በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

አንደኛ ነገሥት 7:1-51

የመጽሐፉ ይዘት

  • የሰለሞን ቤተ መንግሥት (1-12)

  • ከፍተኛ ችሎታና ልምድ የነበረው ኪራም ሰለሞንን ረዳው (13-47)

    • ሁለቱ የመዳብ ዓምዶች (15-22)

    • ከቀለጠ ብረት የተሠራው ባሕር (23-26)

    • አሥሩ የዕቃ ማጓጓዣ ጋሪዎችና የመዳብ ገንዳዎቹ (27-39)

  • ከወርቅ የተሠሩት ዕቃዎች (48-51)

7  ሰለሞንም የራሱን ቤት*+ ሙሉ በሙሉ ሠርቶ ለማጠናቀቅ 13 ዓመት ፈጀበት።+  እሱም የሊባኖስ ደን+ የተባለውን ርዝመቱ 100 ክንድ፣* ወርዱ 50 ክንድ፣ ቁመቱ ደግሞ 30 ክንድ የሆነ ቤት በአራት ረድፍ በተደረደሩ የአርዘ ሊባኖስ ዓምዶች ገነባ፤ በዓምዶቹም ላይ የአርዘ ሊባኖስ ወራጆች+ ነበሩ።  ቤቱም በዓምዶቹ ላይ ባረፉት አግዳሚዎች ላይ የተረበረቡ የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎች ነበሩት፤ ዓምዶቹም* 45 ሲሆኑ በአንዱ ረድፍ ላይ 15 ነበሩ።  በሦስት ረድፍ የተሠሩ ባለ ክፈፍ መስኮቶች ነበሩ፤ በሦስቱም ደርቦች ላይ እያንዳንዱ መስኮት ከሌላኛው መስኮት ጋር ትይዩ ነበር።  በሦስቱ ደርቦች ላይ ያሉት ትይዩ የሆኑ መስኮቶች ከፊት ለፊት ሲታዩ አራት ማዕዘን እንደሆኑ ሁሉ መግቢያዎቹና መቃኖቹም በሙሉ እንዲሁ ነበሩ።  እሱም ርዝመቱ 50 ክንድ፣ ወርዱ ደግሞ 30 ክንድ የሆነ የዓምዶች መተላለፊያ* ሠራ፤ ከፊት ለፊቱም ዓምዶችና ታዛ ያለው በረንዳ ነበር።  በተጨማሪም ፍርድ የሚሰጥበትን የዙፋን+ አዳራሽ* ይኸውም የፍርድ+ አዳራሹን ሠራ፤ አዳራሹንም ከወለሉ አንስቶ እስከ ወራጆቹ ድረስ በአርዘ ሊባኖስ ለበጡት።  በሌላኛው ግቢ+ ያለው ራሱ የሚኖርበት ቤት* የሚገኘው ከአዳራሹ* ጀርባ ሲሆን አሠራራቸውም ተመሳሳይ ነበር። በተጨማሪም ሰለሞን ላገባት ለፈርዖን ልጅ ከዚህ አዳራሽ ጋር የሚመሳሰል ቤት ሠርቶላት ነበር።+  እነዚህ ሁሉ ከውጭ አንስቶ እስከ ትልቁ ግቢ+ ድረስ፣ ከመሠረቱ እስከ ድምድማቱ፣ በውስጥም በውጭም ተለክተው በተጠረቡና በድንጋይ መጋዝ በተቆረጡ ውድ ድንጋዮች የተሠሩ ነበሩ።+ 10  መሠረቱ የተጣለው ውድ በሆኑ ትላልቅ ድንጋዮች ነበር፤ አንዳንዶቹ ድንጋዮች ባለ አሥር ክንድ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ባለ ስምንት ክንድ ነበሩ። 11  በእነዚህም ላይ ተለክተው የተጠረቡ ውድ ድንጋዮችና የአርዘ ሊባኖስ እንጨቶች ነበሩ። 12  ለይሖዋ ቤት ውስጠኛ ግቢና+ ለቤቱ በረንዳ+ እንደተደረገው ሁሉ የትልቁ ግቢ አጥር የተሠራው በሦስት ረድፍ ጥርብ ድንጋይና በአንድ ረድፍ የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃ ነበር። 13  ንጉሥ ሰለሞን መልእክተኛ ልኮ ኪራምን+ ከጢሮስ አስመጣው። 14  ኪራም ከንፍታሌም ነገድ የሆነች የአንዲት መበለት ልጅ ነበር፤ አባቱ የጢሮስ ሰው ሲሆን የመዳብ ሥራ ባለሙያ+ ነበር፤ ኪራም ከማንኛውም የመዳብ* ሥራ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችሎታ፣ ማስተዋልና+ ልምድ ነበረው። በመሆኑም ወደ ንጉሥ ሰለሞን መጥቶ ሥራዎቹን ሁሉ አከናወነለት። 15  እሱም ሁለቱን ዓምዶች+ ከቀለጠ መዳብ ሠራ፤ እያንዳንዱም ዓምድ ቁመቱ 18 ክንድ ነበር፤ ሁለቱ ዓምዶች እያንዳንዳቸው በመለኪያ ገመድ ሲለኩ መጠነ ዙሪያቸው 12 ክንድ ነበር።+ 16  እንዲሁም በዓምዶቹ አናት ላይ የሚሆኑ ሁለት የዓምድ ራሶችን ከመዳብ ሠራ። የአንደኛው የዓምድ ራስ ቁመት አምስት ክንድ የሌላኛው የዓምድ ራስ ቁመትም አምስት ክንድ ነበር። 17  በእያንዳንዱ ዓምድ አናት ላይ ያለው የዓምድ ራስ በሰንሰለት ጉንጉን የተሠሩ መረቦች ነበሩት፤+ በአንደኛው የዓምድ ራስ ላይ ሰባት በሌላኛው የዓምድ ራስ ላይም ሰባት ነበሩ። 18  በዓምዶቹ አናት ላይ ያሉትን የዓምድ ራሶች ለማስጌጥ በአንደኛው መረብ ዙሪያ ሮማኖችን በሁለት ረድፍ ሠራ፤ በሁለቱም የዓምድ ራሶች ላይ እንዲሁ አደረገ። 19  በረንዳው አጠገብ በሚገኙት ዓምዶች አናት ላይ ያሉት የዓምድ ራሶች አራት ክንድ ቁመት ያለው የአበባ ቅርጽ ነበራቸው። 20  የዓምድ ራሶቹ በሁለቱ ዓምዶች ላይ፣ ልክ ከመረብ ሥራው ቀጥሎ ካለው ከሆዱ በላይ ነበሩ፤ በእያንዳንዱ የዓምድ ራስ ዙሪያ 200 ሮማኖች በረድፍ ተደርድረው ነበር።+ 21  እሱም የቤተ መቅደሱን* በረንዳ ዓምዶች አቆመ።+ በስተ ቀኝ* ያለውን ዓምድ አቁሞ ያኪን* ብሎ ሰየመው፤ ከዚያም በስተ ግራ* ያለውን ዓምድ አቁሞ ቦዔዝ* ብሎ ሰየመው።+ 22  የዓምዶቹም አናቶች የአበባ ቅርጽ ነበራቸው። በዚህ መንገድ የዓምዶቹ ሥራ ተጠናቀቀ። 23  ከዚያም ባሕሩን* በቀለጠ ብረት ሠራ።+ ባሕሩ ክብ ቅርጽ የነበረው ሲሆን ከአንዱ ጠርዝ እስከ ሌላኛው ጠርዝ 10 ክንድ፣ ከፍታው ደግሞ 5 ክንድ ነበር፤ መጠነ ዙሪያውም በመለኪያ ገመድ ሲለካ 30 ክንድ ሆነ።+ 24  በባሕሩም ዙሪያ ከጠርዙ ዝቅ ብሎ በእያንዳንዱ ክንድ ላይ በቅል ቅርጽ+ የተሠሩ አሥር ጌጦች ነበሩ፤ ቅሎቹም በሁለት ረድፍ ከባሕሩ ጋር አንድ ወጥ ሆነው ተሠርተው ነበር። 25  ባሕሩ 3ቱ ወደ ሰሜን፣ 3ቱ ወደ ምዕራብ፣ 3ቱ ወደ ደቡብ እንዲሁም 3ቱ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ፊታቸውን ባደረጉ 12 በሬዎች+ ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ባሕሩም ላያቸው ላይ ነበር፤ የሁሉም ሽንጥ ወደ መሃል ገባ ያለ ነበር። 26  የውኃ ማጠራቀሚያው ውፍረት አንድ ጋት* ነበር፤ ጠርዙ የጽዋ ከንፈር ይመስል የነበረ ሲሆን በአበባ ቅርጽ የተሠራ ነበር። የውኃ ማጠራቀሚያውም 2,000 የባዶስ መስፈሪያ* ይይዝ ነበር። 27  ከዚያም አሥር የዕቃ ማጓጓዣ ጋሪዎችን*+ ከመዳብ ሠራ። እያንዳንዱ ጋሪ ርዝመቱ አራት ክንድ፣ ወርዱ አራት ክንድ፣ ቁመቱ ደግሞ ሦስት ክንድ ነበር። 28  የጋሪዎቹ አሠራር እንዲህ ነበር፦ ጋሪዎቹ የጎን መከለያ ነበራቸው፤ የጎን መከለያዎቹም በፍርግርግ መካከል ነበሩ። 29  በፍርግርጎቹ መሃል በነበሩት የጎን መከለያዎች ላይ የአንበሶች፣+ የበሬዎችና የኪሩቦች+ ምስል ነበር፤ በፍርግርጎቹም ላይ እንዲሁ ዓይነት ምስል ነበር። ከአንበሶቹና ከበሬዎቹ በላይና በታች፣ የተንጠለጠሉ የአበባ ጉንጉኖች የሚመስሉ ቅርጾች ነበሩ። 30  እያንዳንዱ የዕቃ ማጓጓዣ ጋሪ አራት የመዳብ መንኮራኩሮችና* የመዳብ ዘንጎች ነበሩት፤ በአራቱ ማዕዘኖች ላይ ያሉት ቋሚዎች ደግሞ ድጋፍ ይሆኗቸው ነበር። ድጋፎቹ ከገንዳው በታች ነበሩ፤ እያንዳንዳቸውም በጎናቸው ወጥ ሆኖ የተሠራ የአበባ ጉንጉን የሚመስል ቅርጽ ነበራቸው። 31  የገንዳው አፍ ያለው በጋሪው አናት ውስጥ ሲሆን አንድ ክንድ ከፍታ ነበረው፤ የጋሪው አፍ ክብ ነበር፤ በአፉ ላይ ያለው ማስቀመጫ አንድ ክንድ ተኩል ከፍታ ነበረው፤ በአፉም ላይ የተቀረጹ ምስሎች ነበሩ። የጎን መከለያዎቹም አራት ማዕዘን እንጂ ክብ አልነበሩም። 32  አራቱ መንኮራኩሮች ከጎን መከለያዎቹ በታች ነበሩ፤ የመንኮራኩሮቹ ድጋፎች ከጋሪው ጋር ተያይዘው ነበር፤ የእያንዳንዱ መንኮራኩር ቁመት አንድ ክንድ ተኩል ነበር። 33  የመንኮራኩሮቹ አሠራር ከሠረገላ መንኮራኩር* አሠራር ጋር ተመሳሳይ ነበር። የመንኮራኩሮቹ ድጋፎች፣ ክፈፎች፣* ራጂዎችና አቃፊዎች ሁሉ ከቀለጠ ብረት የተሠሩ ነበሩ። 34  በእያንዳንዱ ጋሪ አራት ማዕዘኖች ላይ አራት ድጋፎች ነበሩ፤ ድጋፎቹም የጋሪው ክፍል ሆነው* የተሠሩ ነበሩ። 35  በጋሪው አናት ላይ ቁመቱ ግማሽ ክንድ የሆነ ክብ ክፈፍ ነበር፤ እንዲሁም በጋሪው አናት ላይ የሚገኙት ፍርግርጎችና የጎን መከለያዎች የጋሪው ክፍል ሆነው* የተሠሩ ነበሩ። 36  በፍርግርጎቹና በጎን መከለያዎቹም ላይ እንደ ስፋታቸው ኪሩቦችን፣ አንበሶችንና የዘንባባ ዛፍ ምስሎችን ቀረጸባቸው፤ ዙሪያውንም የአበባ ጉንጉን ምስል ሠራበት።+ 37  አሥሩን ጋሪዎች+ የሠራው በዚህ መንገድ ነበር፤ ሁሉም አንድ ዓይነት መጠንና ቅርጽ እንዲኖራቸው ተደርገው በተመሳሳይ መንገድ ቀልጠው የተሠሩ ነበሩ።+ 38  እሱም አሥር የመዳብ ገንዳዎችን+ ሠራ፤ እያንዳንዱ ገንዳ 40 የባዶስ መስፈሪያ ይይዝ ነበር። እያንዳንዱ ገንዳ አራት ክንድ ነበር።* በአሥሩም ጋሪዎች ላይ አንድ አንድ ገንዳ ነበር። 39  ከዚያም አምስቱን ጋሪዎች ከቤቱ በስተ ቀኝ በኩል አምስቱን ጋሪዎች ደግሞ ከቤቱ በስተ ግራ በኩል አደረጋቸው፤ ባሕሩንም ከቤቱ በስተ ቀኝ በኩል፣ በስተ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ አስቀመጠው።+ 40  በተጨማሪም ኪራም+ ገንዳዎቹን፣ አካፋዎቹንና+ ጎድጓዳ ሳህኖቹን+ ሠራ። ኪራምም በይሖዋ ቤት ለንጉሥ ሰለሞን ያከናውን የነበረውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ።+ የሠራቸውም ነገሮች እነዚህ ነበሩ፦ 41  ሁለቱ ዓምዶች፣+ በሁለቱ ዓምዶች አናት ላይ የነበሩት የጎድጓዳ ሳህን ቅርጽ ያላቸው የዓምድ ራሶች፣ በዓምዶቹ አናት ላይ የነበሩትን የጎድጓዳ ሳህን ቅርጽ ያላቸውን ሁለቱን ክብ የዓምድ ራሶች የሚያስጌጡት ሁለት መረቦች፣+ 42  ለሁለቱ መረቦች የተሠሩት 400 ሮማኖች+ ማለትም በሁለቱ ዓምዶች አናት ላይ የነበሩትን የጎድጓዳ ሳህን ቅርጽ ያላቸው የዓምድ ራሶች ለማስጌጥ የተሠሩት በእያንዳንዱ መረብ ላይ በሁለት ረድፍ የተደረደሩት ሮማኖች፣ 43  አሥሩ ጋሪዎችና+ በጋሪዎቹ ላይ የነበሩት አሥር የውኃ ገንዳዎች፣+ 44  ባሕሩና+ ከሥሩ የነበሩት 12 በሬዎች፣ 45  አመድ ማጠራቀሚያዎቹ፣ አካፋዎቹ፣ ጎድጓዳ ሳህኖቹና ኪራም ለይሖዋ ቤት እንዲሆኑ ለንጉሥ ሰለሞን ከተወለወለ መዳብ የሠራቸው ዕቃዎች በሙሉ። 46  ንጉሡ እነዚህ ነገሮች በዮርዳኖስ አውራጃ በሱኮትና በጻረታን መካከል በሚገኝ ስፍራ ከሸክላ በተሠሩ ቅርጽ ማውጫዎች ውስጥ ቀልጠው እንዲሠሩ አደረገ። 47  ሰለሞን ዕቃዎቹ ሁሉ እንዲመዘኑ አላደረገም፤ ምክንያቱም ዕቃዎቹ እጅግ ብዙ ነበሩ። የመዳቡ ክብደት ምን ያህል እንደሆነ አልታወቀም።+ 48  ሰለሞንም ለይሖዋ ቤት መገልገያ የሚሆኑትን የሚከተሉትን ነገሮች ሠራ፦ የወርቅ መሠዊያውን፣+ ገጸ ኅብስት የሚቀመጥበትን የወርቅ ጠረጴዛ፣+ 49  በውስጠኛው ክፍል ፊት በቀኝና በግራ የሚቀመጡትን ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ+ አምስት አምስት መቅረዞች፣+ ከወርቅ የተሠሩትን የፈኩ አበቦች፣+ መብራቶችና መቆንጠጫዎች፣ 50  ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩትን ሳህኖች፣ የእሳት ማጥፊያዎች፣+ ጎድጓዳ ሳህኖች፣ ጽዋዎችና+ መኮስተሪያዎች+ እንዲሁም ከወርቅ የተሠሩትን የውስጠኛው ክፍል+ ማለትም የቅድስተ ቅዱሳኑ በሮችና የመቅደሱ በሮች+ የሚሽከረከሩባቸውን መቆሚያዎች። 51  በዚህ ሁኔታ ንጉሥ ሰለሞን ከይሖዋ ቤት ጋር በተያያዘ መሥራት የሚገባውን ሥራ በሙሉ አጠናቀቀ። ከዚያም ሰለሞን አባቱ ዳዊት የቀደሳቸውን ነገሮች ወደዚያ አስገባ፤+ ብሩን፣ ወርቁንና ዕቃዎቹን በይሖዋ ቤት ግምጃ ቤቶች ውስጥ አስቀመጠ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ቤተ መንግሥት።”
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ክፍሎቹም” አሊያም “ወራጆቹም።” ዕብራይስጡ ‘አሥራ አምስት’ መሆናቸውን ከመግለጽ ውጭ ምንነታቸውን አይናገርም።
ወይም “በረንዳ።”
ወይም “በረንዳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “ከአዳራሹ ቤት።”
ወይም “የነሐስ።” በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ቀጥሎ በሚገኝባቸው ቦታዎች ላይም ይሠራል።
ቅድስቱን ያመለክታል።
ወይም “በስተ ደቡብ።”
“እሱ [ይሖዋን ያመለክታል] አጽንቶ ይመሥርት” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “በስተ ሰሜን።”
“በብርታት” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል።
ወይም “የውኃ ማጠራቀሚያውን።”
ወደ 7.4 ሴንቲ ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ባዶስ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “የውኃ ማጓጓዣ ጋሪዎችን።”
ተሽከርካሪ እግር።
ተሽከርካሪ እግር።
ወይም “ቸርኬዎች።”
ወይም “ከጋሪው ጋር ወጥ ሆነው።”
ወይም “ከጋሪው ጋር ወጥ ሆነው።”
ወይም “መሃል ለመሃል ሲለካ አራት ክንድ ነበር።”