በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

አንደኛ ነገሥት 9:1-28

የመጽሐፉ ይዘት

  • ይሖዋ ዳግመኛ ለሰለሞን ተገለጠለት (1-9)

  • ሰለሞን ለንጉሥ ኪራም የሰጠው ስጦታ (10-14)

  • ሰለሞን ያከናወናቸው የተለያዩ ግንባታዎች (15-28)

9  ሰለሞን የይሖዋን ቤትና የንጉሡን ቤት*+ እንዲሁም ለመሥራት የፈለገውን ነገር ሁሉ ገንብቶ እንደጨረሰ+  ይሖዋ በገባኦን እንደተገለጠለት አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ ተገለጠለት።+  ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “በፊቴ የጸለይከውን ጸሎትና ሞገስ ለማግኘት ያቀረብከውን ልመና ሰምቻለሁ። የገነባኸውን ይህን ቤት ስሜ ለዘለቄታው እንዲጠራበት በማድረግ+ ቀድሼዋለሁ፤ ዓይኔም ሆነ ልቤ ሁልጊዜ በዚያ ይሆናል።+  አንተም አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ያዘዝኩህን ሁሉ በመፈጸም+ በንጹሕ ልብና+ በቅንነት+ በፊቴ ብትሄድ+ እንዲሁም ሥርዓቶቼንና ፍርዴን ብትጠብቅ+  ለአባትህ ለዳዊት ‘ከዘር ሐረግህ በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው አይታጣም’ በማለት በገባሁለት ቃል መሠረት የመንግሥትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።+  ሆኖም እናንተም ሆናችሁ ልጆቻችሁ እኔን ከመከተል ዞር ብትሉ እንዲሁም በፊታችሁ ያስቀመጥኳቸውን ትእዛዛቴንና ደንቦቼን ባትጠብቁ፣ ሄዳችሁም ሌሎች አማልክትን ብታገለግሉና ለእነሱ ብትሰግዱ+  እስራኤላውያንን ከሰጠኋቸው ምድር ላይ አጠፋቸዋለሁ፤+ ለስሜ የቀደስኩትንም ቤት ከፊቴ አስወግደዋለሁ፤+ እስራኤላውያንም በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ መቀለጃና* መሳለቂያ ይሆናሉ።+  ይህም ቤት የፍርስራሽ ክምር ይሆናል።+ በዚያም የሚያልፉ ሰዎች ሁሉ በመገረም ትኩር ብለው እየተመለከቱ ‘ይሖዋ በዚህች ምድርና በዚህ ቤት ላይ እንዲህ ያለ ነገር ያደረገው ለምንድን ነው?’+ በማለት ያፏጫሉ።  ከዚያም እንዲህ ይላሉ፦ ‘ይህ የደረሰባቸው አባቶቻቸውን ከግብፅ ምድር ያወጣውን አምላካቸውን ይሖዋን ትተው ሌሎች አማልክትን ስለተከተሉና ለእነሱ ስለሰገዱ እንዲሁም እነሱን ስላገለገሉ ነው። ይሖዋ ይህን ሁሉ መከራ ያመጣባቸው ለዚህ ነው።’”+ 10  ሰለሞን ሁለቱን ቤቶች ይኸውም የይሖዋን ቤትና የንጉሡን ቤት* ገንብቶ በጨረሰበት በ20ኛው ዓመት ማብቂያ ላይ+ 11  የጢሮስ ንጉሥ ኪራም+ ለሰለሞን የሚፈልገውን ያህል የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎች፣ የጥድ ዛፍ ሳንቃዎችና ወርቅ ሰጠው፤+ ንጉሥ ሰለሞን ደግሞ ለኪራም በገሊላ ምድር የሚገኙ 20 ከተሞችን ሰጠው። 12  ስለሆነም ኪራም ሰለሞን የሰጠውን ከተሞች ለማየት ከጢሮስ ወጥቶ ሄደ፤ ሆኖም በከተሞቹ አልተደሰተም። 13  እሱም “ወንድሜ ሆይ፣ የሰጠኸኝ ምን ዓይነት ከተሞችን ነው?” አለው። ስለዚህ እነዚህ ከተሞች እስከ ዛሬ ድረስ የካቡል ምድር* ተብለው ይጠራሉ። 14  ይህ በእንዲህ እንዳለ ኪራም ለንጉሡ 120 ታላንት* ወርቅ ላከለት።+ 15  ንጉሥ ሰለሞን የይሖዋን ቤት፣+ የራሱን ቤት፣* ጉብታውን፣*+ የኢየሩሳሌምን ቅጥር፣ ሃጾርን፣+ መጊዶንና+ ጌዜርን+ እንዲገነቡ ስለመለመላቸው የግዳጅ ሥራ የሚሠሩ ሠራተኞች+ የሚገልጸው ዘገባ ይህ ነው። 16  (የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ወጥቶ ጌዜርን ያዘ፤ በእሳትም አቃጠላት፤ በተጨማሪም በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩትን ከነአናውያን+ ገደለ። ከተማዋንም የሰለሞን ሚስት ለሆነችው ለልጁ ጎጆ መውጫ* አድርጎ ሰጣት።)+ 17  ሰለሞንም ጌዜርንና ታችኛውን ቤትሆሮንን+ ሠራ፤ 18  በተጨማሪም ባዓላትን፣+ በምድሩ በሚገኘው ምድረ በዳ ውስጥ ያለችውን ትዕማርን 19  እንዲሁም የሰለሞንን የእህልና የዕቃ ማከማቻ ከተሞች በሙሉ፣ የሠረገላ ከተሞቹን፣+ የፈረሰኞቹን ከተሞች እንዲሁም ሰለሞን በኢየሩሳሌም፣ በሊባኖስና በእሱ ግዛት ውስጥ ባለው ምድር ሁሉ መገንባት የፈለጋቸውን ነገሮች በሙሉ ሠራ። 20  ከእስራኤላውያን ወገን ያልሆኑትን+ ከአሞራውያን፣ ከሂታውያን፣ ከፈሪዛውያን፣ ከሂዋውያንና ከኢያቡሳውያን+ የተረፉትን ሕዝቦች በሙሉ 21  ይኸውም እስራኤላውያን ፈጽመው ሊያጠፏቸው ያልቻሏቸውን በምድሪቱ ላይ የቀሩትን ዘሮቻቸውን ሰለሞን እንደ ባሪያ ሆነው የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ መልምሏቸው ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ ይሠራሉ።+ 22  ሆኖም ሰለሞን ከእስራኤላውያን መካከል አንዳቸውንም ባሪያ አላደረገም፤+ ምክንያቱም እነሱ ተዋጊዎቹ፣ አገልጋዮቹ፣ መኳንንቱ፣ የጦር መኮንኖቹ እንዲሁም የሠረገለኞቹና የፈረሰኞቹ አለቆች ነበሩ። 23  ሰለሞን የሚያሠራውን ሥራ የሚከታተሉት ይኸውም ሥራውን የሚሠሩትን ሰዎች በቅርብ የሚቆጣጠሩት የበታች ተቆጣጣሪዎቹ አለቆች 550 ነበሩ።+ 24  የፈርዖን ሴት ልጅ+ ግን ከዳዊት ከተማ+ ወጥታ ሰለሞን ወዳሠራላት ወደ ራሷ ቤት መጣች፤ ከዚያም ጉብታውን*+ ሠራ። 25  ሰለሞን በዓመት ሦስት ጊዜ+ ለይሖዋ በሠራው መሠዊያ ላይ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችንና የኅብረት መሥዋዕቶችን ያቀርብ ነበር፤+ በተጨማሪም በይሖዋ ፊት በነበረው መሠዊያ ላይ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር፤ ቤቱንም አጠናቀቀ።+ 26  እንዲሁም ንጉሥ ሰለሞን በኤዶም ምድር+ በቀይ ባሕር ዳርቻ በኤሎት አጠገብ በምትገኘው በዔጽዮንጋብር+ መርከቦችን ሠራ። 27  ኪራምም ከሰለሞን አገልጋዮች ጋር አብረው እንዲሠሩ አገልጋዮቹን ይኸውም ልምድ ያላቸውን ባሕረኞች ከእነዚህ መርከቦች ጋር ላከ።+ 28  እነሱም ወደ ኦፊር+ በመሄድ 420 ታላንት ወርቅ አምጥተው ለንጉሥ ሰለሞን ሰጡት።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “መተረቻና።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
“የማይረባ ምድር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ሚሎን።” “መሙላት” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል ነው።
ወይም “የሠርግ ስጦታ።”
ወይም “ሚሎን።” “መሙላት” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል ነው።