‘ይሖዋ ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ ጠራችሁ።’—1 ጴጥ. 2:9

መዝሙሮች፦ 95, 74

1. ኢየሩሳሌም ስትጠፋ የነበረውን ሁኔታ ግለጽ።

በ607 ዓ.ዓ በዳግማዊ ናቡከደነጾር የሚመራ ግዙፍ የባቢሎናውያን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ወረረ። በዚያ ወቅት የነበረውን ደም መፋሰስ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “[ናቡከደነጾር] ወጣቶቻቸውን በቤተ መቅደሳቸው ውስጥ በሰይፍ ገደለ፤ ለወጣቱም ሆነ ለድንግሊቱ፣ ለሽማግሌውም ሆነ ለአቅመ ደካማው አልራራም። . . . የእውነተኛውን አምላክ ቤት አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሰ፤ የማይደፈሩ ማማዎቿን ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ እንዲሁም ውድ የሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ አወደመ።”—2 ዜና 36:17, 19

2. ይሖዋ ከኢየሩሳሌም መጥፋት ጋር በተያያዘ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር? አይሁዳውያኑ ምን እንደሚደርስባቸው ተተንብዮ ነበር?

2 የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች፣ ከተማዋ መጥፋቷ ሊያስደነግጣቸው አይገባም ነበር። አይሁዳውያን የአምላክን ሕግ ችላ ማለታቸውን ከቀጠሉ ይሖዋ ለባቢሎናውያን አሳልፎ እንደሚሰጣቸው የአምላክ ነቢያት ለዓመታት ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። በርካታ አይሁዳውያን በሰይፍ ስለት እንደሚሞቱና ከሞት የተረፉት ደግሞ ቀሪ ሕይወታቸውን ባቢሎን ውስጥ በግዞት እንደሚያሳልፉ ትንቢት ተነግሮ ነበር። (ኤር. 15:2) በግዞት የሄዱት አይሁዳውያን ሕይወት ምን ይመስል ነበር? በክርስትና ዘመንስ በባቢሎናውያን ተማርኮ ከመወሰድ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ተፈጽሞ ይሆን? ከሆነስ መቼ?

 የግዞት ሕይወት

3. እስራኤላውያን በባቢሎን በግዞት ያሳለፉት ሕይወት በግብፅ ካሳለፉት የባርነት ሕይወት የሚለየው እንዴት ነው?

3 ነቢያቱ የተናገሩት ነገር ተፈጽሟል። በግዞት የሚወሰዱት እስራኤላውያን፣ ያሉበትን ሁኔታ ተቀብለው ለመኖር ጥረት እንዲያደርጉ ይሖዋ በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት መክሯቸዋል። እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “[በባቢሎን] ቤት ሠርታችሁ በዚያ ኑሩ። አትክልት ተክላችሁ ፍሬውን ብሉ። በግዞት ተወስዳችሁ እንድትኖሩባት ላደረግኳት ከተማም ሰላምን ፈልጉ፤ ስለ እሷም ወደ ይሖዋ ጸልዩ፤ እሷ ሰላም ከሰፈነባት እናንተም በሰላም ትኖራላችሁና።” (ኤር. 29:5, 7) የአምላክን ፈቃድ የተቀበሉት እስራኤላውያን በባቢሎን የነበራቸው ሕይወት መጥፎ አልነበረም ማለት ይቻላል። ባቢሎናውያኑ፣ አይሁዳውያን በተወሰነ መጠንም ቢሆን የራሳቸውን ጉዳዮች እንዲያስተዳድሩ ፈቅደውላቸው ነበር። ምርኮኞቹ በአገሪቱ ውስጥ የመዘዋወር ነፃነትም ጭምር ነበራቸው። ባቢሎን የጥንቱ ዓለም የንግድ መዲና ነበረች፤ በርካታ አይሁዳውያን የንግድ ሙያ እንደተማሩ፣ ሌሎች ደግሞ የተዋጣላቸው የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች እንደሆኑ በቁፋሮ የተገኙ ሰነዶች ያሳያሉ። እንዲያውም አንዳንድ አይሁዳውያን ባለጸጎች ሆነው ነበር። እስራኤላውያን በባቢሎን በግዞት ያሳለፉት ሕይወት፣ ከበርካታ ዘመናት በፊት በግብፅ ካሳለፉት የባርነት ሕይወት ጋር ጨርሶ አይወዳደርም።ዘፀአት 2:23-25ን አንብብ።

4. ባቢሎናውያን በአምላክ ላይ ካመፁት እስራኤላውያን በተጨማሪ እነማንንም በምርኮ ወስደው ነበር? ይህስ አይሁዳውያኑ አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለክ ተፈታታኝ እንዲሆንባቸው ያደረገው እንዴት ነው?

4 በምርኮ የተወሰዱት አይሁዳውያን በቁሳዊ ረገድ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ተሟልተውላቸው ነበር፤ ሆኖም ስለ መንፈሳዊ ፍላጎታቸው ምን ማለት ይቻላል? የይሖዋ ቤተ መቅደስና መሠዊያው ጠፍተው ነበር፤ ካህናቱም ቢሆኑ በተደራጀ መንገድ ሥራቸውን እያከናወኑ አልነበሩም። በግዞት ከተወሰዱት አይሁዳውያን መካከል፣ እንዲህ ያለ ቅጣት እንዲደርስባቸው የሚያደርግ ጥፋት ያልሠሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ይገኙ ነበር፤ ይሁንና በብሔሩ ላይ ከመጣው መከራ እነሱም ቢሆን አላመለጡም። ሆኖም እነዚህ አይሁዳውያን የአምላክን ሕግ ለመጠበቅ የሚችሉትን ያህል ይጥሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ዳንኤል እንዲሁም ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የተባሉት ሦስት ጓደኞቹ በባቢሎን ሲኖሩ ለአይሁዳውያን የተከለከሉ ምግቦችን ከመመገብ ተቆጥበዋል። ከዚህም በተጨማሪ ዳንኤል በጸሎት አማካኝነት ከአምላክ ጋር አዘውትሮ የመነጋገር ልማድ እንደነበረው እናውቃለን። (ዳን. 1:8፤ 6:10) ይሁን እንጂ ፈሪሃ አምላክ ያለው አንድ አይሁዳዊ፣ በአረማውያን አገዛዝ ሥር ሆኖ በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን ትእዛዛት ሙሉ በሙሉ መጠበቅ እንደማይችል ግልጽ ነው።

5. ይሖዋ ለሕዝቡ ምን ቃል ገብቶ ነበር? ይህ ተስፋ አስገራሚ የሆነውስ ለምንድን ነው?

5 ታዲያ እስራኤላውያን እንደቀድሟቸው አምላክን ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለክ የሚችሉበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? በወቅቱ ይህ የሚሆን አይመስልም ነበር። ባቢሎናውያን በምርኮ የወሰዷቸውን ሰዎች ፈጽሞ አይለቁም ነበር። ይሁንና ይህ ፖሊሲ፣ ይሖዋ አምላክ ዓላማውን እንዳይፈጽም ሊያግደው አይችልም። ይሖዋ፣ ሕዝቡ ነፃ እንደሚወጡ ቃል ገብቶ ነበር፤ ያለውም ተፈጽሟል። አምላክ ቃል የገባው ነገር መቼም ቢሆን መፈጸሙ አይቀርም።—ኢሳ. 55:11

በዘመናችን ተመሳሳይ ነገር ተፈጽሟል?

6, 7. በዘመናችን የአምላክ ሕዝቦች በባቢሎን ከተማረኩበት ጊዜ ጋር በተያያዘ በነበረን ግንዛቤ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

6 ክርስቲያኖች በምርኮ ወደ ባቢሎን ከተወሰዱት እስራኤላውያን ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ አጋጥሟቸው ያውቃል? በዘመናችን ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በ1918 በባቢሎን እንደተማረኩና በ1919 ከባቢሎን ነፃ እንደወጡ የሚገልጽ ሐሳብ በዚህ መጽሔት ላይ ለበርካታ ዓመታት ሲወጣ ቆይቷል። ሆኖም በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራሩት ነጥቦች እንደሚያሳዩት ይህን ርዕሰ ጉዳይ እንደገና መመርመሩ አስፈላጊ ሆኗል።

7 እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ታላቂቱ ባቢሎን፣ በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ እንደምታመለክት እናውቃለን። በመሆኑም የአምላክ ሕዝቦች በ1918 በባቢሎን ተማርከዋል ማለት የሚቻለው  እነዚህ ሰዎች በዚያ ወቅት በሆነ መንገድ በሐሰት ሃይማኖት ቀንበር ሥር ከሆኑ ነው። መረጃዎቹ እንደሚያሳዩት ከሆነ ግን ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት በነበሩት አሥርተ ዓመታት ውስጥ የአምላክ ቅቡዓን አገልጋዮች በታላቂቱ ባቢሎን ቀንበር ሥር ከመሆን ይልቅ ከእሷ ነፃ እየወጡ ነበር። በተጨማሪም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቅቡዓኑ ስደት የደረሰባቸው ቢሆንም በዋነኝነት ስደት ያደረሱባቸው ዓለማዊ ባለሥልጣናት እንጂ ታላቂቱ ባቢሎን አልነበረችም። በመሆኑም ‘የይሖዋ ሕዝቦች በታላቂቱ ባቢሎን የተማረኩት በ1918 አይደለም’ ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ይመስላል።

በባቢሎን መማረክ—መቼ?

8. እውነተኛው ክርስትና እንዴት እንደተበከለ አብራራ። (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

8 በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተቀየሩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተቀቡ። እነዚህ አዲስ ክርስቲያኖች “የተመረጠ ዘር፣ ንጉሣዊ ካህናት፣ ቅዱስ ብሔር፣ ልዩ ንብረት እንዲሆን የተለየ ሕዝብ” ሆነዋል። (1 ጴጥሮስ 2:9, 10ን አንብብ።) ሐዋርያት በሕይወት እስካሉ ድረስ የአምላክን ሕዝብ ጉባኤ ይጠብቁ ነበር። በተለይ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ግን “ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች [ተነሱ]።” (ሥራ 20:30፤ 2 ተሰ. 2:6-8) ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በጉባኤ ውስጥ በበላይ ተመልካችነት የማገልገል ኃላፊነት ነበራቸው፤ ከጊዜ በኋላም “ጳጳሳት” ሆኑ። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” ያላቸው ቢሆንም በክርስቲያኖች መካከል የቀሳውስት ቡድን ብቅ ማለት ጀመረ። (ማቴ. 23:8) በአርስቶትልና በፕላቶ ፍልስፍና የተማረኩ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች፣ የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችን ማስተማር የጀመሩ ሲሆን ይህም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ንጹሕ ትምህርት ቀስ በቀስ እየዋጠው ሄደ።

9. የክህደት ክርስትና የሮምን መንግሥት ድጋፍ ያገኘው እንዴት እንደሆነና ይህ ምን እንዳስከተለ አብራራ።

9 በ313 ዓ.ም. አረማዊው ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ለዚህ የክህደት ክርስትና ሕጋዊ እውቅና ሰጠው። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት እጅና ጓንት ሆነው መሥራት ጀመሩ። ለምሳሌ ያህል፣ በኒቂያ ጉባኤ ላይ ተገኝቶ የነበረው ቆስጠንጢኖስ፣ ‘ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው’ የሚለውን ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነውን አርዮስ የተባለ ቄስ በግዞት እንዲቀመጥ አድርጎታል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ በቀዳማዊ ንጉሥ ቲዮዶሸስ (379-395 ዓ.ም.) የግዛት ዘመን፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን (ለክህደት ክርስትና የተሰጠው መጠሪያ) ሮም ውስጥ የመንግሥት ሃይማኖት ሆነ። የታሪክ ምሁራን፣ አረማዊ የነበረው የሮም መንግሥት በአራተኛው መቶ ዘመን “ክርስትናን” እንደተቀበለ ይናገራሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በዚህ ወቅት የክህደት ክርስትና፣ በሮም ግዛት ሥር ከነበሩት የአረማውያን ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ጋር በመዋሃድ የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል ሆኖ ነበር። በስንዴ የተመሰሉት ጥቂት ቁጥር ያላቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች በወቅቱ አምላክን ለማገልገል የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነበር፤ ሆኖም ተሰሚነት አልነበራቸውም። (ማቴዎስ 13:24, 25, 37-39ን አንብብ።) በእርግጥም በባቢሎን ተማርከው ነበር!

10. ከክርስቶስ ልደት በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት መቶ ዓመታት የኖሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ጥያቄ እንዲያነሱ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

10 ያም ቢሆን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት መቶ ዓመታት ውስጥ በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በግሪክኛ ወይም በላቲን ማንበብ ይችሉ ነበር። በመሆኑም በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን ትምህርት ከቤተ ክርስቲያኗ ትምህርት ጋር የማወዳደር አጋጣሚ ነበራቸው። አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ካነበቡት ነገር በመነሳት የቤተ ክርስቲያኗ ትምህርቶች ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የላቸውም የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ፤ እርግጥ ይህን አመለካከታቸውን በግልጽ መናገር አደገኛ አልፎ ተርፎም ለሞት የሚዳርግ ነበር።

11. ቤተ ክርስቲያኗ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዳይችሉ ያደረገችው እንዴት ነው?

11 ውሎ አድሮ ግን አብዛኛው ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስ በሚገኝባቸው ቋንቋዎች መጠቀም እየተወ ሄደ፤ ቤተ ክርስቲያኗ ደግሞ የአምላክን ቃል ሕዝቡ ወደሚጠቀምበት ቋንቋ ለመተርጎም የተደረጉትን  ጥረቶች ተቃወመች። በዚህም የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሚችሉት ቀሳውስቱና አንዳንድ የተማሩ ሰዎች ብቻ ነበሩ፤ በእርግጥ ከቀሳውስቱም መካከል በደንብ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ነበሩ። ቤተ ክርስቲያኗ የምታስተምረውን ነገር የሚቃወም ማንኛውም ሰው ከፍተኛ ቅጣት ይበየንበት ነበር። በመሆኑም ታማኝ የሆኑ የአምላክ ቅቡዕ አገልጋዮች በትናንሽ ቡድኖች ሆነው ለመሰብሰብ ተገደዱ፤ ያውም መሰብሰብ ከቻሉ ነው። ቀደም ሲል የአምላክ ሕዝብ ወደ ባቢሎን በግዞት በተወሰደበት ወቅት እንደሆነው ሁሉ፣ በዚህ ወቅትም “ንጉሣዊ ካህናት” የሆኑት ቅቡዓን በተደራጀ መልኩ ሥራቸውን ማከናወን አልቻሉም። ታላቂቱ ባቢሎን ሕዝቡን ተብትባ ይዛው ነበር!

ብርሃን መታየት ጀመረ

12, 13. ታላቂቱ ባቢሎን በሕዝቡ ላይ የነበራት ተጽዕኖ እንዲዳከም ያደረጉት ሁለት ነገሮች ምንድን ናቸው? አብራራ።

12 ለመሆኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ አምላክን በይፋ ብሎም በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማምለክ ነፃ የሚሆኑበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? አዎ! ውሎ አድሮ የመንፈሳዊ ብርሃን ጭላንጭል ጨለማውን ሰንጥቆ መታየት ጀመረ፤ ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው፣ በ15ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ አካባቢ የተሻለ የማተሚያ መሣሪያ መፈልሰፉ ነው። በምዕራቡ ዓለም የማተሚያ መሣሪያ ከመፈልሰፉ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ የሚባዛው በእጅ በመገልበጥ ሲሆን ሥራው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነበር። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ በቀላሉ አይገኝም ነበር፤ ቢገኝም ደግሞ ዋጋው የሚቀመስ አልነበረም። አንድ የተዋጣለት ገልባጭ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ገልብጦ ለመጨረስ አሥር ወር እንደሚወስድበት ይነገራል! ከዚህም ሌላ ገልባጮቹ እንደ ወረቀት የሚጠቀሙበት ነገር ይኸውም ብራና በጣም ውድ ነበር። የማተሚያ መሣሪያ ግን በጣም የተሻለ አማራጭ ነው። በሕትመት ሥራ የተካነ አንድ ባለሙያ፣ በማተሚያ መሣሪያና በወረቀት በመጠቀም በቀን እስከ 1,300 ገጾችን ማተም ይችላል!

የተሻሉ የማተሚያ መሣሪያዎች መፈልሰፋቸውና ደፋር የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች መነሳታቸው የባቢሎን ተጽዕኖ እንዲዳከም አድርጓል (አንቀጽ 12, 13ን ተመልከት)

13 ጨለማው እንዲገፈፍ አስተዋጽኦ ያደረገው  ሁለተኛው ነገር ደግሞ ደፋር የሆኑ ጥቂት ሰዎች በ16ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ የአምላክን ቃል ሰፊው ሕዝብ በሚጠቀምበት ቋንቋ ለመተርጎም መወሰናቸው ነው። በርካታ ተርጓሚዎች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ይህን ሥራ ጀመሩ። ይህ እርምጃ ቤተ ክርስቲያኗን በጣም አስደነገጣት። የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ፈሪሃ አምላክ ባላቸው ሰዎች እጅ መግባቱ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ስለተሰማቸው ስጋት ገባቸው! ደግሞም ሕዝቡ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያገኝ ማንበብ ጀመረ። ይህም በሕዝቡ አእምሮ ውስጥ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ፈጠረ፦ ‘የአምላክ ቃል ስለ መንጽሔና ስለ ፍታት የሚጠቅሰው የት ጋ ነው? ስለ ሊቀ ጳጳሳትና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ የሚናገር ነገርስ የት አለ?’ እንዲህ ያለ ጥያቄ መነሳቱ ቤተ ክርስቲያኗን በጣም አስቆጣት። ቀሳውስቱ ይህ ትልቅ ድፍረት እንደሆነ ተሰማቸው! በመሆኑም ቤተ ክርስቲያኗ የአጸፋ እርምጃ ወሰደች። የቤተ ክርስቲያኗን ትምህርት የተቃወሙ ሰዎች በመናፍቅነት ተወነጀሉ፤ የሚገርመው ከቤተ ክርስቲያኗ ትምህርቶች አንዳንዶቹ የተመሠረቱት ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት በኖሩት በአርስቶትልና በፕላቶ ፍልስፍና ላይ ነበር። ቤተ ክርስቲያኗ የሞት ፍርድ ስትበይን መንግሥት ፍርዱን ያስፈጽም ነበር። ይህ የተደረገበት ዓላማ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያነቡና በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ጥያቄ እንዳያነሱ ለማስፈራራት ነው። በጥቅሉ ሲታይ ሴራቸው ተሳክቷል። ይሁን እንጂ ለታላቂቱ ባቢሎን ማስፈራሪያ ያልተንበረከኩ ጥቂት ደፋር ሰዎች ነበሩ። የአምላክን ቃል አንድ ጊዜ ስለቀመሱ ተጨማሪ ነገር የማግኘት ጉጉት አደረባቸው! በመሆኑም ከሐሰት ሃይማኖት ነፃ መውጣት የሚቻልበት መድረክ ተመቻቸ።

14. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የፈለጉ ሰዎች ምን አደረጉ? (ለ) ወንድም ራስል እውነትን ለማግኘት ያደረገውን ጥረት አብራራ።

14 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተጠሙ ብዙ ሰዎች ቤተ ክርስቲያኗ ያን ያህል ተጽዕኖ ወደማታሳድርባቸው አገሮች ተሰደዱ። እነዚህ ሰዎች፣ ሌሎች ጫና ሳያደርጉባቸው መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ማጥናት እንዲሁም ባነበቡት ላይ መወያየት ፈልገው ነበር። እንዲህ ዓይነት ነፃነት ካለባቸው አገሮች በአንዷ ይኸውም በዩናይትድ ስቴትስ፣ በ1800ዎቹ መገባደጃ አካባቢ ቻርልስ ቴዝ ራስል እና ተባባሪዎቹ መጽሐፍ ቅዱስን በተደራጀ መልኩ ማጥናት ጀመሩ። መጀመሪያ ላይ የወንድም ራስል ዓላማ፣ ታዋቂ ከሆኑት ሃይማኖቶች መካከል እውነቱን የሚያስተምረው የትኛው ሃይማኖት እንደሆነ ማወቅ ነበር። ክርስቲያን ያልሆኑትን ጨምሮ በርካታ ሃይማኖቶች የሚያስተምሩትን ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በጥንቃቄ አነጻጸረው። ከእነዚህ ሃይማኖቶች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ የአምላክን ቃል በጥብቅ እንደማይከተሉ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደበትም። እንዲያውም በአንድ ወቅት በአካባቢው ያሉ የተወሰኑ ቀሳውስትን ሰብስቦ አወያይቷቸው ነበር፤ ይህን ያደረገው እነዚህ ሰዎች፣ እሱና ተባባሪዎቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኟቸውን እውነቶች እንደሚቀበሉና ለጉባኤዎቻቸው አባላት እንደሚያስተምሩ ተስፋ አድርጎ ነው። ቀሳውስቱ ግን ይህን ማድረግ አልፈለጉም። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የሚከተለውን ሐቅ ለመገንዘብ ተገደዱ፦ የሐሰት ሃይማኖትን የሙጥኝ ለማለት ከመረጡ ሰዎች ጋር ተባብሮ መሥራት የማይቻል ነገር ነው።—2 ቆሮንቶስ 6:14ን አንብብ።

15. (ሀ) ክርስቲያኖች በታላቂቱ ባቢሎን ቀንበር ሥር የሆኑት መቼ ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?

15 እውነተኛ ክርስቲያኖች በባቢሎን የተማረኩት፣ ሐዋርያት በሙሉ ከሞቱ ብዙም ሳይቆይ እንደሆነ ተመልክተናል። ይሁንና መልስ የሚያሻቸው ሌሎች ጥያቄዎችም ይነሳሉ፦ ከ1914 በፊት በነበሩት ዓመታት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ እየወጡ እንደነበር የሚያሳይ ምን ሌላ ማስረጃ አለ? የአምላክ ሕዝቦች በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የስብከት እንቅስቃሴያቸው ስለተዳከመ ይሖዋ አዝኖባቸው ነበር? በዚያ ወቅት የነበሩ አንዳንድ ወንድሞች ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸውን አላልተዋል? ከሆነስ ይህ የይሖዋን ሞገስ አሳጥቷቸዋል? ክርስቲያኖች በሐሰት ሃይማኖት ቀንበር ሥር የሆኑት ከሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ወዲህ ከሆነ ነፃ የወጡት መቼ ነው? እነዚህ ግሩም ጥያቄዎች ናቸው። መልሱን በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።