መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ መሰናክሎችን ማለፍ ችሏል። በዚህም የተነሳ አንተም ይህን መጽሐፍ ማግኘትና ማንበብ ትችላለህ። ደግሞም ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ከመረጥክ እያነበብክ ያለኸው በመጀመሪያው ጽሑፍ ላይ የነበረውን ሐሳብ እንደሆነ መተማመን ትችላለህ። * ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ሳይበሰብስ የቆየው፣ ኃይለኛ ተቃውሞ የተቋቋመውና መልእክቱን ለመለወጥ ሆን ተብሎ የተደረገውን ጥረት ማለፍ የቻለው ለምንድን ነው? መጽሐፉን ልዩ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው?

“አሁን፣ በእጄ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተገኘ ስጦታ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ”

ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሐዋርያው ጳውሎስ “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው” በማለት ከጻፈው ሐሳብ ጋር ይስማማሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ መሰናክሎችን ሊያልፍ የቻለው የአምላክ ቃል ስለሆነና አምላክ ጥበቃ ስላደረገለት እንደሆነ ያምናሉ። በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው ፋይዘል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሰማቸው ነገሮች እውነት መሆናቸውን በራሱ ለማረጋገጥ ሲል ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ለመመርመር ወሰነ። ምርምር ሲያደርግ ያገኘው ነገር አስገረመው። ብዙም ሳይቆይ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ተስፋፍተው የሚገኙት አብዛኞቹ ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሌሉ ተገነዘበ። ከዚህም በላይ አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ በቃሉ ውስጥ ሲያነብ ልቡ ተነካ።

“አሁን፣ በእጄ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተገኘ ስጦታ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ” ይላል። “ደግሞስ አጽናፈ ዓለምን መፍጠር የቻለ አምላክ፣ የምንመራበት መጽሐፍ የመስጠትና ይህን መጽሐፍ የመጠበቅ ኃይል አይኖረውም? ይህ ካልሆነ ደግሞ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ኃይል ገደብ አለው እያልኩ ነው! ለመሆኑ እኔ ማን ሆኜ ነው እንዲህ የምለው?”—ኢሳይያስ 40:8

^ አን.3 በግንቦት 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።