በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

ዘሌዋውያን 13:1-59

የመጽሐፉ ይዘት

  • የሥጋ ደዌን አስመልክቶ የተሰጠ ሕግ (1-46)

  • በልብስ ላይ የሚወጣ ደዌ (47-59)

13  ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦  “አንድ ሰው በቆዳው ላይ እብጠት፣ እከክ ወይም ቋቁቻ ቢወጣበትና ወደ ሥጋ ደዌነት*+ ቢለወጥበት ወደ ካህኑ አሮን ወይም ካህናት ከሆኑት ወንዶች ልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት።+  ካህኑም በቆዳው ላይ ያለውን ቁስል ይመረምራል። ቁስሉ ባለበት ቦታ ላይ ያለው ፀጉር ወደ ነጭነት ከተለወጠና ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ ከሆነ ይህ የሥጋ ደዌ ነው። ካህኑ ቁስሉን ከመረመረ በኋላ ግለሰቡ ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል።  ሆኖም በቆዳው ላይ ያለው ቋቁቻ ነጭ ከሆነና ከቆዳው ዘልቆ የገባ ካልሆነ እንዲሁም በዚያ ቦታ ላይ ያለው ፀጉር ወደ ነጭነት ካልተለወጠ ካህኑ ቁስል የወጣበትን ሰው ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያደርገዋል።+  ከዚያም በሰባተኛው ቀን ካህኑ ሰውየውን ይመረምረዋል፤ ቁስሉ ባለበት ከቆመና በቆዳው ላይ ካልተስፋፋ ካህኑ ሰውየውን ለተጨማሪ ሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያደርገዋል።  “ካህኑም በሰባተኛው ቀን እንደገና ሰውየውን ይመርምረው፤ ቁስሉ ከከሰመና በቆዳው ላይ ካልተስፋፋ ካህኑ ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል፤+ ይህ እከክ ነው። ከዚያም ሰውየው ልብሶቹን ያጥባል፤ ንጹሕም ይሆናል።  ሆኖም ሰውየው መንጻቱን ለማረጋገጥ ካህኑ ፊት ከቀረበ በኋላ እከኩ* በቆዳው ላይ እየተስፋፋ ከሄደ እንደገና ካህኑ ፊት ይቀርባል።  ካህኑም ይመረምረዋል፤ እከኩ በቆዳው ላይ ተስፋፍቶ ከሆነ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ይህ የሥጋ ደዌ ነው።+  “አንድ ሰው የሥጋ ደዌ ቢይዘው ወደ ካህኑ እንዲቀርብ ይደረግ፤ 10  ካህኑም ይመረምረዋል።+ በቆዳው ላይ ነጭ እብጠት ካለና በዚያ ቦታ ላይ ያለውን ፀጉር ወደ ነጭነት ከለወጠው እንዲሁም በእብጠቱ ላይ አፉን የከፈተ ቁስል+ ካለ 11  ይህ በቆዳው ላይ የወጣ ሥር የሰደደ የሥጋ ደዌ ነው፤ ካህኑም ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ሰውየው ርኩስ ስለሆነም ለተወሰነ ጊዜ ተገልሎ እንዲቆይ+ ማድረግ አያስፈልገውም። 12  የሥጋ ደዌው በቆዳው ሁሉ ላይ ቢወጣና የሥጋ ደዌው ካህኑ ሊያየው እስከሚችለው ድረስ ግለሰቡን ከራሱ አንስቶ እስከ እግሮቹ ድረስ ቢያለብሰው 13  እንዲሁም ካህኑ ሲመረምረው የሥጋ ደዌው ቆዳውን ሁሉ አልብሶት ቢያይ ቁስሉ የወጣበት ግለሰብ ንጹሕ* መሆኑን ያስታውቃል። ቆዳው ሙሉ በሙሉ ወደ ነጭነት ተለውጧል፤ ሰውየውም ንጹሕ ነው። 14  ሆኖም በቆዳው ላይ አፉን የከፈተ ቁስል በወጣበት በማንኛውም ጊዜ ሰውየው ርኩስ ይሆናል። 15  ካህኑ አፉን የከፈተ ቁስል ካየ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል።+ አፉን የከፈተው ቁስል ርኩስ ነው። ይህ የሥጋ ደዌ ነው።+ 16  ሆኖም አፉን የከፈተው ቁስል እንደገና ወደ ነጭነት ከተለወጠ ሰውየው ወደ ካህኑ ይመጣል። 17  ካህኑም ይመረምረዋል፤+ ቁስሉ ወደ ነጭነት ከተለወጠ ካህኑ ቁስሉ የወጣበት ግለሰብ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል። ሰውየው ንጹሕ ነው። 18  “አንድ ሰው በቆዳው ላይ እባጭ ቢወጣበትና ቢድን 19  ሆኖም እባጩ በነበረበት ቦታ ላይ ነጭ እብጠት ወይም ነጣ ያለ ቀይ ቋቁቻ ቢወጣ ሰውየው ራሱን ለካህን ያሳይ። 20  ካህኑም ቁስሉን ይመረምረዋል፤+ ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ ከሆነና በዚያ ቦታ ላይ ያለው ፀጉር ወደ ነጭነት ከተለወጠ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ይህ በእባጩ ላይ የወጣ የሥጋ ደዌ ነው። 21  ይሁንና ካህኑ ቁስሉን ሲመረምረው በላዩ ላይ ነጭ ፀጉር ከሌለና ከቆዳው ዘልቆ የገባ ካልሆነ እንዲሁም እየከሰመ ከሆነ ካህኑ ሰውየውን ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያደርገዋል።+ 22  ቁስሉ በቆዳው ላይ እየተስፋፋ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ከሆነ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ይህ ደዌ ነው። 23  ይሁን እንጂ ቋቁቻው ባለበት ከቆመና ካልተስፋፋ ይህ እባጩ ያስከተለው ቁስል ነው፤ ካህኑም ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል።+ 24  “ወይም አንድ ሰው እሳት አቃጥሎት በሰውነቱ ቆዳ ላይ ጠባሳ ቢተውና ጠባሳው ላይ ያለው ያልሻረ ቁስል ነጣ ያለ ቀይ ወይም ነጭ ቋቁቻ ቢሆን 25  ካህኑ ቁስሉን ይመረምረዋል። በቋቁቻው ላይ ያለው ፀጉር ወደ ነጭነት ከተለወጠና ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ ከሆነ ይህ በጠባሳው ላይ የወጣ የሥጋ ደዌ ነው፤ ካህኑም ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ይህ የሥጋ ደዌ ነው። 26  ይሁንና ካህኑ ሲመረምረው በቋቁቻው ላይ ነጭ ፀጉር ከሌለና ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ ካልሆነ እንዲሁም እየከሰመ ከሆነ ካህኑ ሰውየውን ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያደርገዋል።+ 27  ካህኑም በሰባተኛው ቀን ሰውየውን ይመረምረዋል፤ ቁስሉ በቆዳው ላይ እየተስፋፋ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ከሆነ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ይህ የሥጋ ደዌ ነው። 28  ይሁንና ቋቁቻው ባለበት ከቆመና በቆዳው ላይ ካልተስፋፋ እንዲሁም ከከሰመ ይህ ጠባሳው ያስከተለው እብጠት ነው፤ ይህ የጠባሳው ቁስል ስለሆነ ካህኑ ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል። 29  “በአንድ ወንድ ወይም በአንዲት ሴት ራስ ወይም አገጭ ላይ ቁስል ቢወጣ 30  ካህኑ ቁስሉን ይመረምረዋል።+ ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ ከሆነ እንዲሁም በዚያ ቦታ ላይ ያለው ፀጉር ቢጫ ከሆነና ከሳሳ ካህኑ ያ ሰው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል፤ ይህ በራስ ቆዳ ወይም በጢም ላይ የሚወጣ ቁስል ነው። ይህ የራስ ወይም የአገጭ የሥጋ ደዌ ነው። 31  ሆኖም ካህኑ ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ አለመሆኑንና በዚያ ቦታ ላይ ጥቁር ፀጉር አለመኖሩን ካየ ቁስሉ የወጣበትን ሰው ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያድርገው።+ 32  ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቁስሉን ይመረምረዋል፤ ቁስሉ ካልተስፋፋና በዚያ ቦታ ላይ ቢጫ ፀጉር ካልወጣ እንዲሁም ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ ካልሆነ 33  ሰውየው ፀጉሩን ይላጭ፤ ቁስሉ ያለበትን ቦታ ግን አይላጨውም። ከዚያም ካህኑ ቁስሉ የወጣበትን ሰው ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያደርገዋል። 34  “ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቁስሉ ያለበትን ቦታ እንደገና ይመረምረዋል፤ ቁስሉ በቆዳው ላይ ካልተስፋፋና ከቆዳው ዘልቆ የገባ ካልሆነ ካህኑ ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ሰውየውም ልብሶቹን ይጠብ፤ ንጹሕም ይሁን። 35  ሆኖም ሰውየው ከነጻ በኋላ ቁስሉ በቆዳው ላይ እየተስፋፋ መሆኑ በግልጽ ከታየ 36  ካህኑ ይመረምረዋል፤ ቁስሉ በቆዳው ላይ ከተስፋፋ ካህኑ ቢጫ ፀጉር መኖር አለመኖሩን ማየት አያስፈልገውም፤ ሰውየው ርኩስ ነው። 37  ሆኖም ካህኑ ሲመረምረው ቁስሉ ካልተስፋፋና በዚያ ቦታ ጥቁር ፀጉር ከበቀለ ቁስሉ ድኗል ማለት ነው። ሰውየው ንጹሕ ነው፤ ካህኑም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል።+ 38  “አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት በቆዳቸው ላይ ቋቁቻ ቢወጣና ቋቁቻው ደግሞ ነጭ ቢሆን 39  ካህኑ ይመረምራቸዋል።+ በቆዳው ላይ የወጣው ቋቁቻ ደብዘዝ ያለ ነጭ ከሆነ ይህ ቆዳው ላይ የወጣ ጉዳት የሌለው ሽፍታ ነው። ሰውየው ንጹሕ ነው። 40  “አንድ ወንድ ራሱ ቢመለጥና ራሰ በራ ቢሆን ሰውየው ንጹሕ ነው። 41  ሰውየው ከፊት በኩል ቢመለጥና ራሰ በራ ቢሆን ንጹሕ ነው። 42  ሆኖም በራሱ ወይም በግንባሩ ላይ ባለው በራ ላይ ቀላ ያለ ነጭ ቁስል ቢወጣበት ይህ በራሱ ወይም በግንባሩ ላይ የወጣ ሥጋ ደዌ ነው። 43  ካህኑም ሰውየውን ይመረምረዋል፤ በአናቱ ወይም በግንባሩ ላይ ባለው በራ ላይ የወጣው ቁስል ያስከተለው እብጠት ቀላ ያለ ነጭ ከሆነና በቆዳው ላይ ሲታይ የሥጋ ደዌ የሚመስል ከሆነ 44  ሰውየው የሥጋ ደዌ በሽተኛ ነው። ርኩስ ነው፤ በራሱም ላይ ባለው ደዌ የተነሳ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ። 45  የሥጋ ደዌ ያለበት ሰው ልብሶቹ የተቀዳደዱ ይሁኑ፤ ፀጉሩም ይንጨብረር፤ አፍንጫው ሥር እስካለው ጢም ድረስ ተሸፋፍኖ ‘ርኩስ ነኝ፣ ርኩስ ነኝ!’ እያለ ይጩኽ። 46  ሰውየው ደዌው በላዩ ላይ ባለበት ጊዜ ሁሉ ርኩስ ይሆናል። ርኩስ ስለሆነም ከሰዎች ተገልሎ መኖር አለበት። መኖሪያውም ከሰፈሩ ውጭ ይሆናል።+ 47  “ደዌው ከሱፍም ሆነ ከበፍታ የተሠራን ልብስ ቢበክል 48  ወይም የበፍታውንም ሆነ የሱፉን ድር ወይም ማግ አሊያም ቁርበትን ወይም ደግሞ ከቆዳ የተሠራን ማንኛውንም ነገር ቢበክል 49  እንዲሁም ደዌው ያስከተለው ወደ ቢጫነት ያደላ አረንጓዴ ወይም ቀላ ያለ ምልክት ልብሱን፣ ቆዳውን፣ ድሩን፣ ማጉን ወይም ደግሞ ከቆዳ የተሠራውን የትኛውንም ዕቃ ቢበክል ይህ በደዌ ምክንያት የተከሰተ ብክለት ነው፤ ካህኑ እንዲያየው መደረግ አለበት። 50  ካህኑም ደዌውን ይመረምረዋል፤ ደዌው ያለበትም ነገር ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቀመጥ ያድርግ።+ 51  በሰባተኛው ቀን ደዌውን ሲመረምረው ደዌው በልብሱ፣ በድሩ፣ በማጉ ወይም በቆዳው ላይ (ቆዳው ለማንኛውም ዓይነት አገልግሎት የሚውል ይሁን) ተስፋፍቶ ቢገኝ ደዌው አደገኛ ደዌ ነው፤ ዕቃውም ርኩስ ነው።+ 52  እሱም ደዌው ያለበትን ልብስ ወይም የሱፍም ሆነ የበፍታ ድር ወይም ማግ አሊያም ደግሞ ከቆዳ የተሠራ ማንኛውም ዕቃ ያቃጥል፤ ምክንያቱም ይህ አደገኛ ደዌ ነው። በእሳት መቃጠል ይኖርበታል። 53   “ሆኖም ካህኑ ሲመረምረው ደዌው በልብሱ ወይም በድሩ አሊያም በማጉ ወይም ደግሞ ከቆዳ በተሠራው በማንኛውም ዕቃ ላይ ካልተስፋፋ 54  ካህኑ ደዌው ያለበትን ነገር እንዲያጥቡት ያዛል፤ ከዚያም እንደገና ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቀመጥ ያደርጋል። 55  የተበከለው ዕቃ በደንብ ከታጠበ በኋላ ካህኑ ይመረምረዋል። ደዌው ባይስፋፋም እንኳ ብክለቱ መልኩን ካልቀየረ ዕቃው ርኩስ ነው። ዕቃው ከውስጡ ወይም ከውጭው ስለተበላ በእሳት አቃጥለው። 56  “ሆኖም ዕቃው በደንብ ከታጠበ በኋላ ካህኑ ሲመረምረው የተበከለው ክፍል ከደበዘዘ ያን ቦታ ከልብሱ ወይም ከቆዳው አሊያም ከድሩ ወይም ደግሞ ከማጉ ላይ ቀዶ ያወጣዋል። 57   ይሁንና ደዌው በልብሱ ወይም በድሩ አሊያም በማጉ ወይም ደግሞ ከቆዳ በተሠራው በማንኛውም ዕቃ ላይ በሌላ ቦታ አሁንም ከታየ ደዌው እየተስፋፋ ነው፤ ስለዚህ በደዌው የተበከለውን ማንኛውንም ዕቃ በእሳት አቃጥለው።+ 58  ሆኖም በልብሱ ወይም በድሩ አሊያም በማጉ ወይም ደግሞ ከቆዳ በተሠራው በማንኛውም ዕቃ ላይ የተከሰተው ብክለት ስታጥበው ከለቀቀ ዕቃው ለሁለተኛ ጊዜ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። 59  “ከሱፍ ወይም ከበፍታ በተሠራ ልብስ አሊያም በድር ወይም በማግ አሊያም ደግሞ ከቆዳ በተሠራ በማንኛውም ዕቃ ላይ የወጣን ደዌ በተመለከተ ዕቃው ንጹሕ ነው ብሎ ለማስታወቅም ሆነ ርኩስ ነው ለማለት ሕጉ ይህ ነው።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

“የሥጋ ደዌ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ሰፊ ትርጉም ያለው ሲሆን የተለያዩ ተላላፊ የቆዳ በሽታዎችን ሊያመለክት ይችላል። ልብስንና ቤትን የሚበክሉ አንዳንድ በሽታዎችንም ሊጨምር ይችላል።
ወይም “ቁስሉ።”
ወይም “በሽታው የማይተላለፍ።”