በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ቁጥር 4 2017

ኤሊያስ ሁተ እና በዕብራይስጥ ያዘጋጃቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች

ኤሊያስ ሁተ እና በዕብራይስጥ ያዘጋጃቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን የዕብራይስጥ ቋንቋ ማንበብ ትችላለህ? ማንበብ ቀርቶ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ አይተህም እንኳ አታውቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ በ16ኛው መቶ ዘመን ይኖር ስለነበረው ኤሊያስ ሁተ የተባለ ምሁርና በዕብራይስጥ ቋንቋ ስላዘጋጃቸው ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ እትሞች ማወቅህ ለራስህ መጽሐፍ ቅዱስ ያለህን አድናቆት ሊጨምርልህ ይችላል።

ኤሊያስ ሁተ የአሁኗን ጀርመን ከፖላንድና ከቼክ ሪፑብሊክ ጋር በሚያዋስናት ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ጎርሊትዝ የምትባል አንዲት አነስተኛ ከተማ በ1553 ተወለደ። ከጊዜ በኋላ ዬና ውስጥ በሚገኝ የሉተራን ዩኒቨርሲቲ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚነገሩ ቋንቋዎችን አጠና። ገና በ24 ዓመት ዕድሜው ላይፕሲግ ውስጥ በዕብራይስጥ ቋንቋ ጥናት ፕሮፌሰር ሆኖ ተሾመ። ከዚያም በትምህርት መስክ የተሃድሶ አራማጅ በመሆን ተማሪዎች በአራት ዓመት ውስጥ ዕብራይስጥ፣ ግሪክኛ፣ ላቲንና ጀርመንኛ መማር የሚችሉበት ትምህርት ቤት ኑረምበርግ ውስጥ አቋቋመ። በወቅቱ እንዲህ ያለ ትምህርት የሚሰጥበት ሌላ ትምህርት ቤትም ሆነ ዩኒቨርሲቲ አልነበረም።

“ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራ”

ሁተ በ1587 በዕብራይስጥ ያዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ርዕስ የሚገኝበት ገጽ

በ1587 ሁተ በተለምዶ ብሉይ ኪዳን እየተባለ የሚጠራውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የዕብራይስጥ እትም አዘጋጀ። ይህ እትም ዴሬክ ሃ-ኮዴሽ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ትርጉሙም “የቅድስና ጎዳና” ማለት ነው፤ ይህ ስያሜ የተወሰደው ከኢሳይያስ 35:8 ላይ ነው። ይህ እትም “ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራ” እንዲባል ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ በሚያማምሩ ፊደላት የተጻፈ መሆኑ ነው። ከሁሉ በላይ ግን ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የዕብራይስጥ ቋንቋን ለመማር ጥሩ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል።

ሁተ ያዘጋጀው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ የነበረው ለምን እንደሆነ ለመረዳት አንድ ተማሪ መጽሐፍ ቅዱስን በዕብራይስጥ ለማንበብ በሚሞክርበት ጊዜ ያጋጥሙት የነበሩትን ሁለት ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንመልከት። አንደኛ፣ ፊደሉ የተለየና ያልተለመደ ዓይነት ከመሆኑም ሌላ ዕብራይስጥ የሚነበበው ከቀኝ ወደ ግራ ነው፤ ሁለተኛ ደግሞ ከአንድ የዕብራይስጥ ቃል ፊትና ኋላ ቅጥያ ሆነው የሚጨመሩት ፊደላት አንባቢው ሥርወ ቃሉን ለይቶ ለማወቅ እንዲቸገር ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ “ነፍስ” የሚል ትርጉም ያለውን ነፈሽ (נפש) የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል እንመልከት። በሕዝቅኤል 18:4 ላይ ከዚህ ቃል ፊት (ה) የሚል ቅጥያ ፊደል ስለገባ ቃሉ ሃንነፈሽ (הנפשׁ) ተብሎ ተቀምጧል። ቃሉን ለማያውቅ ሰው ሃንነፈሽ (הנפשׁ) የሚለው ቃል ነፈሽ (נפש) ከሚለው ቃል ፈጽሞ የተለየ መስሎ ሊታየው ይችላል።

ሁተ ተማሪዎቹን ለመርዳት ሲል አዲስና የተሻለ የሕትመት ዘዴ ተጠቀመ። እያንዳንዱ ሥርወ ቃል ድፍን በሆኑ ፊደላት እንዲጻፍ ያደረገ ሲሆን ከሥርወ ቃሉ ፊትና ኋላ የሚገቡት ቅጥያ ፊደላት ደግሞ ክፍተት ባላቸው ሆሄያት እንዲጻፉ  አደረገ። ይህ ቀላል ዘዴ ተማሪዎቹ ቋንቋውን በሚማሩበት ወቅት ከአንድ የዕብራይስጥ ቃል ውስጥ ሥርወ ቃሉን ያለምንም ችግር ለይተው ማወቅ እንዲችሉ ረድቷቸዋል። ባለማጣቀሻው የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም (እንግሊዝኛ) በግርጌ ማስታወሻዎቹ ላይ ተመሳሳይ ዘዴ ተጠቅሟል። * በዚህ ትርጉም ላይ የዕብራይስጡ ሥርወ ቃል ደመቅ ብሎ እንዲጻፍ ተደርጓል፤ ይህም ሥርወ ቃሉን ከፊቱና ከኋላው ከሚገቡት ቅጥያ ፊደላት ለመለየት ያስችላል። ከላይ የሚታዩት ፎቶግራፎች በሕዝቅኤል 18:4 ላይ ሁተ ባዘጋጀው የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበትን ዘዴና ባለማጣቀሻው የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በዚሁ ጥቅስ የግርጌ ማስታወሻ ላይ የተጠቀመበትን ዘዴ ያሳያሉ።

“የአዲስ ኪዳን” የዕብራይስጥ እትም

በተጨማሪም ሁተ በተለምዶ አዲስ ኪዳን በመባል የሚጠራውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በ12 ቋንቋዎች አዘጋጅቷል። አሥራ ሁለት ቋንቋዎችን አንድ ላይ አጣምሮ የያዘው ይህ እትም የተዘጋጀው በ1599 ኑረምበርግ ውስጥ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ኑረምበርግ ፖሊግሎት እየተባለ ይጠራል። ሁተ በዚህ እትም ውስጥ የዕብራይስጥ ቋንቋንም ማካተት ፈልጎ ነበር። ይሁንና በዕብራይስጥ ቋንቋ የተዘጋጀ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ለማግኘት “ብዙ ገንዘብ ለመክፈል ፈቃደኛ” የነበረ ቢሆንም ልፋቱ ከንቱ እንደሆነ ተናግሯል። * ስለዚህ አዲስ ኪዳንን ከግሪክኛ ወደ ዕብራይስጥ ራሱ ለመተርጎም ወሰነ። ሁተ ሌሎች ሥራዎቹን ሁሉ ወደ ጎን በመተው ጠቅላላውን የትርጉም ሥራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አጠናቀቀ!

ሁተ ያዘጋጀው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የዕብራይስጥ ትርጉም ምን ያህል የተዋጣለት ነበር? በ19ኛው መቶ ዘመን የኖረ ፍራንትስ ዴሊትሽ የተባለ የታወቀ ምሁር እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የሁተ የዕብራይስጥ ትርጉም አብዛኞቹ ክርስቲያኖች የሌላቸው ዓይነት ጥልቅ የዕብራይስጥ ቋንቋ እውቀት እንደነበረው ያሳያል፤ በመሆኑም የትርጉም ሥራው እንደ ማመሳከሪያ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ነው። በሁሉም ቦታዎች ላይ ማለት ይቻላል፣ ትክክለኛ አገላለጽ መጠቀም መቻሉ በጣም የሚያስደንቅ ነው።”

ዘላቂ ተጽዕኖ ያሳደረ የትርጉም ሥራ

ሁተ ያዘጋጃቸው እትሞች በብዛት ስላልተሸጡ የትርጉም ሥራው ከፍተኛ ገቢ አላስገኘለትም። ይሁን እንጂ ሥራው ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል። ለምሳሌ ያህል፣ በዕብራይስጥ ቋንቋ ያዘጋጀውን አዲስ ኪዳን ዊልያም ሮበርትሰን በ1661፣ ሪቻርድ ካዲክ ደግሞ በ1798 አሻሽለው በድጋሚ አሳትመውታል። ሁተ ግሪክኛውን ጽሑፍ ሲተረጉም ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ በተወሰዱ ጥቅሶች ውስጥ ኪርዮስ (ጌታ) እና ቴኦስ (አምላክ) የሚሉትን የማዕረግ ስሞች ካገኘ ወይም እነዚህ ቃላት ይሖዋን ለማመልከት እንደገቡ ከተሰማው “ይሖዋ” (יהוה፣ የሐወሐ) ብሎ በትክክል ይተረጉማቸው ነበር። ብዙ የአዲስ ኪዳን ትርጉሞች የአምላክን የግል ስም ስለማይጠቀሙ ይህ ትኩረት የሚስብ ነው፤ የሁተ ትርጉም የአምላክ ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ መግባቱ ተገቢ እንደሆነ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።

ከዚህ በኋላ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ስታይ ወይም በባለማጣቀሻው የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ውስጥ የሚገኙትን የግርጌ ማስታወሻዎች ስትመለከት ኤሊያስ ሁተን እና እሱ ያዘጋጃቸውን አስደናቂ የሆኑ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱሶች ማስታወስህ አይቀርም።

^ አን.7 በባለማጣቀሻው የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም፣ ሕዝቅኤል 18:4 ላይ የሚገኘውን ሁለተኛውን የግርጌ ማስታወሻና ተጨማሪ መረጃ 3ለን ተመልከት።

^ አን.9 ምሁራን ከዚያ በፊት የአዲስ ኪዳን የዕብራይስጥ ትርጉሞችን አዘጋጅተው ነበር። ከእነዚህ መካከል የባይዛንታይን መነኩሴ የነበረው ሳይመን አቱማኖስ በ1360 ገደማ ያዘጋጀው ትርጉም ይገኝበታል። ሌላው ደግሞ ኦስቫልት ሽሬከንፉክስ የተባለ ጀርመናዊ ምሁር በ1565 ገደማ ያዘጋጀው ነው። እነዚህ ትርጉሞች ለሕትመት ያልበቁ ሲሆን አሁን ጠፍተዋል።