በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

አንደኛ ነገሥት 14:1-31

የመጽሐፉ ይዘት

  • አኪያህ ስለ ኢዮርብዓም የተናገረው ትንቢት (1-20)

  • ሮብዓም በይሁዳ ላይ የነገሠበት ጊዜ (21-31)

    • ሺሻቅ ያካሄደው ወረራ (25, 26)

14  በዚህ ጊዜ የኢዮርብዓም ልጅ አቢያህ ታመመ።  በመሆኑም ኢዮርብዓም ሚስቱን እንዲህ አላት፦ “እባክሽ፣ ተነሺና የኢዮርብዓም ሚስት መሆንሽን እንዳያውቁ ራስሽን ለውጠሽ ወደ ሴሎ ሂጂ። ነቢዩ አኪያህ ያለው እዚያ ነው። እኔ በዚህ ሕዝብ ላይ ንጉሥ እንደምሆን የተናገረው እሱ ነው።+  አሥር ዳቦና የተቀቡ ቂጣዎች እንዲሁም አንድ ገንቦ ማር ይዘሽ ወደ እሱ ሂጂ። እሱም በልጁ ላይ የሚደርሰውን ነገር ይነግርሻል።”  የኢዮርብዓምም ሚስት እንዳላት አደረገች። ተነስታ ወደ ሴሎ+ በመሄድ ወደ አኪያህ ቤት መጣች። አኪያህ ከማርጀቱ የተነሳ ማየት ተስኖት የነበረ ቢሆንም ዓይኖቹ ፊት ለፊት ትኩር ብለው ይመለከቱ ነበር።  ይሖዋ ግን አኪያህን እንዲህ አለው፦ “የኢዮርብዓም ሚስት ልጇ ስለታመመ ስለ እሱ ልትጠይቅህ እየመጣች ነው። እኔም ምን እንደምትላት እነግርሃለሁ።* እሷም እዚህ ስትደርስ ማንነቷ እንዳይታወቅ ራሷን ትለውጣለች።”  አኪያህም በሩ ጋ ስትደርስ የእግሯን ኮቴ ሰምቶ እንዲህ አላት፦ “የኢዮርብዓም ሚስት ግቢ። ማንነትሽ እንዳይታወቅ ራስሽን የለወጥሽው ለምንድን ነው? መጥፎ ዜና እንድነግርሽ ታዝዣለሁ።  ሂጂና ኢዮርብዓምን እንዲህ በዪው፦ ‘የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ እንድትሆን ከሕዝብህ መካከል አስነሳሁህ።+  ከዚያም መንግሥቱን ከዳዊት ቤት ላይ ቀድጄ ለአንተ ሰጠሁህ።+ አንተ ግን በፊቴ ትክክል የሆነውን ነገር ብቻ በማድረግ ትእዛዛቴን እንደጠበቀውና በሙሉ ልቡ እንደተከተለኝ እንደ አገልጋዬ እንደ ዳዊት አልሆንክም።+  ከዚህ ይልቅ ከአንተ በፊት ከነበሩት ሁሉ የከፋ ድርጊት ፈጸምክ፤ እኔንም ለማስቆጣት ለራስህ ሌላ አምላክና ከብረት የተሠሩ ምስሎችን* ሠራህ፤+ ጀርባህንም ሰጠኸኝ።+ 10  በዚህም የተነሳ በኢዮርብዓም ቤት ላይ ጥፋት አመጣለሁ፤ በእስራኤል ውስጥ የሚገኘውን ምስኪኑንና ደካማውን ጨምሮ የኢዮርብዓም የሆነውን ወንድ* ሁሉ ጠራርጌ አጠፋለሁ፤ አንድ ሰው ፋንድያን ሙልጭ አድርጎ በመጥረግ እንደሚያስወግድ ሁሉ እኔም የኢዮርብዓምን ቤት ሙልጭ አድርጌ እጠርጋለሁ!+ 11  ከኢዮርብዓም ወገን የሆነውን በከተማ ውስጥ የሚሞተውን ሁሉ ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳ ላይ የሚሞተውን ደግሞ የሰማይ አሞሮች ይበሉታል፤ ይሖዋ ይህን ተናግሯልና።”’ 12  “እንግዲህ አሁን ተነስተሽ ወደ ቤትሽ ሂጂ። እግርሽ ከተማዋን እንደረገጠ ልጁ ይሞታል። 13  ከኢዮርብዓም ቤተሰብ መካከል በመቃብር ቦታ የሚቀበረው እሱ ብቻ ስለሆነ እስራኤል ሁሉ አልቅሰው ይቀብሩታል፤ ምክንያቱም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ከኢዮርብዓም ቤት ሁሉ አንድ መልካም ነገር ያገኘበት እሱን ብቻ ነው። 14  ይሖዋም ከዚያን ቀን ጀምሮ እንዲያውም አሁኑኑ፣ የኢዮርብዓምን ቤት+ የሚያስወግድ በእስራኤል ላይ የሚነግሥ ንጉሥ ለራሱ ያስነሳል። 15  ይሖዋ በውኃ ውስጥ እንደሚወዛወዝ ሸምበቆ እስራኤልን ይመታል፤ እንዲሁም እስራኤላውያንን ለአባቶቻቸው ከሰጣቸው ከዚህ መልካም ምድር ላይ ይነቅላቸዋል፤+ ከወንዙም* ማዶ ይበትናቸዋል፤+ ምክንያቱም የማምለኪያ ግንዶችን*+ ለራሳቸው በማቆም ይሖዋን አስቆጥተውታል። 16  እሱም ኢዮርብዓም በሠራው ኃጢአትና እስራኤላውያን እንዲሠሩ ባደረገው ኃጢአት የተነሳ እስራኤልን ይተዋል።”+ 17  በዚህ ጊዜ የኢዮርብዓም ሚስት ተነስታ በመሄድ ወደ ቲርጻ መጣች። ቤቱ ደጃፍ ላይ ስትደርስም ልጁ ሞተ። 18  ይሖዋ በአገልጋዩ በነቢዩ አኪያህ አማካኝነት በተናገረውም መሠረት ቀበሩት፤ እስራኤልም ሁሉ አለቀሰለት። 19  ኢዮርብዓም ስላደረገው ውጊያና+ ስለ አገዛዙ የሚናገረው የቀረው ታሪኩ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፏል። 20  ኢዮርብዓም የገዛበት የጊዜ ርዝመት* 22 ዓመት ነበር፤ ከዚያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤+ በእሱም ምትክ ልጁ ናዳብ ነገሠ።+ 21  ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰለሞን ልጅ ሮብዓም በይሁዳ ላይ ነግሦ ነበር። ሮብዓም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 41 ዓመት ነበር፤ እሱም ይሖዋ ስሙ እንዲኖርባት+ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል በመረጣት ከተማ+ በኢየሩሳሌም ሆኖ ለ17 ዓመት ገዛ። እናቱም ናዕማ የተባለች አሞናዊት+ ነበረች። 22  ይሁዳም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤+ እነሱም በፈጸሙት ኃጢአት የተነሳ ከአባቶቻቸው ይበልጥ አስቆጡት።+ 23  እነሱም ቢሆኑ በእያንዳንዱ ኮረብታ+ ላይና በእያንዳንዱ የለመለመ ዛፍ+ ሥር ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችን፣ የማምለኪያ ዓምዶችንና የማምለኪያ ግንዶችን*+ ለራሳቸው ሠሩ። 24  ሌላው ቀርቶ በምድሪቱ ላይ የቤተ መቅደስ ቀላጮች* ነበሩ።+ ይሖዋ ከእስራኤላውያን ፊት አባሮ ያስወጣቸው ብሔራት ይፈጽሟቸው የነበሩትን አስጸያፊ ነገሮች በሙሉ አደረጉ። 25  ንጉሥ ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፁ ንጉሥ ሺሻቅ+ ኢየሩሳሌምን ለመውጋት መጣ።+ 26  እሱም በይሖዋ ቤት የነበሩትን ውድ ንብረቶችና በንጉሡ ቤት* የነበሩትን ውድ ንብረቶች ወሰደ።+ ሰለሞን የሠራቸውን የወርቅ ጋሻዎች ጨምሮ ሁሉንም ነገር ወሰደ።+ 27  በመሆኑም ንጉሥ ሮብዓም በእነሱ ምትክ የመዳብ ጋሻዎችን ሠርቶ የንጉሡን ቤት በር ለሚጠብቁት የዘብ* አለቆች ሰጣቸው። 28  ዘቦቹም ንጉሡ ወደ ይሖዋ ቤት በመጣ ቁጥር ጋሻዎቹን ያነግቡ ነበር፤ ከዚያም ወደ ዘቦቹ ክፍል ይመልሷቸው ነበር። 29  የቀረው የሮብዓም ታሪክና ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?+ 30  በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ነበር።+ 31  በመጨረሻም ሮብዓም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም+ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። እናቱ ናዕማ የተባለች አሞናዊት+ ነበረች። በእሱም ምትክ ልጁ አብያም*+ ነገሠ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “አንተም እንዲህ እንዲህ ብለህ ንገራት።”
ወይም “ቀልጠው የተሠሩ ሐውልቶችን።”
ቃል በቃል “ግንብ ላይ የሚሸናውን።” ወንዶችን የሚያናንቅ የዕብራይስጥ አገላለጽ ነው።
ኤፍራጥስን ያመለክታል።
ቃል በቃል “የገዛባቸው ቀናት።”
ግብረ ሰዶማውያን ሆነው የሴት ዓይነት ሚና ያላቸውን ወንዶች ያመለክታል።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “የሯጮቹ።”
አቢያህ ተብሎም ይጠራል።