ዶሪን ባሏ ዌስሊ ገና በ54 ዓመት ዕድሜው በፍጥነት እያደገ የሚሄድ የአእምሮ ዕጢ እንዳለበት ሲታወቅ በጣም ደነገጠች። * ሐኪሞቹ በጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚሞት ነገሩት። ዶሪን “ጆሮዬን ማመን አልቻልኩም” በማለት ታስታውሳለች። “ለተወሰኑ ሳምንታት ደንዝዤ ነበር። ይህ በእኛ ላይ ይደርሳል ብዬ አልጠበቅኩም። ሁኔታውን ለመቀበል አልተዘጋጀሁም ነበር።”

ዶሪን ብቻ ሳትሆን ሌሎችም እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ተመሳሳይ ስሜት ይሰማቸዋል። ማንም ሰው በሆነ ወቅት ላይ የማይድን በሽታ ሊይዘው ይችላል። ደስ የሚለው ነገር ብዙዎች የማይድን በሽታ የያዘውን የቤተሰብ አባል ለመንከባከብ ፈቃደኞች ናቸው። ሆኖም ከባድ በሽታ የያዘውን ሰው ማስታመም ፈታኝ ነው። ታዲያ የቤተሰቡ አባላት የማይድን በሽታ የያዘውን ሰው ለማጽናናትና ለመንከባከብ ምን ማድረግ ይችላሉ? በሽተኛውን በሚያስታምሙበት ወቅት የሚሰሟቸውን የተለያዩ ስሜቶች መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው? ግለሰቡ እየደከመ ሲሄድ ምን ነገሮችን ሊጠብቁ ይችላሉ? እስቲ በመጀመሪያ የማይድን በሽታ የያዘውን ሰው መንከባከብ በዛሬው ጊዜ በጣም ተፈታታኝ የሆነበትን ምክንያት እንመልከት።

ዘመኑ የፈጠረው አስቸጋሪ ሁኔታ

የሕክምና ሳይንስ ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ለውጦች አስከትሏል። ከአንድ መቶ ዓመት ገደማ በፊት በበለጸጉት አገሮችም እንኳ አማካዩ የሰው ዕድሜ በጣም አጭር ነበር። ሰዎች ተላላፊ በሽታ ከያዛቸው ወይም አደጋ ካጋጠማቸው ብዙም ሳይቆዩ ይሞቱ ነበር። ሰዎች የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበት አጋጣሚ ውስን ስለነበረ አብዛኞቹ ሕመምተኞች ቤተሰቦቻቸው ሲያስታምሟቸው ከቆዩ በኋላ እዚያው ቤታቸው ይሞታሉ።

በዛሬው ጊዜ ሐኪሞች ዘመናዊ የሕክምና ዘዴዎችን በመጠቀም የሰውን ዕድሜ ማራዘም ችለዋል። ቀደም ባሉት ጊዜያት የአንድን ሰው ሕይወት በአጭሩ ይቀጩ የነበሩ በሽታዎችን አሁን በተሻለ መንገድ ማከም ተችሏል። ይሁን እንጂ በሽተኛው በሕክምና ዕድሜው ተራዘመ ማለት ዳነ ማለት ላይሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ ሕመምተኞቹ አቅም ስለማይኖራቸው ራሳቸውን መንከባከብ አይችሉም። በመሆኑም እንዲህ ያሉ ግለሰቦችን መንከባከብ በጣም አስቸጋሪና አድካሚ ነው።

በዘመናችን ሰዎች የሕክምና አገልግሎት የማግኘት አጋጣሚያቸው እየሰፋ በመምጣቱ ብዙ በሽተኞች የሚሞቱት ቤት  ውስጥ ሳይሆን ሆስፒታል ነው። በዚህ የተነሳ ብዙዎች ሰው ሲሞት የማየት አጋጣሚያቸው የመነመነ ነው። ስለ ሞት ያላቸው ግንዛቤ ውስን መሆኑ እንዲፈሩና እንዲጨነቁ ሊያደርጋቸው ይችላል፤ ይህ ደግሞ የታመመውን የቤተሰብ አባል ከመንከባከብ ወደኋላ እንዲሉ ተጽዕኖ ያሳድርባቸው ይሆናል። ታዲያ በዚህ ረገድ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

ቅድመ ዝግጅት ማድረግ

በዶሪን ላይ ከደረሰው ሁኔታ እንደምንረዳው ብዙ ሰዎች የቤተሰባቸው አባል የማይድን በሽታ እንደያዘው ሲያውቁ በጣም ይደነግጣሉ። በዚህ ጊዜ ጭንቀት፣ ፍርሃትና ሐዘን ሊሰማቸው ይችላል፤ ታዲያ ወደፊት ለሚጠብቃቸው ነገር መዘጋጀት የሚችሉት እንዴት ነው? አንድ የአምላክ ታማኝ አገልጋይ “ጥበበኛ ልብ ማግኘት እንችል ዘንድ፣ ዕድሜያችንን እንዴት መቁጠር እንዳለብን አስተምረን” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 90:12) አንተም ‘ዕድሜህን’ ወይም ያለህን ጊዜ በጥበብ መጠቀም እንድትችል ይሖዋ አምላክ እንዲረዳህ አጥብቀህ መጸለይ ይኖርብሃል፤ ይህም የታመመው የቤተሰብህ አባል ከመሞቱ በፊት በተቻለ መጠን ከእሱ ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ እንድትችል ይረዳሃል።

ይህ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠይቃል። የታመመው የቤተሰብ አባል መናገር የሚችል ከሆነና በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ፈቃደኛ ከሆነ ሕመሙ ተባብሶ ውሳኔ ማድረግ የማይችልበት ሁኔታ ቢፈጠር ማን ይህን ኃላፊነት እንዲወስድ እንደሚፈልግ መጠየቁ ጥበብ ሊሆን ይችላል። መተንፈስ ሲያቅተው ትንፋሹ በሕክምና እርዳታ እንዲመለስለት ይፈልግ እንደሆነና እንዳልሆነ መጠየቅ ጠቃሚ ይሆናል፤ በተጨማሪም ሆስፒታል መግባት ወይም አንዳንድ ሕክምናዎች እንዲደረጉለት የሚፈልግ መሆን አለመሆኑን በግልጽ መወያየት ሕመምተኛው ደክሞ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ በቤተሰቡ አባላት መካከል ሊፈጠር የሚችለውን አለመግባባትና የጥፋተኝነት ስሜት ሊቀንሰው ይችላል። የቤተሰቡ አባላት አስቀድመው በግልጽ መወያየታቸው ሕመሙ እየተባባሰ ሲሄድ ለበሽተኛው እንክብካቤ በማድረግ ላይ እንዲያተኩሩ ያስችላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “መመካከር ከሌለ የታቀደው ነገር ሳይሳካ ይቀራል” ይላል።—ምሳሌ 15:22

መርዳት የሚቻልበት መንገድ

አብዛኛውን ጊዜ የአስታማሚው ተቀዳሚ ድርሻ ሕመምተኛውን ማጽናናት ነው። በማይድን በሽታ የተያዘው ሰው እንደሚወደድና ብቻውን እንዳልሆነ እንዲሰማው ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ሕመምተኛውን ሊያበረታቱትና ጥሩ ስሜት እንዲሰማው ሊያደርጉት የሚችሉ ጽሑፎችን አንብቡለት፤ እንዲሁም የሚወዳቸውን መዝሙሮች ዘምሩለት። ብዙ ሰዎች የቤተሰባቸው አባል እጃቸውን ይዞ ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ሲያናግራቸው ይጽናናሉ።

ብዙውን ጊዜ ሕመምተኛው ሊጠይቁት የመጡትን ሰዎች ማንነት ማወቁ ጠቃሚ ነው። አንድ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው ሌሎቹን የስሜት ሕዋሳቱን አጥቶም እንኳ የመስማት ችሎታውን ሳያጣ ሊቆይ እንደሚችል ይነገራል። ሕመምተኛው  የተኛ ቢመስልም እንኳ በደንብ ሊሰማ ስለሚችል ነቅቶ ባለበት ሰዓት የማትናገረውን ነገር አትናገር።”

የሚቻል ከሆነ አብረኸው ጸልይ። መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስና ጓደኞቹ ከባድ ጫና ደርሶባቸው ስለነበር በሕይወት የመትረፍ ተስፋቸው እንኳ ተሟጦ እንደነበረ ይገልጻል። በዚህ ወቅት ምን እርዳታ ማግኘት ፈልገው ነበር? ጳውሎስ ጓደኞቹን “እናንተም ስለ እኛ ምልጃ በማቅረብ ልትረዱን ትችላላችሁ” ብሏቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 1:8-11) ከባድ ውጥረት ሲያጋጥም ወይም አንድ ሰው በጠና ሲታመም ልባዊ ጸሎት ማቅረብ በጣም አስፈላጊ ነው።

እውነታውን አምናችሁ ተቀበሉ

የምትወዱት ሰው ሊሞት እንደሆነ ማሰቡ ራሱ በጣም ያስጨንቃል። ይህ ምንም አያስደንቅም፤ ምክንያቱም ሞት ተፈጥሯዊ አይደለም። በመሆኑም ሞትን የተለመደ የሕይወት ክፍል አድርገን መቀበል ይከብደናል። (ሮም 5:12) የአምላክ ቃል ሞትን “ጠላት” ብሎ የሚጠራው ለዚህ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:26) ስለዚህ የምንወደው ሰው ሊሞት እንደሆነ ማሰብ አለመፈለጋችን አያስገርምም።

ይሁንና ሊከሰት ስለሚችለው ነገር አስቀድመን ማሰባችን ፍርሃታችን እንዲቀንስ እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንድናተኩር ሊረዳን ይችላል። ሊከሰቱ ከሚችሉት ነገሮች ውስጥ አንዳንዶቹ “ የመጨረሻዎቹ ሳምንታት” በሚለው ሣጥን ውስጥ ተዘርዝረዋል። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች በእያንዳንዱ ሕመምተኛ ላይ ይደርሳሉ ማለት አይደለም ወይም ሣጥኑ ላይ ባለው ቅደም ተከተል ይከሰታሉ ማለት አይደለም። ያም ሆኖ አብዛኞቹ ሕመምተኞች ከእነዚህ ለውጦች ውስጥ ቢያንስ የተወሰኑት ያጋጥሟቸዋል።

የታመመው የቤተሰባችሁ አባል ሲሞት እናንተን ለመርዳት ቃል የገባ የቅርብ ወዳጅ ካለ እሱን መጥራታችሁ ሊጠቅማችሁ ይችላል። ግለሰቡን ሲያስታምሙ የቆዩት የቤተሰቡ አባላት ሟቹ እረፍት ከሚነሳው ሕመም እንደተገላገለና ከዚያ በኋላ ምንም ዓይነት ሥቃይ እንደማይደርስበት በመግለጽ የሚያጽናናቸው ሰው ሊያስፈልጋቸው ይችላል። የሰው ልጆች ፈጣሪ በፍቅር ተገፋፍቶ ‘ሙታን ምንም አያውቁም’ የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—መክብብ 9:5

ታላቁ ተንከባካቢ

ሌሎች የሚያደርጉልንን እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን አለብን

አንድ የቤተሰብ አባል የማይድን በሽታ በሚይዘው ጊዜ ብቻ ሳይሆን በእሱ ሞት የተነሳ ቤተሰቡ ሐዘን ላይ በሚወድቅበት ጊዜም አምላክን መጠጊያ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። አምላክ ሌሎች ሰዎች በቃልም ሆነ በተግባር እንዲያጽናኗችሁ በማነሳሳት ድጋፍ ሊሰጣችሁ ይችላል። ዶሪን እንዲህ ብላለች፦ “ሌሎች የሚያደርጉልኝን እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን እንዳለብኝ ተምሬያለሁ። ደግሞም ሌሎች ብዙ እርዳታ አድርገውልናል። እኔም ሆንኩ ባለቤቴ ይሖዋ ‘እናንተን ለመርዳት ከጎናችሁ ነኝ’ እንዳለን ሆኖ ተሰምቶናል። ያደረገልንን ነገር ፈጽሞ አልረሳውም።”

አዎ፣ ከማንም በላይ የሚንከባከበን ይሖዋ አምላክ ነው። እሱ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን የሚሰማንን ሥቃይና ሐዘን ይረዳልናል። የደረሰብንን ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ ለመስጠት ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ አለው። ከዚህም በላይ በቅርቡ ሞትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚያጠፋና በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት እንደሚያስነሳ ቃል ገብቷል። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 21:3, 4) በዚያን ጊዜ ሁሉም ሰው “ሞት ሆይ፣ ድል አድራጊነትህ የት አለ? ሞት ሆይ፣ መንደፊያህ የት አለ?” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገራቸውን ቃላት ያስተጋባል።—1 ቆሮንቶስ 15:55

^ አን.2 ስሞቹ ተቀይረዋል።