በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

አንደኛ ነገሥት 11:1-43

የመጽሐፉ ይዘት

  • የሰለሞን ሚስቶች ልቡ ወደ ሌላ እንዲያዘነብል አደረጉት (1-13)

  • ሰለሞን ተቃዋሚዎች ተነሱበት (14-25)

  • ኢዮርብዓም አሥር ነገዶች እንደሚሰጡት ቃል ተገባለት (26-40)

  • ሰለሞን ሞተ፤ ሮብዓም ነገሠ (41-43)

11  ይሁንና ንጉሥ ሰለሞን ከፈርዖን ልጅ+ ሌላ ብዙ የባዕድ አገር ሴቶችን+ ማለትም ሞዓባውያን፣+ አሞናውያን፣+ ኤዶማውያን፣ ሲዶናውያንና+ ሂታውያን+ ሴቶችን አፈቀረ።  እነሱም ይሖዋ ለእስራኤላውያን “ከእነሱ ጋር አትቀላቀሉ፤* እነሱም ከእናንተ ጋር አይቀላቀሉ፤ አለዚያ ያለምንም ጥርጥር ልባችሁ አማልክታቸውን ወደ መከተል እንዲያዘነብል ያደርጉታል”+ ብሎ ከነገራቸው ብሔራት ወገን ነበሩ። ሆኖም ሰለሞን ከእነሱ ጋር ተጣበቀ፤ ደግሞም አፈቀራቸው።  እሱም ልዕልቶች የሆኑ 700 ሚስቶች እንዲሁም 300 ቁባቶች ነበሩት፤ ሚስቶቹም ቀስ በቀስ ልቡ ወደ ሌላ እንዲያዘነብል አደረጉት።*  ሰለሞን በሸመገለ+ ጊዜ ሚስቶቹ ልቡ ሌሎች አማልክትን ወደ መከተል እንዲያዘነብል* አደረጉት፤+ ልቡ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ በአምላኩ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ* አልነበረም።  ሰለሞን የሲዶናውያንን እንስት አምላክ አስታሮትንና+ አስጸያፊ የሆነውን የአሞናውያንን አምላክ ሚልኮምን+ ተከተለ።  ሰለሞንም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ፤ አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ይሖዋን ሙሉ በሙሉ አልተከተለም።+  ሰለሞን አስጸያፊ ለሆነው የሞዓብ አምላክ ለከሞሽና አስጸያፊ ለሆነው ለአሞናውያን+ አምላክ ለሞሎክ+ ኢየሩሳሌም ፊት ለፊት በሚገኘው ተራራ ላይ ከፍ ያለ የማምለኪያ ቦታ+ የሠራው በዚህ ጊዜ ነበር።  ለአማልክታቸው የሚጨስ መሥዋዕት ለሚያቀርቡትና ለሚሠዉት የባዕድ አገር ሚስቶቹ ሁሉ ልክ እንደዚሁ አደረገ።  ሰለሞን ሁለት ጊዜ ከተገለጠለት+ ከእስራኤል አምላክ ከይሖዋ ልቡ ስለሸፈተ+ ይሖዋ በሰለሞን ላይ ተቆጣ፤ 10  ደግሞም ሌሎች አማልክትን እንዳይከተል በማዘዝ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ አስጠንቅቆት ነበር።+ እሱ ግን ይሖዋ ያዘዘውን ነገር አልጠበቀም። 11  በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሰለሞንን እንዲህ አለው፦ “ይህን ስላደረግክ እንዲሁም ባዘዝኩህ መሠረት ቃል ኪዳኔንና ደንቦቼን ስላልጠበቅክ መንግሥትህን ቀድጄ ከአንተ እወስደዋለሁ፤ ከአገልጋዮችህም መካከል ለአንዱ እሰጠዋለሁ።+ 12  ሆኖም ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ስል በአንተ ዘመን ይህን አላደርግም። መንግሥትህን ከልጅህ እጅ ላይ እቀደዋለሁ፤+ 13  ይሁንና መንግሥቱን በሙሉ ቀድጄ አልወስድም።+ ስለ አገልጋዬ ስለ ዳዊትና ስለመረጥኳት+ ስለ ኢየሩሳሌም ስል ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ።”+ 14  ከዚያም ይሖዋ ከኤዶም+ ንጉሣዊ ቤተሰብ የሆነውን ኤዶማዊውን ሃዳድን በሰለሞን ላይ ተቃዋሚ አድርጎ አስነሳው።+ 15  ዳዊት ኤዶምን+ ድል ባደረገበት ጊዜ የሠራዊቱ አለቃ የሆነው ኢዮዓብ የተገደሉትን ለመቅበር ወጥቶ የነበረ ሲሆን በኤዶም የሚገኘውን እያንዳንዱን ወንድ ለመግደል ሞክሮ ነበር። 16  (ምክንያቱም ኢዮዓብ በኤዶም የሚገኘውን እያንዳንዱን ወንድ ገድሎ እስኪጨርስ ድረስ ከመላው እስራኤል ጋር በዚያ ለስድስት ወር ተቀምጦ ነበር።) 17  ሆኖም ሃዳድ የአባቱ አገልጋዮች ከሆኑ የተወሰኑ ኤዶማውያን ጋር ሸሸ፤ እነሱም ወደ ግብፅ ሄዱ፤ በወቅቱ ሃዳድ ገና ትንሽ ልጅ ነበር። 18  እነሱም ከምድያም ተነስተው ወደ ፋራን ሄዱ። ከፋራንም+ ሰዎች ይዘው ወደ ግብፅ ይኸውም ወደ ግብፁ ንጉሥ ወደ ፈርዖን መጡ፤ ፈርዖንም ቤትና መሬት ሰጠው፤ ቀለብም እንዲሰፈርለት አደረገ። 19  ሃዳድም በፈርዖን ፊት ሞገስ ስላገኘ ፈርዖን የገዛ ሚስቱን እህት ማለትም የንግሥት ጣፍኔስን እህት ዳረለት። 20  ከጊዜ በኋላ የጣፍኔስ እህት፣ ጌኑባት የተባለ ልጅ ወለደችለት፤ ጣፍኔስም ልጁን በፈርዖን ቤት ውስጥ አሳደገችው፤* ጌኑባት በፈርዖን ቤት ከፈርዖን ልጆች ጋር ኖረ። 21  ሃዳድ በግብፅ ሳለ ዳዊት ከአባቶቹ ጋር እንዳንቀላፋ+ እንዲሁም የሠራዊቱ አለቃ ኢዮዓብ እንደሞተ ሰማ።+ በመሆኑም ሃዳድ ፈርዖንን “ወደ አገሬ እንድሄድ አሰናብተኝ” አለው። 22  ፈርዖን ግን “እዚህ እኔ ጋር እያለህ ምን ጎደለብህና ነው ወደ አገርህ መሄድ የፈለግከው?” አለው። እሱም “ምንም የጎደለብኝ ነገር የለም፤ ብቻ እንድሄድ አሰናብተኝ” አለው። 23  በተጨማሪም አምላክ ከጌታው ከጾባህ ንጉሥ ከሃዳድኤዜር+ የኮበለለውን የኤሊያዳን ልጅ ረዞንን በሰለሞን ላይ ተቃዋሚ አድርጎ አስነሳው።+ 24  እሱም ዳዊት የጾባህን ሰዎች ድል ባደረገበት ጊዜ* ሰዎችን አሰባስቦ የአንድ ወራሪ ቡድን አለቃ ሆነ።+ በመሆኑም ወደ ደማስቆ+ ሄደው በዚያ ሰፈሩ፤ በደማስቆም መግዛት ጀመሩ። 25  ሃዳድ በእስራኤል ላይ ካስከተለው ጉዳት በተጨማሪ ረዞንም በሰለሞን ዘመን ሁሉ የእስራኤል ተቃዋሚ ሆነ፤ በሶርያ ላይ በነገሠበትም ዘመን ሁሉ ለእስራኤል ከፍተኛ ጥላቻ ነበረው። 26  እንዲሁም የሰለሞን አገልጋይ+ የሆነ ኢዮርብዓም+ የተባለ አንድ ኤፍሬማዊ ነበር፤ እሱም ከጸሬዳህ ወገን ሲሆን የናባጥ ልጅ ነበር፤ እናቱም ጽሩዓ የምትባል መበለት ነበረች። እሱም በንጉሡ ላይ ማመፅ* ጀመረ።+ 27  በንጉሡ ላይ ያመፀውም በዚህ የተነሳ ነው፦ ሰለሞን ጉብታውን*+ ሠርቶ እንዲሁም በአባቱ በዳዊት ከተማ+ ቅጥር ላይ የነበረውን ክፍተት ዘግቶ ነበር። 28  ኢዮርብዓም ከፍተኛ ችሎታ ያለው ሰው ነበር። ሰለሞንም ወጣቱ ጠንካራ ሠራተኛ መሆኑን ሲያይ በዮሴፍ ቤት በሚከናወነው የግዳጅ ሥራ ሁሉ ላይ የበላይ ተመልካች አደረገው።+ 29  በዚህ ጊዜ ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም ወጣ፤ ሴሎናዊው ነቢዩ አኪያህም መንገድ ላይ አገኘው። አኪያህ+ አዲስ ልብስ ለብሶ ነበር፤ በሜዳውም ላይ ሁለቱ ብቻቸውን ነበሩ። 30  አኪያህም ለብሶት የነበረውን አዲስ ልብስ ይዞ 12 ቦታ ቀደደው። 31  ከዚያም ኢዮርብዓምን እንዲህ አለው፦ “አሥሩን ቁራጭ ለራስህ ውሰድ፤ ምክንያቱም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እንግዲህ መንግሥቱን ከሰለሞን እጅ እቀደዋለሁ፤ ለአንተም አሥር ነገዶችን እሰጥሃለሁ።+ 32  ሆኖም ስለ አገልጋዬ ስለ ዳዊትና+ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ስለመረጥኳት ከተማ+ ስለ ኢየሩሳሌም ስል አንዱ ነገድ የእሱ እንደሆነ ይቀጥላል።+ 33  ይህን የማደርገው እኔን ትተው+ ለሲዶናውያን እንስት አምላክ ለአስታሮት፣ ለሞዓብ አምላክ ለከሞሽና ለአሞናውያን አምላክ ለሚልኮም ስለሰገዱ ነው፤ አባቱ ዳዊት እንዳደረገው በፊቴ ትክክል የሆነውን ነገር በማድረግ እንዲሁም ደንቦቼንና ድንጋጌዎቼን በመጠበቅ በመንገዴ አልሄዱም። 34  ሆኖም ትእዛዛቴንና ደንቦቼን ስለጠበቀው ስለመረጥኩት አገልጋዬ ስለ ዳዊት+ ስል መንግሥቱን በሙሉ ከእጁ አልወስድም፤ ደግሞም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ አለቃ አደርገዋለሁ። 35  ይሁን እንጂ መንግሥቱን ይኸውም አሥሩን ነገድ ከልጁ እጅ ወስጄ ለአንተ እሰጥሃለሁ።+ 36  አገልጋዬ ዳዊት ስሜ እንዲኖርባት ለራሴ በመረጥኳት ከተማ በኢየሩሳሌም ዘወትር በፊቴ መብራት እንዲኖረው+ ለልጁ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ። 37  እኔም እወስድሃለሁ፤ አንተም በተመኘኸው* ሁሉ ላይ ትገዛለህ፤ በእስራኤልም ላይ ንጉሥ ትሆናለህ። 38  አገልጋዬ ዳዊት እንዳደረገው+ ያዘዝኩህን ሁሉ ብትፈጽም እንዲሁም ደንቦቼንና ትእዛዛቴን በመጠበቅ በመንገዶቼ ብትሄድና በፊቴ ትክክል የሆነውን ነገር ብታደርግ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ። ለዳዊት እንዳደረግኩለት ሁሉ ለአንተም ጸንቶ የሚኖር ቤት እሠራልሃለሁ፤+ እስራኤልንም እሰጥሃለሁ። 39  በዚህም የተነሳ የዳዊትን ዘር አዋርዳለሁ፤+ ይህን የማደርገው ግን ለሁልጊዜ አይደለም።’”+ 40  በመሆኑም ሰለሞን ኢዮርብዓምን ሊገድለው ሞከረ፤ ሆኖም ኢዮርብዓም ተነስቶ ወደ ግብፅ፣+ ወደ ንጉሥ ሺሻቅ+ ሸሸ፤ ሰለሞን እስኪሞትም ድረስ በግብፅ ተቀመጠ። 41  የቀረው የሰለሞን ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉና ጥበቡ በሰለሞን የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?+ 42  ሰለሞን በኢየሩሳሌም ሆኖ በመላው እስራኤል ላይ የገዛበት የጊዜ ርዝመት* 40 ዓመት ነበር። 43  ከዚያም ሰለሞን ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ በእሱም ምትክ ልጁ ሮብዓም+ ነገሠ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የጋብቻ ጥምረት አትመሥርቱ።”
ወይም “ሚስቶቹም ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳደሩበት።”
ወይም “ዞር እንዲል።”
ወይም “ሙሉ በሙሉ ለአምላኩ ለይሖዋ ያደረ።”
“ጡት አስጣለችው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “በገደለበት ጊዜ።”
ቃል በቃል “እጁን ማንሳት።”
ወይም “ሚሎን።” “መሙላት” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል ነው።
ወይም “ነፍስህ በተመኘችው።”
ቃል በቃል “የገዛባቸው ቀናት።”