በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

በአፍሪካና በአሜሪካ መካከል ይደረግ የነበረው የባሪያ ንግድ እጅግ አትራፊ ነበር

ከባርነት ነፃ መውጣት—ጥንትና ዛሬ

ከባርነት ነፃ መውጣት—ጥንትና ዛሬ

ብሌሲንግ * ወደ አውሮፓ የሄደችው ፀጉር ቤት ውስጥ እንደምትሠራ ቃል ተገብቶላት ነበር። ይሁንና ለአሥር ተከታታይ ቀናት ድብደባ ከደረሰባትና በቤተሰቧ ላይ የኃይል እርምጃ እንደሚወሰድ ዛቻ ከተሰነዘረባት በኋላ ሴተኛ አዳሪ ሆና ለመሥራት ተገደደች።

በጥንቷ ግብፅ የነበሩ ባሪያዎችን የሚያሳይ ቅርጽ

ብሌሲንግ፣ አሠሪዋ የጣለችባትን ከ40,000 ዩሮ በላይ የሆነ ዕዳ ለመክፈል በእያንዳንዱ ምሽት ከ200 እስከ 300 ዩሮ ያህል ገንዘብ ማግኘት ይጠበቅባት ነበር። * ብሌሲንግ እንዲህ ብላለች፦ “በተደጋጋሚ ለማምለጥ ባስብም ቤተሰቤ ላይ ጥቃት እንዳይደርስ እፈራ ነበር። በመሆኑም ወጥመድ ውስጥ ገብቼ ነበር።” የብሌሲንግ ታሪክ በዓለም ዙሪያ ተገደው በወሲብ ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ አራት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው።

ወደ 4,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊትም ዮሴፍ የተባለን አንድ ወጣት ወንድሞቹ ሸጠውት ነበር። ከዚያም በአንድ የግብፅ ባለሥልጣን ቤት ውስጥ በባርነት ያገለግል ጀመር። ከብሌሲንግ በተለየ መልኩ ጌታው መጀመሪያ ላይ ዮሴፍን በጥሩ ሁኔታ ይዞት ነበር። ይሁንና የጌታው ሚስት አብሯት እንዲተኛ ያቀረበችለትን ጥያቄ ባለመቀበሉ ‘አስገድዶ ለመድፈር ሞክሯል’ የሚል የሐሰት ክስ ተሰነዘረበት። ከዚያም ወደ እስር ቤት ገብቶ በብረት እንዲታሰር ተደረገ።—ዘፍጥረት 39:1-20፤ መዝሙር 105:17, 18

በዮሴፍ እና በብሌሲንግ መካከል ያለው ልዩነት ዮሴፍ በጥንት ዘመን ብሌሲንግ ደግሞ በ21ኛው መቶ ዘመን መኖራቸው ነው፤ ሆኖም ሁለቱም በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ ናቸው። ይህን ንግድ የሚያካሂዱ ግለሰቦች ሰዎችን የሚመለከቱት ትርፍ እንደሚያስገኝ ሸቀጥ አድርገው ነው።

ጦርነት የባሪያ ንግድ እንዲጧጧፍ አድርጓል

በርካታ አገሮች ጦርነት ማካሄድን ባሪያዎች ለማግኘት የሚያስችል ቀላል መንገድ ሆኖ አግኝተውታል። ግብፃዊው ንጉስ ሳልሳዊ ቱትሞስ በከነዓን ምድር ላይ ጦርነት ካካሄደ በኋላ በአንድ ጊዜ 90,000 ምርኮኞችን ይዞ እንደተመለሰ ይነገራል። ግብፃውያኑ እነዚህን ባሪያዎች በማዕድን ማውጫዎች ውስጥ እንዲሠሩ፣ ቤተ መቅደስ እንዲገነቡ እንዲሁም መተላለፊያ ቦዮችን እንዲሠሩ ያደርጓቸው ነበር።

 ሮማውያንም ቢሆኑ ጦርነት ካካሄዱ በኋላ በርካታ ምርኮኞችን ባሪያ አድርገው ይወስዱ ነበር፤ እንዲያውም ባሪያዎችን ለማግኘት ሲሉ ብቻ ጦርነት የሚያደርጉበት ጊዜ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ ግማሽ የሚያህለው የሮም ነዋሪ ባሪያ እንደነበር ይገመታል። በግብፅና በሮም ውስጥ የነበሩ ባሪያዎች ከፍተኛ የጉልበት ብዝበዛ ይደርስባቸው ነበር። በሮም የማዕድን ማውጫዎች ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ባሪያዎች አማካይ ዕድሜ 30 ዓመት ገደማ ብቻ መሆኑ ይህን ያሳያል።

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የባሪያ ንግድ እየቀነሰ አልመጣም። እንዲያውም ከ16ኛው እስከ 19ኛው መቶ ዘመን ባለው ጊዜ ውስጥ በአፍሪካና በአሜሪካ መካከል ይካሄድ የነበረው የባሪያ ንግድ በዓለም ላይ ከነበሩት እጅግ አትራፊ ንግዶች አንዱ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት ያወጣው ሪፖርት እንደሚጠቁመው በዚያን ወቅት ‘ከ25 እስከ 30 ሚሊዮን የሚሆኑ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ለባርነት ተሽጠዋል።’ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ባሪያዎች የአትላንቲክ ውቅያኖስን ሲያቋርጡ ሕይወታቸው አልፏል። ከዚህ ጉዞ በሕይወት የተረፈ ኦላውዳ ኤክዊያኖ የተባለ አንድ ባሪያ እንዲህ ብሏል፦ “የሴቶቹን የሥቃይ ጩኸት እንዲሁም በሞት እያጣጣሩ ያሉትን ሰዎች ሲቃ መስማት ምን ያህል አሰቃቂ እንደነበር በቃላት መግለጽ ያዳግታል።”

የሚያሳዝነው የባሪያ ንግድ አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው። የዓለም የሥራ ድርጅት፣ በዛሬው ጊዜም እንኳ ወደ 21 ሚልዮን የሚጠጉ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት በባርነት ቀንበር ሥር እየማቀቁ እንደሆነ እንዲሁም ሥራቸውን የሚያከናውኑት በጥቂት ወይም አለምንም ክፍያ እንደሆነ ገልጿል። በዘመናችን ያሉ ባሪያዎች በማዕድን ማውጫዎች፣ በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች፣ በጡብ ማምረቻዎች፣ በሴተኛ አዳሪ ቤቶች እንዲሁም በግለሰብ ቤቶች ውስጥ ይሠራሉ። ይህ ድርጊት ሕገ ወጥ ቢሆንም ይበልጥ በመስፋፋት ላይ ያለ ይመስላል።

በዛሬው ጊዜም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በባርነት ቀንበር ሥር ይማቅቃሉ

ከባርነት ነፃ መውጣት

በርካታ ባሪያዎች ከሚደርስባቸው የጭካኔ ድርጊት የተነሳ ነፃነታቸውን ለማግኘት ትግል አድርገዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ግላዲያተሩ ስፓርታከስ እና 100,000 ገደማ የሚሆኑ ባሪያዎች በሮም ላይ ዓመፅ አካሂደው የነበረ ቢሆንም አልተሳካላቸውም። የካሪቢያን ደሴት በሆነችው በሂስፓኒዮላ የነበሩ ባሪያዎች በ18ኛው መቶ ዘመን በጌቶቻቸው ላይ ዓምፀው ነበር። በሸንኮራ አገዳ እርሻዎች ላይ የሚሠሩት ባሪያዎች የተፈጸመባቸው የጭካኔ ድርጊት ለ13 ዓመታት የዘለቀ ጦርነት እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል፤ በውጤቱም በ1804 የሄይቲ ነፃ መንግስት ተቋቁሟል።

ይሁንና እስካሁን ድረስ ከባርነት ቀንበር ነፃ ለመውጣት ከተደረጉ ጥረቶች ሁሉ እጅግ ስኬታማ ተደርጎ የሚቆጠረው እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ የወጡበት መንገድ ነው። መላው ብሔር ማለትም ሦስት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ከግብፅ ባርነት ነፃ ወጥተዋል። ደግሞም ከነበሩበት ሁኔታ አንጻር ነፃነት ማግኘታቸው የተገባ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በግብፅ ስላሳለፉት ሕይወት ሲናገር “ማንኛውንም ዓይነት የባርነት ሥራ በማሠራት በጭካኔ ያንገላቷቸው ነበር” ይላል። (ዘፀአት 1:11-14) እንዲያውም አንድ የግብፅ  ፈርዖን የእስራኤላውያን ቁጥር እንዳይጨምር ለመግታት ሲል ሕፃናትን የመግደል ዘመቻ አካሂዶ ነበር።—ዘፀአት 1:8-22

እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ የወጡበት መንገድ ለየት ያለ ነበር፤ ምክንያቱም ጣልቃ ገብቶ እስራኤላውያንን ከሚደርስባቸው በደል የገላገላቸው አምላክ ነው። አምላክ ለሙሴ እንዲህ ብሎት ነበር፦ “እየደረሰባቸው [ያለውን] ሥቃይ በሚገባ አውቃለሁ። እኔም ከግብፃውያን እጅ ልታደጋቸው . . . እወርዳለሁ።” (ዘፀአት 3:7, 8) በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ አይሁዳውያን ይህን ክንውን ለማስታወስ እስከዛሬ ድረስ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ።—ዘፀአት 12:14

ባርነት የሚያከትምበት ጊዜ

መጽሐፍ ቅዱስ ‘በይሖዋ ዘንድ ፍትሕ ማዛባት እንደሌለ’ እንዲሁም ይሖዋ መቼም ቢሆን እንደማይለወጥ ማረጋገጫ ይሰጠናል። (2 ዜና መዋዕል 19:7፤ ሚልክያስ 3:6) አምላክ ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው “ለተማረኩት ነፃነትን” እንዲያውጅና “የተጨቆኑትን ነፃ” እንዲያወጣ ነው። (ሉቃስ 4:18) ይህ ሲባል ታዲያ እያንዳንዱ ባሪያ ቃል በቃል ከባርነት ነፃ ይወጣል ማለት ነው? እንደዚያ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ኢየሱስ የተላከው ሰዎችን ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ለማውጣት ነው። ኢየሱስ ‘እውነት ነፃ ያወጣችኋል’ በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:32) ኢየሱስ ያስተማረው እውነት በዛሬው ጊዜም እንኳ ሰዎችን ከተለያዩ ነገሮች ባርነት ነፃ እያወጣቸው ነው።—“ ለየት ካለ ባርነት ነፃ መውጣት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

በእርግጥም አምላክ ዮሴፍንና ብሌሲንግን ከነበሩበት ባርነት ነፃ እንዲወጡ ረድቷቸዋል። ስለ ዮሴፍ የሚናገረውን አስደናቂ ዘገባ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዘፍጥረት መጽሐፍ ከምዕራፍ 39 እስከ 41 ላይ ማግኘት ትችላለህ። ብሌሲንግ ነፃ የወጣችበት መንገድም ቢሆን አስደናቂ ነው።

ብሌሲንግ ከአንድ የአውሮፓ አገር ስትባረር ወደ ስፔን ተጓዘች። በዚያም የይሖዋ ምሥክሮችን አግኝታ ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ሕይወቷን ለማስተካከል ቆርጣ በመነሳት ሌላ ሥራ መሥራት የጀመረች ሲሆን በየወሩ የምትከፍለውን ዕዳ እንድትቀንስላት የቀድሞ አሠሪዋን አሳመነቻት። አንድ ቀን ብሌሲንግ ከቀድሞ አሠሪዋ ስልክ ተደወለላት። ዕዳዋን በሙሉ እንደሰረዘችላት ከነገረቻት በኋላ ይቅርታ እንድታደርግላት ብሌሲንግን ጠየቀቻት። እንዲህ ያደረገችው ለምንድን ነው? እሷም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምራ ነበር! ብሌሲንግ “እውነት አስደናቂ በሆነ መንገድ ነፃ ያወጣችኋል” በማለት ተናግራለች።

ይሖዋ አምላክ እስራኤላውያን ባሪያዎች በግብፅ ይደርስባቸው የነበረውን ጭቆና ሲያይ በጣም አዝኖ ነበር፤ በዛሬው ጊዜም ግፍ ሲፈጸም ሲያይ እንደሚያዝን ምንም ጥርጥር የለውም። እርግጥ ነው፣ ባርነትን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ በሰው ዘር ማኅበረሰብ ላይ ትልቅ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል። ይሁንና አምላክ እንዲህ ያለ ለውጥ እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል። “አምላክ በገባው ቃል መሠረት አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን፤ በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል።”—2 ጴጥሮስ 3:13

^ አን.2 ስሟ ተቀይሯል።

^ አን.3 በዚያን ወቅት የዩሮ ምንዛሪ ከአሜሪካ ዶላር ጋር ተመጣጣኝ ነበር።