በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ቁጥር 4 2017

ዋና ዋና የሚባሉት አብዛኞቹ ሃይማኖቶች የሰው ነፍስ አትሞትም ብለው ያስተምራሉ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሕይወትንና ሞትን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ከሞት በኋላ ሕይወት አለ?

ከሞት በኋላ ሕይወት አለ?

ሕይወትንና ሞትን በተመለከተ ሰዎች የተለያየ አመለካከት አላቸው። አንዳንዶች ሰው ከሞተ በኋላ በሌላ መልክ ወይም በሌላ ስፍራ መኖሩን እንደሚቀጥል ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ ዳግመኛ ተወልደው በሕይወት እንደሚኖሩ ያምናሉ። ሞት የሁሉም ነገር ፍጻሜ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎችም አሉ።

አንተም ይህን ጉዳይ በተመለከተ የራስህ አመለካከት ይኖርህ ይሆናል፤ ምናልባትም ከዚህ ጋር በተያያዘ አስተዳደግህ ወይም በአካባቢህ ያለው አስተሳሰብ ተጽዕኖ አሳድሮብህ ሊሆን ይችላል። ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ‘ስንሞት ምን እንሆናለን?’ የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ ሰዎች የተለያየ አመለካከት አላቸው፤ ታዲያ ለዚህ ግራ የሚያጋባ ጥያቄ አስተማማኝና ትክክለኛ መልስ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?

ለብዙ መቶ ዘመናት የሃይማኖት መሪዎች የሰው ነፍስ እንደማትሞት ሲያስተምሩ ኖረዋል። ዋና ዋና የሚባሉት አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ማለትም ክርስትና፣ ሂንዱይዝም፣ የአይሁድ እምነት፣ እስልምናና ሌሎች ሃይማኖቶች ሰው ሲሞት ከሥጋው ተለይታ የምትሄድና በመንፈሳዊው ዓለም መኖሯን የምትቀጥል የማትሞት ነፍስ አለች ብለው ያስተምራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የቡድሂዝም እምነት ተከታዮች ‘አንድ ሰው ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ጊዜያት እንደገና እየተወለደ ይኖራል፤ በመጨረሻም ከሥቃይ ይገላገላል’ ብለው ያምናሉ። ይህ አስደሳች ሁኔታ ኒርቫና ይባላል።

እንዲህ ባሉ ትምህርቶች የተነሳ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አብዛኞቹ ሰዎች ሞት ወደ ሌላ ዓለም የሚያሸጋግረን በር እንደሆነ አድርገው ያምናሉ። ስለዚህ ብዙዎች ሞት በሕይወት ዑደት ውስጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር ከመሆኑም ሌላ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ያለ ነገር ነው ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል? የሚቀጥለውን ርዕስ እንድታነብ እናበረታታሃለን። የዚህ ጥያቄ መልስ ሊያስገርምህ ይችላል።