በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ቁጥር 2 2017

መስጠት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

መስጠት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

“አውቶቡሱ መሄድ ይችላል፤ ቻይናዊው ግን እዚሁ ይቆያል!” እነዚህ ቃላት ደቡብ አሜሪካ ውስጥ የሚገኝን አንድ አገር ድንበር አቋርጣ ለመሄድ አውቶቡስ ውስጥ ተቀምጣ የምትጠብቀው አሌክሳንድራ ጆሮ ውስጥ ጥልቅ አሉ። ምን እንደተፈጠረ ለማየት ከተቀመጠችበት ስትነሳ አንድ ቻይናዊ ያጋጠመውን ችግር በተሰባበረ ስፓንኛ ለድንበር ጠባቂው ለማስረዳት ሲታገል ተመለከተች። አሌክሳንድራ በቻይንኛ ቋንቋ የሚመራ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አባል ስለነበረች ለቻይናዊው አስተረጎመችለት።

ቻይናዊው ሕጋዊ ነዋሪ እንደሆነ ሆኖም ገንዘቡና ሰነዶቹ እንደተሰረቁበት ተናገረ። ድንበር ጠባቂው መጀመሪያ ላይ ቻይናዊውን አላመነውም ነበር፤ አሌክሳንድራም ብትሆን በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የተሰማራች መስሎት ነበር። በኋላ ላይ ቻይናዊው የተናገረውን የተቀበለው ቢሆንም ሕጋዊ ሰነዶች ባለመያዙ የገንዘብ ቅጣት ጣለበት። ቻይናዊው ምንም ገንዘብ ስላልነበረው አሌክሳንድራ 20 ዶላር አበደረችው። ቻይናዊው ላሳየችው ደግነት በጣም ካመሰገናት በኋላ ካበደረችው ገንዘብ በላይ እንደሚመልስላት ነገራት። አሌክሳንድራ ይህን ያደረገችው በምላሹ የሆነ ነገር እንዲደረግላት ፈልጋ እንዳልሆነ ነገረችው፤ ከዚህ ይልቅ ሌሎችን መርዳት ተገቢ እንደሆነ ስለምታምን ይህን በማድረጓ ደስተኛ እንደሆነች ገለጸችለት። ከዚያም የተወሰኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከሰጠችው በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና አበረታታችው።

ሰዎች ጨርሶ ለማያውቁት ግለሰብ ስላሳዩት እንዲህ ያለ ደግነት መስማት በጣም የሚያስደስት ነው፤ የተለያየ ሃይማኖት ተከታዮችም ሆኑ ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ። አንተስ እንዲህ ያለ ደግነት ለማሳየት ፈቃደኛ ነህ? ይህ ጥያቄ ትኩረታችንን ሊስብ ይገባል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” በማለት ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ከሳይንስ አንጻርም ካየነው ጥያቄው ትኩረት የሚስብ ነው፤ ምክንያቱም ተመራማሪዎች መስጠት ጠቃሚ እንደሆነ ደርሰውበታል። መስጠት ምን ጥቅሞች እንዳሉት እስቲ እንመልከት።

‘በደስታ የሚሰጥ’

ከብዙ ተሞክሮዎች ማየት እንደሚቻለው መስጠት ደስታ ያስገኛል። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው እንደሚወድ’ ጽፏል። ጳውሎስ ይህን ያለው የእምነት አጋሮቻቸው ያጋጠማቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲወጡ በልግስና እርዳታ ስላደረጉ ክርስቲያኖች ሲናገር ነው። (2 ቆሮንቶስ 8:4፤ 9:7) ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ እነዚህ ክርስቲያኖች ደስተኛ የሆኑት ለወንድሞቻቸው መስጠትና እነሱን መርዳት በመቻላቸው እንደሆነ ያሳያል።

እንዲያውም አንድ ጥናት እንደሚያሳየው መስጠት “ከደስታ፣ ከማኀበራዊ ሕይወት እንዲሁም ከመተማመን ጋር የተያያዙትን የአእምሯችንን ክፍሎች ያነቃቃቸዋል፤ ይህም ልዩ የሆነ የእርካታ ስሜት ይፈጥርልናል።” አንድ ሌላ ጥናት ደግሞ “በጥናቱ ላይ የተሳተፉት ሰዎች ገንዘባቸውን ለራሳቸው ከመጠቀም ይልቅ ለሌላ ሰው መስጠታቸው ይበልጥ ደስተኛ እንዳደረጋቸው” ገልጿል።

ባለብህ የአቅም ገደብ የተነሳ ማድረግ የምትችለው ነገር ውስን እንደሆነ ተሰምቶህ ያውቃል? እንደ እውነቱ ከሆነ ማንኛውም ሰው ‘መስጠት’ የሚያስገኘውን ደስታ ማጣጣም ይችላል። አንድ ሰው በትክክለኛው ዝንባሌ ተነሳስቶ እስከሰጠ ድረስ የስጦታው መጠን ምንም ለውጥ  አያመጣም። አንዲት የይሖዋ ምሥክር የተወሰነ መዋጮ እና የሚከተለውን መልእክት ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች ልካለች፦ “ለብዙ ዓመታት በይሖዋ ምሥክሮች መሰብሰቢያ አዳራሽ መዋጮ የማደርገው በጣም አነስተኛ ገንዘብ ነበር። ይሖዋ አምላክ ግን ምንጊዜም ከሰጠሁት የበለጠ ሰጥቶኛል። . . . ለይሖዋ ሥራ መዋጮ ማድረግ የምችልበት አጋጣሚ ስለከፈታችሁልኝ በጣም አመሰግናለሁ። ትልቅ መጽናኛ ሆኖኛል።”

እርግጥ ነው፣ ለሌሎች መስጠት የምንችለው ገንዘብ ብቻ አይደለም። መስጠት የምንችላቸው በርካታ ነገሮች አሉ።

መስጠት ለጤና ጠቃሚ ነው

መስጠት ራሳችሁንም ሆነ ሌሎችን ይጠቅማል

መጽሐፍ ቅዱስ “ደግ ሰው ራሱን ይጠቅማል፤ ጨካኝ ሰው ግን በራሱ ላይ መከራ ያመጣል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 11:17) ደግ ሰው ለጋስ ነው፤ ለሌሎች ጊዜውን፣ ኃይሉንና ትኩረቱን ጨምሮ በርካታ ነገሮችን ለመስጠት ፈቃደኛ ነው። እንዲህ ማድረጉ ብዙ ጥቅሞች ያስገኝለታል፤ ለምሳሌ ለሌሎች ደግነት ማሳየት ለጤና ጠቃሚ ነው።

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ሌሎችን ለመርዳት ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች የመታመምና በመንፈስ ጭንቀት የመያዝ አጋጣሚያቸው ጠባብ ነው። በጥቅሉ ሲታይ የተሻለ ጤንነት አላቸው። እንደ መልቲፕል ስክለሮሲስ ወይም ኤች አይ ቪ ያሉ ከባድ የጤና ችግሮች ያሉባቸው አንዳንድ ሰዎች እንኳ በልግስና መስጠታቸው ጤናቸው እንዲሻሻል አድርጓል። በተጨማሪም ከአልኮል ሱስ ለመላቀቅ እየታገሉ ያሉ ሰዎች ሌሎችን መርዳታቸው፣ የሚሰማቸውን ጭንቀት እንደሚቀንስላቸው እንዲሁም የአልኮል ሱሱ እንዳያገረሽባቸው እንደሚረዳቸው መመልከት ተችሏል።

በልግስና የሚሰጥ ሰው ከላይ የተዘረዘሩትን ጥቅሞች የሚያገኘው “እንደ ርኅራኄ፣ ቅንነትና ደግነት ያሉት ባሕርያት አሉታዊ ስሜትን ለማስወገድ ስለሚረዱ” እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በተጨማሪም መስጠት ውጥረትንና የደም ግፊትን ለመቀነስ ይረዳል። የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎችም እንኳ ሌሎችን ለመርዳት ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ ከሐዘኑ ጋር ተያይዞ ሊያጋጥማቸው ከሚችለው የመንፈስ ጭንቀት በተሻለ ፍጥነት መላቀቅ ይችላሉ።

በእርግጥም መስጠት ብዙ ጥቅሞች አሉት!

መስጠት ወደ ሌሎች ይጋባል

ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዲህ ሲል አበረታቷቸዋል፦ “ለሰዎች ስጡ፤ እነሱም ይሰጧችኋል። ተትረፍርፎ እስኪፈስ ድረስ በተጠቀጠቀና በተነቀነቀ ጥሩ መስፈሪያ ሰፍረው በእቅፋችሁ ይሰጧችኋል። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ መልሰው ይሰፍሩላችኋል።” (ሉቃስ 6:38) ለሌሎች መስጠትህ እነሱም አመስጋኝ መሆናቸውን እንዲያሳዩና በልግስና እንዲሰጡ ሊያነሳሳቸው ይችላል። በመሆኑም መስጠት የትብብርና የወዳጅነት መንፈስ እንዲሰፍን ያደርጋል።

መስጠት የትብብርና የወዳጅነት መንፈስ እንዲሰፍን ያደርጋል

ሰዎች ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይ ጥናት የሚያደርጉ ተመራማሪዎች “ሰዎች የራሳቸውን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየታቸው ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ እንደሚያነሳሳ” አስተውለዋል። ሌላው ቀርቶ “ሰዎች ስላሳዩት አስገራሚ የሆነ ደግነት ማንበብ እንኳ ሌሎች ሰዎችን ይበልጥ ለጋስ እንዲሆኑ ያነሳሳቸዋል።” አንድ ጥናት እንደሚገልጸው ከሆነ “አንድ ሰው የሚያደርገው ነገር በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል፤ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ፈጽሞ የማያውቃቸው ወይም በአካል አግኝቷቸው የማያውቅ ሊሆኑ ይችላሉ።” በሌላ አነጋገር አንድ የደግነት ተግባር ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው በመተላለፍ በመላው ማኅበረሰብ ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። እንዲህ ባለ ማኅበረሰብ ውስጥ መኖር አትፈልግም? በእርግጥም ብዙ ሰዎች ለጋስ  በሆኑ ቁጥር የምናገኘው ጥቅምም እየጨመረ ይሄዳል!

ከፍሎሪዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የተገኘ አንድ ተሞክሮ ይህን በግልጽ ያሳያል። ከባድ አውሎ ነፋስ በአካባቢው ላይ ጉዳት ካደረሰ በኋላ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ ለመስጠት በፈቃደኝነት ራሳቸውን አቀረቡ። እድሳት ለሚያደርጉለት ቤት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እስኪመጡላቸው እየጠበቁ ሳለ ከጎናቸው ያለው ቤት አጥር እንደተጎዳ አስተዋሉ፤ በመሆኑም አጥሩን አደሱት። አጥሩ የታደሰለት ግለሰብ ከጊዜ በኋላ ለይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ለተደረገልኝ ነገር ከልብ አመሰግናለሁ። እነዚህ ሰዎች በጣም ደጎች እንደሆኑ አስተውያለሁ” ብሏል። ይህ ግለሰብ እነዚህ ሰዎች ላሳዩት ደግነት ያለውን አመስጋኝነት ለመግለጽ “የይሖዋ ምሥክሮች ለሚያከናውኑት አስደናቂ ሥራ” እንዲውል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት ልኳል።

ከሁሉ የላቀ ምሳሌ የተወልንን አካል ምሰሉ

በሳይንሳዊ ምርምር የተገኘ አንድ አስገራሚ እውነታ አለ፤ ይህም “ሁላችንም ሰዎችን የመርዳት ዝንባሌ በውስጣችን ያለ መሆኑ ነው።” ልጆች “አፍ ከመፍታታቸው በፊትም እንኳ ከራሳቸው ይልቅ የሌሎችን ጥቅም የማስቀደም ባሕርይ እንደሚያሳዩ” ጥናቱ ገልጿል። ይህ ባህርይ ሊኖራቸው የቻለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሰው ልጆች የተፈጠሩት ‘በአምላክ መልክ’ እንደሆነ ማለትም መሠረታዊ የሆኑትን የአምላክን ባሕርያት ማንጸባረቅ እንዲችሉ ተደርገው እንደሆነ ይናገራል።—ዘፍጥረት 1:27

ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ካሉት አስደናቂ ባሕርያት መካከል አንዱ ልግስና ነው። ሕይወትንና በሕይወታችን ደስተኛ ለመሆን የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ ሰጥቶናል። (የሐዋርያት ሥራ 14:17፤ 17:26-28) በተጨማሪም አምላክ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል፤ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት በሰማይ ስላለው አባታችን እንዲሁም ለእኛ ስላለው ዓላማ ማወቅ እንችላለን። ይህ መጽሐፍ አምላክ ወደፊት ደስተኛ እንድንሆን የሚያስችለንን ዝግጅት እንዳደረገም ይነግረናል። * (1 ዮሐንስ 4:9, 10) ይሖዋ ለጋስ አምላክ ሲሆን አንተም የተፈጠርከው በእሱ መልክ ነው። በመሆኑም የእሱን ምሳሌ በመከተል ለሌሎች በልግስና መስጠትህ ራስህን የሚጠቅምና የአምላክን ሞገስ የሚያስገኝልህ መሆኑ ምንም አያስገርምም።—ዕብራውያን 13:16

በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰችው አሌክሳንድራስ ምን አጋጥሟት ይሆን? በአውቶቡሱ ውስጥ አብሯት ይጓዝ የነበረ አንድ መንገደኛ ገንዘቧን እንዳባከነች ነግሯት ነበር፤ የረዳችው ሰው ግን አውቶቡሱ በሚቆምበት ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ጓደኞቹ ጋር ተገናኝቶ አሌክሳንድራ ያበደረችውን 20 ዶላር ወዲያውኑ ከፈለ። በተጨማሪም አሌክሳንድራ በሰጠችው ማበረታቻ መሠረት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። አሌክሳንድራ ከሦስት ወር በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች በፔሩ በቻይንኛ ቋንቋ ባደረጉት ትልቅ ስብሰባ ላይ ሰውየውን ስታገኘው በጣም ተደሰተች። ሰውየው አሌክሳንድራ ላደረገችለት ነገር ሁሉ አመስጋኝነቱን ለመግለጽ እሷንና አብረዋት ወደ ስብሰባው የተጓዙትን ሰዎች ወደ ራሱ ምግብ ቤት በመውሰድ ጋበዛቸው።

መስጠትም ሆነ ሌሎችን መርዳት ትልቅ ደስታ ያስገኛል። እግረ መንገድህን ደግሞ ሰዎች የመልካም ስጦታዎች ሁሉ ምንጭ ስለሆነው ስለ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ እንዲያውቁ የመርዳት አጋጣሚ ታገኝ ይሆናል፤ ይህም ደስታህ እጥፍ ድርብ እንዲሆን ያደርጋል! (ያዕቆብ 1:17) ታዲያ መስጠት የሚያስገኘውን በረከት እያጨድክ ነው?

^ አን.21 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት። መጽሐፉ www.jw.org/am ላይም ይገኛል። የሕትመት ውጤቶች > መጻሕፍትና ብሮሹሮች በሚለው ሥር ተመልከት።