በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በደንብ አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

ኢየሱስ በማቴዎስ 18:15-17 ላይ የሚገኘውን ምክር የሰጠው ከምን ዓይነት ኃጢአት ጋር በተያያዘ ነው?

ኢየሱስ፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ሰዎች ተወያይተው ሊፈቱት ስለሚችሉ፣ ይህ ካልሆነ ግን ለውገዳ ስለሚያበቃ ከባድ በደል እየተናገረ ነበር። እንዲህ ያለው በደል፣ የአንድን ሰው ስም ሆን ብሎ ከማጥፋት ወይም ከማጭበርበር ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።—w16.05 ገጽ 7

ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ የበለጠ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ ትችላለህ?

የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ፦ ለመማር ዝግጁ ሆነህ አንብብ፤ ተግባራዊ ልታደርጋቸው የምትችላቸውን ትምህርቶች ለማግኘት ጥረት አድርግ። ‘ይህን ሐሳብ ሌሎችን ለመርዳት ልጠቀምበት የምችለው እንዴት ነው?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን ራስህን ጠይቅ። ባነበብከው ነገር ላይ ምርምር ለማድረግ ባሉን የምርምር መሣሪያዎች ተጠቀም።—w16.05 ከገጽ 24-26

አንድ ክርስቲያን የትንሣኤ ተስፋ እንዳለ ቢያምንም የሚወደውን ሰው በሞት ሲያጣ ቢያዝን ስህተት ነው?

አንድ ክርስቲያን በትንሣኤ ተስፋ ማመኑ፣ የሚወደውን ሰው በሞት ሲያጣ እንዳያዝን አያደርገውም። አብርሃም፣ ሣራ ስትሞት አዝኗል። (ዘፍ. 23:2) በጊዜ ሂደት ሐዘኑ እየቀለለ ይመጣል።—wp16.3 ገጽ 4

በሕዝቅኤል ምዕራፍ 9 ላይ የተጠቀሰው የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘ ሰው እንዲሁም መሣሪያ የያዙት ስድስት ሰዎች ማንን ያመለክታሉ?

ኢየሩሳሌምን በማጥፋቱ ሥራ የተካፈለውንና ወደፊትም በአርማጌዶን ወቅት ጥፋት የሚያመጣውን በሰማይ ያለ ሠራዊት ያመለክታሉ። በዘመናችን፣ የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው የሚያመለክተው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፤ ከጥፋቱ በሚተርፉ ሰዎች ላይ ምልክት የሚያደርግባቸው እሱ ነው።—w16.06 ከገጽ 16-17

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ዓይነት ፈተናዎችን አልፏል?

መጽሐፍ ቅዱስ ካጋጠሙት ፈተናዎች መካከል (1) እንደ ፓፒረስና ብራና ባሉት ሊበላሹ በሚችሉ ነገሮች ላይ መጻፉ፣ (2) የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች መጽሐፉን ለማጥፋት ሙከራ ማድረጋቸው፣ (3) አንዳንዶች መልእክቱን ለመቀየር መሞከራቸው ይገኙበታል።—wp16.4 ከገጽ 4-7

ክርስቲያኖች ኑሯቸውን ማቅለል የሚችሉት እንዴት ነው?

የሚያስፈልጓችሁን ነገሮች ብቻ ለዩ፤ አላስፈላጊ ወጪዎችን ቀንሱ። አቅማችሁን ያገናዘበ ባጀት አውጡ። የማትጠቀሙባቸውን ዕቃዎች አስወግዱ፤ ያለባችሁን ዕዳ ሁሉ ክፈሉ። ሰብዓዊ ሥራ የምትሠሩበትን ሰዓት ቀንሱ፤ አገልግሎታችሁን ለማስፋት ዕቅድ አውጡ።—w16.07 ገጽ 10

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ከወርቅ ወይም ከብር የበለጠ ዋጋ ያለው ነገር ምንድን ነው?

ኢዮብ 28:12, 15 እንደሚገልጸው መለኮታዊ ጥበብ ከወርቅም ሆነ ከብር የላቀ ዋጋ አለው። ይህን ጥበብ ለማግኘት ስትጥር ምንጊዜም ትሑት መሆንና ጠንካራ እምነት መያዝ ይኖርብሃል።—w16.08 ከገጽ 18-19

በዛሬው ጊዜ አንድ ወንድም ጢሙን ቢያሳድግ ተገቢ ነው?

በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ፣ አንድ ወንድም ጢሙን ሥርዓታማ በሆነ መንገድ እስከተከረከመ ድረስ ጢሙን ማሳደጉ ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል፤ እንዲህ ማድረጉ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንዳይቀበሉ እንቅፋት አይፈጥርም። ያም ቢሆን አንዳንድ ወንድሞች ጢማቸውን ላለማሳደግ ይወስኑ ይሆናል። (1 ቆሮ. 8:9) በሌሎች ባሕሎች ወይም አካባቢዎች ደግሞ ክርስቲያን አገልጋዮች ጢማቸውን ማሳደጋቸው በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የለውም።—w16.09 ገጽ 21

ስለ ዳዊትና ጎልያድ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እውነት መሆኑን መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

የጎልያድ ቁመት፣ በዘመናችን የዓለማችን ረጅም ሰው ተብሎ በታሪክ መዝገብ ከሰፈረው ሰው ቁመት የሚበልጠው በ15 ሳንቲ ሜትር ብቻ ነው። ስለ ዳዊት ቤት የሚናገሩ ጥንታዊ ጽሑፎች መገኘታቸው እንዲሁም ኢየሱስ የተናገረው ነገር፣ ዳዊት በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን ያረጋግጣሉ። ዘገባው ላይ የተጠቀሱት ቦታዎችም በእውን ያሉ ቦታዎች ናቸው።—wp16.5 ገጽ 13

በእውቀት፣ በማስተዋልና በጥበብ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

አንድ ሰው እውቀት አለው የሚባለው መረጃዎች ሲኖሩት ነው። ማስተዋል ያለው ሰው ደግሞ አንዱ መረጃ ከሌላው መረጃ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ይገነዘባል። ጥበብ ያለው ሰው ግን እውቀትንና ማስተዋልን አንድ ላይ አቀናጅቶ፣ ማመዛዘን የታከለበት እርምጃ ይወስዳል።—w16.10 ገጽ 18