በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

1 ነገሥት 6:1-38

የመጽሐፉ ይዘት

  • ሰለሞን ቤተ መቅደሱን ሠራ (1-38)

    • የውስጠኛው ክፍል (19-22)

    • ኪሩቦች (23-28)

    • ግድግዳው ላይ የተቀረጹት ምስሎች፣ በሮቹና የውስጠኛው ግቢ (29-36)

    • ቤተ መቅደሱን ገንብቶ ለመጨረስ ሰባት ዓመት ገደማ ፈጀ (37, 38)

6  እስራኤላውያን* ከግብፅ ምድር በወጡ+ በ480ኛው ዓመት ይኸውም ሰለሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ዚፍ*+ በተባለው በሁለተኛው ወር ሰለሞን የይሖዋን ቤት መሥራት ጀመረ።*+  ንጉሥ ሰለሞን ለይሖዋ የሠራው ቤት ርዝመቱ 60 ክንድ፣* ወርዱ 20 ክንድ፣ ቁመቱ ደግሞ 30 ክንድ ነበር።+  ከቅድስቱ* ፊት ለፊት ያለው በረንዳ+ ርዝመቱ* 20 ክንድ ሲሆን ይህም ከቤቱ ወርድ ጋር እኩል ነው። በረንዳው ከቤቱ አሥር ክንድ ወደ ፊት ወጣ ያለ ነበር።  ለቤቱም እየጠበቡ የሚሄዱ ክፈፎች*+ ያሏቸውን መስኮቶች ሠራ።  በተጨማሪም በቤቱ ግድግዳ ዙሪያ ተቀጥላ ቤት ሠራ። ቤቱ የተሠራው በቤቱ ግድግዳ ዙሪያ ይኸውም በቤተ መቅደሱና* በውስጠኛው ክፍል+ ግድግዳ ዙሪያ ነበር፤ በዚህ መንገድ በዙሪያው ተቀጥላ ክፍሎችን ሠራ።+  የታችኛው ተቀጥላ ክፍል ወርድ አምስት ክንድ፣ የመካከለኛው ወርድ ስድስት ክንድ፣ የላይኛው ወርድ ደግሞ ሰባት ክንድ ነበር፤ ከቤቱ ግድግዳ ጋር የሚያያዝ ምንም ነገር እንዳይኖር በቤቱ ግድግዳ ዙሪያ ተሸካሚዎችን* ሠርቶ ነበር።+  ቤቱ የተገነባው ሁሉ ነገር ባለቀለት ተፈልፍሎ በወጣ ድንጋይ ነበር፤+ በመሆኑም ቤቱ በተገነባበት ጊዜ የመዶሻ ወይም የመጥረቢያ አሊያም የማንኛውም የብረት መሣሪያ ድምፅ ቤቱ ውስጥ አልተሰማም።  የታችኛው ተቀጥላ ክፍል መግቢያ የሚገኘው በስተ ደቡብ* በኩል ባለው የቤቱ ጎን ነበር፤+ በተጨማሪም ከታችኛው ወደ መካከለኛው ደርብ እንዲሁም ከመካከለኛው ወደ ላይኛው ደርብ የሚያስወጣ ጠመዝማዛ ደረጃ ነበር።  እሱም ቤቱን ገንብቶ አጠናቀቀ፤+ ቤቱንም ከአርዘ ሊባኖስ በተሠሩ ተሸካሚዎችና ርብራቦች ከደነው።+ 10  በቤቱ ዙሪያ እያንዳንዳቸው ቁመታቸው አምስት ክንድ የሆነ ተቀጥላ ክፍሎችን ሠራ፤+ ክፍሎቹም ከቤቱ ጋር በአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎች ተያይዘው ነበር። 11  ይህ በእንዲህ እንዳለ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሰለሞን መጣ፦ 12  “በደንቦቼ ብትሄድ፣ ፍርዶቼን ብትፈጽምና በትእዛዛቴ መሠረት በመሄድ ሁሉንም ብትጠብቃቸው+ እኔም እየገነባህ ያለኸውን ይህን ቤት በተመለከተ ለአባትህ ለዳዊት የገባሁለትን ቃል እፈጽምልሃለሁ፤+ 13  እንዲሁም በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁ፤+ ሕዝቤን እስራኤልንም አልተውም።”+ 14  ሰለሞንም ቤቱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የግንባታ ሥራውን ገፋበት። 15  ውስጠኛውን የቤቱን ግድግዳ በአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎች ሠራ። ቤቱንም ከወለሉ አንስቶ እስከ ኮርኒሱ ወራጆች ድረስ በሳንቃ ለበጠ፤ የቤቱንም ወለል በጥድ ጣውላ ለበጠው።+ 16  እንዲሁም ከቤቱ በስተ ኋላ በኩል ከወለሉ አንስቶ እስከ ወራጁ ድረስ በአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎች የተሠራ ባለ 20 ክንድ ክፍል ገነባ፤ በውስጡም፣* የውስጠኛውን ክፍል+ ይኸውም ቅድስተ ቅዱሳኑን+ ሠራ። 17  ከፊቱ ያለው የቤቱ ክፍል ይኸውም ቤተ መቅደሱ*+ 40 ክንድ ነበር። 18  በቤቱ በውስጠኛው በኩል ያለው አርዘ ሊባኖስ የቅሎችና+ የፈኩ አበቦች+ ምስል ተቀርጾበት ነበር። ሙሉ በሙሉ በአርዘ ሊባኖስ የተሠራ ነበር፤ ምንም የሚታይ ድንጋይ አልነበረም። 19  እሱም የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት+ በዚያ ለማስቀመጥ ቤቱ ውስጥ የውስጠኛውን ክፍል+ አዘጋጀ። 20  ውስጠኛው ክፍል ርዝመቱ 20 ክንድ፣ ወርዱ 20 ክንድ እንዲሁም ቁመቱ 20 ክንድ ነበር፤+ በንጹሕ ወርቅም ለበጠው፤ መሠዊያውንም+ በአርዘ ሊባኖስ ለበጠው። 21  ሰለሞን ቤቱን ከውስጥ በኩል በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤+ በወርቅ በተለበጠው በውስጠኛው ክፍል+ ፊት ለፊትም የወርቅ ሰንሰለት ዘረጋ። 22  ቤቱ ሙሉ በሙሉ እስኪለበጥ ድረስ ቤቱን በሙሉ በወርቅ ለበጠው፤ በውስጠኛው ክፍል አጠገብ ያለውን መሠዊያም+ ሙሉ በሙሉ በወርቅ ለበጠው። 23  በውስጠኛው ክፍል ውስጥ እያንዳንዳቸው አሥር ክንድ ቁመት ያላቸውን+ ሁለት ኪሩቦች+ ከጥድ እንጨት* ሠራ። 24  የኪሩቡ አንድ ክንፍ አምስት ክንድ ሲሆን ሌላኛውም ክንፉ አምስት ክንድ ነበር። ከአንዱ ክንፍ ጫፍ እስከ ሌላው ክንፍ ጫፍ አሥር ክንድ ነበር። 25  ሁለተኛውም ኪሩብ አሥር ክንድ ነበር። ሁለቱ ኪሩቦች ተመሳሳይ መጠንና ቅርጽ ነበራቸው። 26  የአንደኛው ኪሩብ ቁመት አሥር ክንድ ነበር፤ የሌላኛውም ኪሩብ እንደዚሁ ነበር። 27  ከዚያም ኪሩቦቹን+ ውስጠኛው ክፍል* ውስጥ አስቀመጣቸው። የኪሩቦቹም ክንፎች ተዘርግተው ስለነበር የአንደኛው ኪሩብ ክንፍ አንደኛው ግድግዳ ጋ፣ የሌላኛው ኪሩብ ክንፍ ደግሞ ሌላኛው ግድግዳ ጋ ይደርስ ነበር፤ ወደ ቤቱ መሃል የተዘረጉት ክንፎቻቸው ደግሞ ይነካኩ ነበር። 28  ኪሩቦቹንም በወርቅ ለበጣቸው። 29  በቤቱ ግድግዳ ሁሉ ላይ ይኸውም በውስጠኛውና በውጨኛው ክፍሎች ዙሪያ ሁሉ የኪሩቦችን፣+ የዘንባባ ዛፎችንና+ የፈኩ አበቦችን+ ምስል ቀረጸ፤ 30  የቤቱን ወለል ይኸውም የውስጠኛውንም ሆነ የውጨኛውን ክፍሎች ወለል በወርቅ ለበጠው። 31  ለውስጠኛው ክፍል መግቢያ የሚሆኑ በሮችን፣ በጎንና በጎን የሚቆሙ ዓምዶችንና መቃኖችን አንድ አምስተኛ* አድርጎ ከጥድ እንጨት ሠራ። 32  ሁለቱ በሮች ከጥድ እንጨት የተሠሩ ነበሩ፤ በበሮቹም ላይ የኪሩቦችን፣ የዘንባባ ዛፎችንና የፈኩ አበቦችን ምስል ቀረጸባቸው፤ በወርቅም ለበጣቸው፤ ደግሞም ወርቁን በኪሩቦቹና በዘንባባ ዛፎቹ ላይ ጠፈጠፈው። 33  ለቤተ መቅደሱ* መግቢያ የሚሆኑትንና የአንድ አራተኛው* ክፍል የሆኑትን የጥድ እንጨት መቃኖች የሠራው በዚሁ መንገድ ነበር። 34  እሱም ከጥድ እንጨት ሁለት በሮች ሠራ። ሁለት ታጣፊ ሳንቃዎች ያሉት አንዱ በር በመሽከርከሪያዎቹ ላይ፣ ሁለት ታጣፊ ሳንቃዎች ያሉት ሌላኛውም በር በመሽከርከሪያዎቹ ላይ ተገጥሞ ነበር።+ 35  እሱም ኪሩቦችን፣ የዘንባባ ዛፎችንና የፈኩ አበቦችን ምስል ቀረጸ፤ ቅርጾቹንም በወርቅ ለበጣቸው። 36  የውስጠኛውንም ግቢ+ ወደ ላይ በተነባበረ ሦስት ረድፍ ጥርብ ድንጋይና በአንድ ረድፍ የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃ ሠራው።+ 37  በ4ኛው ዓመት በዚፍ* ወር የይሖዋ ቤት መሠረት ተጣለ፤+ 38  በ11ኛው ዓመት በቡል* ወር (ማለትም በስምንተኛው ወር) የቤቱ እያንዳንዱ ነገር በንድፉ መሠረት ተሠርቶ ተጠናቀቀ።+ በመሆኑም ቤቱን ገንብቶ ለመጨረስ ሰባት ዓመት ፈጀበት።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “የእስራኤል ወንዶች ልጆች።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ8ን ተመልከት።
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ከቤተ መቅደሱ።” ቅድስቱን እንደሚያመለክት ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።
ወይም “ወርዱ።”
ወይም “ሰያፍ ጠርዝ።”
ቅድስቱን ያመለክታል።
ወይም “ገባ ያሉ ማስቀመጫዎችን።”
ቃል በቃል “በስተ ቀኝ።”
የቤቱን ውስጥ ያመለክታል።
ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት የሚገኘውን ቅድስቱን ያመለክታል።
ቃል በቃል “ከዘይት እንጨት።”
ቅድስተ ቅዱሳኑን ያመለክታል።
የበሩን ፍሬም አሠራር ወይም የበሮቹን መጠን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ቅድስቱን ያመለክታል።
የበሩን ፍሬም አሠራር ወይም የበሮቹን መጠን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።