በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

ዕዝራ 5:1-17

የመጽሐፉ ይዘት

  • አይሁዳውያን ዳግመኛ ቤተ መቅደሱን መገንባት ጀመሩ (1-5)

  • ታተናይ ለንጉሥ ዳርዮስ የላከው ደብዳቤ (6-17)

5  ከዚያም ነቢዩ ሐጌና+ የኢዶ+ የልጅ ልጅ የሆነው ነቢዩ ዘካርያስ+ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለነበሩ አይሁዳውያን፣ ይመራቸው በነበረው በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩ።  በዚህ ጊዜ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና+ የየሆጼዴቅ ልጅ የሆሹዋ+ በኢየሩሳሌም የነበረውን የአምላክን ቤት መልሰው መገንባት ጀመሩ፤+ አብረዋቸው የነበሩት የአምላክ ነቢያትም ያግዟቸው ነበር።+  በወቅቱ፣ ከወንዙ ባሻገር* የነበረው ክልል ገዢ የሆነው ታተናይ እና ሸታርቦዘናይ እንዲሁም ግብረ አበሮቻቸው ወደ እነሱ መጥተው “ይህን ቤት እንድትገነቡና እንድታዋቅሩ ማን ትእዛዝ ሰጣችሁ?” ሲሉ ጠየቋቸው።  ከዚያም “ይህን ሕንፃ እየገነቡ ያሉት ሰዎች ስም ማን ነው?” አሏቸው።  ሆኖም አምላክ ለአይሁዳውያን ሽማግሌዎች+ ጥበቃ ያደርግላቸው* ስለነበር መልእክቱ ለዳርዮስ ተልኮ ጉዳዩን የሚመለከት ደብዳቤ ከዚያ እስኪመጣ ድረስ ሥራውን ሊያስቆሟቸው አልቻሉም።  ከወንዙ ባሻገር ያለው ክልል ገዢ የሆነው ታተናይ፣ ሸታርቦዘናይና ከወንዙ ባሻገር ያለው ክልል የበታች ገዢዎች የሆኑት ግብረ አበሮቹ ለንጉሥ ዳርዮስ የላኩት ደብዳቤ ቅጂ ይህ ነው፤  እንዲህ የሚል መልእክት ጽፈው ላኩለት፦ “ለንጉሥ ዳርዮስ፦ “ሰላም ለአንተ ይሁን!  በይሁዳ አውራጃ ወደሚገኘው ወደ ታላቁ አምላክ ቤት እንደሄድንና ቤቱ በትላልቅ ድንጋዮች እየተገነባ፣ በግንቡም ላይ ሳንቃዎች እየተነጠፉ መሆናቸውን ንጉሡ ይወቅ። ሕዝቡ ሥራውን በትጋት እያከናወነ ሲሆን ሥራውም በእነሱ ጥረት እየተፋጠነ ነው።  ሽማግሌዎቹንም ‘ይህን ቤት እንድትገነቡና እንድታዋቅሩ ማን ትእዛዝ ሰጣችሁ?’ አልናቸው።+ 10  በተጨማሪም ግንባር ቀደም ሆነው የሚመሩትን ሰዎች ስም ጽፈን ለአንተ ለማሳወቅ የሰዎቹን ስም እንዲነግሩን ጠየቅናቸው። 11  “እነሱም የሚከተለውን ምላሽ ሰጡን፦ ‘እኛ የሰማይና የምድር አምላክ አገልጋዮች ነን፤ አሁን መልሰን የምንገነባው ከበርካታ ዓመታት በፊት ተገንብቶ የነበረውን ይኸውም ታላቁ የእስራኤል ንጉሥ ገንብቶ ያጠናቀቀውን ቤት ነው።+ 12  ሆኖም አባቶቻችን የሰማይን አምላክ ስላስቆጡት+ ለከለዳዊው ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነጾር+ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እሱም ይህን ቤት አፈራርሶ+ ሕዝቡን በግዞት ወደ ባቢሎን ወሰደ።+ 13  ይሁንና በባቢሎን ንጉሥ በቂሮስ የግዛት ዘመን የመጀመሪያ ዓመት ንጉሥ ቂሮስ ይህ የአምላክ ቤት ተመልሶ እንዲገነባ ትእዛዝ ሰጠ።+ 14  በተጨማሪም ንጉሥ ቂሮስ፣ ናቡከደነጾር በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ አውጥቶ ወደ ባቢሎን ቤተ መቅደስ የወሰዳቸውን የአምላክን ቤት የወርቅና የብር ዕቃዎች ከባቢሎን ቤተ መቅደስ አወጣ።+ እነዚህም ዕቃዎች ቂሮስ ገዢ አድርጎ+ ለሾመው ሸሽባጻር*+ ለተባለ ሰው ተሰጡ። 15  ቂሮስም እንዲህ አለው፦ “እነዚህን ዕቃዎች ውሰድ። ሄደህም በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ አስቀምጣቸው፤ የአምላክም ቤት ቀድሞ በነበረበት ቦታ ላይ ተመልሶ ይገንባ።”+ 16  ከዚያም ሸሽባጻር መጥቶ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የአምላክን ቤት መሠረት ጣለ፤+ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ቤቱ በመገንባት ላይ ነው፤ ሆኖም ገና አላለቀም።’+ 17  “እንግዲህ አሁን፣ ንጉሡ መልካም መስሎ ከታየው ንጉሥ ቂሮስ በኢየሩሳሌም የነበረው ያ የአምላክ ቤት ተመልሶ እንዲገነባ ትእዛዝ ሰጥቶ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማረጋገጥ በባቢሎን በሚገኘው የንጉሡ ግምጃ ቤት ምርመራ ይካሄድ፤+ ይህን በተመለከተም ንጉሡ ያስተላለፈው ውሳኔ ይላክልን።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ኤፍራጥስን ተሻግሮ።”
ቃል በቃል “የአምላካቸው ዓይን በአይሁዳውያን ሽማግሌዎች ላይ።”
በዕዝራ 2:2 እና 3:8 ላይ ዘሩባቤል የተባለው ሳይሆን አይቀርም።