በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ቁጥር 4 2017

ይሖዋ የተባለው የአምላክ ቅዱስ ስም የተጻፈባቸው አራት የዕብራይስጥ ፊደላት፤ የሚነበቡት ከቀኝ ወደ ግራ ነው

አነስተኛዋ የዕብራይስጥ ፊደል ምን ታረጋግጣለች?

አነስተኛዋ የዕብራይስጥ ፊደል ምን ታረጋግጣለች?

አምላክ የገባቸው ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ እርግጠኛ ነበር፤ ያስተማረውም ትምህርት አድማጮቹ እንዲህ ያለ እምነት እንዲያድርባቸው አድርጓል። የተራራውን ስብከት በሰጠበት ወቅት የተናገረው ምሳሌ በማቴዎስ 5:18 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይና ምድር ቢያልፉ እንኳ እነዚህ ሁሉ ነገሮች እስኪከናወኑ ድረስ ከሕጉ አንዲት [አነስተኛዋ] ፊደል ወይም የአንዷ ፊደል ጭረት ሳትፈጸም አትቀርም።”

በጣም አነስተኛዋ የዕብራይስጥ ፊደል י (ዮድ) ስትሆን ይሖዋ የተባለው የአምላክ ቅዱስ ስም ከተጻፈባቸው አራት የዕብራይስጥ ፊደላት መካከል የመጀመሪያዋ ናት። * ጸሐፍትና ፈሪሳውያን የአምላክ ሕግ ከተጻፈባቸው ቃላትና ፊደሎች በተጨማሪ እያንዳንዷ ‘የፊደል ጭረት’ ትልቅ ትርጉም እንዳላት አድርገው ያስቡ ነበር።

ኢየሱስ በሕጉ ላይ የሰፈረው እያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ ሳይፈጸም ከሚቀር ሰማይና ምድር ቢያልፍ እንደሚቀል መናገሩ ነበር። ሆኖም ግዑዞቹ ሰማያትና ምድር ለዘላለም እንደሚኖሩ ቅዱሳን መጻሕፍት ያረጋግጡልናል። (መዝሙር 78:69) ስለዚህ ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሐሳብ በሕጉ ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ ሳይፈጸም እንደማይቀር ያመለክታል።

ይሖዋ እያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ ያሳስበዋል ማለት ነው? እንዴታ! ለምሳሌ ያህል፣ የጥንቶቹ እስራኤላውያን ለፋሲካ የሚሠዉትን በግ አጥንት ፈጽሞ መስበር እንደሌለባቸው ተነግሯቸው ነበር። (ዘፀአት 12:46) ይህ ብዙም ትኩረት የማይሰጠው ዝርዝር ጉዳይ ሊመስል ይችላል። ለመሆኑ እስራኤላውያን ከበጉ አጥንቶች የትኛውንም መስበር የሌለባቸው ለምን እንደሆነ ገብቷቸው ነበር? ምናልባት አልገባቸውም ይሆናል። ይሖዋ ግን ይህ ዝርዝር ሕግ መሲሑ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሲሞት ከአጥንቶቹ ውስጥ አንዱም እንደማይሰበር የሚያመለክት ትንቢት እንደሆነ ያውቅ ነበር።—መዝሙር 34:20፤ ዮሐንስ 19:31-33, 36

ታዲያ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ምን ያስተምሩናል? እኛም ይሖዋ አምላክ የገባቸው ተስፋዎች አንድ በአንድ እንደሚፈጸሙ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ኢየሱስ አነስተኛ ከሆነችው የዕብራይስጥ ፊደል ጋር በተያያዘ የተናገረው ሐሳብ ለዚህ ማረጋገጫ ይሆነናል!

^ አን.3 በጣም አነስተኛዋ የግሪክኛ ፊደል ኢዮታ ስትሆን ከዕብራይስጧ አነስተኛ ፊደል י (ዮድ) ጋር ተመሳሳይ ናት። የሙሴ ሕግ በመጀመሪያ የተጻፈውና ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈው በዕብራይስጥ ስለሆነ ኢየሱስ እየጠቀሰ የነበረው ስለ ዕብራይስጧ ፊደል ሳይሆን አይቀርም።