በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ኅዳር 2017

በደስታ ዘምሩ!

በደስታ ዘምሩ!

“ለአምላካችን የውዳሴ መዝሙር መዘመር ጥሩ ነው።”—መዝ. 147:1

መዝሙሮች፦ 10, 2

1. መዝሙር ምን ለማድረግ አጋጣሚ ይሰጠናል?

አንድ ታዋቂ ገጣሚ ‘ቃላት፣ አንድን ሐሳብ በአእምሯችን እንድንሥል ያደርጉናል። ሙዚቃ ወይም መዝሙር ደግሞ የሚተላለፈው ሐሳብ ስሜታችንን እንዲኮረኩረው ያደርጋል’ ብሎ ነበር። በሰማይ ያለውን አባታችንን ይሖዋን ለማወደስና ለእሱ ያለንን ፍቅር በመዝሙር ለመግለጽ ከሚያስችሉ ሐሳቦች የተሻለ ስሜታችንን ሊኮረኩር የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ጥያቄ የለውም! በእርግጥም፣ ለብቻችንም ይሁን በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሆነን የምንዘምረው መዝሙር በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑ የሚያስገርም አይደለም።

2, 3. (ሀ) አንዳንዶች በጉባኤ ውስጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው መዘመርን በተመለከተ ምን ይሰማቸዋል? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 አንተስ በጉባኤ ውስጥ ድምፅህን ከፍ አድርገህ መዘመርን በተመለከተ ምን ይሰማሃል? እንዲህ ማድረግ ያሳፍርሃል? በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ውስጥ ወንዶች፣ ሰው በተሰበሰበበት ቦታ መዘመር ያሳፍራቸው ይሆናል። እንዲህ ያለው አመለካከት በመላው ጉባኤ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፤ በተለይ ደግሞ ኃላፊነት ያላቸው ወንዶች፣ ጉባኤ ላይ መዝሙር በሚዘመርበት ወቅት የማይዘምሩ አሊያም በሌሎች እንቅስቃሴዎች የሚጠመዱ ከሆነ ይህ ሌሎችም ከመዘመር ወደኋላ እንዲሉ ሊያደርጋቸው ይችላል።—መዝ. 30:12

3 መዝሙርን እንደ አምልኳችን ክፍል አድርገን የምንመለከተው ከሆነ መዝሙር ሲዘመር ወደ ውጭ አንወጣም፤ እንዲሁም ይህ የስብሰባው ክፍል እንዳያመልጠን እንጠነቀቃለን። እንግዲያው ሁላችንም ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘ለአምልኮ በምናደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ  ለሚዘመሩት መዝሙሮች ምን አመለካከት አለኝ? በደስታ እንዳልዘምር እንቅፋት የሚሆንብኝን ማንኛውንም ነገር መወጣት የምችለው እንዴት ነው? መዝሙሮቻችንን ከልብ በመነጨ ስሜት ለመዘመርስ ምን ማድረግ እችላለሁ?’

መዝሙር በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው

4, 5. በጥንቷ እስራኤል ለአምልኮ ከሚቀርቡ መዝሙሮች ጋር በተያያዘ ምን ዝግጅት ተደርጎ ነበር?

4 ከጥንት ጊዜ አንስቶ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ይሖዋን በሙዚቃ ያወድሱ ነበር። የጥንቶቹ እስራኤላውያን ይሖዋን በታማኝነት ያገለግሉ በነበረበት ዘመን፣ መዝሙር በአምልኳቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ ይሰጠው የነበረ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ ዳዊት በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለሚካሄደው አገልግሎት ዝግጅት ሲያደርግ በመዝሙር ለይሖዋ ውዳሴ የሚያቀርቡ 4,000 ሌዋውያንን አደራጅቶ ነበር። ከእነዚህም መካከል “ለይሖዋ በሚቀርበው መዝሙር የሠለጠኑ . . . ይኸውም በዚህ የተካኑ” 288 ሌዋውያን ነበሩ።—1 ዜና 23:5፤ 25:7

5 በቤተ መቅደሱ ምረቃ ወቅት፣ ሙዚቃ ትልቅ ሚና ነበረው። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “መለከት ነፊዎቹና ዘማሪዎቹ በኅብረት ይሖዋን ባወደሱና ባመሰገኑ ጊዜ እንዲሁም . . . ይሖዋን በማወደስ የመለከቱን፣ የሲምባሉንና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ድምፅ ባሰሙ ጊዜ . . . የይሖዋ ክብር የእውነተኛውን አምላክ ቤት [ሞላው]።” ይህ ምንኛ እምነትን የሚያጠናክር እንደሆነ መገመት ይቻላል!—2 ዜና 5:13, 14፤ 7:6

6. ነህምያ የኢየሩሳሌም ገዢ በነበረበት ወቅት ከመዝሙር ጋር በተያያዘ ምን ለየት ያለ ዝግጅት አድርጎ ነበር?

6 ነህምያ፣ ታማኝ ከሆኑት እስራኤላውያን ጋር በመሆን የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እንደገና በገነባበት ጊዜ፣ ዘማሪ የሆኑትን ሌዋውያን የተሟላ የሙዚቃ መሣሪያ እንዲኖራቸው አድርጎ አደራጅቷቸዋል። የኢየሩሳሌም ቅጥሮች በተመረቁበት ጊዜ ነህምያ ለየት ያለ የሙዚቃ ዝግጅት እንዲኖር ያደረገ ሲሆን ይህም ለፕሮግራሙ ድምቀት ሰጥቶታል። በወቅቱ “ሁለት ትላልቅ የዘማሪ ቡድኖች” ተዘጋጅተው ነበር። እነዚህ የዘማሪ ቡድኖች በቅጥሩ ላይ በተቃራኒ አቅጣጫዎች በመሄድ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ባለው ቅጥር ላይ ተገናኙ፤ በዚያም ሆነው ያሰሙት የውዳሴ መዝሙር ከሩቅ ይሰማ ነበር። (ነህ. 12:27, 28, 31, 38, 40, 43) ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ከልብ በመነጨ ስሜት ያቀረቡትን ይህን የውዳሴ መዝሙር ሲሰማ እንደተደሰተ ጥርጥር የለውም።

7. ኢየሱስ ክርስቲያኖች በሚያቀርቡት አምልኮ ውስጥ መዝሙር ትልቅ ቦታ እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

7 የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላም ሙዚቃ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ጉልህ ቦታ ነበረው። በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው ምሽት ላይ ኢየሱስ የጌታ ራት በዓልን ካቋቋመ በኋላ ከሐዋርያቱ ጋር መዝሙር ዘምሯል።ማቴዎስ 26:30ን አንብብ።

8. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች አምላክን በመዝሙር በማወደስ ረገድ ምን ምሳሌ ትተውልናል?

8 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በኅብረት ሆነው አምላክን በመዝሙር በማወደስ ረገድ ምሳሌ ትተውልናል። እነዚያ ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ የሚሰበሰቡት በግለሰቦች መኖሪያ ቤት ውስጥ ቢሆንም ይህ መሆኑ ለይሖዋ በግለት እንዳይዘምሩ አላደረጋቸውም። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያን ወንድሞቹን “በመዝሙራት፣ ለአምላክ በሚቀርብ ውዳሴና በአመስጋኝነት መንፈስ በሚዘመሩ መንፈሳዊ ዝማሬዎች ትምህርትና ማበረታቻ መስጠታችሁን ቀጥሉ፤ በልባችሁም ለይሖዋ ዘምሩ” በማለት በመንፈስ መሪነት አበረታቷቸዋል። (ቆላ. 3:16) በመዝሙር መጽሐፋችን ላይ የሚገኙት መዝሙሮችም “በአመስጋኝነት መንፈስ [የሚዘመሩ] መንፈሳዊ ዝማሬዎች” ናቸው። እነዚህ መዝሙሮች “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ክፍል ናቸው።—ማቴ. 24:45

በልበ ሙሉነት እንድንዘምር ምን ሊረዳን ይችላል?

9. (ሀ) አንዳንዶች በጉባኤም ሆነ በትላልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከልብ በመነጨ ስሜት እንዳይዘምሩ የሚያደርጋቸው ምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር የምንዘምረው እንዴት ሊሆን ይገባል? በዚህ ረገድ ቅድሚያውን ሊወስዱ የሚገባቸው እነማን ናቸው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

9 በቤተሰብህ ውስጥ፣ በምትኖርበት አካባቢ አሊያም ባለህበት ባሕል ውስጥ መዘመር የተለመደ ነገር  ባይሆንስ? ዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ዘፋኞች የሚጫወቱትን ሙዚቃ ለማዳመጥ አስችሎናል። ይሁንና በመዝናኛው ዓለም ውስጥ ያሉትን ሰዎች ድምፅ ከራስህ ድምፅ ጋር ስታወዳድር ብቃት እንደሌለህ ሊሰማህ ይችላል። ሆኖም ይህ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ከመዘመር ወደኋላ እንድትል ሊያደርግህ አይገባም። ሁላችንም ለይሖዋ የመዘመር ኃላፊነት አለብን። ስለዚህ የመዝሙር መጽሐፍህን ከፍ አድርገህ በመያዝና ራስህን ቀና በማድረግ ከልብ በመነጨ ስሜት ዘምር! (ዕዝራ 3:11፤ መዝሙር 147:1ን አንብብ።) በአሁኑ ጊዜ በብዙ የስብሰባ አዳራሾቻችን ውስጥ የመዝሙሮቹ ግጥሞች በስክሪኖች ላይ ይታያሉ፤ ይህም ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለመዘመር ይረዳናል። በተጨማሪም ለሽማግሌዎች የሚዘጋጀው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት፣ የመንግሥቱን መዝሙሮች መዘመርን የሚያካትት መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ይህም ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ በመዘመር ረገድ ቅድሚያውን መውሰድ እንዳለባቸው ይጠቁማል።

10. ድምፃችንን ከፍ አድርገን እንዳንዘምር የሚያግደን ፍርሃት ከሆነ ምን ነገር ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው?

10 አንዳንዶች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዳይዘምሩ እንቅፋት ከሚሆኑባቸው ነገሮች አንዱ ፍርሃት ነው። ድምፃቸው ከሌሎች በጣም ወጣ ብሎ እንዳይሰማ ይፈሩ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ‘ድምፄ ለጆሮ ደስ የማይል ሊሆን ይችላል’ ብለው ያስባሉ። ይሁንና በንግግራችን “ሁላችንም ብዙ ጊዜ [እንደምንሰናከል]” እናስታውስ። (ያዕ. 3:2) ታዲያ በዚህ ምክንያት ከመናገር እንቆጠባለን? እንግዲያው በጣም ጥሩ የሚባል ድምፅ ባይኖረንም እንኳ ይሖዋን በመዝሙር ከማወደስ ወደኋላ ልንል አይገባም።

11, 12. የመዘመር ችሎታችንን ለማሻሻል የሚረዱን አንዳንድ ሐሳቦች ምንድን ናቸው?

11 ከመዘመር ወደኋላ እንድንል የሚያደርገን ሌላው ነገር ደግሞ እንዴት መዘመር እንዳለብን አለማወቃችን ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የመዘመር ችሎታችንን ለማሻሻል የሚረዱን አንዳንድ ነገሮች አሉ። *

12 አተነፋፈስህን ማስተካከልህ ድምፅህን ከፍ አድርገህ በግለት ለመዘመር ይረዳሃል። አምፖል እንዲበራ የሚያደርገው የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሆነ ሁሉ  እኛም ስንናገር ወይም ስንዘምር ድምፃችን ኃይል እንዲኖረው የሚያደርገው ትንፋሻችን ነው። በምትዘምርበት ወቅት የድምፅህ መጠን፣ ስትናገር ከምትጠቀምበት ማነስ የለበትም፤ እንዲያውም ከዚያ ከፍ ማለት ይኖርበታል። (በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 181 እስከ 184 ላይ “አተነፋፈስህን መቆጣጠር” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር የቀረቡትን ሐሳቦች ተመልከት።) ቅዱሳን መጻሕፍት ከመዝሙር ጋር በተያያዘ የይሖዋ አገልጋዮች ‘እልል እንዲሉ’ በሌላ አባባል ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንዲዘምሩ የሚያበረታቱበት ጊዜ አለ።—መዝ. 33:1-3

13. ይበልጥ በልበ ሙሉነት ለመዘመር ምን ሊረዳን እንደሚችል አብራራ።

13 በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ላይ አሊያም ለብቻችሁ ሆናችሁ የሚከተሉትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሩ፦ በመዝሙር መጽሐፋችን ላይ ካሉት የምትወዷቸው መዝሙሮች መካከል አንዱን ምረጡ። ስንኞቹን ጮክ ብላችሁና በልበ ሙሉነት አንብቡ። ቀጥሎም የድምፃችሁን መጠን ሳትቀንሱ አንዱን ስንኝ በአንድ ትንፋሽ አንብቡት። ከዚያም ይህንን ስንኝ በዚያው ስሜት ዘምሩት። (ኢሳ. 24:14) በዚህ ጊዜ ስትዘምሩ ድምፃችሁ ይበልጥ ኃይል ይኖረዋል፤ ይህ ደግሞ ጥሩ ነገር ነው። አፍራችሁ ድምፃችሁን ዝቅ ለማድረግ አትሞክሩ።

14. (ሀ) ስንዘምር ድምፃችን ኃይል እንዲኖረው ምን ማድረግ ይኖርብናል? (“ የመዘመር ችሎታህን ለማሻሻል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) የድምፅ ችግሮችን ለማሻሻል የሚረዱ ምን ጠቃሚ ነጥቦች አግኝተሃል?

14 ስትዘምር አፍህን በደንብ ካልከፈትክ ድምፅህ ኃይል አይኖረውም። በመሆኑም ስትናገር ከምታደርገው ይበልጥ አፍህን በደንብ ከፍተህ መዘመርህም ጠቃሚ ነው። ድምፅህ ደከም ያለ አሊያም ደግሞ ቀጭንና የሰለለ እንደሆነ ከተሰማህ ምን ማድረግ ትችላለህ? እነዚህን ችግሮች ለማሻሻል የሚረዱ ጠቃሚ ሐሳቦችን በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም በተባለው መጽሐፍ ገጽ 184 ላይ “አንዳንድ የድምፅ ችግሮችን ማሻሻል” በሚለው ሣጥን ውስጥ ማግኘት ትችላለህ።”

ከልብ በመነጨ ስሜት ዘምሩ

15. (ሀ) በ2016 በተደረገው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ምን ማስታወቂያ ተነግሮ ነበር? (ለ) አዲስ የመዝሙር መጽሐፍ እንዲወጣ ምክንያት የሆኑት አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

15 ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንስልቬንያ በ2016 ባደረገው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ፣ የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ስቲቨን  ሌት አስደሳች ማስታወቂያ ተናግሮ ነበር፤ ወንድም ሌት ለይሖዋ ‘በደስታ ዘምሩ’ የሚል ርዕስ ያለውን አዲስ የመዝሙር መጽሐፍ በቅርቡ በስብሰባዎቻችን ላይ መጠቀም እንደምንጀምር ሲያስታውቅ ሁላችንም ተደስተን ነበር። ወንድም ሌት እንደገለጸው የመዝሙር መጽሐፋችን እንዲሻሻል የተደረገበት አንዱ ምክንያት ተሻሽሎ ከወጣው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንዲጣጣም ሲባል ነው። በ2013 ተሻሽሎ በወጣው የእንግሊዝኛ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የማይገኙ አገላለጾችን ከመዝሙር መጽሐፋችን ላይ ማውጣት ወይም ማስተካከል አስፈላጊ ሆኗል። በተጨማሪም ከስብከቱ ሥራችን ጋር የተያያዙ እንዲሁም ለቤዛው ያለንን አድናቆት የሚገልጹ አዳዲስ መዝሙሮች እንዲካተቱ ተደርጓል። ከዚህም ሌላ መዝሙር በአምልኳችን ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንደመሆኑ መጠን፣ የበላይ አካሉ ከአዲስ ዓለም ትርጉም ጋር የሚመሳሰል ሽፋን ያለውና በከፍተኛ ጥራት የተዘጋጀ መጽሐፍ እንዲወጣ ወስኗል።

16, 17. በአዲሱ የመዝሙር መጽሐፍ ላይ ምን ማስተካከያዎች ተደርገዋል?

16 ለይሖዋ ‘በደስታ ዘምሩ’ የተባለው መጽሐፍ ለአጠቃቀም አመቺ እንዲሆን ሲባል መዝሙሮቹ የተቀመጡት በርዕሰ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የመጀመሪያዎቹ 12 መዝሙሮች ስለ ይሖዋ፣ ቀጣዮቹ 8 መዝሙሮች ደግሞ ስለ ኢየሱስና ስለ ቤዛው የሚያወሱ ናቸው። በተጨማሪም መጽሐፉ የርዕሰ ጉዳይ ማውጫ ያለው ሲሆን ይህም መዝሙሮችን መምረጥ (ለምሳሌ ለሕዝብ ንግግር) ቀላል እንዲሆን ያደርጋል።

17 ሁሉም ሰው ከልቡ መዘመር እንዲችል ለመርዳት ሲባል፣ በአንዳንዶቹ ግጥሞች ላይ ያለውን ሐሳብ ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ብዙም የማይሠራባቸውን ቃላት ለማስቀረት ተሞክሯል። አንዳንዶቹ ቃላት፣ በስፋት በሚሠራባቸውና ለመረዳት ቀላል በሆኑ ቃላት ተተክተዋል። “ልብህን ጠብቅ” የሚለው ርዕስ “ልባችንን እንጠብቅ” በሚለው መተካቱ ተገቢ ነው። ለምን? ምክንያቱም የቀድሞው መዝሙር፣ ሌሎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው መመሪያ የምንሰጥ ሊያስመስል ይችላል፤ በመሆኑም በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙት አዲሶች፣ ጥናቶች፣ ተመላልሶ መጠየቅ የሚደረግላቸው ሰዎች፣ ወጣቶች እንዲሁም እህቶች ይህን መዝሙር መዘመር ሊከብዳቸው ይችላል። ስለዚህ በመዝሙሩ ርዕስና በግጥሞቹ ላይ ማስተካከያ ተደርጓል።

በቤተሰብ አምልኮ ላይ መዝሙሮችን ተለማመዱ (አንቀጽ 18⁠ን ተመልከት)

18. በአዲሱ የመዝሙር መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን መዝሙሮች መለማመድ ያለብን ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

18 ለይሖዋ ‘በደስታ ዘምሩ’ በተባለው የመዝሙር መጽሐፍ ላይ የሚገኙት ብዙዎቹ መዝሙሮች የጸሎት ይዘት አላቸው። በእነዚህ መዝሙሮች አማካኝነት የውስጥ ስሜትህን ለይሖዋ መግለጽ ትችላለህ። ሌሎቹ መዝሙሮች ደግሞ “ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች [ያነቃቁናል]።” (ዕብ. 10:24) የመዝሙሮቹን ዜማ፣ ምት እና ግጥም በደንብ ለማወቅ ጥረት ልናደርግ ይገባል። jw.org ላይ የሚገኘውን በዘማሪዎች ቡድን በእንግሊዝኛ የተዘመረ መዝሙር ማዳመጣችን በዚህ ረገድ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። መዝሙሮቹን ቤታችን ሆነን መለማመዳችን በልበ ሙሉነትና ከልብ በመነጨ ስሜት ለመዘመር ያስችለናል። *

19. በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሁሉ ለይሖዋ በምናቀርበው አምልኮ መካፈል የሚችሉት እንዴት ነው?

19 መዝሙር በአምልኳችን ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንደሆነ አንዘንጋ። ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና አድናቆት ለመግለጽ የሚያስችል ግሩም መንገድ ነው። (ኢሳይያስ 12:5ን አንብብ።) ድምፅህን ከፍ አድርገህ ከልብህ ስትዘምር ሌሎችም በልበ ሙሉነት እንዲዘምሩ ታበረታታለህ። በእርግጥም ወጣቶችን፣ አዋቂዎችንና አዲሶችን ጨምሮ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሁሉ በመዝሙር አማካኝነት ለይሖዋ በምናቀርበው አምልኮ መካፈል ይችላሉ። እንግዲያው መዝሙር ከመዘመር ወደኋላ አንበል፤ ይልቁንም መዝሙራዊው በመንፈስ መሪነት የሰጠውን ‘ለይሖዋ ዘምሩ’ የሚለውን መመሪያ ተግባራዊ እናድርግ። አዎን ሁላችንም በደስታ እንዘምር!—መዝ. 96:1

^ አን.11 ስንዘምር ድምፃችንን ለማሻሻል የሚረዱን ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘት JW ብሮድካስቲንግ ላይ የወጣውን የታኅሣሥ 2014 ወርሃዊ ፕሮግራም (እንግሊዝኛ) ተመልከት፤ (ቪዲዮው ከስቱዲዮአችን በሚለው ሥር ይገኛል።)

^ አን.18 በትላልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ የጠዋቱና የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም የሚጀምረው አሥር ደቂቃ በሚወስድ ሙዚቃ ነው፤ ይህም ቀጥሎ ያለውን መዝሙር ለመዘመር እንድንጓጓ ያደርገናል። በኦርኬስትራ ታጅበው የሚቀርቡት እነዚህ መዝሙሮች የተዘጋጁት፣ ልባችንንና አእምሯችንን ቀጥሎ ለሚቀርበው ትምህርት በሚያዘጋጅ መንገድ ነው። በመሆኑም ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ቦታችንን ይዘን እነዚህን ሙዚቃዎች በጥሞና እንድንከታተል ማበረታቻ ተሰጥቶናል።