በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በኢንተርኔት | መጽሐፍ ቅዱስ–አዲስ ዓለም ትርጉም

ኤርምያስ 40:1-16

የመጽሐፉ ይዘት

  • ናቡዛራዳን ኤርምያስን በነፃ ለቀቀው (1-6)

  • ጎዶልያስ በምድሪቱ ላይ ተሾመ (7-12)

  • በጎዶልያስ ላይ ሴራ ተጠነሰሰ (13-16)

40  የዘቦች አለቃ የሆነው ናቡዛራዳን+ ኤርምያስን ከራማ+ በነፃ ከለቀቀው በኋላ ወደ ኤርምያስ የመጣው የይሖዋ ቃል ይህ ነው። ናቡዛራዳን ኤርምያስን ወደዚያ ሲወስደው እጆቹ በሰንሰለት ታስረው ነበር፤ ደግሞም ወደ ባቢሎን በግዞት እየተወሰዱ ከነበሩት የኢየሩሳሌምና የይሁዳ ግዞተኞች ሁሉ መካከል ነበር።  ከዚያም የዘቦቹ አለቃ ኤርምያስን ወስዶ እንዲህ አለው፦ “አምላክህ ይሖዋ በዚህ ስፍራ ላይ ይህ ጥፋት እንደሚመጣ አስቀድሞ ተናግሯል፤  በይሖዋ ላይ ኃጢአት ስለሠራችሁና ቃሉን ስላልታዘዛችሁ ይሖዋ በተናገረው መሠረት ይህን ጥፋት አመጣ። ይህ ነገር በእናንተ ላይ የደረሰው ለዚህ ነው።+  እጆችህ የታሰሩበትን ሰንሰለት ዛሬ እፈታልሃለሁ። ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን መሄድ መልካም መስሎ ከታየህ መሄድ ትችላለህ፤ እኔም እንከባከብሃለሁ። ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን መሄድ ካልፈለግክ ግን መቅረት ትችላለህ። እነሆ፣ ምድሪቱ ሁሉ በፊትህ ናት። ወደመረጥከው ቦታ መሄድ ትችላለህ።”+  ኤርምያስ ከመመለሱ በፊት ናቡዛራዳን እንዲህ አለው፦ “የባቢሎን ንጉሥ በይሁዳ ከተሞች ላይ ወደ ሾመው ወደ ሳፋን+ ልጅ፣ ወደ አኪቃም+ ልጅ ወደ ጎዶልያስ+ ተመለስ፤ በሕዝቡም መካከል ከእሱ ጋር ተቀመጥ፤ ወይም ደግሞ ወደመረጥከው ቦታ ሂድ።” ከዚያም የዘቦቹ አለቃ ስንቅና ስጦታ ሰጥቶ አሰናበተው።  በመሆኑም ኤርምያስ በምጽጳ+ ወደሚገኘው ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ሄዶ በምድሪቱ በቀሩት ሕዝብ መካከል ከእሱ ጋር መኖር ጀመረ።  በኋላም ከሰዎቻቸው ጋር በየቦታው የነበሩት የሠራዊቱ አለቆች የባቢሎን ንጉሥ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በምድሪቱ ላይ እንደሾመው እንዲሁም ወደ ባቢሎን በግዞት ባልተወሰዱትና በምድሪቱ ላይ በሚገኙት ድሆች የሆኑ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ላይ እንደሾመው ሰሙ።+  ስለሆነም በምጽጳ+ ወደሚገኘው ወደ ጎዶልያስ መጡ። እነሱም የነታንያህ ልጅ እስማኤል፣+ የቃሬሃ ልጆች የሆኑት ዮሃናን+ እና ዮናታን፣ የታንሁመት ልጅ ሰራያህ፣ የነጦፋዊው የኤፋይ ልጆችና የማአካታዊው ልጅ የዛንያህ+ እንዲሁም አብረዋቸው የነበሩት ሰዎች ናቸው።  የሳፋን ልጅ፣ የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ለእነሱና አብረዋቸው ለነበሩት ሰዎች እንዲህ ብሎ ማለላቸው፦ “ከለዳውያንን ማገልገል አያስፈራችሁ። በምድሪቱ ላይ ኑሩ፤ የባቢሎንንም ንጉሥ አገልግሉ፤ መልካምም ይሆንላችኋል።+ 10  እኔም ወደ እኛ በሚመጡት ከለዳውያን ፊት እናንተን ወክዬ ለመቅረብ* በምጽጳ እቀመጣለሁ። እናንተ ግን ወይን፣ የበጋ ፍሬዎችና* ዘይት አከማቹ፤ በማጠራቀሚያ ዕቃዎቻችሁም ውስጥ ክተቱ፤ በያዛችኋቸው ከተሞችም ውስጥ ኑሩ።”+ 11  በሞዓብ፣ በአሞንና በኤዶም እንዲሁም በሌሎች አገሮች ሁሉ የነበሩት አይሁዳውያንም በሙሉ የባቢሎን ንጉሥ የተወሰኑ ቀሪዎች በይሁዳ ምድር እንዲኖሩ እንደፈቀደላቸውና የሳፋንን ልጅ፣ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በእነሱ ላይ እንደሾመ ሰሙ። 12  በመሆኑም አይሁዳውያኑ በሙሉ ከተበተኑባቸው ቦታዎች ሁሉ ይመለሱ ጀመር፤ በይሁዳ ምድር በምጽጳ ወዳለው ወደ ጎዶልያስ መጡ። እነሱም ወይንና የበጋ ፍሬዎችን በብዛት አከማቹ። 13  የቃሬሃ ልጅ ዮሃናን እና በየቦታው የነበሩት የሠራዊቱ አለቆች ሁሉ በምጽጳ ወዳለው ወደ ጎዶልያስ መጡ። 14  እንዲህም አሉት፦ “የአሞናውያን+ ንጉሥ ባአሊስ አንተን ለመግደል* የነታንያህን ልጅ እስማኤልን እንደላከው አታውቅም?”+ የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ግን አላመናቸውም። 15  ከዚያም የቃሬሃ ልጅ ዮሃናን፣ ጎዶልያስን በምጽጳ በሚስጥር እንዲህ አለው፦ “ሄጄ የነታንያህን ልጅ እስማኤልን ልግደለው፤ ማንም አያውቅም። ለምን ይግደልህ?* ወደ አንተ የተሰበሰቡት የይሁዳ ሰዎች ሁሉ ለምን ይበተኑ? የይሁዳ ቀሪዎችስ ለምን ይጥፉ?” 16  የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ+ ግን የቃሬሃን ልጅ ዮሃናንን “ስለ እስማኤል የምትነግረኝ ነገር እውነት ስላልሆነ እንዲህ አታድርግ” አለው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ለመቆም።”
የበጋ ፍሬ በዋነኝነት የሚያመለክተው “በለስን” ሲሆን “ቴምርንም” ሊጨምር ይችላል።
ወይም “ነፍስህን ለማጥፋት።”
ወይም “ነፍስህን ለምን ያጥፋት?”