በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

1 ነገሥት 18:1-46

የመጽሐፉ ይዘት

  • ኤልያስ ከአብድዩና ከአክዓብ ጋር ተገናኘ (1-18)

  • ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ የባአል ነቢያትን ተገዳደረ (19-40)

    • “በሁለት ሐሳብ የምታነክሱት እስከ መቼ ነው?” (21)

  • የሦስት ዓመት ተኩሉ ድርቅ አበቃ (41-46)

18  ከተወሰነ ጊዜ በኋላም በሦስተኛው ዓመት+ የይሖዋ ቃል “ሂድና አክዓብ ፊት ቅረብ፤ እኔም በምድሩ ላይ ዝናብ አዘንባለሁ”+ ሲል ወደ ኤልያስ መጣ።  ስለሆነም ኤልያስ አክዓብ ፊት ለመቅረብ ሄደ፤ በዚህ ወቅት ረሃቡ በሰማርያ ክፉኛ ጸንቶ ነበር።+  በዚህ ጊዜ አክዓብ በቤቱ ላይ አዛዥ የነበረውን አብድዩን ጠራው። (አብድዩ ይሖዋን በጣም ይፈራ ነበር፤  ኤልዛቤል+ የይሖዋን ነቢያት እያጠፋች በነበረበት ጊዜም አብድዩ 100 ነቢያትን ወስዶ 50ውን በአንድ ዋሻ 50ውን ደግሞ በሌላ ዋሻ ውስጥ ከደበቃቸው በኋላ ምግብና ውኃ ይሰጣቸው ነበር።)  ከዚያም አክዓብ አብድዩን እንዲህ አለው፦ “በምድሪቱ ላይ ወደሚገኙት የውኃ ምንጮች ሁሉና ሸለቆዎች* ሁሉ ሂድ። እንስሶቻችን በሙሉ እንዳያልቁ፣ ፈረሶቹንና በቅሎዎቹን በሕይወት ማቆየት የሚያስችል በቂ ሣር እናገኝ ይሆናል።”  በመሆኑም አቋርጠውት የሚሄዱትን ምድር ተከፋፈሉ። አክዓብ ለብቻው በአንድ በኩል፣ አብድዩም ለብቻው በሌላ በኩል ሄደ።  አብድዩ እየተጓዘ ሳለ ኤልያስን መንገዱ ላይ አገኘው። እሱም ወዲያውኑ ስላወቀው በግንባሩ ተደፋ፤ ከዚያም “ጌታዬ ኤልያስ ሆይ፣ በእርግጥ አንተ ነህ?” አለው።+  ኤልያስም “አዎ፣ እኔ ነኝ። ሄደህ ለጌታህ ‘ኤልያስ እዚህ አለ’ ብለህ ንገረው” አለው።  እሱ ግን እንዲህ አለው፦ “እኔ አገልጋይህ እንድሞት ለአክዓብ አሳልፈህ የምትሰጠኝ ምን ኃጢአት ሠርቼ ነው? 10  ሕያው በሆነው አምላክህ በይሖዋ እምላለሁ፣ ጌታዬ አንተን ፍለጋ ሰው ያልላከበት አንድም ብሔር ሆነ መንግሥት የለም። እነሱም ‘እዚህ የለም’ ባሉት ጊዜ ያ መንግሥትም ሆነ ብሔር አንተን አለማግኘቱን በመሐላ እንዲያረጋግጥለት ያደርግ ነበር።+ 11  አንተ ደግሞ አሁን ‘ሄደህ ለጌታህ “ኤልያስ እዚህ አለ” ብለህ ንገረው’ ትለኛለህ። 12  ከአንተ ተለይቼ ስሄድ የይሖዋ መንፈስ ወደማላውቀው ቦታ ይወስድሃል፤+ ለአክዓብ ብነግረውና ሳያገኝህ ቢቀር እንደሚገድለኝ የታወቀ ነው። ነገር ግን እኔ አገልጋይህ ከወጣትነቴ ጀምሮ ይሖዋን ስፈራ ኖሬአለሁ። 13  ኤልዛቤል የይሖዋን ነቢያት በገደለች ጊዜ ከይሖዋ ነቢያት መካከል 100ዎቹን ወስጄ ሃምሳ ሃምሳ በማድረግ ዋሻ ውስጥ እንደደበቅኳቸው እንዲሁም ምግብና ውኃ እሰጣቸው እንደነበር ጌታዬ አልሰማም?+ 14  አሁን ግን አንተ ‘ሄደህ ለጌታህ “ኤልያስ እዚህ አለ” ብለህ ንገረው’ ትለኛለህ። እሱም በእርግጠኝነት ይገድለኛል።” 15  ሆኖም ኤልያስ “በማገለግለው* ሕያው በሆነው በሠራዊት ጌታ በይሖዋ እምላለሁ፣ ዛሬ እሱ ፊት እቀርባለሁ” አለ። 16  ስለዚህ አብድዩ ወደ አክዓብ ሄዶ ነገረው፤ አክዓብም ኤልያስን ለማግኘት ሄደ። 17  አክዓብም ልክ ኤልያስን ሲያየው “በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ችግር የምትፈጥረው* አንተ ነህ?” አለው። 18  በዚህ ጊዜ ኤልያስ እንዲህ አለው፦ “የይሖዋን ትእዛዛት በመተውና ባአልን በመከተል በእስራኤል ላይ ችግር የምትፈጥሩት+ አንተና የአባትህ ቤት እንጂ እኔ አይደለሁም። 19  ይልቅስ አሁን እስራኤላውያንን በሙሉ፣ ከኤልዛቤል ማዕድ ከሚበሉት 450 የባአል ነቢያትና 400 የማምለኪያ ግንድ*+ ነቢያት ጋር በቀርሜሎስ+ ተራራ ላይ ሰብስብልኝ።” 20  በመሆኑም አክዓብ ወደ እስራኤል ሰዎች ሁሉ መልእክት ላከ፤ ነቢያቱንም በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ሰበሰበ። 21  ከዚያም ኤልያስ ወደ ሕዝቡ ሁሉ ቀርቦ “በሁለት ሐሳብ የምታነክሱት እስከ መቼ ነው?+ እውነተኛው አምላክ፣ ይሖዋ ከሆነ እሱን ተከተሉ፤+ ባአል ከሆነ ደግሞ እሱን ተከተሉ!” አላቸው። ሕዝቡ ግን አንዲት ቃል አልመለሰለትም። 22  ከዚያም ኤልያስ እንዲህ አላቸው፦ “ከይሖዋ ነቢያት መካከል የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤+ የባአል ነቢያት ግን 450 ናቸው። 23  እንግዲህ አሁን ሁለት ወይፈኖች ይስጡን፤ እነሱም አንድ ወይፈን መርጠው በየብልቱ እየቆራረጡ በእንጨቱ ላይ ያድርጉት፤ ሆኖም እሳት አያንድዱበት። እኔ ደግሞ ሌላኛውን ወይፈን አዘጋጅቼ በእንጨቱ ላይ አደርገዋለሁ፤ ሆኖም እሳት አላነድበትም። 24  ከዚያም እናንተ የአምላካችሁን ስም ትጠራላችሁ፤+ እኔም የይሖዋን ስም እጠራለሁ። እሳት በመላክ መልስ የሚሰጠው አምላክ እሱ እውነተኛው አምላክ እንደሆነ ያሳያል።”+ በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ “ያልከው ነገር ጥሩ ነው” አሉ። 25  ኤልያስም የባአል ነቢያትን “እናንተ ብዙ ስለሆናችሁ በቅድሚያ አንድ ወይፈን መርጣችሁ አዘጋጁ። ከዚያም የአምላካችሁን ስም ጥሩ፤ ሆኖም እሳት አታንድዱበት” አላቸው። 26  በመሆኑም የተሰጣቸውን ወይፈን ወስደው አዘጋጁ፤ ከጠዋት አንስቶ እስከ እኩለ ቀን ድረስም “ባአል ሆይ፣ መልስልን!” እያሉ የባአልን ስም ጠሩ። ሆኖም ድምፅ የለም፤ የሚመልስም አልነበረም።+ በሠሩትም መሠዊያ ዙሪያ እያነከሱ ዞሩ። 27  እኩለ ቀን ገደማም ኤልያስ እንዲህ በማለት ያፌዝባቸው ጀመር፦ “ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ እንጂ! አምላክ እኮ ነው!+ ምናልባት በሐሳብ ተውጦ ይሆናል፤ ወይም ሊጸዳዳ ሄዶ ይሆናል።* አሊያም ደግሞ ተኝቶ ሊሆን ስለሚችል የሚቀሰቅሰው ያስፈልገው ይሆናል!” 28  እነሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይጮኹ እንደ ልማዳቸውም ደም በደም እስኪሆኑ ድረስ ሰውነታቸውን በጩቤና በጦር ይተለትሉ ነበር። 29  እኩለ ቀን አልፎ የእህል መባ እስከሚቀርብበትም ጊዜ ድረስ እንደ እብድ* ሲያደርጋቸው ቆየ፤ ሆኖም ምንም ድምፅ የለም፤ የሚመልስም የለም፤ ትኩረት የሰጠም አልነበረም።+ 30  በኋላም ኤልያስ ሕዝቡን ሁሉ “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ እሱ ቀረቡ። ከዚያም ፈርሶ የነበረውን የይሖዋን መሠዊያ ጠገነ።+ 31  በመቀጠልም ኤልያስ “ስምህ እስራኤል ይባላል”+ የሚል የይሖዋ ቃል በመጣለት በያዕቆብ ወንዶች ልጆች ነገዶች ቁጥር ልክ 12 ድንጋዮችን ወሰደ። 32  በድንጋዮቹም በይሖዋ ስም መሠዊያ ሠራ።+ በመሠዊያውም ዙሪያ ሁለት የሲህ መስፈሪያ* ዘር ሊያዘራ የሚችል ስፋት ያለው ቦይ ቆፈረ። 33  ከዚያም እንጨቶቹን ረበረበ፤ ወይፈኑንም በየብልቱ ቆራርጦ በእንጨቶቹ ላይ አደረገ።+ ቀጥሎም “በአራት ጋኖች ውኃ ሞልታችሁ በሚቃጠለው መባና በእንጨቱ ላይ አፍስሱ” አለ። 34  ከዚያም “አሁንም ድገሙ” አለ። እነሱም ደገሙ። “ለሦስተኛ ጊዜ ድገሙ” አላቸው። እነሱም ለሦስተኛ ጊዜ ደገሙ። 35  ውኃውም መሠዊያውን ዙሪያውን አጥለቀለቀው፤ ቦዩንም በውኃ ሞላው። 36  ነቢዩ ኤልያስም የምሽቱ የእህል መባ በሚቀርብበት ጊዜ+ ገደማ ወደ ፊት ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፦ “የአብርሃም፣+ የይስሐቅና+ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ በእስራኤል ውስጥ አምላክ እንደሆንክ፣ እኔም አገልጋይህ እንደሆንኩና እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያደረግኩት በአንተ ቃል እንደሆነ ዛሬ ይታወቅ።+ 37  ይሖዋ ሆይ፣ መልስልኝ! እነዚህ ሰዎች አንተ ይሖዋ እውነተኛው አምላክ እንደሆንክና ልባቸውን ወደ አንተ እየመለስክ መሆንህን እንዲያውቁ መልስልኝ።”+ 38  በዚህ ጊዜ የይሖዋ እሳት ወርዶ የሚቃጠለውን መባ፣ እንጨቱን፣ ድንጋዮቹንና አፈሩን በላ፤+ በቦዩ ውስጥ የነበረውንም ውኃ ላሰ።+ 39  ሕዝቡ ሁሉ ይህን ሲያዩ ወዲያውኑ በግንባራቸው ተደፉ፤ ከዚያም “እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ነው! እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ነው!” አሉ። 40  በዚህ ጊዜ ኤልያስ “የባአልን ነቢያት ያዟቸው! አንዳቸውም እንዳያመልጡ!” አላቸው። እነሱም ወዲያውኑ ያዟቸው፤ ኤልያስም ወደ ቂሾን ጅረት*+ ይዟቸው በመውረድ በዚያ አረዳቸው።+ 41  ኤልያስም አክዓብን “የከባድ ዝናብ ድምፅ እያጉረመረመ ስለሆነ ሂድ ብላ፤ ጠጣም” አለው።+ 42  በመሆኑም አክዓብ ሊበላና ሊጠጣ ሲወጣ ኤልያስ ደግሞ ወደ ቀርሜሎስ አናት ወጣ፤ ፊቱንም በጉልበቶቹ መካከል አድርጎ ወደ መሬት አቀረቀረ።+ 43  ከዚያም አገልጋዩን “እባክህ ውጣና ወደ ባሕሩ አቅጣጫ ተመልከት” አለው። እሱም ወጥቶ ተመለከተና “ኧረ ምንም የለም” አለ። ኤልያስም ሰባት ጊዜ “ተመልሰህ ሂድ” አለው። 44  በሰባተኛውም ጊዜ አገልጋዩ “እነሆ! የሰው እጅ የምታክል ትንሽ ደመና ከባሕሩ እየወጣች ነው” አለ። ኤልያስም “ሄደህ አክዓብን ‘ሠረገላህን አዘጋጅ! ዝናቡ እንዳያግድህ ወደዚያ ውረድ!’ በለው” አለው። 45  በዚህ ጊዜ ሰማዩ በደመና ጠቆረ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ከባድ ዝናብም ይጥል ጀመር፤+ አክዓብም እየጋለበ ወደ ኢይዝራኤል+ ሄደ። 46  ሆኖም የይሖዋ እጅ በኤልያስ ላይ መጣ፤ እሱም ልብሱን ጠቅልሎ መቀነቱ ውስጥ በመሸጎጥ* ከአክዓብ ፊት ፊት እየሮጠ እስከ ኢይዝራኤል ድረስ ሄደ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ደረቅ ወንዞች።”
ቃል በቃል “ፊቱ በምቆመው።”
ወይም “እስራኤል እንዲጠላ የምታደርገው።”
“መንገድ ሄዶ ይሆናል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነቢያት።”
አንድ ሲህ 7.33 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ወይም “እሱም ወገቡን ታጥቆ።”