በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ኅዳር 2016

የይሖዋን መጽሐፍ ከፍ አድርጋችሁ ትመለከታላችሁ?

የይሖዋን መጽሐፍ ከፍ አድርጋችሁ ትመለከታላችሁ?

“የአምላክን ቃል ከእኛ በሰማችሁ ጊዜ . . . እንደ አምላክ ቃል አድርጋችሁ ተቀብላችሁታል፤ ደግሞም የአምላክ ቃል ነው።”—1 ተሰ. 2:13

መዝሙሮች፦ 96, 94

1-3. በኤዎድያንና በሲንጤኪ መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር ያደረገው ምን ሊሆን ይችላል? እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ምን ማድረግ እንችላለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

የይሖዋ አገልጋዮች፣ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። ሁላችንም ፍጽምና ስለሚጎድለን አልፎ አልፎ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ያስፈልገናል። ታዲያ ምክር ሲሰጠን ምን እናደርጋለን? በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩትን ኤዎድያን እና ሲንጤኪ የተባሉ ክርስቲያኖች እንደ ምሳሌ እንመልከት። በእነዚህ ቅቡዕ እህቶች መካከል ከባድ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። ችግሩ ምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። ሆኖም ምሳሌ እንዲሆነን ያህል፣ የሚከተለው ሁኔታ እንደተፈጠረ አድርገን እናስብ።

2 ኤዎድያን ቤቷ ምግብ ሠርታ አንዳንድ ወንድሞችንና እህቶችን የጋበዘች ሲሆን ጥሩ ጊዜ አሳልፈዋል እንበል። ሲንጤኪ ግን አልተጋበዘችም፤ ሆኖም ወንድሞች በግብዣው እንደተደሰቱ ሰማች። ሲንጤኪ ‘ኤዎድያን ሳትጋብዘኝ መቅረቷ በጣም የሚገርም ነው! እኔኮ ከማንም በላይ የምቀርባት ይመስለኝ ነበር’ ብላ ሊሆን ይችላል። ሲንጤኪ፣ ኤዎድያን እንደማትወዳት ስለተሰማት እሷን በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ጀመረች። በመሆኑም ሲንጤኪ፣ በኤዎድያን ግብዣ ላይ የነበሩትን ወንድሞችና እህቶች በሙሉ ጋበዘች፤ ኤዎድያንን  ግን አልጠራቻትም! በኤዎድያንና በሲንጤኪ መካከል የተፈጠረው ችግር የጉባኤውን ሰላም ሊያደፈርስ ይችል ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ፣ እነዚህ እህቶች መጨረሻ ላይ ምን እንዳደረጉ ባይገልጽልንም ጳውሎስ በፍቅር ተነሳስቶ ለሰጣቸው ምክር ጥሩ ምላሽ ሰጥተው መሆን አለበት።—ፊልጵ. 4:2, 3

3 በዛሬው ጊዜም በይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤዎች ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ሆኖም የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምክር በተግባር ካዋልን እንዲህ ያሉ ችግሮችን መፍታት አልፎ ተርፎም እንዳይፈጠሩ ማድረግ እንችላለን። የአምላክን ቃል ከፍ አድርገን የምንመለከት ከሆነ ደግሞ በውስጡ የሚገኙትን መመሪያዎች እንከተላለን።—መዝ. 27:11

የአምላክ ቃል ስሜታችንን ስለ መቆጣጠር ምን ይላል?

4, 5. የአምላክ ቃል ቁጣችንን ለመቆጣጠር የሚረዳ ምን ምክር ይሰጣል?

4 እንደተናቅን ወይም ተገቢ ያልሆነ ነገር እንደተደረገብን በሚሰማን ጊዜ ስሜታችንን መቆጣጠር ከባድ ሊሆንብን ይችላል። በዘራችን፣ በቆዳችን ቀለም አሊያም በውጫዊ ገጽታችን ምክንያት ብንነቀፍ ስሜታችን በጣም እንደሚጎዳ የታወቀ ነው። ይህን ያደረገው የእምነት ባልንጀራችን ሲሆን ደግሞ ሁኔታው ምንኛ የከፋ ይሆናል! ሰዎች ፍጹማን ባለመሆናቸው ምክንያት እንዲህ ያለ መጥፎ ባሕርይ ማሳየታቸው አይቀርም፤ ታዲያ የአምላክ ቃል ይህን ተቋቁመን ለማለፍ የሚያስችል ምክር ይዟል?

5 ይሖዋ፣ የሰው ልጆች ስሜታቸውን ካልተቆጣጠሩ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ያውቃል። በምንቆጣበት ወይም በምንበሳጭበት ወቅት፣ በኋላ ላይ የሚቆጨንን ነገር ልንናገር ወይም ልናደርግ እንችላለን። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስሜታችንን እንድንቆጣጠር እንዲሁም ቶሎ እንዳንቆጣ የሚሰጠንን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ምንኛ ጠቃሚ ነው! (ምሳሌ 16:32ን እና መክብብ 7:9ን አንብብ።) ማንኛችንም ብንሆን ቶሎ ቅር ላለመሰኘትና ይበልጥ ይቅር ባይ ለመሆን ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልገን ጥርጥር የለውም። ይሖዋና ኢየሱስ ይቅር ባይ መሆንን ትልቅ ቦታ ይሰጡታል። (ማቴ. 6:14, 15) አንተስ ይቅር ባይ ከመሆን ወይም ቁጣህን ከመቆጣጠር ጋር በተያያዘ ይበልጥ መሥራት ያስፈልግህ ይሆን?

6. ምሬት እንዳያድርብን መጠንቀቅ የሚገባን ለምንድን ነው?

6 ቁጣቸውን የመቆጣጠር ችግር ያለባቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ምሬት ያድርባቸዋል። በመሆኑም ሌሎች ይርቋቸዋል። በምሬት የተሞላ ሰው በጉባኤ ውስጥ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በውስጡ ያለውን ምሬት ወይም ጥላቻ ለመደበቅ ጥረት ቢያደርግም በልቡ ያለው ክፋት “በጉባኤ መካከል ይገለጣል።” (ምሳሌ 26:24-26) ሽማግሌዎች፣ ይህ ግለሰብ ምሬትና ጥላቻ እንዲሁም ቂም መያዝ በአምላክ ድርጅት ውስጥ ቦታ እንደሌላቸው እንዲገነዘብ ሊረዱት ይችላሉ። ተወዳዳሪ የሌለው የይሖዋ መጽሐፍ በዚህ ረገድ ግልጽ መመሪያ ይሰጣል። (ዘሌ. 19:17, 18፤ ሮም 3:11-18) አንተስ በምክሩ ትስማማለህ?

ይሖዋ እንዴት እንደሚመራን አትርሱ

7, 8. (ሀ) ይሖዋ የድርጅቱን ምድራዊ ክፍል የሚመራው እንዴት ነው? (ለ) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት አንዳንድ መመሪያዎች የትኞቹ ናቸው? ልንታዘዛቸው የሚገባውስ ለምንድን ነው?

7 ይሖዋ በድርጅቱ ምድራዊ ክፍል ውስጥ የሚገኙ አገልጋዮቹን ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ይመራቸዋል እንዲሁም ይመግባቸዋል፤ ይህን ባሪያ የሚመራው ደግሞ ‘የጉባኤው ራስ’ ክርስቶስ ነው። (ማቴ. 24:45-47፤ ኤፌ. 5:23) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው የበላይ አካል ሁሉ ታማኝና ልባም ባሪያም መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈስ መሪነት እንደተጻፈ የአምላክ ቃል ወይም መልእክት አድርጎ የሚቀበለው ከመሆኑም ሌላ ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። (1 ተሰሎንቄ 2:13ን አንብብ።) ለእኛ ጥቅም ተብለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሰፈሩት መመሪያዎች ወይም ትምህርቶች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?

8 መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዘውትረን በስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ ያዘናል። (ዕብ. 10:24, 25) እንዲሁም  ትምህርታችን አንድ እንዲሆን አጥብቆ ያሳስበናል። (1 ቆሮ. 1:10) የይሖዋ ቃል፣ ከምንም ነገር በላይ የአምላክን መንግሥት እንድናስቀድም ይመክረናል። (ማቴ. 6:33) በተጨማሪም ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ምሥራቹን ከቤት ወደ ቤት፣ በአደባባይና መደበኛ ባልሆነ መንገድ የመስበክ ኃላፊነትና መብት እንደተሰጠን ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሥራ 5:42፤ 17:17፤ 20:20) የአምላክ ቃል፣ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የድርጅቱን ንጽሕና መጠበቅ እንዳለባቸው ይናገራል። (1 ቆሮ. 5:1-5, 13፤ 1 ጢሞ. 5:19-21) ይሖዋ በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ሁሉ አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን መጠበቅ እንዳለባቸውም ተናግሯል።—2 ቆሮ. 7:1

9. የአምላክን ቃል እንድንረዳ ኢየሱስ ያዘጋጀልን ብቸኛ መስመር የትኛው ነው?

9 አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስን እነሱ በፈለጉት መንገድ መተርጎም እንደሚችሉ ይሰማቸው ይሆናል። ይሁንና ኢየሱስ መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርበው ‘በታማኙ ባሪያ’ በኩል ብቻ ነው። ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ተከታዮቹ የአምላክን ቃል እንዲማሩና መመሪያዎቹን እንዲከተሉ ለመርዳት ከ1919 ጀምሮ በዚህ ባሪያ ሲጠቀም ቆይቷል። እኛም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መመሪያዎች በመታዘዝ ለጉባኤው ንጽሕና፣ ሰላምና አንድነት አስተዋጽኦ እናበረክታለን። እያንዳንዳችን ‘ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ምግብ ለሚያቀርብበት መስመር ታማኝ ነኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው።

የይሖዋ ሠረገላ በፍጥነት እየተጓዘ ነው!

10. የሕዝቅኤል መጽሐፍ የይሖዋን ድርጅት ሰማያዊ ክፍል እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል?

10 በጽሑፍ የሰፈረው የይሖዋ ቃል ስለ ድርጅቱ ሰማያዊ ክፍል ለማወቅ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ሕዝቅኤል በተመለከተው ራእይ ላይ የአምላክ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል በሠረገላ ተመስሏል። (ሕዝ. 1:4-28) ይህን ሠረገላ የሚቆጣጠረው ይሖዋ ሲሆን ሠረገላው የይሖዋ መንፈስ ወደመራው አቅጣጫ ሁሉ ይሄዳል። የድርጅቱ ሰማያዊ ክፍል ደግሞ ምድራዊውን ክፍል ይመራዋል። ይህ ሠረገላ በፍጥነት እየተጓዘ ነው! ባለፈው አሥር ዓመት በድርጅቱ ውስጥ ስለተከናወኑት ለውጦች እስቲ ቆም ብለህ አስብ፤ ከእነዚህ ለውጦች በስተጀርባ የይሖዋ እጅ አለበት። ክርስቶስና ቅዱሳን መላእክት ይህን ክፉ ዓለም የሚያጠፉበት ጊዜ በተቃረበበት በዚህ ዘመን፣ የይሖዋ ሠረገላ የእሱን ስም ለማስቀደስና የሉዓላዊነቱን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እየገሰገሰ ነው!

በግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በትጋት የሚሠሩትን በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ከልብ እናደንቃቸዋለን! (አንቀጽ 11ን ተመልከት)

11, 12. የይሖዋ ድርጅት እያከናወናቸው ያሉት አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

11 የአምላክ ድርጅት ምድራዊ ክፍል በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት እያከናወነ ስላለው ነገር ለማሰብ ሞክር። ግንባታ፦ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ያለውን አዲሱን የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በመገንባቱ ሥራ በትጋት ተካፍለዋል። በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች በዓለም አቀፉ ንድፍና ግንባታ ክፍል አመራር ሥር በመሆን አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾችን በመገንባትና ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በማስፋፋት ሥራ እየተካፈሉ ነው። እንዲህ ባሉት ፕሮጀክቶች ላይ ራሳቸውን ሳይቆጥቡ የሚሠሩ በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች በመኖራቸው ምንኛ አመስጋኞች ነን! በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንዲህ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል  የገንዘብ መዋጮ ያደርጋሉ። ሕዝቡ በዚህ መንገድ ትሕትናና ታማኝነት ስለሚያሳዩ ይሖዋ ይባርካቸዋል።—ሉቃስ 21:1-4

12 ትምህርት፦ መለኮታዊ ትምህርት የሚሰጥባቸውን የተለያዩ ትምህርት ቤቶች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። (ኢሳ. 2:2, 3) የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት፣ ለአዲስ ቤቴላውያን የተዘጋጀ ትምህርት ቤት፣ የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት፣ ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት፣ ለወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀ ትምህርት ቤት፣ የጉባኤ ሽማግሌዎች ትምህርት ቤት፣ የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት እንዲሁም ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀ ትምህርት ቤት አለን። በእርግጥም ይሖዋ ሕዝቡን ማስተማር የሚያስደስተው አምላክ ነው! በተጨማሪም በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎች የሚገኙበት jw.org የተባለው ድረ ገጻችን ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲማሩ እየረዳ ነው። ይህ ድረ ገጽ፣ ለልጆችና ለቤተሰቦች የተዘጋጁ ክፍሎች ያሉት ከመሆኑም ሌላ የዜና ዘገባዎችንም ይዟል። ታዲያ jw.orgን በአገልግሎትህና በቤተሰብ አምልኮህ ላይ እየተጠቀምክበት ነው?

ለይሖዋ ታማኝ ሁኑ፤ ድርጅቱንም ደግፉ

13. የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች መሆናችን ምን ኃላፊነት ያስከትልብናል?

13 የይሖዋ ድርጅት አባል መሆን ምንኛ መታደል ነው! እርግጥ ነው፣ የአምላክን መሥፈርቶች እንዲሁም እሱ የሚጠብቅብንን ነገሮች ማወቃችን፣ ትክክል የሆነውን ነገር የማድረግና የእሱን ሉዓላዊነት የመደገፍ ኃላፊነት ያስከትልብናል። ይህ ዓለም በሥነ ምግባር እያዘቀጠ ሲሄድ እኛ ግን አምላክን በመምሰል “ክፉ የሆነውን ነገር [መጥላት]” ይኖርብናል። (መዝ. 97:10) “ጥሩውን መጥፎ፣ መጥፎውንም ጥሩ የሚሉ” ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎችን ከመከተል እንርቃለን። (ኢሳ. 5:20) አምላክን ማስደሰት ስለምንፈልግ አካላዊ፣ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ እንጥራለን። (1 ቆሮ. 6:9-11) ይሖዋን እንወደዋለን፤ በእሱም እንታመናለን፤ በመሆኑም ውድ በሆነው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት በግልጽ የሰፈሩ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን በመኖር ለእሱ ያለንን ታማኝነት እናሳያለን። በቤት፣ በጉባኤ፣ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤትም ሆነ በየትኛውም ቦታ እነዚህን መሥፈርቶች ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። (ምሳሌ 15:3) ለአምላክ ታማኝ መሆናችንን ማሳየት የምንችልባቸውን ተጨማሪ መንገዶች ደግሞ እስቲ እንመልከት።

14. ክርስቲያን ወላጆች ለአምላክ ታማኝ መሆናቸውን ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

14 የልጆች አስተዳደግ፦ ክርስቲያን ወላጆች በአምላክ ቃል መሠረት ልጆቻቸውን በማሠልጠን ለይሖዋ ታማኝ እንደሆኑ ያሳያሉ። ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች፣ የሚኖሩበት ማኅበረሰብ ስለ ልጆች አስተዳደግ ያለው አመለካከት ተጽዕኖ እንዳያደርግባቸው ይጠነቀቃሉ። የዓለም መንፈስ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ቦታ የለውም። (ኤፌ. 2:2) አንድ ክርስቲያን አባት ‘በእኛ አገር ልጆችን የሚያሠለጥኑት እናቶች ናቸው’ ብሎ ሊያስብ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን የማያሻማ መመሪያ ይሰጣል፦ “አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን . . . በይሖዋ ተግሣጽና ምክር [ትምህርት፤ መመሪያ] አሳድጓቸው።” (ኤፌ. 6:4 ግርጌ) አምላክን የሚፈሩ አባቶችና እናቶች፣ ልጆቻቸው እንደ ሳሙኤል እንዲሆኑ ይፈልጋሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ “ሳሙኤል እያደገ ሄደ፤ ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር” ይላል።—1 ሳሙ. 3:19

15. ከባድ ውሳኔዎችን በምናደርግበት ጊዜ ለይሖዋ ታማኝ እንደሆንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

15 ውሳኔ፦ በሕይወታችን ውስጥ ከባድ ውሳኔ ስናደርግ ለአምላክ ያለንን ታማኝነት የምናሳይበት አንዱ መንገድ ከቃሉና ከድርጅቱ መመሪያ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ነው። ይህ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በምሳሌ ለማስረዳት፣ በርካታ ወላጆችን የሚነካ አንድ ጉዳይ እንመልከት። በሌላ አገር የሚኖሩ አንዳንድ ወላጆች፣ ልጆች ሲወልዱ ልጆቻቸውን ዘመዶቻቸው እንዲንከባከቧቸው ወደ አገራቸው ይልካሉ፤ ይህም ወላጆች፣ በሄዱበት አገር እየሠሩ ገንዘብ መላካቸውን ለመቀጠል ያስችላቸዋል።  ይህ የግል ውሳኔ እንደሆነ አይካድም፤ ሆኖም ለምናደርጋቸው ውሳኔዎች በአምላክ ፊት ተጠያቂ እንደሆንን መዘንጋት አይኖርብንም። (ሮም 14:12ን አንብብ።) የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ግምት ውስጥ ሳናስገባ ከቤተሰባችን አሊያም ከሥራ ምርጫችን ጋር የተያያዙ አስፈላጊ ውሳኔዎችን ማድረግ ጥበብ ይሆናል? በፍጹም! አካሄዳችንን አቃንተን መምራት ስለማንችል የሰማዩ አባታችን እርዳታ ያስፈልገናል።—ኤር. 10:23

16. አንዲት እናት፣ ልጅ ስትወልድ ምን ውሳኔ ተደቀነባት? ትክክለኛውን ውሳኔ ለማድረግ የረዳትስ ምንድን ነው?

16 በሌላ አገር እየኖረች ሳለ ልጅ የወለደች አንዲት ሴት፣ ልጇን አያቶቹ እንዲያሳድጉት ወደ ትውልድ አገሯ ለመላክ አስባ ነበር። በዚህ ወቅት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። በጥናቷ እድገት እያደረገች ስትሄድ፣ ልጇን የይሖዋ አገልጋይ እንዲሆን የማሠልጠኑ ኃላፊነት የእሷ እንደሆነና አምላክ እንዲህ እንድታደርግ እንደሚጠብቅባት ተማረች። (መዝ. 127:3፤ ምሳሌ 22:6) ይህች ወጣት ቅዱሳን ጽሑፎች በሚያበረታቱን መሠረት ለይሖዋ ልቧን አፈሰሰች። (መዝ. 62:7, 8) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን ለምታስጠናት ሴት የልቧን አውጥታ ነገረቻት፤ ሌሎች የጉባኤ አባላትንም አማከረች። ወዳጅ ዘመዶቿ፣ ልጇን ወደ አያቶቹ እንድትልክ ተጽዕኖ ቢያሳድሩባትም እንዲህ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ወሰነች። ባለቤቷ፣ ጉባኤው ሚስቱንም ሆነ ልጃቸውን ምን ያህል እንደተንከባከባቸው ሲመለከት ልቡ ስለተነካ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንዲሁም ከባለቤቱና ከልጁ ጋር በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። ይህች እናት፣ ይሖዋ ላቀረበችው ልባዊ ጸሎት ምላሽ እንደሰጠ ስትገነዘብ ምንኛ እንደተደሰተች መገመት አያዳግትም!

17. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችንን በተመለከተ ምን መመሪያዎች ተሰጥተውናል?

17 መመሪያ መከተል፦ ለአምላክ ታማኝ እንደሆንን የምናሳይበት ሌላው መንገድ ከድርጅቱ የሚሰጠንን መመሪያ መከተል ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችንን በተመለከተ የተሰጡንን ሐሳቦች እንደ ምሳሌ እንመልከት። አንድን ሰው፣ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ በቋሚነት ማስጠናት ከጀመርን ብዙም ሳይቆይ ግለሰቡን ከድርጅቱ ጋር ለማስተዋወቅ ጥቂት ደቂቃዎች እንድንመድብ ተበረታተናል። በመንግሥት አዳራሻችን ውስጥ ምን ይከናወናል? የሚለውን ቪዲዮ እና በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው? የተባለውን ብሮሹር በመጠቀም ይህን ማድረግ እንችላለን። እድገት ከሚያደርግ ጥናት ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ አጥንተን ስንጨርስ ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ እንድናስጠናው ሐሳብ ቀርቦልናል፤ ግለሰቡ ቢጠመቅም እንኳ ይህን ማድረጋችን ተገቢ ነው። ድርጅቱ ይህን መመሪያ የሰጠው አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ‘በእምነት ጸንተው መኖር’ እንዲችሉ ነው። (ቆላ. 2:7) አንተስ የይሖዋ ድርጅት የሚሰጣቸውን እንዲህ ያሉ መመሪያዎች ትታዘዛለህ?

18, 19. ይሖዋን እንድናመሰግን የሚያነሳሱን አንዳንድ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

18 ይሖዋን እንድናመሰግነው የሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች አሉን! ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው። (ሥራ 17:27, 28) ውድ የሆነ ስጦታ ይኸውም ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። በተሰሎንቄ እንደነበሩት ክርስቲያኖች እኛም የይሖዋን መልእክት እንደ አምላክ ቃል አድርገን በመቀበል አድናቆታችንን እናሳያለን።—1 ተሰ. 2:13

19 በጽሑፍ የሰፈረው የአምላክ ቃል በእጃችን ስላለ ወደ ይሖዋ መቅረብ ችለናል፤ እሱም ወደ እኛ ቀርቧል። (ያዕ. 4:8) በሰማይ ያለው አባታችን የድርጅቱ አባል የመሆን ውድ መብት ሰጥቶናል። ከይሖዋ ያገኘናቸውን እንዲህ ያሉ በረከቶች በጣም እናደንቃለን! “ይሖዋ ጥሩ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በማለት እንደዘመረው መዝሙራዊ ይሰማናል። (መዝ. 136:1) መዝሙር 136 ላይ “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” የሚለው አገላለጽ 26 ጊዜ ተጠቅሷል። ለይሖዋና ለድርጅቱ ታማኝ ከሆንን የዘላለም ሕይወት ስለምናገኝ የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት እንመለከታለን!