በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ቁጥር 5 2016

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ማጽናኛ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው?

ችግር ሲያጋጥመን ማጽናኛ ማግኘት

ችግር ሲያጋጥመን ማጽናኛ ማግኘት

ችግርና መከራ በተለያየ መልኩ ያጋጥመናል። እርግጥ ስለ ሁሉም ዓይነት ችግር እያነሳን መወያየት አንችልም፤ ሆኖም ቀደም ሲል የጠቀስናቸውን አራት ምሳሌዎች አንድ በአንድ እንመልከት። የተለያየ ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች ከአምላክ እውነተኛ መጽናኛ ያገኙት እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር።

ከሥራ መባረር

“ያገኘሁትን ማንኛውንም ሥራ ሳልመርጥ መሥራትን የተማርኩ ሲሆን በጣም አስፈላጊ ላልሆኑ ነገሮች የምናወጣውን ወጪ ቀነስን።”—ጆናታን

ሴት የተባለ አንድ ከሥራ የተባረረ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ ከሥራ የተባረርነው በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ነው። * ለሁለት ዓመታት ያህል የኖርነው ቤተሰብ በሚያደርግልን እርዳታና አንዳንድ ተባራሪ ሥራዎችን እየሠራን ነበር። በዚህም የተነሳ ባለቤቴ ፕሪሲላ የመንፈስ ጭንቀት ያዛት፤ እኔም ዋጋ ቢስ እንደሆንኩ ተሰማኝ።

“ሁኔታውን ለመቋቋም የረዱን ነገሮች አሉ። ፕሪሲላ፣ ኢየሱስ በማቴዎስ 6:34 ላይ የተናገረውን ሐሳብ ዘወትር ታስታውስ ነበር። ኢየሱስ እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች ስላሉት ስለ ነገ መጨነቅ እንደሌለብን ተናግሯል። በተጨማሪም ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረቧ በጽናት ለመቀጠል የሚያስችል ብርታት ሰጥቷታል። እኔን ያጽናናኝ ደግሞ መዝሙር 55:22 ነው። እንደ መዝሙራዊው ሁሉ እኔም ሸክሜን በይሖዋ ላይ ጣልኩ፤ እሱም ደግፎኛል። አሁን ሥራ ያለኝ ቢሆንም ኢየሱስ በማቴዎስ 6:20-22 ላይ ከተናገረው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መንገድ ኑሯችንን ቀላል አድርገናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከአምላክ ጋርም ሆነ እርስ በርሳችን ይበልጥ ተቀራርበናል።”

ጆናታን ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “አነስተኛ በሆነው የቤተሰባችን ንግድ ላይ ኪሳራ ሲደርስ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ፍርሃት አድሮብኝ ነበር። የኢኮኖሚው ቀውስ የ20 ዓመት ልፋታችንን መና አስቀርቶታል። ከባለቤቴ ጋር ስለ ገንዘብ መጨቃጨቅ ጀመርን። ክሬዲት ካርዳችን ተቀባይነት አያገኝም ብለን ስለፈራን በክሬዲት ካርዳችን እንኳ መግዛት አልቻልንም።

“ይሁን እንጂ አምላክ በቃሉና በመንፈሱ አማካኝነት ጥሩ ውሳኔዎች እንድናደርግ ረድቶናል። ያገኘሁትን ማንኛውንም ሥራ ሳልመርጥ መሥራትን የተማርኩ ሲሆን በጣም አስፈላጊ ላልሆኑ ነገሮች የምናወጣውን ወጪ ቀነስን። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን የእምነት አጋሮቻችን ድጋፍ አልተለየንም። ለራሳችን ያለንን ግምት እንዳናጣ የረዱን ሲሆን ሁኔታው በጣም ከባድ በሚሆንብን ጊዜ ደግሞ የእርዳታ እጃቸውን ዘርግተውልናል።”

 የትዳር መፍረስ

ራኬል እንዲህ ብላለች፦ “ባሌ በድንገት ጥሎኝ ሲሄድ ስሜቴ በጣም ተጎድቶና ተናድጄ ነበር። በከባድ ሐዘንም ተዋጥኩ። ይሁን እንጂ ወደ አምላክ ቀረብኩ፤ እሱም አጽናንቶኛል። በየዕለቱ ወደ እሱ እጸልይ ስለነበር የአምላክ ሰላም ልቤን ጠብቆልኛል። የተሰበረውን ልቤን እንደጠገነልኝ ተሰምቶኛል።

“ደግሞም ለቃሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ ምስጋና ይግባውና ያደረብኝን ንዴትና ቂም ማሸነፍ ችያለሁ። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም 12:21 ላይ ‘በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ’ በማለት የተናገረውን ሐሳብ ተግባራዊ አደረኩ።

“‘ጠፍቷል ብሎ ለመተውም ጊዜ አለው።’ . . . አሁን አዳዲስ ግቦች አውጥቼ ትኩረቴን በዚያ ላይ አድርጌያለሁ።”—ራኬል

“አንድ አስተዋይ ጓደኛዬ የሰጠኝ ምክር ያለፈውን በመርሳት ወደ ፊት እንድቀጥል ረድቶኛል። መክብብ 3:6 ላይ ያለውን ‘ጠፍቷል ብሎ ለመተውም ጊዜ አለው’ የሚለውን ጥቅስ አሳየኝ። ምክሩ ጠንከር ያለ ቢሆንም በወቅቱ የሚያስፈልገኝ ይህ ነበር። አሁን አዳዲስ ግቦች አውጥቼ ትኩረቴን በዚያ ላይ አድርጌያለሁ።”

ኤልዛቤት እንዲህ ብላለች፦ “ትዳራችሁ ሲፈርስ ድጋፍ ማግኘት ያስፈልጋችኋል። ምንጊዜም ድጋፍ የምታደርግልኝ የምወዳት ጓደኛ አለችኝ። አብራኝ ታለቅስና ታጽናናኝ ነበር፤ እንደማልፈለግ ሳይሆን ተወዳጅ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ታደርግ ነበር። ይሖዋ የውስጤ ቁስል እንዲሽር ለመርዳት በእሷ እንደተጠቀመ ይሰማኛል።”

ሕመም ወይም እርጅና

“ከጸለይኩ በኋላ የአምላክ መንፈስ ብርታት ሲሰጠኝ ይሰማኛል።”—ሉዊስ

በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ሉዊስ ከባድ የልብ ሕመም ስላለባቸው ከአንዴም ሁለቴ ሞት አፋፍ ደርሰው ነበር። አሁን በየቀኑ ለ16 ሰዓታት ኦክሲጂን ይሰጣቸዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “ዘወትር ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። ከጸለይኩ በኋላ የአምላክ መንፈስ ብርታት ሲሰጠኝ ይሰማኛል። ጸሎት በጽናት ለመቀጠል የሚያስፈልገኝን ድፍረት ይሰጠኛል፤ ምክንያቱም በይሖዋ ላይ እምነት አለኝ፤ እንዲሁም እንደሚያስብልኝ አውቃለሁ።”

በ80ዎቹ ዓመታት ውስጥ የሚገኙት ፔትራ ደግሞ እንዲህ ብለዋል፦ “መሥራት የምፈልጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤ ግን ምን ያደርጋል አቅም የለኝም። ጉልበቴ እየደከመ መሄዱን አምኖ መቀበል በጣም ከብዶኛል። በጣም ይደክመኛል፣ እንዲሁም ያለ መድኃኒት መኖር አልችልም። ብዙ ጊዜ የማስበው፣ ኢየሱስ የሚቻል ከሆነ ሊደርስበት የነበረው መከራ እንዲያልፍለት አባቱን የተማጸነበትን መንገድ ነው። ይሖዋ በዚህ ወቅት ለኢየሱስ ብርታት ሰጥቶታል፤ እኔንም ያበረታኛል። በየዕለቱ የማቀርበው  ጸሎት እንደ መድኃኒት ሆኖልኛል። ወደ አምላክ ከጸለይኩ በኋላ ቀለል ይልልኛል።”—ማቴዎስ 26:39

ወደ 30 ለሚጠጉ ዓመታት መልቲፕል ስክለሮሲስ ከሚባል የነርቭ በሽታ ጋር ሲታገል የኖረው ሁሊያንም እንደዚሁ ይሰማዋል። እንዲህ ብሏል፦ “በቢሮ ወንበር ፋንታ የአካል ጉዳተኞች ወንበር መጠቀም ጀምሬያለሁ። ይሁን እንጂ ሕይወቴን ሌሎችን ለማገልገል ስለምጠቀምበት ዋጋ እንዳለኝ ይሰማኛል። ሌሎችን መርዳት ሥቃይን የሚያስታግስ ሲሆን ይሖዋም በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ እንደሚያበረታን የገባውን ቃል ይፈጽማል። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ እኔም ‘ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ’ ብዬ ከልቤ መናገር እችላለሁ።”—ፊልጵስዩስ 4:13

የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት

አንቶኒዮ እንዲህ ብሏል፦ “አባቴ በመኪና አደጋ በሞተ ጊዜ መጀመሪያ ላይ ማመን አቅቶኝ ነበር። አባቴ ምንም ያጠፋው ነገር አልነበረም፤ የተገጨው በእግረኞች መንገድ ላይ እየሄደ ሳለ ነው። ይሁን እንጂ ምንም ማድረግ አልቻልኩም። አባቴ ሕይወቱ ከማለፉ በፊት ለአምስት ቀናት ራሱን እንደሳተ ቆይቷል። በእናቴ ፊት ላለማልቀስ እንደምንም ብዬ ራሴን እቆጣጠር ነበር፤ ብቻዬን ስሆን ግን ስቅስቅ ብዬ አለቅሳለሁ። ‘ለምን? ለምን?’ እያልኩ ራሴን በተደጋጋሚ እጠይቅ ነበር።

“በእነዚያ እጅግ አሳዛኝ ቀናት ስሜቴን ለመቆጣጠር እንዲረዳኝና ሰላም እንዲሰጠኝ ዘወትር ይሖዋን እለምነው ነበር። ደግሞም ቀስ በቀስ እየተረጋጋሁ መጣሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም ‘ያልተጠበቁ ክስተቶች’ ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ የሚናገር መሆኑን አስታወስኩ። አምላክ ስለማይዋሽ አባቴን ዳግመኛ በትንሣኤ እንደማገኘው እርግጠኛ ነኝ።”—መክብብ 9:11፤ ዮሐንስ 11:25፤ ቲቶ 1:2

“የአውሮፕላን አደጋው የልጃችንን ሕይወት ቢቀጥፍም ከልጃችን ጋር ያሳለፍናቸው አስደሳች ጊዜያት አሁንም ከአእምሯችን አልጠፉም።”—ሮበርት

በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ሮበርትም ይህን ሐሳብ ይጋራል። እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የተጠቀሰውን የአእምሮ ሰላም አግኝተናል። ይህን ያገኘነው ለይሖዋ በመጸለያችን ነው። እንዲህ ያለው ውስጣዊ ሰላም ስለ ትንሣኤ ተስፋ ለዜና ዘጋቢዎች በተረጋጋ መንገድ ለመናገር አስችሎናል። የአውሮፕላን አደጋው የልጃችንን ሕይወት ቢቀጥፍም ከልጃችን ጋር ያሳለፍናቸው አስደሳች ጊዜያት አሁንም ከአእምሯችን አልጠፉም። በዚህ ላይ ለማተኮር ጥረት እናደርጋለን።

“የእምነት አጋሮቻችን ስለ እምነታችን ተረጋግተን ስንናገር በቴሌቪዥን እንዳዩን ሲነግሩን ይህን ማድረግ የቻልነው በእነሱ ጸሎት እንደሆነ ገልጸንላቸዋል። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የላኳቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሚያጽናኑ መልእክቶች ይሖዋ በእነሱ አማካኝነት እየደገፈን እንደሆነ እንዳምን አድርገውኛል።”

ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች አምላክ የተለያዩ ችግሮችና ተፈታታኝ ሁኔታዎች ላጋጠሟቸው ሰዎች መጽናኛ መስጠት እንደሚችል ያሳያሉ። አንተንስ ሊያጽናናህ ይችላል? በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠመህ መከራ ምንም ሆነ ምን፣ አንተም በመከራህ ወቅት መጽናኛ ማግኘት ትችላለህ። * ታዲያ ይሖዋ እንዲረዳህ ለምን በጸሎት አትጠይቀውም? እሱ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ነው።—2 ቆሮንቶስ 1:3

^ አን.5 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.23 ወደ አምላክ ለመቅረብና እሱ የሚሰጠውን መጽናኛ ለማግኘት የምትፈልግ ከሆነ በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ማነጋገር ወይም በአቅራቢያህ ወዳለው ቅርንጫፍ ቢሮ መጻፍ ትችላለህ።