በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ቁጥር 4 2016

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ኢየሱስ የሥጋ ደዌ ሕሙማንን የያዘበት መንገድ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው?

የጥንቶቹ አይሁዳውያን በወቅቱ በነበረው የሥጋ ደዌ እንዳይያዙ ይፈሩ ነበር። አስፈሪ የሆነው ይህ ተላላፊ በሽታ የታማሚውን የነርቭ ጫፎች በማጥቃት ዘላቂ ጉዳትና የመልክ መበላሸት ያስከትል ነበር። በወቅቱ የሥጋ ደዌ መድኃኒት አልነበረውም። ከዚህ ይልቅ በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ከሰዎች ተገልለው እንዲኖሩ የሚደረግ ከመሆኑም ሌላ ይህ በሽታ እንዳለባቸው ለሌሎች የማሳወቅ ግዴታ ነበረባቸው።—ዘሌዋውያን 13:45, 46

የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ስለ ሥጋ ደዌ ከተገለጹት ውጭ ሌሎች ሕጎችን ያወጡ ሲሆን ይህም የሕመምተኞቹ ሕይወት ከባድ እንዲሆን አድርጎ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ረቢዎቹ ያወጡት ደንብ ማንኛውም ሰው የሥጋ ደዌ ካለበት ሰው ቢያንስ 2 ሜትር መራቅ እንዳለበት ይገልጽ ነበር። ነፋስ እየነፈሰ ከሆነ ደግሞ ርቀቱ 45 ሜትር መሆን እንዳለበት ያዛል። አንዳንድ የታልሙድ ሕግ ተንታኞች የሥጋ ደዌ ሕሙማን “ከሰፈሩ ውጭ” እንዲኖሩ የሚገልጸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ድንጋጌ መሠረት አድርገው የሥጋ ደዌ ሕመምተኞች በግንብ ከታጠሩ ከተሞች ውጭ መኖር እንዳለባቸው ይገልጹ ነበር። በዚህ ምክንያት አንድ ረቢ የሥጋ ደዌ ያለበት ሰው ከተማው ውስጥ ቢያገኝ ድንጋይ ይወረውርበትና “ወደ መኖሪያህ ተመለስ፤ ሌሎች ሰዎችን አታርክስ” ይለው ነበር።

በዚህ ረገድ ኢየሱስ ምንኛ የተለየ ነበር! የሥጋ ደዌ ሕሙማንን ከማባረር ይልቅ ይዳስሳቸው አልፎ ተርፎም ይፈውሳቸው ነበር።—ማቴዎስ 8:3

የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ፍቺን የሚፈቅዱት በምን ምክንያት ነበር?

የፍቺ ወረቀት፣ 71/72 ዓ.ም.

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. በነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ዘንድ ፍቺ አከራካሪ ጉዳይ ነበር። በመሆኑም በአንድ ወቅት አንዳንድ ፈሪሳውያን ኢየሱስን ለመፈተን “አንድ ሰው በማንኛውም ምክንያት ሚስቱን እንዲፈታ ሕግ ይፈቅድለታል?” ሲሉ ጠይቀውት ነበር።—ማቴዎስ 19:3

የሙሴ ሕግ አንድ ሰው “ነውር የሆነ ነገር” ካገኘባት ሚስቱን ሊፈታት እንደሚችል ይገልጽ ነበር። (ዘዳግም 24:1) በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ረቢዎች የዚህን ሕግ አተረጓጎም በተመለከተ ሁለት ተቃራኒ አመለካከት ነበራቸው። ሻምማይ ተብሎ የሚጠራው በጣም ጥብቅ አመለካከት የነበረው ቡድን ከዚህ ሕግ በመነሳት ለፍቺ መሠረት የሚሆነው ብቸኛው ምክንያት “ንጽሕናን ማጉደል” ማለትም ምንዝር መፈጸም እንደሆነ ያምን ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ሂለል የተባለው ቡድን አባላት አንድ ሰው ከሚስቱ ጋር የገጠመው አለመስማማት በጣም ቀላል ቢሆንም እንኳ እሷን ለመፍታት ሕጉ እንደሚፈቅድለት ያምናሉ። በመሆኑም አንድ ሰው ሚስቱ ያዘጋጀችለት ራት ካልጣፈጠው ወይም ከእሷ የበለጠ ውብ የሆነች ሴት ካገኘ ሚስቱን ሊፈታት ይችላል።

ታዲያ ኢየሱስ ፈሪሳውያኑ ላቀረቡለት ጥያቄ ምን መልስ ሰጠ? “በፆታ ብልግና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል” የሚል ግልጽ መልስ ሰጠ።—ማቴዎስ 19:6, 9