳይ ለሕይወት የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ጥረት ማድረግ አለብን። ይሖዋ፣ ሰው “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ” ይፈልጋል። (2 ጴጥ. 3:9) አንተስ እንዲህ ዓይነት ፍላጎት አለህ? ይበልጥ መሐሪ ለመሆንና የርኅራኄ ስሜት ለማዳበር የምንጥር ከሆነ በአገልግሎታችን ይበልጥ በቅንዓት ለመካፈል እንነሳሳለን፤ ይህን ስናደርግ ደግሞ ይበልጥ ደስተኞች እንሆናለን።

12. የአምላክ አገልጋዮች፣ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ላለማድረግ የሚጠነቀቁት ለምንድን ነው?

12 ስለ ሕይወት የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዳለን ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ነገሮችን ለማስወገድ በመጣር ነው። በምናሽከረክርበትም ሆነ ሌሎች ነገሮችን በምንሠራበት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፤ የአምልኮ ቦታችንን ስንገነባ፣ ስናድስ ወይም ወደ እነዚህ ቦታዎች ስንጓዝም ተመሳሳይ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። ይበልጥ ሊያሳስበን የሚገባው የራሳችንም ሆነ የሌሎች ደህንነትና ጤንነት እንጂ አንድን ነገር በታቀደለት ጊዜ መጨረሳችን፣ ብዙ መሥራት መቻላችን አሊያም የገንዘብ ጉዳይ አይደለም። ፍትሐዊ የሆነው አምላካችን ምንጊዜም የሚያደርገው ትክክልና ተገቢ የሆነውን ነገር ነው። እኛም እሱን መምሰል እንፈልጋለን። በተለይ ሽማግሌዎች የራሳቸውም ሆነ አብረዋቸው የሚሠሩት ሰዎች ደህንነት ለአደጋ እንዳይጋለጥ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። (ምሳሌ 22:3) አንድ ሽማግሌ የደህንነት መመሪያዎችን እንድትከተል ከጠቆመህ ምክሩን ተግባራዊ አድርገው። (ገላ. 6:1) ለሕይወት የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ካዳበርክ “በደም ዕዳ ተጠያቂ [አትሆንም]።”

“ማኅበረሰቡ እነዚህን ደንቦች መሠረት በማድረግ . . . ፍርድ ይስጥ”

13, 14. እስራኤላውያን ሽማግሌዎች የይሖዋን ፍትሕ ማንጸባረቅ የሚችሉት እንዴት ነበር?

13 ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ሽማግሌዎችን የእሱን የላቁ የፍትሕ መሥፈርቶች እንዲከተሉ አሳስቧቸዋል። በመጀመሪያ፣ ሽማግሌዎቹ የተፈጸመውን ነገር በትክክል ለማወቅ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከዚያም ሳያውቅ ነፍስ ያጠፋው ሰው ምሕረት ይገባው እንደሆነ ለመወሰን በሚሞክሩበት ጊዜ የነፍሰ ገዳዩን ዝንባሌ፣ ለሟቹ ያለውን አመለካከትና ከዚያ በፊት ያደረጋቸውን ነገሮች ግምት ውስጥ ያስገባሉ። ሽማግሌዎቹ የአምላክ ዓይነት ፍትሕ ለማሳየት ሲሉ ግለሰቡ፣ የሰው ነፍስ ያጠፋው “በጥላቻ ተነሳስቶ” ወይም “ተንኮል አስቦ” መሆን አለመሆኑን ያጣራሉ። (ዘኁልቁ 35:20-24ን አንብብ።) የምሥክሮችን ቃል የሚቀበሉ ከሆነ ደግሞ ግለሰቡ ነፍስ ያጠፋው ሆን ብሎ እንደሆነ ለመፍረድ ቢያንስ የሁለት ሰዎች ምሥክርነት ያስፈልጋል።—ዘኁ. 35:30

14 ሽማግሌዎቹ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ትክክለኛውን መረጃ ካገኙ በኋላ፣ ግለሰቡ በፈጸመው ድርጊት ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ የሰውየውን ማንነት ይኸውም ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ማጤን ይኖርባቸዋል። ሽማግሌዎቹ፣ ማስተዋል ማለትም ከአንድ ሁኔታ በስተ ጀርባ ያለውን ነገር የመመልከትና ጉዳዩን ጠለቅ ብሎ የማየት ችሎታ ያስፈልጋቸዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ያስፈልጋቸዋል፤ ይህ መንፈስ የሚያደርጉት ውሳኔ መለኮታዊ ማስተዋል፣ ምሕረትና ፍትሕ የተንጸባረቀበት እንዲሆን ይረዳቸዋል።—ዘፀ. 34:6, 7

15. ኢየሱስ ለኃጢአተኞች የነበረው አመለካከት ፈሪሳውያን ከነበራቸው አመለካከት የሚለየው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

15 በሌላ በኩል ፈሪሳውያን ትኩረት የሚያደርጉት ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ ‘ምን ዓይነት የልብ ዝንባሌ አለው?’ በሚለው ላይ ሳይሆን በፈጸመው ድርጊት ላይ ብቻ ነበር። ለምሳሌ፣ ኢየሱስ በማቴዎስ ቤት በተዘጋጀ ግብዣ ላይ መገኘቱን ፈሪሳውያን ሲያዩ ደቀ መዛሙርቱን “መምህራችሁ ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቋቸው። በዚህ ጊዜ የአምላክ ልጅ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም። እንግዲያው ሄዳችሁ ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ የሚለውን ቃል ትርጉም አስተውሉ። እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ልጠራ ነውና።” (ማቴ. 9:9-13) ክርስቶስ ይህን ማለቱ ከባድ ኃጢአትን አቅልሎ እንደሚመለከት የሚያሳይ ነው? በፍጹም። እንዲያውም ኢየሱስ፣ ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ ግብዣ አቅርቧል። (ማቴ. 4:17) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በዚያ ከነበሩት ‘ቀረጥ ሰብሳቢዎችና  ኃጢአተኞች’ መካከል ቢያንስ አንዳንዶቹ ለውጥ ማድረግ ይፈልጉ እንደነበር አስተውሏል። እነዚህ ሰዎች ወደ ማቴዎስ ቤት የመጡት ምግብ ለመብላት ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ከእነሱ መካከል “ብዙዎቹ [ኢየሱስን] መከተል ጀምረው ነበር።” (ማር. 2:15) የሚያሳዝነው አብዛኞቹ ፈሪሳውያን፣ ክርስቶስ ለእነዚህ ሰዎች የነበረው ዓይነት አመለካከት አልነበራቸውም። ፈሪሳውያን ፍትሐዊና መሐሪ የሆነውን አምላክ እንደሚያመልኩ ቢናገሩም ሌሎች ሰዎችን እንደ ኃጢአተኛ የሚቆጥሩ ሲሆን መለወጥ እንደማይችሉ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር።

16. በፍርድ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግሉ ወንድሞች ምን ለማስተዋል ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል?

16 በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች “ፍትሕን ይወዳል” የተባለለትን ይሖዋን ለመምሰል ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። (መዝ. 37:28) በመጀመሪያ፣ ኃጢአት ተፈጽሞ መሆኑን ለማረጋገጥ ‘ጉዳዩን በጥልቀት መመርመርና ማጣራት’ አለባቸው። ኃጢአት መፈጸሙን ካረጋገጡ፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በሰፈሩት መመሪያዎች መሠረት ጉዳዩን መያዝ ይኖርባቸዋል። (ዘዳ. 13:12-14) ጉዳዩን በሚመለከተው የፍርድ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች፣ ከባድ ኃጢአት የፈጸመው ክርስቲያን ንስሐ መግባት አለመግባቱን በጥንቃቄ ያመዛዝናሉ። አንድ ሰው ንስሐ እንደገባና እንዳልገባ ማወቅ ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። ግለሰቡ ንስሐ መግባቱን ለማወቅ ስለፈጸመው ድርጊት ያለውን አመለካከት፣ ዝንባሌውንና የልቡን ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። (ራእይ 3:3) ኃጢአት የሠራ ግለሰብ ምሕረት ለማግኘት ንስሐ መግባት ይኖርበታል። *

17, 18. ሽማግሌዎች አንድ ሰው ከልቡ ንስሐ መግባቱን ማስተዋል የሚችሉት እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

17 ከይሖዋና ከኢየሱስ በተለየ ሽማግሌዎች የሰውን ልብ ማንበብ አይችሉም። ሽማግሌ ከሆንክ አንድ ሰው ከልቡ ንስሐ መግባቱን ማስተዋል የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ ጥበብና ማስተዋል ለማግኘት ጸልይ። (1 ነገ. 3:9) ሁለተኛ፣ ‘በዚህ ዓለም ሐዘን’ እና “አምላካዊ በሆነ መንገድ [በማዘን]” ማለትም ከልብ ንስሐ በመግባት መካከል ያለውን ልዩነት ማስተዋል እንድትችል የአምላክን ቃል እንዲሁም ታማኙ ባሪያ ያወጣቸውን ጽሑፎች መርምር። (2 ቆሮ. 7:10, 11) ቅዱሳን መጻሕፍት ንስሐ የገቡና ንስሐ ያልገቡ ኃጢአተኞችን እንዴት እንደሚገልጿቸው ለማስተዋል ሞክር። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነዚህ ሰዎች ስሜት፣ አመለካከትና ድርጊት ምን ይላል?

18 በመጨረሻም፣ ግለሰቡ በሠራው ኃጢአት ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ስለ ማንነቱ ለማሰብ ጥረት አድርግ። ኃጢአት የፈጸመውን ግለሰብ አስተዳደግና የቀድሞ ሕይወት እንዲሁም ግለሰቡ አንድን ነገር ለማድረግ የተነሳሳበትን ምክንያትና ያሉበትን የአቅም ገደቦች ከግምት አስገባ። የክርስቲያን ጉባኤ ራስ የሆነውን ኢየሱስን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ትንቢት ይዟል፦ “ዓይኑ እንዳየ አይፈርድም ወይም ጆሮው በሰማው ነገር ላይ ብቻ ተመሥርቶ አይወቅስም። ለችግረኞች በትክክል ይፈርዳል፤ በምድር ላሉ የዋሆች ጥቅም ሲል ሌሎችን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይወቅሳል።” (ኢሳ. 11:3, 4) እናንት ሽማግሌዎች፣ በክርስቶስ ሥር ያላችሁ የበታች እረኞች ናችሁ፤ በመሆኑም ኢየሱስ፣ እሱ የሚሰጠውን ዓይነት ፍርድ እንድትሰጡ ይረዳችኋል። (ማቴ. 18:18-20) ፍትሕንና ምሕረትን ለማሳየት የሚጥሩ አሳቢ የሆኑ ሽማግሌዎች ስላሉን አመስጋኝ ልንሆን አይገባም? ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ምሕረትንና ፍትሕን እንድናሳይ ለመርዳት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚያደርጉትን ጥረት ከልብ እናደንቃለን!

19. ከመማጸኛ ከተሞች ዝግጅት ከምናገኛቸው ትምህርቶች ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ያሰብከው የትኛውን ነው?

19 የሙሴ ሕግ “የእውቀትና የእውነት መሠረታዊ [ገጽታዎችን]” ይዟል፤ ሕጉ ስለ ይሖዋና ስለ ጽድቅ መሥፈርቶቹ ያስተምረናል። (ሮም 2:20) ለምሳሌ የመማጸኛ ከተሞች ዝግጅት፣ ‘በእውነተኛ ፍትሕ ላይ ተመሥርቶ መፍረድ’ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ሽማግሌዎችን ያስተምራቸዋል፤ በተጨማሪም ይህ ዝግጅት ‘አንዳችን ለሌላው ታማኝ ፍቅርና ምሕረት’ ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ሁላችንንም ያስተምረናል። (ዘካ. 7:9) እርግጥ ክርስቲያኖች በሕጉ ሥር አይደለንም። ሆኖም ይሖዋ አይለወጥም፤ አሁንም ቢሆን ለፍትሕና ለምሕረት ትልቅ ቦታ ይሰጣል። በራሱ መልክ የፈጠረንንና የእሱን ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ የሰጠንን ብሎም መሸሸጊያ የሚሆነንን አምላክ ስለምናመልክ ምንኛ ታድለናል!

^ አን.16 በመስከረም 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 30 ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።