በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

ኤርምያስ 44:1-30

የመጽሐፉ ይዘት

  • በግብፅ የነበሩ አይሁዳውያን እንደሚጠፉ ተነገረ (1-14)

  • ሕዝቡ የአምላክን ማስጠንቀቂያ አቃለለ (15-30)

    • ‘የሰማይን ንግሥት’ አመለኩ (17-19)

44  በግብፅ ምድር+ ይኸውም በሚግዶል፣+ በጣፍነስ፣+ በኖፍ*+ እና በጳትሮስ+ ምድር ለሚኖሩ አይሁዳውያን ሁሉ እንዲነገር ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፦  “የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ከተሞች በሙሉ ያመጣሁትን ጥፋት ሁሉ አይታችኋል፤+ ዛሬ ማንም የማይኖርባቸው የፍርስራሽ ክምር ሆነዋል።+  ይህም የሆነው እናንተም ሆነ አባቶቻችሁ ወደማታውቋቸው ሌሎች አማልክት+ ሄደው ለእነሱ መሥዋዕት በማቅረብና እነሱን በማገልገል እኔን ለማስቆጣት በፈጸሙት ክፉ ድርጊት የተነሳ ነው።+  አገልጋዮቼን ነቢያትን ሁሉ ወደ እናንተ ላክኋቸው፤ “እባካችሁ፣ እኔ የምጠላውን ይህን አስጸያፊ ነገር አታድርጉ” በማለት ደግሜ ደጋግሜ ላክኋቸው።+  እነሱ ግን አልሰሙም፤ ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት ከማቅረብ+ በመቆጠብም ከክፉ መንገዳቸው ለመመለስ ጆሯቸውን አልሰጡም።  በመሆኑም ቁጣዬና ንዴቴ ፈሰሰ፤ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ጎዳናዎችም ላይ ነደደ፤ እነሱም ዛሬ እንደሚታዩት የፍርስራሽ ክምርና ጠፍ መሬት ሆነዋል።’+  “አሁንም የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ወንዶችና ሴቶች፣ ልጆችና ሕፃናት ሁሉ ከይሁዳ ጠፍተው ለራሳችሁ አንድም ቀሪ እንዳይተርፍ በራሳችሁ* ላይ ለምን ታላቅ ጥፋት ታመጣላችሁ?  ለመኖር በሄዳችሁባት በግብፅ ምድር ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት በማቅረብ በእጃችሁ ሥራ የምታስቆጡኝ ለምንድን ነው? ትጠፋላችሁ፤ በምድር ብሔራትም ሁሉ መካከል ለእርግማንና ለነቀፋ ትዳረጋላችሁ።+  በይሁዳ ምድርና በኢየሩሳሌም ጎዳናዎች አባቶቻችሁ የሠሩትን ክፉ ሥራ፣ የይሁዳ ነገሥታት የሠሩትን ክፉ ሥራና+ ሚስቶቻቸው የሠሩትን ክፉ ሥራ+ እንዲሁም እናንተ ራሳችሁ የሠራችሁትን ክፉ ሥራና ሚስቶቻችሁ የሠሩትን ክፉ ሥራ ረሳችሁት?+ 10  እነሱ እስከ ዛሬ ድረስ ራሳቸውን ዝቅ አላደረጉም፤* የፍርሃትም ስሜት አላደረባቸውም፤+ በእናንተና በአባቶቻችሁ ፊት ያኖርኩትን ሕጌንና ሥርዓቴንም አልተከተሉም።’+ 11  “ስለዚህ የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፣ በእናንተ ላይ ጥፋት ለማምጣትና ይሁዳን ሁሉ ለመደምሰስ ቆርጬ ተነስቻለሁ። 12  በግብፅ ምድር ለመኖር ወደዚያ ለመሄድ ቆርጠው የተነሱትንም የይሁዳ ቀሪዎች እወስዳለሁ፤ ሁሉም በግብፅ ምድር ይጠፋሉ።+ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ከትንሹ እስከ ትልቁ ድረስ በረሃብ ያልቃሉ፤ በሰይፍና በረሃብ ይሞታሉ። ለእርግማን፣ ለውርደትና ለነቀፋ ይዳረጋሉ፤ መቀጣጫም ይሆናሉ።+ 13  ኢየሩሳሌምን እንደቀጣሁ ሁሉ በግብፅ ምድር የሚኖሩትንም በሰይፍ፣ በረሃብና በቸነፈር* እቀጣለሁ።+ 14  በግብፅ ምድር ለመኖር የሄዱት የይሁዳ ቀሪዎችም አምልጠው ወይም በሕይወት ተርፈው ወደ ይሁዳ ምድር አይመለሱም። ወደዚያ ለመመለስና በዚያ ለመኖር ቢመኙም እንኳ* ከጥቂት ሰዎች በስተቀር አምልጦ የሚመለስ አይኖርም።’” 15  ሚስቶቻቸው ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት ያቀርቡ እንደነበረ የሚያውቁ ወንዶች ሁሉ፣ ብዙ ሆነው የተሰበሰቡት ሚስቶቻቸው ሁሉ እንዲሁም በግብፅ ምድር+ ይኸውም በጳትሮስ+ የሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ለኤርምያስ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ 16  “በይሖዋ ስም የነገርከንን ቃል አንሰማም። 17  ይልቁንም አፋችን የተናገረውን ቃል ሁሉ መፈጸማችን አይቀርም፤ እኛና አባቶቻችን እንዲሁም ነገሥታታችንና መኳንንታችን በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ላይ እናደርግ እንደነበረው ‘ለሰማይ ንግሥት’* መሥዋዕት እናቀርባለን፤ ለእሷም የመጠጥ መባ እናፈሳለን፤+ በዚያን ጊዜ እስክንጠግብ ድረስ እንበላና ተመችቶን እንኖር ነበር፤ ጥፋት የሚባል ነገርም አልገጠመንም። 18  ‘ለሰማይ ንግሥት’* መሥዋዕት ማቅረብና የመጠጥ መባ ማፍሰስ ካቆምንበት ጊዜ ጀምሮ ግን ሁሉን ነገር አጥተናል፤ እንዲሁም በሰይፍና በረሃብ አልቀናል።” 19  ሴቶቹም አክለው እንዲህ አሉ፦ “ደግሞስ ‘ለሰማይ ንግሥት’* መሥዋዕት እናቀርብና የመጠጥ መባ እናፈስ በነበረበት ጊዜ፣ በእሷ ምስል የመሥዋዕት ቂጣ የምንጋግረውና ለእሷ የመጠጥ መባ የምናፈሰው ባሎቻችንን ሳናማክር ነበር?” 20  በዚህ ጊዜ ኤርምያስ ለሕዝቡ ሁሉ ይኸውም ለወንዶቹ፣ ለሚስቶቻቸውና እያናገሩት ለነበሩት ሰዎች ሁሉ እንዲህ አለ፦ 21  “እናንተ፣ አባቶቻችሁ፣ ነገሥታታችሁ፣ መኳንንታችሁና በምድሪቱ የሚኖረው ሕዝብ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ላይ ያቀረባችኋቸውን መሥዋዕቶች+ ይሖዋ አልዘነጋም፤ በልቡም አኑሯቸዋል! 22  በመጨረሻም ይሖዋ የፈጸማችኋቸውን ክፉ ድርጊቶችና የሠራችኋቸውን አስጸያፊ ነገሮች ሊታገሥ አልቻለም፤ ምድራችሁም ዛሬ እንደምታዩት ባድማ ስፍራ፣ አስፈሪ ቦታና ሰው የማይኖርባት ቦታ ሆነች፤ ለእርግማንም ተዳረገች።+ 23  እነዚህን መሥዋዕቶች ስላቀረባችሁ፣ ደግሞም የይሖዋን ቃል ባለመታዘዝ እንዲሁም የእሱን ሕግ፣ ደንብና ማሳሰቢያ ባለመከተል በይሖዋ ላይ ኃጢአት ስለሠራችሁ ዛሬ እንደምታዩት ይህ ጥፋት ደርሶባችኋል።”+ 24  ኤርምያስ ለሕዝቡ ሁሉና ለሴቶቹ ሁሉ እንዲህ ሲል አክሎ ተናገረ፦ “በግብፅ ምድር የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎች ሁሉ፣ የይሖዋን ቃል ስሙ። 25  የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እናንተና ሚስቶቻችሁ በአፋችሁ የተናገራችሁትን በእጃችሁ ፈጽማችሁታል፤ እንዲህ ብላችኋልና፦ “‘ለሰማይ ንግሥት’* መሥዋዕት ለማቅረብና ለእሷ የመጠጥ መባ ለማፍሰስ የተሳልነውን ስእለት በእርግጥ እንፈጽማለን።”+ እናንተ ሴቶች የገባችሁትን ስእለት በእርግጥ ታደርሳላችሁ፤ ስእለታችሁንም ትፈጽማላችሁ።’ 26  “ስለዚህ በግብፅ ምድር የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎች ሁሉ የይሖዋን ቃል ስሙ፦ ‘“እነሆ፣ በገዛ ራሴ ታላቅ ስም እምላለሁ” ይላል ይሖዋ፤ “በመላው የግብፅ ምድር፣ የትኛውም የይሁዳ ሰው ‘ሕያው በሆነው በሉዓላዊው ጌታ በይሖዋ እምላለሁ’+ በማለት ከእንግዲህ ስሜን በመሐላ አይጠራም።+ 27  መልካም ነገር ሳይሆን ጥፋት ለማምጣት እከታተላቸዋለሁ፤+ በግብፅ ምድር የሚኖሩ የይሁዳ ሰዎች ሁሉ ፈጽሞ እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍና በረሃብ ያልቃሉ።+ 28  ጥቂት ሰዎች ብቻ ከሰይፍ አምልጠው ከግብፅ ምድር ወደ ይሁዳ ምድር ይመለሳሉ።+ ከዚያም በግብፅ ምድር ለመኖር ወደዚያ የመጡት የይሁዳ ቀሪዎች ሁሉ ከእኔ ወይም ከእነሱ፣ የማን ቃል እንደተፈጸመ ያውቃሉ!”’” 29  “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በእናንተ ላይ ጥፋት ለማምጣት የተናገርኩት ቃል መፈጸሙ እንደማይቀር ታውቁ ዘንድ በዚህ ስፍራ እንደምቀጣችሁ ይህ ምልክት ይሆናችኋል። 30  ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን ጠላቱ ለሆነውና ሕይወቱን ሊያጠፋ ይፈልግ* ለነበረው ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነጾር* አሳልፌ እንደሰጠሁ ሁሉ የግብፁን ንጉሥ፣ ፈርዖን ሆፍራንም ለጠላቶቹና ሕይወቱን ለማጥፋት ለሚፈልጉት* ሰዎች አሳልፌ እሰጣለሁ።”’”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በሜምፊስ።”
ወይም “በነፍሳችሁ።”
ወይም “አልተሸማቀቁም።”
ወይም “በበሽታ።”
ወይም “ነፍሳቸውን ቢያነሱም እንኳ።”
ከሃዲ እስራኤላውያን የሚያመልኳት አምላክ የማዕረግ ስም ነው፤ የመራባት ሴት አምላክ ልትሆን ትችላለች።
ከሃዲ እስራኤላውያን የሚያመልኳት አምላክ የማዕረግ ስም ነው፤ የመራባት ሴት አምላክ ልትሆን ትችላለች።
ከሃዲ እስራኤላውያን የሚያመልኳት አምላክ የማዕረግ ስም ነው፤ የመራባት ሴት አምላክ ልትሆን ትችላለች።
ከሃዲ እስራኤላውያን የሚያመልኳት አምላክ የማዕረግ ስም ነው፤ የመራባት ሴት አምላክ ልትሆን ትችላለች።
ወይም “ነፍሱን ይፈልጋት።”
ቃል በቃል “ለናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
ወይም “ነፍሱን ለሚፈልጓት።”