ትንሽ ልጅ እያለህ የወደቅክበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? ምናልባት እጅህ ቆስሎ ወይም ጉልበትህ ተላልጦ ይሆናል። እናትህ እንዴት እንዳባበለችህ ወይም እንዳጽናናችህ ትዝ ይልሃል? ምናልባት ቁስሉን ጠራርጋ በፋሻ አስራልህ ይሆናል። ብታለቅስም እናትህ እቅፍ አድርጋ በሚያጽናኑ ቃላት ስታባብልህ ሕመምህን ወዲያውኑ ረስተኸው ይሆናል። በዚያ ዕድሜ ላይ በቀላሉ መጽናናት ይቻላል።

ይሁን እንጂ እያደግን ስንሄድ ሕይወት ይበልጥ እየተወሳሰበ ይሄዳል። የሚያጋጥሙን ችግሮች ከባድ ስለሚሆኑ በቀላሉ መጽናናት አንችልም። የሚያሳዝነው ነገር የትልልቅ ሰዎች ችግር ፋሻ በማሰር ወይም እናት በምትሰጠው ፍቅር የሚፈታ አይደለም። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።

  • ከሥራ ተባረህ ታውቃለህ? ከሆነ በዚህ ምክንያት የተሰማህን ድንጋጤ መቼም ቢሆን አትረሳው ይሆናል። ሁሊያን ከሥራ መባረሩን በሰማ ጊዜ በጣም ደንግጦ እንደነበር ይናገራል። ‘ቤተሰቤን የማስተዳድረው እንዴት ነው? ድርጅቱ፣ ብዙ ዓመት ከለፋሁለት በኋላ እንዴት እንደማይረባ ነገር አውጥቶ ይጥለኛል?’ የሚሉት ጥያቄዎች አስጨንቀውት ነበር።

  • ወይም ትዳርህ በመፍረሱ በጣም ደንግጠህ ይሆናል። ራኬል እንዲህ ብላለች፦ “ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ባሌ በድንገት ጥሎኝ ሄደ፤ በዚህ ወቅት በከፍተኛ ሐዘን ተዋጥኩ። ልቤ በሐዘን ተሰበረ። ሐዘኑ ያስከተለብኝ ስሜታዊ ብቻ ሳይሆን አካላዊ ሥቃይም ጭምር ነበር። ፍርሃት ለቀቀብኝ።”

  • ወይም ደግሞ ምንም መሻሻል የማያሳይ ከባድ የጤና ችግር ይኖርብህ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ፣ “ሕይወቴን ተጸየፍኳት፤ በሕይወት መቀጠል አልፈልግም” በማለት እንደተናገረው እንደ ታማኙ ኢዮብ ይሰማህ ይሆናል። (ኢዮብ 7:16) ምናልባት አንተም “አንዳንድ ጊዜ፣ ሞቴን ቁጭ ብዬ እየጠበቅሁ እንዳለሁ ይሰማኛል” በማለት እንደተናገሩት በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እንዳሉት እንደ ሉዊስ ይሰማህ ይሆናል።

  • አሊያም ደግሞ የምትወደውን የቤተሰብህን አባል በሞት በማጣትህ መጽናኛ ማግኘት አስፈልጎህ ይሆናል። ሮበርት እንዲህ ብሏል፦ “ልጄ በሚያሳዝን ሁኔታ በአውሮፕላን አደጋ ሲሞት መጀመሪያ ላይ መቀበል ከብዶኝ ነበር። ከዚያም ሐዘኑ ይሰማኝ ጀመር፤ ስሜቱ መጽሐፍ ቅዱስ ማርያም የሚሰማትን ስሜት አስመልክቶ ‘በአንቺም ውስጥ ትልቅ ሰይፍ ያልፋል’ በማለት ከገለጸው ጋር ይመሳሰላል።”—ሉቃስ 2:35

ሮበርት፣ ሉዊስ፣ ራኬልና ሁሊያን የደረሰባቸው ነገር እጅግ አሳዛኝ ቢሆንም መጽናናት ችለዋል። ከማንም በላይ መጽናኛ መስጠት ከሚችለው ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ መጽናኛ አግኝተዋል። ታዲያ አምላክ መጽናኛ የሚሰጠው እንዴት ነው? ለአንተስ የሚያስፈልግህን መጽናኛ ይሰጥህ ይሆን?