“ሕዝቡን የሚያበረታታ የምትናገሩት ቃል ካላችሁ ተናገሩ።”—ሥራ 13:15

መዝሙሮች፦ 121, 45

1, 2. ማበረታቻ መስጠት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

“ወላጆቼ አበረታተውኝ አያውቁም፤ እንዲያውም በጣም ይነቅፉኛል። የሚናገሩት ነገር ስሜት የሚጎዳ ነው።” ይህን ያለችው የ18 ዓመቷ ክሪስቲና ናት። [1] አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ብስለት እንደሚጎድለኝ፣ መቼም ቢሆን እንደማልሻሻልና ወፍራም እንደሆንኩ ይናገራሉ። በዚህ ምክንያት ብዙ ጊዜ የማለቅስ ሲሆን ከእነሱ ጋር አለመነጋገርን እመርጣለሁ። ጨርሶ ዋጋ እንደሌለኝ ይሰማኛል።” በእርግጥም ማበረታቻ የሚሰጠን ከሌለ ሕይወት ምንኛ ከባድ ይሆናል!

2 በሌላ በኩል ደግሞ ማበረታቻ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። ሩቤን የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “አልረባም ከሚል ስሜት ጋር ለበርካታ ዓመታት ስታገል ኖሬያለሁ። አንድ ቀን፣ የጉባኤ ሽማግሌ ከሆነ አንድ ወንድም ጋር እያገለገልኩ ሳለ ወንድም እንደከፋኝ አስተዋለ። ምን እንደሚሰማኝ ስነግረው ርኅራኄ በሚንጸባረቅበት መንገድ አዳመጠኝ። ከዚያም እያከናወንኩ ያለሁትን መልካም ነገር ጠቀሰልኝ። በተጨማሪም እያንዳንዳችን ከብዙ ድንቢጦች እንደምንበልጥ ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ አስታወሰኝ። ይህ ጥቅስ ብዙ ጊዜ ወደ አእምሮዬ የሚመጣ ሲሆን ባስታወስኩት ቁጥር ልቤ ይነካል። ወንድም የተናገረው ነገር በአመለካከቴ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።”—ማቴ. 10:31

3. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ ማበረታቻን በተመለከተ ምን ብሏል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

3 መጽሐፍ ቅዱስ አዘውትሮ ማበረታቻ የመስጠትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የሚገልጽ መሆኑ ሊያስገርመን አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞች፣ ሕያው ከሆነው አምላክ  በመራቅ እምነት የለሽ የሆነ ክፉ ልብ ከእናንተ መካከል በማናችሁም ውስጥ እንዳያቆጠቁጥ ተጠንቀቁ፤ ከዚህ ይልቅ ከእናንተ መካከል አንዳችሁም ኃጢአት ባለው የማታለል ኃይል እንዳትደነድኑ . . . በየዕለቱ እርስ በርሳችሁ ተበረታቱ።” (ዕብ. 3:12, 13) አንድ ሰው በተናገረው ሐሳብ መንፈሳችሁ የታደሰበትን ጊዜ ታስታውሳላችሁ? ከሆነ እርስ በርስ እንድንበረታታ የተሰጠን ትእዛዝ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘባችሁ አይቀርም። እስቲ ሦስት ጥያቄዎችን እንመርምር፦ ማበረታቻ መስጠት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ፣ ኢየሱስና ጳውሎስ ሌሎችን ካበረታቱበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን? ውጤታማ የሆነ ማበረታቻ መስጠት የምንችለውስ እንዴት ነው?

የሰው ልጆች ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል

4. እነማን ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል? በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ሌሎችን የማያበረታቱት ለምንድን ነው?

4 ሁላችንም ማበረታቻ ያስፈልገናል። በተለይ ከልጆች ጋር በተያያዘ ይህ እውነት ነው። ቲሞቲ ኤቫንዝ የተባሉ ምሁር “ተክሎች ውኃ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ [ልጆችም] ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል” በማለት ተናግረዋል። አክለውም “አንድ ልጅ ማበረታቻ የሚሰጠው ከሆነ ዋጋ እንዳለውና ሌሎች እንደሚያደንቁት ይሰማዋል” ብለዋል። ይሁንና የምንኖረው በሚያስጨንቅ ዘመን ውስጥ ነው። ሰዎች ራስ ወዳዶችና ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው ስለሆኑ ሌሎችን ማበረታታት የተለመደ አይደለም። (2 ጢሞ. 3:1-5) አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን የማያደንቁት፣ የራሳቸው ወላጆች ምንም ዓይነት ማበረታቻ ሰጥተዋቸው ስለማያውቁ ነው። በሥራው ዓለም ያሉ በርካታ ሰዎችም በሥራ ቦታቸው ጨርሶ ማበረታቻ እንደማያገኙ በምሬት ይናገራሉ።

5. ማበረታቻ ምን ነገሮችን ያካትታል?

5 ማበረታቻ መስጠት አንድ ሰው ላደረገው መልካም ነገር ማመስገንን ይጨምራል። በተጨማሪም ሰዎች ያሏቸውን ጥሩ ባሕርያት በማድነቅ ወይም ‘ተስፋ የቆረጡትን የሚያጽናና’ ነገር በመናገር ሌሎችን ማበረታታት ይቻላል። (1 ተሰ. 5:14 ግርጌ) አብዛኛውን ጊዜ “ማበረታቻ” ተብሎ የሚተረጎመው የግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ፍቺ “ከጎኔ ሁን” የሚል ነው። ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ስናገለግል እነሱን የሚያበረታታ ነገር ለመናገር አጋጣሚዎች ማግኘታችን አይቀርም። (መክብብ 4:9, 10ን አንብብ።) ታዲያ አመቺ አጋጣሚዎችን ተጠቅመን፣ ሌሎችን እንድንወዳቸውና እንድናደንቃቸው የሚያደርጉንን ምክንያቶች እንነግራቸዋለን? ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠታችን በፊት “በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ ቃል . . . ምንኛ መልካም ነው!” በሚለው ጥቅስ ላይ ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው።—ምሳሌ 15:23

6. ዲያብሎስ ተስፋ ሊያስቆርጠን የሚፈልገው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

6 ሰይጣን ዲያብሎስ፣ ተስፋ ከቆረጥን በመንፈሳዊም ሆነ በሌሎች አቅጣጫዎች እንደምንዳከም ስለሚያውቅ ተስፋ ሊያስቆርጠን ይፈልጋል። ምሳሌ 24:10 “በመከራ ቀን ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል” ይላል። ሰይጣን፣ ጻድቁን ኢዮብን ተስፋ ለማስቆረጥ ሲል የተለያዩ መከራዎች ያመጣበት ከመሆኑም ሌላ የሐሰት ውንጀላዎች እንዲሰነዘሩበት አድርጓል፤ ሆኖም ሙከራው አልተሳካለትም። (ኢዮብ 2:3፤ 22:3፤ 27:5) እኛም የቤተሰባችንንና የጉባኤውን አባላት በማበረታታት የዲያብሎስን ሥራ ማክሸፍ እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን ቤታችንንም ሆነ የመንግሥት አዳራሻችንን ደስታ የምናገኝበትና ከመንፈሳዊ አደጋ ነፃ የምንሆንበት ስፍራ ለማድረግ ይረዳል።

ማበረታቻ በመስጠት ረገድ መልካም ምሳሌዎች

7, 8. (ሀ) ይሖዋ ማበረታቻ መስጠትን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው የሚያሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ስጥ። (ለ) ወላጆች ይሖዋን ለመምሰል ምን ማድረግ ይችላሉ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

7 ይሖዋ፦ መዝሙራዊው፣ “ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ ተስፋ የቆረጡትንም ያድናል” ሲል ዘምሯል። (መዝ. 34:18 ግርጌ) ኤርምያስ በፍርሃት በተዋጠበትና ተስፋ በቆረጠበት ጊዜ ይሖዋ ይህን ታማኝ ነቢይ አደፋፍሮታል። (ኤር. 1:6-10) አረጋዊው ነቢይ ዳንኤል፣ አምላክ አንድ መልአክ ልኮ “እጅግ የተወደድክ” ወይም “እጅግ የተከበርክ” በማለት ባጽናናው ጊዜ ምንኛ ተበረታቶ  ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው! (ዳን. 10:8, 11, 18, 19 ግርጌ) አንተስ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አስፋፊዎች፣ አቅኚዎች እንዲሁም በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶች ታበረታታለህ?

8 አምላክ፣ ከሚወደው ልጁ ጋር ለብዙ ዘመናት አብሮ ቢሠራም ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ምስጋናና ማበረታቻ እንደማያስፈልገው አልተሰማውም። እንዲያውም ይሖዋ በሁለት ወቅቶች “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት ስለ ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴ. 3:17፤ 17:5) በዚህ መንገድ አምላክ ኢየሱስን ያበረታታው ከመሆኑም ሌላ ሥራውን እንደሚያደንቅ ገልጾለታል። ኢየሱስ በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ እንዲሁም ምድራዊ ሕይወቱን ሊያጠናቅቅ ሲል እነዚህን ቃላት መስማቱ በጣም አበረታቶት መሆን አለበት። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ባለው ምሽት በከፍተኛ ጭንቀት ተውጦ በነበረበት ጊዜም ይሖዋ መልአኩን ልኮ አበረታቶታል። (ሉቃስ 22:43) ወላጆች የሆንን፣ ልጆቻችንን አዘውትረን በማበረታታት እንዲሁም አንድን ነገር ጥሩ አድርገው ሲሠሩ በማድነቅ የይሖዋን ምሳሌ እንከተል። በየቀኑ በትምህርት ቤት የእምነት ፈተና የሚያጋጥማቸው ከሆነ ደግሞ ተጨማሪ ማበረታቻ ልንሰጣቸው ይገባል።

9. ኢየሱስ ሐዋርያቱን ከያዘበት መንገድ ምን እንማራለን?

9 ኢየሱስ፦ ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ባቋቋመበት ምሽት ሐዋርያቱ የኩራት ዝንባሌ እንዳላቸው ተመልክቶ ነበር። ኢየሱስ ራሱን ዝቅ በማድረግ እግራቸውን ቢያጥብም ከመካከላቸው ታላቅ የሆነው ማን እንደሆነ መከራከራቸውን አልተዉም፤ ጴጥሮስ ደግሞ ከልክ በላይ በራሱ ተማምኖ ነበር። (ሉቃስ 22:24, 33, 34) ያም ቢሆን ኢየሱስ፣ ታማኝ ሐዋርያቱን በፈተናዎቹ ከጎኑ ሳይለዩ እንደቆዩ በመጥቀስ አመስግኗቸዋል። እሱ ከሠራው የበለጠ ሥራ እንደሚሠሩ አስቀድሞ የተናገረ ከመሆኑም ሌላ አምላክ እንደሚወዳቸው ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ሉቃስ 22:28፤ ዮሐ. 14:12፤ 16:27) እኛም ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘በልጆቼም ሆነ በሌሎች ሰዎች ድክመት ላይ ከማተኮር ይልቅ ያከናወኑትን ጥሩ ነገር በማድነቅ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ልከተል አይገባም?’

10, 11. ሐዋርያው ጳውሎስ ሌሎችን ማበረታታት አስፈላጊ መሆኑን እንደተገነዘበ ያሳየው እንዴት ነው?

10 ሐዋርያው ጳውሎስ፦ ጳውሎስ በጻፋቸው ደብዳቤዎች ላይ ለእምነት ባልንጀሮቹ ያለውን አድናቆት ገልጿል። ከአንዳንዶቹ ጋር ለዓመታት አብሮ ስለተጓዘ ያሉባቸውን ድክመቶች እንደሚያውቅ ጥርጥር የለውም፤ ያም ቢሆን ስለ እነሱ መልካም ነገር ተናግሯል። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ ስለ ጢሞቴዎስ ሲናገር ‘በጌታ ልጄ የሆነው የምወደውና ታማኝ የሆነው’ በማለት ገልጾታል፤ በተጨማሪም ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ ለሌሎች ክርስቲያኖች ከልቡ እንደሚያስብ ተናግሯል። (1 ቆሮ. 4:17፤ ፊልጵ. 2:19, 20) ሐዋርያው ስለ ቲቶ ለቆሮንቶስ ጉባኤ ሲጽፍ ደግሞ “ለእናንተ ጥቅም አብሮኝ የሚሠራ ባልደረባዬ” በማለት ለእሱ ያለውን አድናቆት ገልጿል። (2 ቆሮ. 8:23) ጢሞቴዎስና ቲቶ፣ ጳውሎስ ለእነሱ ያለውን አመለካከት ሲያውቁ ምንኛ ተበረታተው ይሆን!

11 ጳውሎስና በርናባስ፣ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል ከዚያ ቀደም ጥቃት ተሰንዝሮባቸው ወደነበሩ ቦታዎች ተመልሰው ሄደዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በልስጥራ ከባድ ተቃውሞ አጋጥሟቸው የነበረ ቢሆንም ወደዚያ ተመልሰው በመሄድ አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ አበረታተዋል። (ሥራ 14:19-22) በኤፌሶን ደግሞ በቁጣ የተሞሉ ሰዎች በጳውሎስ ላይ ተነስተውበት ነበር። የሐዋርያት ሥራ 20:1, 2 እንዲህ ይላል፦ “ሁከቱ ሲበርድ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን አስጠራቸው፤ ካበረታታቸውና ከተሰናበታቸው በኋላ ወደ መቄዶንያ ጉዞ ጀመረ። በሚያልፍባቸው ስፍራዎች የሚያገኛቸውን ደቀ መዛሙርት በብዙ ቃል እያበረታታ ወደ ግሪክ መጣ።” ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ ሌሎችን ማበረታታት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ያምን ነበር።

በዛሬው ጊዜ ሌሎችን አበረታቱ

12. ስብሰባዎቻችን እርስ በርስ እንድንበረታታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉት እንዴት ነው?

12 በሰማይ ያለው አባታችን በደግነት ተነሳስቶ አዘውትረን የምንሰበሰብበት ዝግጅት ያደረገበት አንዱ ምክንያት በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ እርስ በርስ እንድንበረታታ  ነው። (ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የኢየሱስ ተከታዮች ሁሉ እኛም አንድ ላይ የምንሰበሰበው ለመማርና እርስ በርስ ለመበረታታት ነው። (1 ቆሮ. 14:31) በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰችው ክሪስቲና እንዲህ ብላለች፦ “በስብሰባዎች ላይ መገኘት በጣም የሚያስደስተኝ በዚያ ፍቅርና ማበረታቻ ስለማገኝ ነው። አንዳንድ ጊዜ ወደ መንግሥት አዳራሹ የምደርሰው መንፈሴ ተደቁሶ ነው። ሆኖም እህቶች ወደ እኔ መጥተው እቅፍ ካደረጉኝ በኋላ እንዳማረብኝ ይነግሩኛል። በተጨማሪም እንደሚወዱኝና መንፈሳዊ እድገት ማድረጌ እንዳስደሰታቸው ይገልጹልኛል። እነሱ የሚሰጡኝ ማበረታቻ መንፈሴን ያድሰዋል!” ሁላችንም “እርስ በርሳችን እንድንበረታታ” የተሰጠንን ምክር ተግባራዊ በማድረግ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ስናበረክት ጉባኤው ምንኛ አስደሳች ይሆናል!—ሮም 1:11, 12

13. ለብዙ ዓመታት ይሖዋን ያገለገሉ ሰዎችም እንኳ ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

13 ለብዙ ዓመታት ይሖዋን ያገለገሉ ሰዎችም እንኳ ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ኢያሱን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አምላክን ለዓመታት በታማኝነት አገልግሏል። ያም ቢሆን ይሖዋ፣ እንደሚከተለው ብሎ ኢያሱን እንዲያበረታታው ለሙሴ ነግሮታል፦ “በዚህ ሕዝብ ፊት የሚሻገረውም ሆነ አንተ ያየሃትን ምድር እንዲወርሱ የሚያደርገው ኢያሱ ስለሆነ እሱን መሪ አድርገህ ሹመው፤ አደፋፍረው፤ አበረታታውም።” (ዘዳ. 3:27, 28) ኢያሱ፣ እስራኤላውያንን እየመራ ተስፋይቱን ምድር ድል አድርጎ የመቆጣጠር ከባድ ኃላፊነት ሊሰጠው ነው። ወደፊት ተፈታታኝ ሁኔታዎች የሚያጋጥሙት ከመሆኑም ሌላ ቢያንስ አንድ ጊዜ በውጊያ ይሸነፋል። (ኢያሱ 7:1-9) በእርግጥም ኢያሱ መበረታታትና መደፋፈር ያስፈለገው መሆኑ የሚያስገርም አይደለም! እኛም የአምላክን መንጋ ለመንከባከብ ተግተው የሚሠሩትን ሽማግሌዎችና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች እናበረታታቸው። (1 ተሰሎንቄ 5:12, 13ን አንብብ።) አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ ወንድሞች በጉብኝታችን ምን ያህል እንደተደሰቱ የሚገልጽ የምስጋና ደብዳቤ ይሰጡናል። እነዚህን ደብዳቤዎች የምናስቀምጣቸው ሲሆን በሚከፋን ጊዜ አውጥተን እናነባቸዋለን። ይህን ማድረጋችን በእጅጉ ያበረታታናል።”

ልጆቻችንን ከልብ የምናበረታታቸው ከሆነ እድገት ያደርጋሉ (አንቀጽ 14ን ተመልከት)

14. ሌሎችን ማድነቃችንና ማበረታታታችን የምንሰጠው ምክር ይበልጥ ኃይል እንዲኖረው የሚያደርገው እንዴት ነው?

14 ክርስቲያን ሽማግሌዎችም ሆኑ ወላጆች፣ ሌሎችን ማድነቃቸውና ማበረታታታቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሚሰጡበት ጊዜ ምክሩ ይበልጥ ኃይል እንዲኖረው ያደርጋል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጳውሎስ የሰጣቸውን ምክር ተግባራዊ በማድረጋቸው ሐዋርያው አመስግኗቸዋል፤ ይህም ትክክል የሆነውን ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ አበረታቷቸው መሆን አለበት። (2 ቆሮ. 7:8-11) ሁለት ልጆች ያሉት አንድሬአስ እንዲህ ብሏል፦ “ማበረታቻ መስጠት ልጆች በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉና ብስለት እንዲኖራቸው ይረዳል። ማበረታቻ፣ የሰጣችሁት ምክር ወደ ልባቸው ዘልቆ እንዲገባ ለማድረግ ያስችላል። ልጆቻችን ትክክለኛው አካሄድ የቱ እንደሆነ ቢያውቁም ይህን ማድረግ የሕይወታቸው  ክፍል የሚሆነው ሁልጊዜ ማበረታቻ የምንሰጣቸው ከሆነ ነው።”

ውጤታማ የሆነ ማበረታቻ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?

15. ሌሎችን ማበረታታት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

15 የእምነት ባልንጀሮቻችሁ የሚያደርጉትን ጥረትና መልካም ባሕርያቸውን እንደምታደንቁ ግለጹላቸው። (2 ዜና 16:9፤ ኢዮብ 1:8) ባለንበት ሁኔታ የተነሳ፣ የመንግሥቱን ሥራ ለመደገፍ ማከናወን የምንችለው ነገርና የምናደርገው መዋጮ ውስን ሊሆን ይችላል፤ ያም ቢሆን ይሖዋና ኢየሱስ ሁላችንም በዚህ ረገድ የምናደርገውን ጥረት በጣም ያደንቃሉ። (ሉቃስ 21:1-4ን እና 2 ቆሮንቶስ 8:12ን አንብብ።) በዕድሜ ከገፉ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መካከል አንዳንዶቹ በስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና ተሳትፎ ለማድረግ እንዲሁም በአገልግሎት አዘውትረው ለመካፈል ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ። ታዲያ እነዚህን ክርስቲያኖች እንደምናደንቃቸው ልንገልጽላቸውና ልናበረታታቸው አይገባም?

16. ሌሎችን ከማበረታታት ወደኋላ ማለት የሌለብን ለምንድን ነው?

16 ሌሎችን ለማበረታታት የሚያስችሏችሁን አጋጣሚዎች ፈልጉ። ወንድሞቻችንን እንድናደንቅ የሚያደርግ ነገር ካስተዋልን ይህን ከማድረግ ወደኋላ የምንልበት ምን ምክንያት አለ? ጳውሎስና በርናባስ፣ በጵስድያ በምትገኘው አንጾኪያ በነበሩበት ጊዜ ያጋጠማቸውን ነገር እንመልከት። በዚያ የነበረው ምኩራብ አለቆች “ወንድሞች ሆይ፣ ሕዝቡን የሚያበረታታ የምትናገሩት ቃል ካላችሁ ተናገሩ” አሏቸው። በምላሹም ጳውሎስ ግሩም ንግግር ሰጣቸው። (ሥራ 13:13-16, 42-44) እኛም ሌሎችን የሚያበረታታ ነገር መናገር የምንችል ከሆነ ለምን ዝም እንላለን? ሌሎችን የማበረታታት ልማድ ካለን እነሱም በምላሹ ያበረታቱናል።—ሉቃስ 6:38

17. የምንሰጠው ማበረታቻ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

17 መልካም ጎናቸውን ለይታችሁ በመጥቀስ ከልባችሁ አድንቁ። ማበረታቻና አድናቆት በራሱ ጠቃሚ ቢሆንም ኢየሱስ ለትያጥሮን ጉባኤ የላከው መልእክት እንደሚያሳየው አንድን ነገር ለይቶ በመጥቀስ ማመስገን ይበልጥ ውጤታማ ነው። (ራእይ 2:18, 19ን አንብብ።) ለምሳሌ ወላጆች፣ ልጆቻቸው መንፈሳዊ እድገት እያደረጉ እንደሆነ ያሳዩበትን አቅጣጫ ለይተው በመጥቀስ አድናቆታቸውን ሊገልጹላቸው ይችላሉ። አሊያም ደግሞ አንዲት ነጠላ እናት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩባትም ልጆቿን ለማሠልጠን ከምታደርገው ጥረት ጋር በተያያዘ የምናደንቀውን ነገር ልንነግራት እንችላለን። እንዲህ ያለው አድናቆትና ማበረታቻ ግሩም ውጤት ያስገኛል።

18, 19. ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸውን ማነጽ የምንችለው እንዴት ነው?

18 ሙሴ ኢያሱን እንዲያበረታታውና እንዲያደፋፍረው ይሖዋ ነግሮት ነበር፤ ይሁንና እኛ አንድን ሰው እንድናበረታታ ይነግረናል ብለን መጠበቅ የለብንም። ይሁንና የእምነት ባልንጀሮቻችንንም ሆነ ሌሎችን ስናበረታታ አምላክ ደስ ይለዋል። (ምሳሌ 19:17፤ ዕብ. 12:12) ለምሳሌ ያህል፣ የሕዝብ ንግግር ላቀረበው ወንድም ከንግግሩ ጠቃሚ ምክር እንዳገኘን ወይም አንድን ጥቅስ ያብራራበት መንገድ እንደነካን በመጥቀስ ልናመሰግነው እንችላለን። አንዲት እህት ጉባኤያቸው መጥቶ ንግግር ለሰጠ አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ጽፋለታለች፦ “ያወራነው ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ቢሆንም ልቤ ምን ያህል እንዳዘነ አስተውለህ አጽናንተኸኛል፤ እንዲሁም መንፈሴን አድሰህልኛል። ከመድረክም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የተናገርከው በደግነት የተሞላ ሐሳብ፣ የይሖዋ ስጦታ እንደሆነ ተሰምቶኛል።”

19 ጳውሎስ “አሁን እያደረጋችሁት እንዳለው እርስ በርስ ተበረታቱ እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ” በማለት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ከልባችን የምንጥር ከሆነ ሌሎችን በመንፈሳዊ ማነጽ የምንችልባቸው የተለያዩ መንገዶች ማግኘታችን አይቀርም። (1 ተሰ. 5:11) ሁላችንም ‘በየዕለቱ እርስ በርሳችን የምንበረታታ’ ከሆነ የይሖዋን ልብ እንደምናስደስት ጥርጥር የለውም።

^ [1] (አንቀጽ 1) አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።