በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

ዕዝራ 7:1-28

የመጽሐፉ ይዘት

  • ዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ (1-10)

  • አርጤክስስ ለዕዝራ የጻፈው ደብዳቤ (11-26)

  • ዕዝራ ይሖዋን አወደሰ (27-28)

7  ከእነዚህ ነገሮች በኋላ በፋርሱ ንጉሥ በአርጤክስስ+ የግዛት ዘመን ዕዝራ*+ ከባቢሎን ተመለሰ። ዕዝራ የሰራያህ+ ልጅ፣ ሰራያህ የአዛርያስ ልጅ፣ አዛርያስ የኬልቅያስ+ ልጅ፣  ኬልቅያስ የሻሉም ልጅ፣ ሻሉም የሳዶቅ ልጅ፣ ሳዶቅ የአኪጡብ ልጅ፣  አኪጡብ የአማርያህ ልጅ፣ አማርያህ የአዛርያስ+ ልጅ፣ አዛርያስ የመራዮት ልጅ፣  መራዮት የዘራህያህ ልጅ፣ ዘራህያህ የዑዚ ልጅ፣ ዑዚ የቡቂ ልጅ፣  ቡቂ የአቢሹዓ ልጅ፣ አቢሹዓ የፊንሃስ+ ልጅ፣ ፊንሃስ የአልዓዛር+ ልጅ፣ አልዓዛር የካህናት አለቃ የሆነው የአሮን+ ልጅ ነበር።  ይህ ዕዝራ ከባቢሎን ወጣ። እሱም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ የሰጠውን የሙሴን ሕግ ጠንቅቆ የሚያውቅ ገልባጭ* ነበር።*+ የአምላኩ የይሖዋ እጅ በእሱ ላይ ስለነበር ንጉሡ የጠየቀውን ሁሉ ሰጠው።  ንጉሥ አርጤክስስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ከእስራኤላውያን፣ ከካህናቱ፣ ከሌዋውያኑ፣+ ከዘማሪዎቹ፣+ ከበር ጠባቂዎቹና+ ከቤተ መቅደስ አገልጋዮቹ*+ መካከል የተወሰኑት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ።  ዕዝራም ንጉሡ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ኢየሩሳሌም ደረሰ።  በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ከባቢሎን ተነስቶ ጉዞ ጀመረ፤ መልካም የሆነው የአምላኩ እጅ በእሱ ላይ ስለነበር+ በአምስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ኢየሩሳሌም ደረሰ። 10  ዕዝራ የይሖዋን ሕግ ለመመርመርና ተግባራዊ ለማድረግ+ እንዲሁም ሥርዓቱንና ፍርዱን በእስራኤል ውስጥ ለማስተማር+ ልቡን አዘጋጅቶ* ነበር። 11  ንጉሥ አርጤክስስ የይሖዋን ትእዛዛትና ለእስራኤላውያን ያወጣቸውን ሥርዓቶች በማጥናት ለተካነውና* ገልባጭ* ለሆነው ለካህኑ ዕዝራ የሰጠው ደብዳቤ ቅጂ ይህ ነው፦ 12  * “ከንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ፣+ የሰማይ አምላክ ሕግ ገልባጭ* ለሆነው ለካህኑ ዕዝራ፦ ሰላም ለአንተ ይሁን። እንግዲህ 13  በግዛቴ ውስጥ ካሉ የእስራኤል ሕዝቦች እንዲሁም ከእነሱ ካህናትና ሌዋውያን መካከል ከአንተ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ሁሉ እንዲሄድ ትእዛዝ ሰጥቻለሁ።+ 14  ንጉሡና ሰባቱ አማካሪዎቹ በእጅህ የሚገኘው የአምላክህ ሕግ በይሁዳና በኢየሩሳሌም በተግባር ላይ እየዋለ እንደሆነና እንዳልሆነ እንድትመረምር ልከውሃል፤ 15  እንዲሁም ንጉሡና አማካሪዎቹ በኢየሩሳሌም ለሚኖረው ለእስራኤል አምላክ በፈቃደኝነት የሰጡትን ብርና ወርቅ፣ 16  ከመላው የባቢሎን አውራጃ ከተቀበልከው* ብርና ወርቅ እንዲሁም ሕዝቡና ካህናቱ በኢየሩሳሌም ለሚገኘው ለአምላካቸው ቤት በፈቃደኝነት ከሰጡት ስጦታ ጋር ይዘህ እንድትሄድ አዘዋል።+ 17  በዚህም ገንዘብ ሳትዘገይ በሬዎችን፣+ አውራ በጎችንና+ የበግ ጠቦቶችን+ ከእህል መባዎቻቸውና+ ከመጠጥ መባዎቻቸው+ ጋር ግዛ፤ እነዚህንም በኢየሩሳሌም በሚገኘው በአምላካችሁ ቤት መሠዊያ ላይ አቅርባቸው። 18  “በተረፈው ብርና ወርቅ እንደ አምላካችሁ ፈቃድ አንተም ሆንክ ወንድሞችህ መልካም መስሎ የታያችሁን አድርጉበት። 19  በአምላክህ ቤት ለሚቀርበው አገልግሎት እንዲሆኑ የተሰጡህን ዕቃዎች በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም ወስደህ በአምላክ ፊት ታስቀምጣቸዋለህ።+ 20  ለአምላክህ ቤት መስጠት የሚጠበቅብህን ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ከንጉሡ ግምጃ ቤት አውጥተህ ትሰጣለህ።+ 21  “እኔ ንጉሥ አርጤክስስ ከወንዙ ባሻገር* ባለው ክልል የምትገኙትን የግምጃ ቤት ኃላፊዎች በሙሉ የሰማይ አምላክ ሕግ ገልባጭ* የሆነው ካህኑ ዕዝራ+ የጠየቃችሁን ነገር ሁሉ በአስቸኳይ እንድትፈጽሙለት ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፤ 22  እንዲሁም እስከ 100 ታላንት* ብር፣ እስከ 100 የቆሮስ* መስፈሪያ ስንዴ፣ እስከ 100 የባዶስ* መስፈሪያ የወይን ጠጅና+ እስከ 100 የባዶስ መስፈሪያ ዘይት+ ድረስ ስጡት፤ እንዲሁም የፈለገውን ያህል ጨው+ ስጡት። 23  በንጉሡ ግዛትና በልጆቹ ላይ ቁጣ እንዳይወርድ+ የሰማይ አምላክ፣ የሰማይን አምላክ ቤት አስመልክቶ ያዘዘው ሁሉ በትጋት ይፈጸም።+ 24  በተጨማሪም ከካህናቱ፣ ከሌዋውያኑ፣ ከሙዚቀኞቹ፣+ ከበር ጠባቂዎቹ፣ ከቤተ መቅደስ አገልጋዮቹም*+ ሆነ ይህን የአምላክ ቤት ከሚሠሩት ሰዎች መካከል በአንዳቸውም ላይ ምንም ዓይነት ቀረጥ፣ ግብር+ ወይም የኬላ ቀረጥ መጣል እንደማትችሉ እወቁ። 25  “አንተም ዕዝራ፣ አምላክህ የሰጠህን ጥበብ* ተጠቅመህ ከወንዙ ባሻገር ባለው ክልል ለሚኖሩት ሕዝቦች በሙሉ፣ የአምላክህን ሕጎች ለሚያውቁ ሁሉ ፍርድ የሚሰጡ ሕግ አስከባሪዎችንና ዳኞችን ሹም፤ ሕጎቹን የማያውቅ ሰው ካለም አስተምሩት።+ 26  እንዲሁም የአምላክህን ሕግና የንጉሡን ሕግ የማያከብር ማንኛውም ሰው ቅጣቱ ሞትም ይሁን ከአገር መባረር ወይም ገንዘብ አሊያም እስራት አፋጣኝ የፍርድ እርምጃ ይወሰድበት።” 27  እንዲህ ያለውን ነገር ይኸውም በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የይሖዋን ቤት የማስዋቡን ሐሳብ በንጉሡ ልብ ውስጥ ያኖረው የአባቶቻችን አምላክ ይሖዋ ይወደስ!+ 28  በንጉሡና+ በአማካሪዎቹ+ እንዲሁም ኃያላን በሆኑት የንጉሡ መኳንንት ሁሉ ፊት ታማኝ ፍቅር አሳይቶኛል። በመሆኑም የአምላኬ የይሖዋ እጅ በላዬ ስለነበር ድፍረት አገኘሁ፤* ከእኔም ጋር አብረው እንዲሄዱ ከእስራኤል መካከል መሪ* የሆኑትን ሰበሰብኩ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“እርዳታ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ጸሐፊ።”
ወይም “የሙሴን ሕግ በመገልበጥ የተካነ ነበር።”
ወይም “ከናታኒሞቹ።” ቃል በቃል “ከተሰጡት ሰዎች።”
ወይም “በልቡ ቆርጦ።”
ወይም “ቃላት ለሚገለብጠው።”
ወይም “ጸሐፊ።”
ከዕዝራ 7:12 እስከ 7:26 ያለው መጀመሪያ የተጻፈው በአረማይክ ቋንቋ ነበር።
ወይም “ጸሐፊ።”
ቃል በቃል “ካገኘኸው።”
ወይም “ኤፍራጥስን ተሻግሮ።”
ወይም “ጸሐፊ።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ቆሮስ 220 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ባዶስ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ከናታኒሞቹም።” ቃል በቃል “ከተሰጡት ሰዎችም።”
ቃል በቃል “በእጅህ ባለው በአምላክህ ጥበብ።”
ወይም “ራሴን አበረታሁ።”
ቃል በቃል “ራስ።”