በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

ሁለተኛ ዜና መዋዕል 31:1-21

የመጽሐፉ ይዘት

  • ሕዝቅያስ የሐሰት አምልኮን አስወገደ (1)

  • ካህናቱና ሌዋውያኑ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ ተደረገ (2-21)

31  ከዚህ በኋላ በዚያ የተገኙት እስራኤላውያን በሙሉ ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው በመላው ይሁዳና ቢንያም እንዲሁም በኤፍሬምና በምናሴ+ የነበሩትን የማምለኪያ ዓምዶች+ ሰባበሩ፤ የማምለኪያ ግንዶቹን*+ ቆረጡ፤ ከፍ ያሉትንም የማምለኪያ ቦታዎችና+ መሠዊያዎቹን+ አፈራረሱ፤ ምንም ያስቀሩት ነገር አልነበረም፤ ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን በሙሉ ወደየከተሞቻቸው፣ እያንዳንዳቸውም ወደየርስታቸው ተመለሱ።  ከዚያም ሕዝቅያስ ካህናቱን በየምድባቸው፣+ ሌዋውያኑንም በየምድባቸው+ ሾማቸው፤ እያንዳንዱን ካህንና ሌዋዊ በተሰጠው ሥራ መሠረት ደለደለ።+ እነሱም የሚቃጠለውን መባና የኅብረት መሥዋዕቶቹን ያቀርባሉ፣ ያገለግላሉ እንዲሁም በይሖዋ ቤተ መቅደስ ዙሪያ ባሉት የግቢዎቹ* በሮች ለእሱ ምስጋናና ውዳሴ ያቀርባሉ።+  በይሖዋ ሕግ ላይ በተጻፈው መሠረት ጠዋትና ማታ የሚቀርበውን መባ+ እንዲሁም በየሰንበቱ፣+ በየወር መባቻውና+ በበዓላት ወቅት+ የሚቀርቡትን የሚቃጠሉ መባዎች ጨምሮ ለሚቃጠሉት መባዎች+ እንዲውል ከንጉሡ ንብረት ላይ የተወሰነ ድርሻ ይሰጥ ነበር።  በተጨማሪም ሕዝቅያስ የይሖዋን ሕግ በጥብቅ መከተል* እንዲችሉ በኢየሩሳሌም የሚኖረው ሕዝብ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ ተገቢውን ድርሻ እንዲሰጥ አዘዘ።+  ትእዛዙ እንደወጣ እስራኤላውያን የእህሉን፣ የአዲሱን የወይን ጠጅ፣ የዘይቱን፣+ የማሩንና የእርሻውን ፍሬ+ ሁሉ በኩራት በብዛት ሰጡ፤ ከእያንዳንዱም ነገር ላይ አንድ አሥረኛውን አትረፍርፈው አመጡ።+  በይሁዳ ከተሞች ይኖሩ የነበሩት የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብም ከከብቶቻቸውና ከበጎቻቸው አንድ አሥረኛውን እንዲሁም ለአምላካቸው ለይሖዋ ከተለዩት ቅዱስ የሆኑ ነገሮች ላይ አንድ አሥረኛውን አመጡ።+ ያመጡትንም ብዙ ቦታ ላይ ቆለሉት።  በሦስተኛው ወር+ ያመጡትን መዋጮ መከመር የጀመሩ ሲሆን በሰባተኛው ወር+ አጠናቀቁ።  ሕዝቅያስና መኳንንቱ መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ ይሖዋን አወደሱ፤ ሕዝቡን እስራኤልንም ባረኩ።  ሕዝቅያስ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ሲጠይቃቸው 10  ከሳዶቅ ቤት የሆነው የካህናት አለቃው አዛርያስ እንዲህ አለው፦ “መዋጮውን ወደ ይሖዋ ቤት ማምጣት+ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ሕዝቡ እስኪጠግብ ድረስ ሲበላ ቆይቷል፤ ገና ያልተነካ ብዙ ነገር አለ፤ ይሖዋ ሕዝቡን ስለባረከ ይህን ያህል ብዛት ያለው ነገር ሊተርፍ ችሏል።”+ 11  በዚህ ጊዜ ሕዝቅያስ በይሖዋ ቤት ማከማቻ ክፍሎች*+ እንዲያዘጋጁ አዘዘ፤ እነሱም አዘጋጁ። 12  ከዚያም መዋጮውን፣ አንድ አሥረኛውንና*+ ቅዱስ የሆኑትን ነገሮች በታማኝነት ማምጣታቸውን ቀጠሉ፤ ሌዋዊው ኮናንያ የእነዚህ ሁሉ ነገሮች ተቆጣጣሪ ሆኖ ተሹሞ የነበረ ሲሆን ወንድሙ ሺምአይ ደግሞ የእሱ ምክትል ነበር። 13  የሂኤል፣ አዛዝያ፣ ናሃት፣ አሳሄል፣ የሪሞት፣ ዮዛባድ፣ ኤሊዔል፣ ይስማክያ፣ ማሃት እና በናያህ በንጉሥ ሕዝቅያስ ትእዛዝ ኮናንያን እና ወንድሙን ሺምአይን የሚረዱ ሹሞች ነበሩ፤ አዛርያስም የእውነተኛው አምላክ ቤት ተቆጣጣሪ ነበር። 14  የምሥራቁ በር ጠባቂ የሆነው ሌዋዊው+ የይምናህ ልጅ ቆረ ለእውነተኛው አምላክ በበጎ ፈቃድ የሚቀርቡትን መባዎች+ ይቆጣጠር ነበር፤ ደግሞም ለይሖዋ የተሰጠውን መዋጮና+ እጅግ ቅዱስ የሆኑትን ነገሮች+ ያከፋፍል ነበር። 15  በእሱም አመራር ሥር ኤደን፣ ሚንያሚን፣ የሹዋ፣ ሸማያህ፣ አማርያህ እና ሸካንያህ የነበሩ ሲሆን በየምድቦቹ ውስጥ ላሉት ወንድሞቻቸው፣+ ለትልቁም ሆነ ለትንሹ ድርሻቸውን እኩል ለማከፋፈል በካህናቱ ከተሞች+ ታማኝነት በሚጠይቅ ቦታ ላይ ተሹመው ነበር። 16  ይህም ስማቸው በትውልድ ሐረግ መዝገቡ ላይ ለሰፈሩት ሦስት ዓመትና ከዚያ በላይ ለሆናቸው ወንዶች የሚከፋፈለውን ሳይጨምር ነው፤ እነሱም በይሖዋ ቤት ለማገልገል በየዕለቱ ይመጡና እንደየምድባቸው ያሉባቸውን ኃላፊነቶች ይፈጽሙ ነበር። 17  ካህናቱ፣ 20 ዓመትና ከዚያ በላይ+ እንደሆናቸው ሌዋውያን ሁሉ በትውልድ ሐረግ መዝገቡ ላይ የሰፈሩት በየአባቶቻቸው ቤት+ እንደየምድብ ሥራቸው ነበር።+ 18  የትውልድ ሐረግ መዝገቡ ልጆቻቸውን፣ ሚስቶቻቸውን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በሙሉ፣ መላውን የሌዋውያን ማኅበረሰብ ይጨምራል፤ እነሱ በተሾሙበት ታማኝነት የሚጠይቅ ቦታ የተነሳ ቅዱስ ለሆነው ነገር ራሳቸውን ቀድሰዋል፤ 19  በተጨማሪም መዝገቡ ላይ በከተሞቻቸው ዙሪያ ባሉ የግጦሽ መሬቶች ላይ የሚኖሩት የአሮን ዘሮች የሆኑት ካህናትም ይገኛሉ።+ በሁሉም ከተሞች ውስጥ በካህናት ቤተሰብ ውስጥ ላሉት ወንዶች ሁሉና በሌዋውያን የትውልድ ሐረግ መዝገብ ላይ ለተጻፉት በሙሉ እንዲያከፋፍሉ በስም ተጠቅሰው ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንዶች ነበሩ። 20  ሕዝቅያስ በመላው ይሁዳ ይህን አደረገ፤ በአምላኩ በይሖዋም ፊት ጥሩና ትክክል የሆነውን አደረገ፤ ለእሱም ታማኝ ነበር። 21  ከእውነተኛው አምላክ ቤት+ አገልግሎት ጋርም ሆነ ከሕጉና ከትእዛዙ ጋር በተያያዘ አምላኩን ይፈልግ ዘንድ የጀመረውን ሥራ ሁሉ፣ በሙሉ ልቡ አከናወነ፤ ደግሞም ተሳካለት።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “የሰፈሮቹ።”
ወይም “ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ሕግ ማደር።”
ወይም “መመገቢያ ክፍሎች።”
ወይም “አሥራቱንና።”