በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ከዓለማዊ አስተሳሰብ ራቁ

ከዓለማዊ አስተሳሰብ ራቁ

“በዓለም . . . ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።”—ቆላ. 2:8

መዝሙሮች፦ 38, 31

1. ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ ምን ምክር ሰጥቷቸዋል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ደብዳቤ የጻፈው በሮም ለመጀመሪያ ጊዜ ታስሮ በነበረበት ወቅት ማለትም ከ60-61 ዓ.ም. ገደማ ባለው ጊዜ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ “መንፈሳዊ ግንዛቤ” የማዳበርን ማለትም ነገሮችን ይሖዋ በሚያይበት መንገድ የማየትን አስፈላጊነት ለእምነት ባልንጀሮቹ ጠቁሟቸዋል። (ቆላ. 1:9) አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ይህን የምለው ማንም ሰው አግባብቶ እንዳያታልላችሁ ነው። በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።” (ቆላ. 2:4, 8) ከዚህም ሌላ ጳውሎስ፣ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው አንዳንድ አስተሳሰቦች ትክክል ያልሆኑበትን ምክንያት እንዲሁም ዓለማዊ አስተሳሰብ ፍጽምና የጎደላቸውን ሰዎች ትኩረት የሚስበው ለምን እንደሆነ አብራርቷል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ዓለማዊ አስተሳሰብ ካለው ጥበበኛ እንደሆነና ከሌሎች እንደሚበልጥ ሊሰማው ይችላል። ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው ወንድሞች፣ ከዓለማዊ አስተሳሰብና ትክክል ካልሆኑ ልማዶች እንዲርቁ ለመርዳት ሲል ነው።—ቆላ. 2:16, 17, 23

2. ዓለማዊ አስተሳሰብን የሚያንጸባርቁ ሐሳቦችን መመርመራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

2 ዓለማዊ አስተሳሰብ፣ ሰዎች የይሖዋን መመሪያዎች ችላ እንዲሉ ወይም አቅልለው እንዲመለከቱ የሚያደርግ ሲሆን ይህ አስተሳሰብ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ደግሞ ቀስ በቀስ እምነታችንን ሊያዳክመው ይችላል። ሁላችንም በቴሌቪዥንና በኢንተርኔት አማካኝነት አሊያም በሥራ ቦታችን ወይም በትምህርት ቤት እንዲህ ላለው አስተሳሰብ እንጋለጣለን። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ አእምሯችንን እንዳይበክለው መከላከል የምንችለው እንዴት ነው? ዓለማዊ አስተሳሰብን የሚያንጸባርቁ አምስት ሐሳቦችን እንዲሁም  እነዚህ ሐሳቦች ተጽዕኖ እንዳያሳድሩብን መከላከል የምንችለው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።

በአምላክ ማመን ያስፈልገናል?

3. ብዙ ሰዎች የትኛው አስተሳሰብ ይማርካቸዋል? ለምንስ?

3 “በአምላክ ባላምንም ጥሩ ሰው መሆን እችላለሁ።” በብዙ አገሮች ውስጥ ሰዎች በአምላክ እንደማያምኑ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ሃይማኖታዊ ዝንባሌ እንደሌላቸው ይገልጻሉ። እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት ‘አምላክ አለ?’ የሚለውን ጉዳይ በቁም ነገር አስበውበት ላይሆን ይችላል፤ ከዚህ ይልቅ ተጠያቂነት ሳይኖርባቸው ያሻቸውን ነገር ማድረግ ስለሚፈልጉ ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 10:4ን አንብብ።) ሌሎች ደግሞ “በአምላክ ማመን ሳያስፈልገኝ ላቅ ባሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መመራት እችላለሁ” ብለው ሲናገሩ አዋቂ እንደሆኑ ይሰማቸዋል።

4. ፈጣሪ እንደሌለ የሚናገር ሰው ቢገጥመን የትኛውን ምሳሌ መጠቀም እንችላለን?

4 በአምላክ የማያምኑ ሰዎች፣ ፈጣሪ እንደሌለ የሚናገሩት በማስረጃ ላይ ተመሥርተው ነው? አንድ ሰው “ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን ቢመረምር የሚያገኘው ግራ የሚያጋቡ መረጃዎችን ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን መልሱ ቀላል ነው። አንድ ቤት፣ የሚሠራው ሳይኖር በራሱ ሊገኝ እንደማይችል የታወቀ ነው፤ ታዲያ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ያለ ሠሪ እንዴት በራሳቸው ሊገኙ ይችላሉ? ከሴሎች መካከል ያን ያህል ውስብስብ ያልሆኑት እንኳ ራሳቸውን ማባዛት ይችላሉ፤ ይህንን ማድረግ የሚችል ቤት ግን የለም። እነዚህ ሴሎች ለመራባት የሚያስፈልገውን መረጃ ማስቀመጥና ወደ አዲሶቹ ሴሎች ማስተላለፍ ይችላሉ። ታዲያ እንዲህ ያለ ችሎታ ያላቸው ሴሎች ንድፍ የተገኘው ከየት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ ቤት ሠሪ እንዳለው የታወቀ ነው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው” የሚል መልስ ይሰጠናል።—ዕብ. 3:4

5. “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለማወቅ በአምላክ ማመን አያስፈልግም” የሚለው ሐሳብ ስህተት የሆነው ለምንድን ነው?

5 ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለማወቅ በአምላክ ማመን እንደማያስፈልግ ለሚናገሩ ሰዎችስ ምን ምላሽ ልንሰጥ እንችላለን? በአምላክ የማያምኑ ሰዎችም እንኳ አንዳንድ ጥሩ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ሊከተሉ እንደሚችሉ የአምላክ ቃል ይናገራል። (ሮም 2:14, 15) ለምሳሌ ያህል፣ እነዚህ ሰዎች ወላጆቻቸውን ያከብሩና ይወዱ ይሆናል። ይሁን እንጂ ትክክልና ስህተት ለሆኑት ነገሮች መሥፈርት ማውጣት ያለበት አፍቃሪ የሆነው ፈጣሪያችን መሆኑን የማይቀበል ሰው፣ ትክክል ናቸው ብሎ የሚመራባቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ምን ያህል አስተማማኝ ሊሆኑ ይችላሉ? (ኢሳ. 33:22) አስተዋይ የሆኑ በርካታ ሰዎች፣ በዓለም ላይ ያሉትን አስከፊ ሁኔታዎች ሲመለከቱ የሰው ልጆች የግድ የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ይሰማቸዋል። (ኤርምያስ 10:23ን አንብብ።) ስለዚህ አንድ ሰው በአምላክ መኖር የማያምንና የእሱን መሥፈርቶች የማይከተል ከሆነ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ሙሉ በሙሉ መለየት እንደሚችል ማሰብ አይኖርብንም።—መዝ. 146:3

ሃይማኖት ያስፈልገናል?

6. ብዙ ሰዎች ስለ ሃይማኖት ምን አመለካከት አላቸው?

6 “ሃይማኖት ባይኖርህም ደስተኛ ሕይወት መምራት ትችላለህ።” ብዙ ሰዎች ሃይማኖት አሰልቺና አላስፈላጊ ነገር እንደሆነ ስለሚሰማቸው እንዲህ ያለው ዓለማዊ አስተሳሰብ ይማርካቸዋል። በተጨማሪም በርካታ ሃይማኖቶች ስለ ገሃነመ እሳት ስለሚያስተምሩ፣ አባሎቻቸው አሥራት እንዲሰጡ ጫና ስለሚያደርጉ ወይም ፖለቲካ ውስጥ ስለሚገቡ ሰዎች ከአምላክ እንዲርቁ ያደርጋሉ። በመሆኑም ያለ ሃይማኖት ደስተኛ ሆኖ መኖር እንደሚቻል የሚሰማቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ አያስገርምም! እንደነዚህ ያሉት ሰዎች “አምላክን ማምለክ እፈልጋለሁ፤ የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል መሆን ግን አልፈልግም” ብለው ይናገሩ ይሆናል።

7. እውነተኛው ሃይማኖት ደስታ የሚያስገኘው እንዴት ነው?

7 በእርግጥ አንድ ሰው ሃይማኖት ሳይኖረው ደስተኛ ሕይወት መምራት ይችላል? አንድ ሰው የሐሰት ሃይማኖትን ባይከተል ደስተኛ ሊሆን እንደሚችል አይካድም፤ ይሁን እንጂ “ደስተኛው አምላክ” ከተባለው ከይሖዋ ጋር ዝምድና የሌለው ሰው እውነተኛ ደስታ ሊኖረው አይችልም። (1 ጢሞ. 1:11) አምላክ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ሌሎችን የሚጠቅም ነው። አገልጋዮቹም ሌሎችን ለመርዳት ጥረት ስለሚያደርጉ ደስተኞች ናቸው። (ሥራ 20:35) ለምሳሌ ያህል፣ እውነተኛው  ሃይማኖት ደስተኛ ቤተሰብ ለመገንባት የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመልከት። እውነተኛው አምልኮ የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርስ እንዲከባበሩ፣ የጋብቻ ቃለ መሐላቸውን አክብደው እንዲመለከቱ፣ ከምንዝር እንዲርቁ፣ ልጆቻቸውን ሥርዓታማ አድርገው እንዲያሳድጉ እንዲሁም ለቤተሰባቸው አባላት እውነተኛ ፍቅር እንዲያሳዩ ያበረታታል። በዚህም ምክንያት እውነተኛውን አምልኮ የሚከተሉ ሰዎችን ያቀፉት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጉባኤዎች አንድነት፣ ሰላምና ደስታ የሰፈነባቸው መሆን ችለዋል።—ኢሳይያስ 65:13, 14ን አንብብ።

8. እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘው ምን እንደሆነ ለማብራራት ማቴዎስ 5:3⁠ን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

8 ‘አንድ ሰው አምላክን ሳያገለግል ደስተኛ ሕይወት መምራት ይችላል’ የሚለው ዓለማዊ አስተሳሰብ ትክክል እንዳልሆነ እንዴት ማስረዳት እንችላለን? እስቲ የሚከተለውን ጥያቄ አስብ፦ ሰዎችን ደስተኛ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? አንዳንዶች ደስታ የሚያገኙት ከሥራቸው፣ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች አሊያም ከትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች ነው። ሌሎች ደግሞ ቤተሰባቸውን ወይም ጓደኞቻቸውን መንከባከብ ያስደስታቸዋል። እነዚህ ነገሮች መጠነኛ ደስታ እንደሚያስገኙ አይካድም፤ ይሁንና በሕይወታችን ውስጥ ዘላቂ ደስታ ለማግኘት ይህ ብቻውን በቂ አይደለም። ከእንስሳት በተለየ የሰው ልጆች ፈጣሪያቸውን ማወቅና እሱን ማገልገል ይችላሉ። የተፈጠርነው ይህን በማድረግ ደስታ እንድናገኝ ተደርገን ነው። (ማቴዎስ 5:3ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች እሱን ለማምለክ አንድ ላይ መሰብሰብ የሚያስደስታቸው ከመሆኑም ሌላ እርስ በርስ ለመበረታታት ያስችላቸዋል። (መዝ. 133:1) በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር፣ ንጹሕ ሥነ ምግባር እንዲሁም ግሩም ተስፋ ስላላቸው ደስተኛ ሕይወት ይመራሉ።

የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ያስፈልጉናል?

9. (ሀ) የፆታ ግንኙነትን አስመልክቶ ብዙዎች ምን ዓይነት አመለካከት አላቸው? (ለ) የአምላክ ቃል ከጋብቻ ውጭ የፆታ ግንኙነት መፈጸምን የሚከለክለው ለምንድን ነው?

9 “ከጋብቻ ውጭ የፆታ ግንኙነት መፈጸም ምን ስህተት አለው?” አንዳንድ ሰዎች “በሕይወታችን መደሰት አለብን። ከጋብቻ ውጭ የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚወገዘው ለምንድን ነው?” ይሉን ይሆናል። ይሁንና “ክርስቲያኖች የፆታ ብልግናን ማውገዝ የለባቸውም” የሚለው አመለካከት ስህተት ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የአምላክ ቃል የፆታ ብልግናን ያወግዛል። * (1 ተሰሎንቄ 4:3-8ን አንብብ።) ይሖዋ ፈጣሪያችን ስለሆነ የምንመራባቸውን ሕጎች የማውጣት ሥልጣን አለው። ጋብቻን ያቋቋመው አምላክ ሲሆን የፆታ ግንኙነት እንዲፈጸም የፈቀደው በባልና ሚስት መካከል ብቻ ነው። አምላክ ሕጎችን ያስቀመጠልን ስለሚወደን ነው። እነዚህን ሕጎች መታዘዛችን ይጠቅመናል። ቤተሰቦች የአምላክን ሕጎች የሚታዘዙ ከሆነ በመካከላቸው ፍቅርና መከባበር ይኖራል፤ እንዲሁም ያለስጋት መኖር ይችላሉ። አምላክ፣ ሕጎቹን ሆን ብለው የሚጥሱ ሰዎችን በቸልታ አይመለከትም።—ዕብ. 13:4

10. አንድ ክርስቲያን ከፆታ ብልግና መራቅ የሚችለው እንዴት ነው?

10 የአምላክ ቃል ከፆታ ብልግና መራቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል። ከፆታ ብልግና መራቅ የምንችልበት አንዱ መንገድ በምንመለከታቸው ነገሮች ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል። ስለዚህ ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው።” (ማቴ. 5:28, 29) በመሆኑም አንድ ክርስቲያን የብልግና ምስሎችን ከመመልከት ወይም የፆታ ብልግናን የሚያበረታቱ ሙዚቃዎችን ከማዳመጥ መቆጠብ ይኖርበታል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ “በምድር ያሉትን የአካል ክፍሎቻችሁን ግደሉ” ብሏቸዋል፤ ጳውሎስ ከዘረዘራቸው ነገሮች መካከል “የፆታ ብልግና” ይገኝበታል። (ቆላ. 3:5) በተጨማሪም ከፆታ ብልግና ጋር ስለተያያዙ ነገሮች ላለማሰብና ላለማውራት መጠንቀቅ ይኖርብናል።—ኤፌ. 5:3-5

ሥራችን በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዝ ይገባል?

11. ሰዎች ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ በሚያስችል የሥራ መስክ መሰማራት የሚፈልጉት ለምን ሊሆን ይችላል?

11 “ለደስታ ቁልፉ በሥራችን ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ነው።” ብዙ ሰዎች ጥሩ ደሞዝና ማዕረግ በሚያስገኝ  የሥራ መስክ መሰማራትን በሕይወታችን ውስጥ ዋነኛ ግባችን እንድናደርገው ያበረታቱን ይሆናል። እንዲህ ያለው የሥራ መስክ ትልቅ ቦታ ላይ ለመድረስ ብሎም ሥልጣንና ሀብት ለማግኘት ያስችል ይሆናል። ብዙዎች የሕይወታቸው ዋነኛ ግብ እንዲህ ባለው የሥራ መስክ መሰማራት በመሆኑ አንድ ክርስቲያንም ተመሳሳይ አመለካከት ሊያድርበት ይችላል።

12. ለደስታ ቁልፉ በሥራችን ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ነው?

12 ሥልጣን በሚያስገኝና አንቱ በሚያስብል የሥራ መስክ መሰማራት በእርግጥ ዘላቂ ደስታ ያስገኛል? በፍጹም። ሰይጣን በሌሎች ላይ የመሠልጠንና የመከበር ምኞት እንደነበረው አስታውስ፤ ይሁንና እነዚህን ነገሮች ማግኘቱ ደስተኛ አላደረገውም፤ እንዲያውም በቁጣ ተሞልቷል። (ማቴ. 4:8, 9፤ ራእይ 12:12) ከዚህ በተቃራኒ ግን ሰዎች ስለ አምላክ እንዲያውቁና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ መርዳት ታላቅ ደስታ ያስገኛል። እንዲህ ያለ ደስታ ሊያስገኝ የሚችል ሌላ የሥራ መስክ የለም። ከዚህም ሌላ ይህ ዓለም የፉክክር መንፈስን ያስፋፋል። ሰዎች ከሌሎች ልቀው እንዲገኙ ግፊት የሚደረግባቸው ሲሆን ይህም ቅናት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ የእነዚህ ሰዎች አካሄድ “ነፋስን እንደማሳደድ” መሆኑን ይገልጻል።—መክ. 4:4

13. (ሀ) ለሰብዓዊ ሥራችን ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? (ለ) ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ከጻፈው ደብዳቤ መመልከት እንደሚቻለው እውነተኛ ደስታ ያስገኘለት ምንድን ነው?

13 ሁሉም ሰው መተዳደሪያ እንደሚያስፈልገው የታወቀ ነው፤ ደግሞም በምንወደው የሥራ መስክ ላይ ለመሰማራት መፈለጋችን ምንም ስህተት የለውም። ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዘው ሰብዓዊ ሥራችን መሆን የለበትም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።” (ማቴ. 6:24) ይሖዋን ለማገልገልና የእሱን ቃል ለሌሎች ለማስተማሩ ሥራ ቅድሚያ ስንሰጥ ወደር የሌለው ደስታ እናገኛለን። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ያለ ደስታ አግኝቶ ነበር። ጳውሎስ ወጣት እያለ በአይሁድ ሃይማኖት ውስጥ ትልቅ ቦታ ላይ የመድረስ አጋጣሚ ነበረው፤ እውነተኛ ደስታ ያስገኘለት ግን ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መሰማራቱና ሰዎች የአምላክን ቃል ተምረው ሕይወታቸውን ሲለውጡ መመልከቱ ነው። (1 ተሰሎንቄ 2:13, 19, 20ን አንብብ።) እንዲህ ያለ ደስታ የሚያስገኝ ሌላ የሥራ መስክ የለም።

ዘላቂ ደስታ የሚያስገኘው፣ ሰዎች ስለ አምላክ እንዲያውቁ መርዳት ነው (አንቀጽ 12, 13⁠ን ተመልከት)

በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች መፍታት እንችላለን?

14. በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች የሰው ልጆች በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ የሚገልጸው ሐሳብ ብዙዎችን የሚማርከው ለምንድን ነው?

14 “በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች የሰው ልጆች በራሳቸው መፍታት ይችላሉ።” ይህ ዓለማዊ አስተሳሰብ ብዙዎችን የሚማርከው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይህ ሐሳብ ትክክል ከሆነ ‘የሰው ልጆች የአምላክ  አመራር አያስፈልጋቸውም እንዲሁም የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ’ ማለት ነው። የሰው ልጆች በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ የሚገልጸው ሐሳብ አሳማኝ እንዲመስል የሚያደርገው ሌላም ምክንያት አለ፤ ጦርነት፣ ወንጀል፣ በሽታና ድህነት እየቀነሱ እንደሆነ የሚገልጹ ጥናቶች አሉ። አንድ ዘገባ “የሰው ልጆች ሕይወት እየተሻሻለ የመጣው፣ ሰዎች ዓለማችንን የተሻለች ቦታ ለማድረግ ቆርጠው በመነሳታቸው ነው” ብሏል። ይሁንና እንደነዚህ ያሉት አስተያየቶች፣ የሰው ልጅ ለረጅም ዘመናት ሲያሠቃዩት ለኖሩት ችግሮች መፍትሔ እያገኘ እንደሆነ ያሳያሉ? መልሱን ለማወቅ እስቲ እውነታውን እንመልከት።

15. በዓለም ላይ ያሉት ችግሮች ምን ያህል ከባድ ደረጃ ላይ እንዳሉ የሚያሳዩት የትኞቹ እውነታዎች ናቸው?

15 ጦርነት፦ በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከ60 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ሕይወት እንደጠፋ ይገመታል። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላም ቢሆን የሰው ልጆች ጦርነትን ማስቀረት አልቻሉም። እስከ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ በጦርነት አሊያም በደረሰባቸው ስደት የተነሳ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር 65 ሚሊዮን ገደማ ደርሷል። በ2015 ብቻ እንኳ 12.4 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል። ወንጀል፦ በአንዳንድ አካባቢዎች የተወሰኑ የወንጀል ዓይነቶች ቢቀንሱም ሌሎች የወንጀል ዓይነቶች ለምሳሌ በኮምፒውተር አማካኝነት የሚፈጸም ወንጀል፣ የቤት ውስጥ ጥቃትና ሽብርተኝነት በአስደንጋጭ ፍጥነት እየጨመሩ ነው። ከዚህም ሌላ ብዙዎች ሙስና በዓለም ዙሪያ እየተባባሰ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በእርግጥም የሰው ልጆች ወንጀልን ማስወገድ አልቻሉም። በሽታ፦ አንዳንድ በሽታዎች መድኃኒት እንደተገኘላቸው የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በ2013 የወጣ ዘገባ እንደሚያሳየው ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በታች የሆኑ ዘጠኝ ሚሊዮን ሰዎች በልብ ሕመም፣ በካንሰር፣ በመተንፈሻ አካላት ሕመም፣ በስኳር በሽታና ጭንቅላታቸው ውስጥ ደም በመፍሰሱ ምክንያት በየዓመቱ ይሞታሉ። ድህነት፦ የዓለም ባንክ እንደገለጸው በ1990 በአፍሪካ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ቁጥር 280 ሚሊዮን ነበር፤ በ2012 ግን ይህ ቁጥር ወደ 330 ሚሊዮን አሻቅቧል።

16. (ሀ) በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች ማስወገድ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ኢሳይያስ እና መዝሙራዊው የአምላክ መንግሥት የትኞቹን በረከቶች እንደሚያመጣ ተንብየዋል?

16 በዛሬው ጊዜ ያለውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት የሚቆጣጠሩት ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ጦርነትን፣ ወንጀልን፣ በሽታንና ድህነትን ማስወገድ እንደማይችሉ ግልጽ ነው፤ ይህን ማድረግ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው። ይሖዋ ለሰው ልጆች ምን እንደሚያደርግ እስቲ እንመልከት። ጦርነት፦ የአምላክ መንግሥት ለጦርነት መንስኤ የሚሆኑትን እንደ ራስ ወዳድነት፣ ምግባረ ብልሹነት፣ የብሔርተኝነት ስሜትና የሐሰት ሃይማኖት ያሉ ነገሮች ያስወግዳል፤ አልፎ ተርፎም ሰይጣንን እንኳ ያጠፋዋል። (መዝ. 46:8, 9) ወንጀል፦ የአምላክ መንግሥት በአሁኑ ጊዜም እንኳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በመካከላቸው ፍቅርና መተማመን እንዲኖር እያስተማረ ነው፤ ይህን ማድረግ የሚችል ሌላ መንግሥት የለም። (ኢሳ. 11:9) በሽታ፦ ይሖዋ ለሕዝቡ የተሟላ ጤንነት ይሰጣቸዋል። (ኢሳ. 35:5, 6) ድህነት፦ ይሖዋ ድህነትን ያስወግዳል፤ እንዲሁም ሕዝቡ ደስተኛ ሕይወት እንዲመሩና ከእሱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ያደርጋል። ገንዘብ ሊያስገኘው የማይችለው ዓይነት ሕይወት ይሰጣቸዋል።—መዝ. 72:12, 13

“እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ” እወቁ

17. ከዓለማዊ አስተሳሰብ መራቅ የምትችለው እንዴት ነው?

17 ሰዎች፣ አንተ ከምታምንበት ነገር ጋር የሚጋጭ ዓለማዊ ሐሳብ ሲሰነዝሩ ከሰማህ በጉዳዩ ላይ የአምላክ ቃል ምን እንደሚል ምርምር አድርግ፤ እንዲሁም ከአንድ የጎለመሰ የእምነት ባልንጀራህ ጋር ተወያዩበት። እንዲህ ያለው ዓለማዊ አስተሳሰብ የብዙዎችን ትኩረት የሚስበው ለምን እንደሆነ፣ ስህተት የሆነበትን ምክንያትና ይህን እንዴት ማስረዳት እንደምትችል ቆም ብለህ አስብ። በእርግጥም ሁላችንም ጳውሎስ ለቆላስይስ ጉባኤ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ካደረግን ዓለማዊ አስተሳሰብ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን መከላከል እንችላለን፤ ጳውሎስ “በውጭ ካሉት ጋር ባላችሁ ግንኙነት በጥበብ መመላለሳችሁን ቀጥሉ። ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ [እወቁ]” በማለት ተናግሯል።—ቆላ. 4:5, 6

^ አን.9 በአንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ ከዮሐንስ 7:53 እስከ 8:11 ላይ የሚገኘው ሐሳብ፣ በበኩረ ጽሑፉ ላይ እንደሌለ ብዙ ሰዎች አይገነዘቡም። አንዳንዶች፣ ምንዝር መፈጸም ስህተት እንደሆነ መናገር የሚችለው ኃጢአት የሌለበት ሰው ብቻ እንደሆነ ለመግለጽ ይህን ጥቅስ እንደ ማስረጃ ያቀርባሉ። ሆኖም አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ “አንድ ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ ከሴትየዋ ጋር የተኛው ሰውም ሆነ ሴትየዋ ሁለቱም ይገደሉ” ይላል።—ዘዳ. 22:22