“አንቺ ሴት።” ኢየሱስ ሴቶችን በዚህ መንገድ የጠራባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ለ18 ዓመታት ጎብጣ የኖረችን አንዲት ሴት በፈወሰበት ወቅት “አንቺ ሴት፣ ከበሽታሽ ተገላግለሻል” ብሏት ነበር። (ሉቃስ 13:10-13) ኢየሱስ ይህን አጠራር እናቱን ባነጋገረበት ጊዜም ጭምር ተጠቅሞበታል፤ በወቅቱ ይህ አጠራር አክብሮት የሚንጸባረቅበት ተደርጎ ይቆጠር ነበር። (ዮሐ. 19:26 አ.መ.ት፤ 20:13) በሌላ በኩል ደግሞ ከአክብሮት በተጨማሪ ሌላ ዓይነት ስሜትን የሚያንጸባርቅ አጠራር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል።

“ልጄ ሆይ።” መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንዳንድ ሴቶች ደግነትና ርኅራኄ በሚንጸባረቅባቸው በእነዚህ ቃላት እንደተጠሩ ይገልጻል። ኢየሱስ ለ12 ዓመታት ደም ይፈሳት የነበረችን ሴት ባነጋገረበት ወቅት በዚህ መንገድ ጠርቷታል። ይህች ሴት ወደ ኢየሱስ በቀረበችበት ጊዜ ያደረገችው ነገር የአምላክን ሕግ የሚጥስ ነበር፤ ምክንያቱም ሕጉ እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባት ሴት ርኩስ እንደሆነች ይገልጻል። አንዳንዶች ከነበረባት በሽታ አንጻር፣ ከሰው ጋር መቀላቀሏ ተገቢ እንዳልሆነ ይናገሩ ይሆናል። (ዘሌ. 15:19-27) ሆኖም ይህች ሴት እርዳታ ማግኘት በጣም ያስፈልጋት ነበር። “በርካታ ሐኪሞች ጋር የሄደች ሲሆን ሕክምናው ለብዙ ሥቃይ ዳርጓት ነበር፤ ያላትን ጥሪት ሁሉ ብትጨርስም ሕመሙ ባሰባት እንጂ አልተሻላትም።”—ማር. 5:25, 26

ይህች ሴት ቀስ ብላ በሕዝቡ መካከል በማለፍ ከኢየሱስ ኋላ መጥታ የልብሱን ዘርፍ ነካች። በዚህ ጊዜ፣ ይፈሳት የነበረው ደም ወዲያውኑ ቆመ! ሴትየዋ ማንም ሰው ሳያያት መሄድ እንደምትችል ተስፋ አድርጋ ነበር፤ ሆኖም ኢየሱስ “የነካኝ ማን ነው?” በማለት ጠየቀ። (ሉቃስ 8:45-47) ሴትየዋም እየፈራችና እየተንቀጠቀጠች መጥታ በኢየሱስ ፊት በመደፋት “ምንም ሳታስቀር እውነቱን ነገረችው።”—ማር. 5:33

ኢየሱስ፣ ሴትየዋን ለማረጋጋት ሲል በደግነት “ልጄ ሆይ አይዞሽ!” አላት። (ማቴ. 9:22) የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እንደሚናገሩት “ልጄ ሆይ” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት “ደግነትንና ርኅራኄን” ለመግለጽ ሊሠራባቸው ይችላል። በተጨማሪም ኢየሱስ “እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ፤ ከሚያሠቃይ ሕመምሽም ተፈወሽ” በማለት አጽናናት።—ማር. 5:34

ባለጸጋው እስራኤላዊ ቦዔዝም ሞዓባዊቷን ሩት የጠራት በዚህ መንገድ ነበር። ሩትም ብትሆን ከማታውቀው ሰው እርሻ ላይ ገብስ እየቃረመች በመሆኑ ፍርሃት ተሰምቷት መሆን አለበት። ቦዔዝ “ልጄ ሆይ፣ ስሚኝ” አላት። ከዚያም ከእሱ እርሻ መቃረሟን እንድትቀጥል አበረታታት። ሩትም በቦዔዝ ፊት በግንባሯ በመደፋት፣ እሷ የባዕድ አገር ሰው ሆና ሳለ እንዲህ ያለ ደግነት ያሳያት ለምን እንደሆነ ጠየቀችው። ቦዔዝም እንዲህ በማለት ተጨማሪ ማበረታቻ ሰጣት፦ “ለአማትሽ [ለመበለቷ ናኦሚ] ያደረግሽላትን ሁሉ . . . በሚገባ ሰምቻለሁ። ላደረግሽው ሁሉ ይሖዋ ብድራትሽን ይመልስልሽ።”—ሩት 2:8-12

ኢየሱስና ቦዔዝ፣ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሊከተሉት የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትተዋል! ለምሳሌ ያህል፣ ሁለት ሽማግሌዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ እርዳታና ማበረታቻ የሚያስፈልጋትን አንዲት ክርስቲያን ያነጋግሩ ይሆናል። ሽማግሌዎቹ በጸሎት የይሖዋን አመራር ከጠየቁና እህት የምትናገረውን ነገር በጥሞና ካዳመጡ በኋላ በአምላክ ቃል ላይ ተመሥርተው ማበረታቻና ማጽናኛ ሊሰጧት ይችላሉ።—ሮም 15:4