ዲያብሎስ ማን ወይም ምንድን ነው?

ምን ትላለህ? ዲያብሎስ . . .

  • መንፈሳዊ አካል ነው?

  • በሰዎች ውስጥ ያለ ክፋት ነው?

  • ሰዎች በምናባቸው የፈጠሩት ነገር ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ዲያብሎስ ኢየሱስን አነጋግሮታል፤ እንዲሁም ‘ፈትኖታል።’ (ማቴዎስ 4:1-4) ስለዚህ ዲያብሎስ በምናብ የተፈጠረ ነገር ወይም የክፋት ሐሳብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ክፉ የሆነ መንፈሳዊ አካል ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ሌላስ ነገር አለ?

  • በመጀመሪያ ዲያብሎስ ቅዱስ መልአክ ነበረ፤ ነገር ግን “በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም።” (ዮሐንስ 8:44) ሐሰተኛ ከመሆኑም ሌላ በአምላክ ላይ ዓመፀ።

  • ሌሎች መላእክትም ከሰይጣን ጋር በመተባበር በአምላክ ላይ ዓመፁ።—ራእይ 12:9

  • ዲያብሎስ፣ ስለ እሱ መኖር እንዳያውቁ ብዙዎችን አሳውሯል።—2 ቆሮንቶስ 4:4

ዲያብሎስ ሰዎችን መቆጣጠር ይችላል?

አንዳንዶች ምን ይላሉ? ‘ዲያብሎስ ሰዎችን ይቆጣጠራል’ የሚባለው ነገር ማታለያ እንደሆነ የሚሰማቸው አሉ፤ ሌሎች ደግሞ ክፉ መናፍስት እንዳይቆጣጠሯቸው በጣም ይፈራሉ። አንተ ምን ይመስልሃል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው።” (1 ዮሐንስ 5:19) ዲያብሎስ በሰው ዘር ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር ቢሆንም እያንዳንዱን ሰው ይቆጣጠራል ማለት ግን አይደለም።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ሌላስ ነገር አለ?

  • ዲያብሎስ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ለማሳደር ሲል ማታለያዎችን ይጠቀማል።—2 ቆሮንቶስ 11:14

  • ክፉ መናፍስት አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን ይቆጣጠራሉ።—ማቴዎስ 12:22

  • በአምላክ እርዳታ፣ ዲያብሎስን ‘መቃወም’ ትችላለህ።—ያዕቆብ 4:7