በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ ምን ፈተናዎችን አልፏል?

ልናውቀው የሚገባ ታሪክ

ልናውቀው የሚገባ ታሪክ

መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች ሃይማኖታዊ ጽሑፎች የተለየ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል የብዙ የሰዎችን እምነት ለረጅም ጊዜ ሲቀርጽ የኖረ መጽሐፍ የለም። በሌላ በኩል ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ብዙ ትችት የተሰነዘረበት መጽሐፍ የለም።

ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ምሁራን በዘመናችን ያሉት መጽሐፍ ቅዱሶች ከመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች በትክክል የተገለበጡ መሆናቸውን ይጠራጠራሉ። አንድ የሃይማኖታዊ ጥናቶች ፕሮፌሰር እንዲህ ብለዋል፦ “አሁን ያሉን ቅጂዎች ከመጀመሪያው ጽሑፍ ጋር አንድ መሆናቸውን እርግጠኛ መሆን አንችልም። በእጃችን ያሉት ቅጂዎች በስህተት የተሞሉ ናቸው፤ እንዲሁም ከእነዚህ ቅጂዎች ውስጥ አብዛኞቹ የተጻፉት የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ከተዘጋጁ ከዘመናት በኋላ ከመሆኑም ሌላ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በሁለቱ መካከል በሺዎች የሚቆጠሩ ልዩነቶች አሉ።”

ሌሎች ደግሞ በሃይማኖታቸው የተነሳ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት ይጠራጠራሉ። ለምሳሌ ክርስቲያን ያልሆነ ቤተሰብ ውስጥ ያደገው ፋይዘል መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቅዱስ ቢሆንም እንደተለወጠ ተምሯል። “በዚህም የተነሳ ሰዎች ከእኔ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መነጋገር ሲፈልጉ የማነጋግራቸው በጥርጣሬ መንፈስ ነው። ምክንያቱም የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ የላቸውም። የያዙት የተለወጠውን መጽሐፍ ነው!” በማለት ተናግሯል።

መጽሐፍ ቅዱስ የተለወጠ መሆን አለመሆኑ ለውጥ ያመጣል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው፦ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚገልጻቸው የሚያጽናኑ ተስፋዎች በመጀመሪያው ጽሑፍ ውስጥ መኖራቸውን እርግጠኛ መሆን ካልቻልክ ልትተማመንባቸው ትችላለህ? (ሮም 15:4) በዘመናችን ያሉት መጽሐፍ ቅዱሶች በሰዎች የተጻፉ የተሳሳቱ ቅጂዎች ከሆኑ ከሥራ፣ ከቤተሰብ ወይም ከአምልኮ ጋር የተያያዙ ከባድ ውሳኔዎችን ለማድረግ በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ትጠቀማለህ?

የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች በአሁኑ ጊዜ ባይገኙም በእጅ የተገለበጡትን ጨምሮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ጥንታዊ ቅጂዎችን ማግኘት እንችላለን። እነዚህ ጥንታዊ ቅጂዎች በዘመናት ብዛት በስብሰው ከመጥፋት የተረፉት እንዲሁም የደረሰባቸውን ተቃውሞና የያዙትን መልእክት ለመቀየር የተደረጉ ሙከራዎችን የተቋቋሙት እንዴት ነው? እነዚህን ፈተናዎች ተቋቁመው ማለፋቸው አሁን በእጅህ የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ መሆኑን እርግጠኛ እንድትሆን የሚረዳህ እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ፈተናዎችን እንዴት እንዳለፈ የሚገልጹትን ርዕሶች እንድታነብ እንጋብዝሃለን።