“ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናል፤ . . . በሕይወት ያሉትም ከእንግዲህ ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለእነሱ ለሞተውና ለተነሳው እንዲኖሩ እሱ ለሁሉም ሞቷል።”—2 ቆሮንቶስ 5:14, 15

አንድ ልዩ የሆነ ስጦታ ሲሰጠን አድናቆታችንን መግለጽ እንዳለብን የታወቀ ነው። ኢየሱስ በወቅቱ መድኃኒት ባልነበረው አስከፊ በሽታ ተይዘው የነበሩትን አሥር ሰዎች በፈወሰበት ወቅት እንዲህ የማድረግን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። ከአሥሩ ሰዎች መካከል አንዱ “አምላክን በታላቅ ድምፅ እያመሰገነ ተመለሰ።” ከዚያም ኢየሱስ “የነጹት አሥሩም አይደሉም እንዴ? ታዲያ ዘጠኙ የት አሉ?” አለ። (ሉቃስ 17:12-17) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይህ ታሪክ ሌሎች ያሳዩንን ደግነት ቶሎ እንደምንረሳ ያሳያል።

ቤዛው ከሌሎች ስጦታዎች ሁሉ የተለየ ነው። እስካሁን ለሰው ልጆች ከተሰጡት ስጦታዎች ሁሉ እጅግ የላቀ ነው። ታዲያ አምላክ ላደረገልህ ነገር አድናቆትህን ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

  • ስጦታውን ስለሰጠው አካል ለማወቅ ጥረት አድርግየሰው ልጆች በቤዛው አማካኝነት የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ማድረግ ያለባቸው ነገር አለ። ኢየሱስ ወደ አምላክ ሲጸልይ እንዲህ ብሏል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው።” (ዮሐንስ 17:3) አንድ ሰው፣ ልጅ እያለህ ሕይወትህን እንዳተረፈልህ ብትሰማ ስለዚያ ሰውም ሆነ  አንተን ለማዳን ስለተነሳሳበት ምክንያት ይበልጥ የማወቅ ፍላጎት አይኖርህም? የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ የሚያስችለውን ቤዛ የሰጠው ይሖዋ አምላክ፣ ስለ እሱ ማንነት እንድታውቅ ብቻ ሳይሆን ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንድትመሠርት ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” የሚል ማበረታቻ ይሰጣል።—ያዕቆብ 4:8

  • በቤዛው ላይ እምነት እንዳለህ አሳይ። “በወልድ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።” (ዮሐንስ 3:36) በቤዛው ላይ እምነት እንዳለህ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምትችለው በሥራ ነው። (ያዕቆብ 2:17) ይህ ሥራ ምንድን ነው? አንድ ስጦታ የአንተ የሚሆነው ስጦታውን ስትቀበል ነው። ከቤዛው ስጦታም ተጠቃሚ ለመሆን ይህን ስጦታ መቀበል ይኖርብሃል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? አምላክን በሚያስደስት መንገድ መኖር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅና በዚያ መሠረት ለመኖር ጥረት በማድረግ ነው። * እንዲሁም አምላክ ይቅር እንዲልህና ንጹሕ ሕሊና እንዲሰጥህ መጸለይ ይኖርብሃል። በቤዛው ላይ እምነት እንዳለህ ካሳየህ ዘላቂ ሰላም፣ ደህንነት እንዲሁም እውነተኛ ደስታ እንደምታገኝ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ወደ አምላክ ቅረብ!—ዕብራውያን 11:1

  • በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝ። ኢየሱስ የቤዛውን ዝግጅት እንድናስብ ሲል በዓመት አንዴ የሚከበር በዓል አቋቁሟል። ይህን በዓል አስመልክቶ ሲናገር “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሏል። (ሉቃስ 22:19) የይሖዋ ምሥክሮች ሚያዝያ 3, 2009 ዓ.ም. (ሚያዝያ 11, 2017) ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ በዓል ያከብራሉ። አንድ ሰዓት ገደማ በሚቆየው በዚህ ፕሮግራም ላይ፣ የኢየሱስ ሞት ምን ትርጉም እንዳለውና አሁንም ሆነ ወደፊት ምን ጥቅም እንደሚያስገኝ የሚያብራራ ንግግር ይቀርባል። ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ 20 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተዋል። አንተም በዚህ በዓል ላይ በመገኘት አምላክ ለሰጠን ከሁሉ የላቀ ስጦታ ያለህን አድናቆት እንድታሳይ እንጋብዝሃለን።

^ አን.7 ስለ አምላክ ለማወቅና ወደ እሱ ለመቅረብ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን መማር ስለሚቻልበት መንገድ ለማወቅ የይሖዋ ምሥክሮችን ማነጋገር ወይም www.jw.org/am የተሰኘውን ድረ ገጻችንን መጎብኘት ትችላለህ።