በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

“ለጋስ ሰው ይባረካል”

“ለጋስ ሰው ይባረካል”

መሥዋዕት ማቅረብ ከጥንትም ጀምሮ የእውነተኛው አምልኮ ዋነኛ ክፍል ነበር። እስራኤላውያን የእንስሳት መሥዋዕት ያቀርቡ የነበረ ሲሆን ክርስቲያኖችም የሚታወቁት “የውዳሴ መሥዋዕት” በማቅረብ ነው። ሆኖም አምላክን እጅግ የሚያስደስቱት ሌሎች መሥዋዕቶችም አሉ። (ዕብ. 13:15, 16) ቀጥሎ የቀረቡት ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት እነዚህ መሥዋዕቶች ደስታና በረከት ያመጣሉ።

በጥንት ዘመን የኖረችው ሐና የተባለች ታማኝ የአምላክ አገልጋይ፣ ወንድ ልጅ ለመውለድ በጣም ብትመኝም መሃን ነበረች። ሐና፣ ወንድ ልጅ ብትወልድ “በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለይሖዋ [እንደምትሰጠው]” በጸሎት በመግለጽ ተሳለች። (1 ሳሙ. 1:10, 11) ከጊዜ በኋላ ሐና የፀነሰች ሲሆን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሳሙኤል አለችው። ሐና በተሳለችው መሠረት፣ ሳሙኤል ጡት ከጣለ በኋላ ወደ ማደሪያው ድንኳን ወሰደችው። ሐና የራሷን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በማሳየቷ ይሖዋ ባርኳታል። ሐና አምስት ተጨማሪ ልጆችን በማግኘት የተካሰች ሲሆን ሳሙኤልም ነቢይና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ የመሆን መብት አግኝቷል።—1 ሳሙ. 2:21

በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም ልክ እንደ ሐና እና ሳሙኤል ሕይወታቸውን ለአምላክ ወስነው ፈጣሪያቸውን የማገልገል መብት ተሰጥቷቸዋል። በተጨማሪም ይሖዋን ለማምለክ ስንል የምንከፍለው ማንኛውም መሥዋዕት የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያስገኝ ኢየሱስ ቃል ገብቷል።—ማር. 10:28-30

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረች ዶርቃ የምትባል አንዲት ክርስቲያን “መልካም በማድረግና ምጽዋት በመስጠት” ማለትም ሌሎችን ለመርዳት ስትል መሥዋዕት በመክፈል ትታወቅ ነበር። የሚያሳዝነው ግን ዶርቃ “ታማ ሞተች”፤ በዚህም ምክንያት ጉባኤው ከባድ ሐዘን ላይ ወደቀ። ደቀ መዛሙርቱ፣ ጴጥሮስ በአቅራቢያው እንዳለ ሲሰሙ ቶሎ እንዲመጣ አጥብቀው ለመኑት። ጴጥሮስ መጥቶ ዶርቃን ከሞት ሲያስነሳት ደቀ መዛሙርቱ ምን ያህል እንደተደሰቱ መገመት ይቻላል፤ ይህም አንድ ሐዋርያ የፈጸመው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበ የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው! (ሥራ 9:36-41) አምላክ የዶርቃን መሥዋዕት አልረሳም። (ዕብ. 6:10) ዶርቃ ስላሳየችው ልግስና የሚገልጸው ታሪክም ለእኛ ምሳሌ እንዲሆን በአምላክ ቃል ውስጥ ተመዝግቧል።

ሐዋርያው ጳውሎስም በተመሳሳይ ለሰዎች ትኩረት በመስጠትና ሌሎችን ለመርዳት ጊዜውን በማዋል ልግስና አሳይቷል፤ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበሩ ክርስቲያን ወንድሞቹ ሲጽፍ “በእኔ በኩል ስለ እናንተ ያለኝን ሁሉ፣ ራሴንም ጭምር ብሰጥ እጅግ ደስ ይለኛል” ብሏል። (2 ቆሮ. 12:15) ለሌሎች ሲባል የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ እርካታ የሚያመጣ ከመሆኑም ሌላ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ይኸውም የይሖዋን በረከትና ሞገስ እንደሚያስገኝ ጳውሎስ ከራሱ ተሞክሮ ተምሯል።—ሥራ 20:24, 35

ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማራመድና የእምነት አጋሮቻችንን ለመርዳት ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ስናውል ይሖዋ ይደሰታል። የመንግሥቱን ስብከት ሥራ መደገፍ የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶችስ አሉ? እንዴታ! በፍቅር ተገፋፍተን ከምናከናውናቸው ነገሮች በተጨማሪ በፈቃደኝነት መዋጮ በማድረግ አምላክን ማክበር እንችላለን። እነዚህ መዋጮዎች ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ ለማስፋፋት የሚውሉ ሲሆን ይህም ሚስዮናውያንንና በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማሩ ሌሎች ክርስቲያኖችን መደገፍን ይጨምራል። ከዚህም ሌላ ጽሑፎችንና ቪዲዮዎችን ለማዘጋጀትና ለመተርጎም፣ በአደጋ ጊዜ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ እንዲሁም አዳዲስ የስብሰባ አዳራሾችን ለመገንባት የሚውለው ገንዘብ የሚገኘው በፈቃደኝነት ከምናደርገው መዋጮ ነው። “ለጋስ ሰው [እንደሚባረክ]” እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ከዚህም በላይ ያሉንን ውድ ነገሮች ለይሖዋ ስንሰጥ እሱን እናከብረዋለን።—ምሳሌ 3:9፤ 22:9