በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ 12:1-21

የመጽሐፉ ይዘት

  • ጳውሎስ ያያቸው ራእዮች (1-7ሀ)

  • “ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ ተሰጠኝ” (7ለ-10)

  • ከምርጦቹ ሐዋርያት አላንስም (11-13)

  • ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያሳየው አሳቢነት (14-21)

12  ልኩራራ ይገባኛል። ምንም ጥቅም ባይኖረውም እንኳ ከጌታ የተቀበልኳቸውን ተአምራዊ ራእዮችና+ ጌታ የገለጠልኝን መልእክቶች+ እናገራለሁ።  የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነ አንድ ሰው አውቃለሁ፤ ይህ ሰው ከ14 ዓመት በፊት ወደ ሦስተኛው ሰማይ ተነጠቀ፤ የተነጠቀው በሥጋ ይሁን ከሥጋ ውጭ አላውቅም፤ አምላክ ግን ያውቃል።  አዎ፣ እንዲህ ያለ ሰው አውቃለሁ፤ በሥጋ ይሁን ከሥጋ ውጭ አላውቅም፤ አምላክ ግን ያውቃል፤  ይህ ሰው ወደ ገነት ተነጥቆ በአንደበት ሊገለጹ የማይችሉና ሰው እንዲናገራቸው ያልተፈቀዱ ቃላት ሰማ።  እንዲህ ባለው ሰው እኩራራለሁ፤ ሆኖም በድክመቶቼ ካልሆነ በስተቀር በራሴ አልኩራራም።  ልኮራ ብፈልግ እንኳ የምናገረው እውነት ስለሆነ ምክንያታዊነት እንደሚጎድለኝ ሆኜ ልቆጠር አይገባም። ይሁንና ማንም በእኔ ላይ ከሚያየውና ከእኔ ከሚሰማው በላይ እንደሆንኩ አድርጎ እንዳይገምተኝ ይህን ከማድረግ እቆጠባለሁ፤  እንዲህ ያሉ አስደናቂ ነገሮች ስለተገለጡልኝ ብቻ ማንም ሰው ለእኔ ከፍ ያለ ግምት ሊኖረው አይገባም። እንዳልታበይ ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ ተሰጠኝ፤+ ይህም እንዳልታበይ ዘወትር የሚያሠቃየኝ* የሰይጣን መልአክ* ነው።  ይህ ነገር ከእኔ እንዲርቅ ጌታን ሦስት ጊዜ ለመንኩት።  እሱ ግን “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ምክንያቱም ኃይሌ ፍጹም የሚሆነው በምትደክምበት ጊዜ ነው” አለኝ።+ እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል በእኔ ላይ እንደ ድንኳን እንዲኖር እጅግ ደስ እያለኝ በድክመቴ እኩራራለሁ። 10  ስለሆነም ስለ ክርስቶስ ስል በድክመት፣ በስድብ፣ በእጦት፣ በስደትና በችግር ደስ እሰኛለሁ። ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና።+ 11  ምክንያታዊነት የሚጎድለኝ ሆኛለሁ። እንዲህ እንድሆን ያስገደዳችሁኝ እናንተ ናችሁ፤ እናንተ ስለ እኔ ብቃት መመሥከር መቻል ነበረባችሁና። ምንም እንኳ እኔ ከምንም የማልቆጠር ብሆንም ከእናንተ የተራቀቁ ሐዋርያት በአንዲት ነገር እንኳ አላንስም።+ 12  ደግሞም የሐዋርያነቴን ማስረጃዎች በታላቅ ጽናት+ እንዲሁም ምልክቶችን፣ ድንቅ ነገሮችንና ተአምራትን በመፈጸም አሳይቻችኋለሁ።+ 13  እናንተ ከሌሎች ጉባኤዎች ያነሳችሁት በምንድን ነው? ምናልባት እኔ በእናንተ ላይ ሸክም ሳልሆን በመቅረቴ ሊሆን ይችላል፤+ እንዲህ ከሆነ ይህን ጥፋቴን በደግነት ይቅር በሉኝ። 14  እነሆ ወደ እናንተ ለመምጣት ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛ ጊዜዬ ነው፤ በእናንተ ላይ ሸክም አልሆንም። እኔ የምፈልገው እናንተን እንጂ ንብረታችሁን አይደለምና፤+ ደግሞም ለልጆቻቸው+ ሀብት ማከማቸት የሚጠበቅባቸው ወላጆች ናቸው እንጂ ልጆች ለወላጆቻቸው አያከማቹም። 15  በእኔ በኩል ስለ እናንተ* ያለኝን ሁሉ፣ ራሴንም ጭምር ብሰጥ እጅግ ደስ ይለኛል።+ እኔ ይህን ያህል አጥብቄ ከወደድኳችሁ እናንተ ለእኔ ያላችሁ ፍቅር ከዚህ ያነሰ ሊሆን ይገባል? 16  የሆነ ሆኖ ሸክም አልሆንኩባችሁም።+ ነገር ግን እናንተ “መሠሪ” እንደሆንኩና “አታልዬ” እንዳጠመድኳችሁ ትናገራላችሁ። 17  ለመሆኑ ወደ እናንተ ከላክኋቸው ሰዎች መካከል በአንዱ እንኳ ተጠቅሜ ከእናንተ አላግባብ ጥቅም ለማግኘት ሞክሬአለሁ? 18  ቲቶ ወደ እናንተ እንዲመጣ ገፋፋሁት፤ ከእሱም ጋር ወንድምን ላክሁት። ለመሆኑ ቲቶ ከእናንተ አላግባብ ጥቅም ለማግኘት ሞክሮ ነበር?+ ከእሱ ጋር በአንድ መንፈስ አልተመላለስንም? አካሄዳችንስ አንድ አልነበረም? 19  እስካሁን ድረስ የምታስቡት እኛ ለእናንተ የመከላከያ መልስ እየሰጠን እንዳለን አድርጋችሁ ነው? እኛ የክርስቶስ ተከታዮች ሆነን የምንናገረው በአምላክ ፊት ነው። ይሁንና የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ሁሉንም ነገር የምናደርገው እናንተን ለማነጽ ነው። 20  እኔ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ ምናልባት እኔ እንደምፈልገው ሳትሆኑ እንዳላገኛችሁ፣ እናንተም እኔን እንደምትፈልጉት ሆኜ ሳታገኙኝ እንዳትቀሩ እሰጋለሁ፤ እንዲያውም ጠብ፣ ቅናት፣ ኃይለኛ ቁጣ፣ ንትርክ፣ ስም ማጥፋት፣ ሐሜትና ብጥብጥ እንዲሁም በኩራት የተወጠሩ ሰዎች እንዳይኖሩ እሰጋለሁ። 21  እንደገና በምመጣበት ጊዜ ምናልባት አምላኬ በፊታችሁ ያሳፍረኝ ይሆናል፤ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ኃጢአት ፈጽመው ከሠሩት ርኩሰት፣ የፆታ ብልግናና* ዓይን ያወጣ ምግባር* ንስሐ ባልገቡት በርካታ ሰዎች አዝን ይሆናል ብዬ እፈራለሁ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የሚመታኝ።”
ወይም “መልእክተኛ።”
ወይም “ስለ ነፍሳችሁ።”
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “እፍረተ ቢስነት የሚንጸባረቅበት ምግባር።” ግሪክኛ፣ አሴልጊያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።