በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ኤርምያስ 32:1-44

የመጽሐፉ ይዘት

  • ኤርምያስ መሬት ገዛ (1-15)

  • ኤርምያስ ያቀረበው ጸሎት (16-25)

  • ይሖዋ የሰጠው መልስ (26-44)

32  የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በ10ኛው ዓመት ይኸውም ናቡከደነጾር* በነገሠ በ18ኛው ዓመት ወደ ኤርምያስ የመጣው የይሖዋ ቃል ይህ ነው።+  በዚያን ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከቦ ነበር፤ ነቢዩ ኤርምያስም በይሁዳ ንጉሥ ቤት፣* በክብር ዘቦቹ ግቢ+ ታስሮ ነበር።  የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ እንዲህ በማለት አስሮት ነበርና፦+ “እንዲህ ብለህ ትንቢት የምትናገረው ለምንድን ነው? አንተ እንዲህ ትላለህ፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ይህችን ከተማ በባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እሱም ይይዛታል፤+  የይሁዳም ንጉሥ ሴዴቅያስ ከከለዳውያን እጅ አያመልጥም፤ ያላንዳች ጥርጥር በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፎ ይሰጣል፤ ከንጉሡም ጋር ፊት ለፊት ይነጋገራል፤ በዓይኖቹም ያየዋል።”’+  ‘ሴዴቅያስን ወደ ባቢሎን ይወስደዋል፤ ትኩረቴን ወደ እሱ እስካዞር ድረስም በዚያ ይቆያል’ ይላል ይሖዋ። ‘ከከለዳውያን ጋር መዋጋታችሁን ብትቀጥሉም እንኳ አይሳካላችሁም።’”+  ኤርምያስ እንዲህ አለ፦ “የይሖዋ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦  ‘እነሆ፣ የአጎትህ* የሻሉም ልጅ ሃናምኤል ወደ አንተ መጥቶ “የመቤዠት መብት ያለህ የመጀመሪያው ሰው አንተ ስለሆንክ+ በአናቶት+ የሚገኘውን መሬቴን ለራስህ ግዛው” ይልሃል።’”  ይሖዋ በተናገረው መሠረት የአጎቴ ልጅ ሃናምኤል እኔ ወዳለሁበት ወደ ክብር ዘቦቹ ግቢ መጥቶ እንዲህ አለኝ፦ “በቢንያም አገር፣ በአናቶት የሚገኘውን መሬቴን እባክህ ግዛኝ፤ የመውረስና የመቤዠት መብት ያለህ አንተ ነህና። ስለዚህ መሬቱን ለራስህ ግዛው።” ይህ የሆነው ይሖዋ በተናገረው ቃል መሠረት እንደሆነ ተረዳሁ።  በመሆኑም በአናቶት ያለውን መሬት ከአጎቴ ልጅ ከሃናምኤል ላይ ገዛሁ። እኔም ሰባት ሰቅልና* አሥር የብር ሰቅል ገንዘብ መዝኜ ሰጠሁት።+ 10  ከዚያም የውል ሰነድ+ ካዘጋጀሁ በኋላ በማኅተም አሸግኩት፤ ምሥክሮችንም ጠርቼ+ ገንዘቡን በሚዛን መዘንኩ። 11  በመመሪያውና በሕጉ መሠረት የታሸገውን እንዲሁም ያልታሸገውን የግዢውን የውል ሰነድ ወሰድኩ፤ 12  ከዚያም የግዢውን የውል ሰነድ በአጎቴ ልጅ በሃናምኤል፣ በግዢው ውል ላይ በፈረሙት ምሥክሮች እንዲሁም በክብር ዘቦቹ ግቢ+ ተቀምጠው በነበሩት አይሁዳውያን ሁሉ ፊት ለማህሴያህ ልጅ፣ ለነሪያህ+ ልጅ ለባሮክ+ ሰጠሁት። 13  ባሮክንም በእነሱ ፊት እንዲህ ብዬ አዘዝኩት፦ 14  “የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነዚህን የውል ሰነዶች፣ የታሸገውንም ሆነ ያልታሸገውን የግዢ የውል ሰነድ ወስደህ ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አስቀምጣቸው።’ 15  የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘በዚህች ምድር፣ ቤቶችና የእርሻ ቦታዎች እንዲሁም የወይን እርሻዎች እንደገና ይገዛሉ።’”+ 16  የግዢውን የውል ሰነድ ለነሪያህ ልጅ ለባሮክ ከሰጠሁት በኋላ እንዲህ ብዬ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ፦ 17  “አቤቱ፣ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ! እነሆ፣ አንተ ሰማያትንና ምድርን በታላቅ ኃይልህና በተዘረጋች ክንድህ ሠርተሃል።+ አንተ ምንም የሚሳንህ ነገር የለም፤ 18  ለሺዎች ታማኝ ፍቅር ታሳያለህ፤ ይሁንና የአባቶችን በደል ከእነሱ በኋላ በሚመጡት ልጆቻቸው ላይ* ትመልሳለህ፤+ አንተ እውነተኛ፣ ታላቅና ኃያል አምላክ ነህ፤ ስምህም የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ነው። 19  በምክር ታላቅ፣* በሥራም ኃያል ነህ፤+ ለእያንዳንዱ እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ለመክፈል+ ዓይኖችህ የሰው ልጆችን መንገዶች ሁሉ ያያሉ።+ 20  እስከ ዛሬ ድረስ የሚነገርላቸውን ምልክቶችና ተአምራት በግብፅ ምድር አደረግክ፤ በዚህም መንገድ አሁን እየሆነ እንዳለው ሁሉ በእስራኤልና በሰው ልጆች መካከል ለራስህ ስም አተረፍክ።+ 21  ሕዝብህን እስራኤልን በምልክቶች፣ በተአምራት፣ በኃያል እጅ፣ በተዘረጋች ክንድና አስፈሪ በሆኑ ክንውኖች ከግብፅ ምድር አወጣህ።+ 22  “ከጊዜ በኋላም ለአባቶቻቸው ለመስጠት የማልክላቸውን+ ወተትና ማር የምታፈሰውን ይህችን ምድር ሰጠሃቸው።+ 23  እነሱም ገብተው ምድሪቱን ወረሷት፤ ሆኖም ቃልህን አልታዘዙም ወይም በሕግህ አልተመላለሱም። እንዲያደርጉ ያዘዝካቸውን ነገር ሁሉ አላደረጉም፤ ከዚህም የተነሳ ይህን ሁሉ ጥፋት በላያቸው አመጣህ።+ 24  እነሆ፣ ከተማዋን ለመያዝ ሰዎች በዙሪያዋ የአፈር ቁልል ደልድለዋል፤+ ከሰይፉ፣+ ከረሃቡና ከቸነፈሩ*+ የተነሳ ከተማዋ እየወጓት ባሉት ከለዳውያን እጅ መውደቋ አይቀርም፤ አሁን እንደምታየው አንተ ያልከው ሁሉ ተፈጽሟል። 25  ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ግን ከተማዋ በከለዳውያን እጅ መውደቋ የማይቀር ቢሆንም ‘መሬቱን ለራስህ በምሥክሮች ፊት በገንዘብ ግዛ’ አልከኝ።” 26  በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ኤርምያስ መጣ፦ 27  “እነሆ፣ እኔ የሰው ዘር* ሁሉ አምላክ፣ ይሖዋ ነኝ። ለመሆኑ እኔ የሚሳነኝ ነገር አለ? 28  ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፣ ይህችን ከተማ ለከለዳውያንና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነጾር* እሰጣታለሁ፤ እሱም ይይዛታል።+ 29  ይህችን ከተማ የሚወጓት ከለዳውያንም ይገባሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል፤+ ደግሞም ከተማዋን እንዲሁም ሕዝቡ እኔን ለማስቆጣት ሲሉ በጣሪያዎቻቸው ላይ ለባአል መሥዋዕቶች ያቀረቡባቸውንና ለሌሎች አማልክት የመጠጥ መባ ያፈሰሱባቸውን ቤቶች+ በእሳት ያቃጥሏቸዋል።’ 30  “‘የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ ከልጅነታቸው ጀምሮ በፊቴ ክፉ የሆነውን ነገር ብቻ አድርገዋልና፤+ የእስራኤል ሕዝብ በእጃቸው ሥራ እኔን ማስቆጣታቸውን አልተዉም’ ይላል ይሖዋ። 31  ‘ይህች ከተማ ከገነቧት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ቁጣዬንና ንዴቴን ከማነሳሳት በስተቀር ምንም የፈየደችው ነገር የለም፤+ በመሆኑም ከፊቴ አስወግዳታለሁ፤+ 32  ይህም የሆነው የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ ይኸውም እነሱ፣ ነገሥታታቸው፣+ መኳንንታቸው፣+ ካህናታቸው፣ ነቢያታቸው፣+ የይሁዳ ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እኔን ለማስቆጣት በሠሩት ክፉ ነገር ሁሉ የተነሳ ነው። 33  ለእኔ ፊታቸውን ሳይሆን ጀርባቸውን ሰጡ፤+ ደግሜ ደጋግሜ ላስተምራቸው ብሞክርም፣ አንዳቸውም ተግሣጼን ለመቀበል ፈቃደኛ አይደሉም።+ 34  ስሜ የተጠራበትንም ቤት ለማርከስ አስጸያፊ ጣዖቶቻቸውን በዚያ አስቀመጡ።+ 35  በተጨማሪም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለሞሎክ በእሳት አሳልፈው ለመስጠት በሂኖም ልጅ ሸለቆ*+ ያሉትን የባአልን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች ሠርተዋል፤+ ይሁዳን ኃጢአት ለማሠራት ይህን አስጸያፊ ነገር እንዲፈጽሙ እኔ አላዘዝኩም፤+ ፈጽሞም በልቤ አላሰብኩም።’* 36  “ስለዚህ እናንተ በሰይፍ፣ በረሃብና በቸነፈር ለባቢሎን ንጉሥ አልፋ ትሰጣለች ስለምትሏት ስለዚህች ከተማ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ 37  ‘እነሆ፣ እነሱን በመዓቴና በታላቅ ቁጣዬ ከበተንኩባቸው አገሮች ሁሉ አንድ ላይ እሰበስባቸዋለሁ፤+ ወደዚህም ቦታ መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ ያለስጋት እንዲኖሩም አደርጋለሁ።+ 38  እነሱም ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።+ 39  ለእነሱም ሆነ ከእነሱ በኋላ ለሚመጡት ልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ ዘወትር እኔን እንዲፈሩ+ አንድ ልብና አንድ መንገድ እሰጣቸዋለሁ።+ 40  ደግሞም ለእነሱ መልካም ነገር ከማድረግ እንዳልቆጠብ+ ከእነሱ ጋር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን እገባለሁ፤+ ከእኔም እንዳይርቁ በልባቸው ውስጥ እኔን የመፍራት መንፈስ አሳድራለሁ።+ 41  ለእነሱ መልካም በማድረግ እጅግ ደስ እሰኛለሁ፤+ በሙሉ ልቤና በሙሉ ነፍሴም* በዚህች ምድር ላይ አጽንቼ እተክላቸዋለሁ።’”+ 42  “ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘በዚህ ሕዝብ ላይ ይህን ሁሉ ታላቅ ጥፋት እንዳመጣሁ፣ ልክ እንዲሁ ቃል የገባሁላቸውን መልካም ነገር ሁሉ አመጣላቸዋለሁ።+ 43  እናንተ “ሰውም ሆነ እንስሳ የማይኖርባት ጠፍ መሬት ናት፤ ለከለዳውያንም ተሰጥታለች” ብትሉም በዚህች ምድር ላይ እንደገና መሬት ይገዛል።’+ 44  “‘ተማርከው የተወሰዱባቸውን ሰዎች መልሼ ስለማመጣቸው፣+ በቢንያም አገር፣ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ባሉ ቦታዎች፣ በይሁዳ ከተሞች፣+ በተራራማው ምድር ባሉ ከተሞች፣ በዝቅተኛው ስፍራ ባሉ ከተሞችና+ በደቡብ በሚገኙ ከተሞች መሬት በገንዘብ ይገዛል፤ የግዢ ውል ተዘጋጅቶ በማኅተም ይታሸጋል፤ ምሥክሮችም ይጠራሉ’+ ይላል ይሖዋ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
የአባቱን ወንድም ያመለክታል።
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ጉያ።”
ወይም “ከዓላማዎችህ ጋር በተያያዘ ታላቅ።”
ወይም “ከበሽታው።”
ቃል በቃል “የሥጋ።”
ቃል በቃል “ለናቡከደረጾር።” ናቡከደነጾር የሚለው ስም የሚጻፍበት ሌላው መንገድ ነው።
የቃላት መፍቻው ላይ “ገሃነም” የሚለውን ተመልከት።
ወይም “ፈጽሞ ወደ አእምሮዬ መጥቶ አያውቅም።”